Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እንዲህም አለ!

ሰሞኑን ወደ ተለያዩ ፋርማሲዎች ጎራ የምልበት አጋጣሚ ተከሰተና አንዳንድ ነገሮችን ለመታዘብ ዕድል አገኘሁ፡፡ በሐኪሞች የታዘዙትን የተለያዩ መድኃኒቶች ለማግኘት ወደ 12 የሚደርሱ ፋርማሲዎች ደጃፍ ለመርገጥ ተገድጃለሁ፡፡ አጋጣሚ ሆኖ በሦስት ተከታታይ ቀናት ወደ ስድስት የሚደርሱ መድኃኒቾችን ማዘዣዎች ይዤ ጎራ ያልኩባቸው መድኃኒት ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ እንደ ሁኔታው ይለያያል፡፡

በተለይ ግን አዲስ አበባ ውስጥ የመድኃኒቶች ዋጋ ውድነትን በቅጡ እንድገነዘብ አድርጎኛል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም የመድኃኒት እጥረት እንዳለም ከሰሞኑ ገጠመኝ ለመታዘብ ችያለሁ፡፡ የማይገኙ የተባሉ አንዳንድ መድኃኒቶች መደበኛ ከሚባለው ዋጋቸው በላይ እየተቸበቸቡ ስለመሆኑም ማረጋገጥ ችያለሁ፡፡ ተገልጋዮች የሕይወት ጉዳይ ሆኖባቸው በገበያ ላይ የለም የሚባሉ መድኃኒቶችን በተጋነነ ዋጋ መግዛት ግድ ሆኖባቸው ለአላስፈላጊ ወጪ ሲዳረጉ ማየት በራሱ ያማል፡፡ አንዳንድ ፋርማሲዎች የሙያ ግዴታቸውን ወደ ጎን ትተው አጋጣሚውን በመጠቀም ያለ ከልካይ በሌለ ዋጋ መድኃኒት ሲሸጡ የስግብግብነታቸው መጠን ልክ ማለፉን የሚያመለክት ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

በአንፃሩ ደግሞ በአንዳንድ መድኃኒት ቤቶች የአገልግሎት አሰጣጥ እንደዚህም ያሉ ለሙያቸው የተገዙ አገልጋዮች አሉ እንድል አድርገውልኛል፡፡ ለምዶብን ህፀፆችን እየፈለግን ችግሮችን አጉልተን እናሳያለን እንጂ፣ ጥቂት ቢሆኑም ከገንዘብ ይልቅ ሙያዊ ግዴታቸውን የሚወጡ አገልጋዮች አሉና እነሱን አለማመሥገን ንፉግነት ይሆናል፡፡ ምናልባትም ለሌሎች ምሳሌ ሊሆን ይችላልና ከ12ቱ የመድኃኒት መደብሮች በአንደኛው ያጋጠመኝን መልካም መስተንግዶ መናገር አግባብ በመሆኑ፣ ይህንን ገጠመኜን ማንሳት ወድጃለሁ፡፡

ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ የአገልግሎት አሰጣጡ ለየት ያለብኝንና በመልካም ልጠቅሰው የፈለግኩት የመድኃኒት መደብር ጀሞ አካባቢ የሚገኝ ነው፡፡ የዚህ መድኃኒት ቤት ፋርማሲስት ወጣት ነው፡፡ ወደ እዚህ መደብር የገባሁት ሕክምና ላይ ለሚገኙ የቤተሰቤ አባል የታዘዙልኝን ሁለት መድኃኒቶች ለመግዛት ነበር፡፡ ወጣቱ ፋርማሲስት የትዕዛዝ ወርቀቱን ተመለከተና ሁለቱ መድኃኒቶች ተመሳሳይነት ያላቸው መሆኑን አስረዳኝ፡፡ ከሁለቱ አንዱ እሱ ጋር እንዳለ ነግሮኝ ዋጋውንም ከገለጸልኝ በኋላ፣ መድኃኒት ስላለ ብቻ እንደማይሸጥልኝ ነገረኝ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሁለቱ መድኃኒቶች ተመሳሳይነት ያላቸውና የተሻለ ያለው መድኃኒቱ ደግሞ እሱ ጋር እንደሌለ ገለጸልኝ፡፡ መድኃኒቱን ያዘዘው ዶክተር ከሁለቱ አንዱን ካገኘሁ እንድገዛ እንደ አማራጭ የተጻፈ ሊሆን እንደሚችል ገልጾልኝ ስለመድኃኒቶቹ ይዘትና ልዩነት በደንብ አስረዳኝ፡፡

የዚህ ወጣት ፋርማሲስት ገለጻ፣ ቅን ምልከታና እኔን ለማገዝ ያደረገው ጥረት እጅግ ደነቀኝ፡፡ ያለውን መድኃኒት ሸጦ ገንዘቡን ኪሱ ከመክተት የበለጠ፣ ተገልጋዩን እኔን ለማገዝ ያደረጋቸው ጥረቶችን ሁሉ እንደ ብርቅ አየሁት፡፡ ምናልባት ሌላ ቦታ ቢሆን እጁ ላይ ያለውን መድኃኒት ሸጦልኝ መገላገል ይችል ነበር፡፡ ይህንን ግን አላደረገም፡፡ ብዙውን ጊዜ መድኃኒት ስገዛ ከሚገጥሙኝ አሳዛኝ አጋጣሚዎች የተለየ  አስተናጋጅ በመሆኑ እንዲህም ያለ ቅን አገልጋይ መኖሩ ተስፋ እንድናደርግ፣ ከግብይትና ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ዘወትር የምናማርርበትን ነገር የሚያክም ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡  

ባለሙያው መድኃኒቶቹን ወዳዘዘው ዶክተር ተመልሼ እንዳነጋግር ነገረኝ፡፡ እንዳለውም ትዕዛዙን ወደ ሰጠው ዶክተር ተመልሼ ፋርማሲስቱ ያለኝን በሙሉ ነገርኩት፡፡ ዶክተሩም ፋርማሲስቱ ያለው ትክክል መሆኑን ገለጸልኝ፡፡ የተሻለ የተባለውን መድኃኒት ለማግኘት ብዙ መድኃኒት ቤቶችን አስሼ ማግኘት አልቻልኩም፡፡

ዶክተሩ ተለዋጭ መድኃኒት ካለ ቢቀይርልኝ ብዬ ሐሳብ አቀረብኩ፡፡ መጀመርያው በክሊኒኩ ውስጥ በሚገኘው ፋርማሲ ውስጥ መድኃኒቶቹ ስለሌሉ ከውጭ እንድገዛ የተደረገ በመሆኑ፣ መድኃኒቶቹ ከጠፉ የግድ ሌላ አማራጭ ስለሚያስፈልግ ይህንኑ አስቤ ነበር ጥያቄ ያቀረብኩት፡፡ መጨረሻ ላይ ግን የሚፈለገው መድኃኒት እዚያው በክሊኒኩ ፋርማሲ ውስጥ እንደሚገኝ አንድ ነርስ ቀስ ብላ ነገረችን፡፡ ዋጋው ግን ይህንን ያህል ነው አለችኝ፡፡ በዚህ ሰዓት ሌላ ነገር ማሰብ አልፈለግኩም፡፡ የለም የተባለው መድኃኒት በተባለው ዋጋ ገዛሁ፡፡ ነገሩ ከንክኖኝ የመድኃኒቱ ዋጋ ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ወጣ ብዬ ጠየቅሁ፡፡ ከሁለትና ከሦስት እጥፍ በላይ የከፈልኩበት እንደሆነ አረጋገጥኩ፡፡ እንዲህ ያለው ነገር ምን ሊባል ይችላል? የአገልግሎት አሰጣጣችን ምን ያህል እንደታመመ ያሳየናል፡፡ አክብሮት ወደ ሰጠሁት ፋርማሲስት ልመልሳችሁ፡፡  

በክሊኒኩ የሉም የተባሉ መድኃኒቶችን ለመግዛት ይህንኑ ፋርማሲ ምርጫ አድርጌ አራት ጊዜ ሄጃለሁ፡፡ በእነዚህ ምልልሶቼ የተረዳሁት ነገር ቢኖር ወጣቱ ፋርማሲስት ደንበኞችን በሚያስተናግድበት ጊዜ ይሰጣቸው የነበሩ ምክሮች ፈጽሞ የተለየና ተገልጋይ በተመሳሳይ መንገድ የማስተናገድ ልምድ ያለው መሆኑን እንዳረጋግጥ አድርጎኛል፡፡

ሌላው ቀርቶ ከዚህ ፋርማሲ ውጪ ገዝቻቸው በነበሩ መድኃኒቶች ደረሰኝ የሰጠኝ አልነበረም፡፡ በጥያቄ ነበር ደረሰኝ ያገኘሁት፡፡ በዚህ ወጣት ፋርማሲ ውስጥ ግን ደረሰኝ ያለ ጥያቄ መሰጠቱ ሌላው በጎ መገለጫው ነበር፡፡ በሌላኛው ቀን ሌላ መድኃኒት ለመግዛት ወደ እዚሁ ፋርማሲ የመጣሁት ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ነበር፡፡ ደንበኞች ስለነበሩ እነሱን እንዲያስተናግድ ጠበቅነውና የምንፈልገውን መድኃኒት ጠየቅነው፡፡

በዚህ መሀል ግን አንድ ደንበኛ ‹‹Azitromicine›› የተባለ መድኃኒት ይገዛ ነበርና እንዴት መጠቀም እንዳለበት በደንብ አስረዳውና የመድኃኒቱ 192.00 ብር መሆኑን ገልጾ ክፍያ ፈጽሞ ወጣ፡፡ ይሄኔ ጓደኛዬ ‹‹Azitromicine›› የተባለው መድኃኒት የገዛው ሰው ከወጣ በኋላ እርግጠኛ ለመሆን የመድኃኒቱን ዋጋ ጠየቀ፡፡ በእርግጥም 192.00 ብር መሆኑን አረጋገጠ፡፡ በጣም ተናዶ ከሦስት ቀናት በፊት ይህንኑ መድኃኒት በ450.00 ብር እንደገዛው ነገረን፡፡ መድኃኒቱ የሚመረትባቸው አገሮች ሲለያዩ እንዲህ ያለው የዋጋ ልዩነት ሊኖር ይችላልና ምናልባት እሱ ከሆነ ብሎ ሲያረጋግጥ መድኃኒቱ እሱ የገዛው ዓይነት ነው፡፡ በተወሰነ ርቀት ላይ በሚገኙ ፋርማሲዎች መካከል የዋጋ ልዩነት ከእጥፍ በላይ መሆኑ ግራ አጋባን፡፡  

ከወጣን በኋላ በቅርብ ያገኘናቸው ፋርማሲዎች ውስጥ መድኃኒቱን ጠየቅን፣ አንዱ ቦታ 320.00 ብር፣ አንዱ ቦታ 400.00 ብር እንደሆነ ተነገረን፡፡ አግራሞታችን ጨመረ አንድ ዓይነት መድኃኒት በተለያዩ ፋርማሲዎች በዚህን ያህል ደረጃ የዋጋ ልዩነት ማሳየቱ አስገረመን፡፡ በዚሁ ፋርማሲ የገጠመኝን ሌላ መልካም ነገር ልጨምር፡፡ ከታዘዙልኝ መድኃኒቶች አንደኛውን መድኃኒት እንዲሰጠኝ ነገርኩት፡፡ መድኃኒቱ ለረዥም ጊዜ የሚወሰድ በመሆኑ አንድ እሽግ ብቻ ከምገዛ ጨምሬ መግዛት እንደምፈልግ ገለጽኩለት፡፡ እሱ ግን አሁንም ገቢውን አላሰበም፡፡ ‹‹አንዳንዴ መድኃኒቶች አለርጂክ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ መጀመርያ በዚህ ሞክሬ ችግር ከሌለው ጨምረህ ትገዛለህ አለኝ፡፡ ተመሳሳይ መድኃኒቶች አሉ ካልተስማማችሁ ለዶክተሩ ነግራችሁ ማስለወጥ እንደሚቻል አስረዳኝና አንዱን እሽግ ብቻ ገዝቼ ወጣሁ፡፡ እንዲህ ያለውን ያብዛልን ከማለት ውጪ ሌላ ምን ይባላል!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት