Friday, September 22, 2023

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት ትኩሳት ሲሆን የታየበት አጋጣሚ በርካታ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ይህ ይጎድለዋል፣ እንዲህ ቢደረግ ወይም አንዳንድ ነገር ቢካተትበት በሚል የሚነሱ ጥያቄዎች ከባድ ተቃርኖ ሲገጥማቸው ማየት የተለመደ ነው፡፡ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ወይም ለውጥ በተነሳ ቁጥር፣ ‹‹ሕገ መንግሥቱ የሚነካው በመቃብራችን ላይ ነው፤›› የሚል ጠንካራ አፀፋ ሲሰጥ መስማት የተለመደ ሆኖ ነው የኖረው፡፡

ከሰሞኑም ቢሆን ይህን መሰሉ አተካሮ የተደገመ ይመስላል፡፡ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ያቀረበው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጥናት መነጋገሪያ መሆኑን ተከትሎ፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ፓርቲ ባወጣው መግለጫ ጠንካራ ተቃውሞ ማሰማቱ የዚሁ ነፀብራቅ ሆኖ ነበር የታየው፡፡

ኦፌኮ በመግለጫው፣ ‹‹በሕገ መንግሥት ማሻሻያ ስም የኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ሥርዓት እንዲናድና አገሪቱ እንድትፈራርስ መደላድል እየተዘጋጀ ነው፤›› በማለት፣ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ያዘጋጀውን የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጥናት ተቃውሞታል፡፡ ኦፌኮ ከጥናቱ አጠናን ሥልት ጀምሮ በበርካታ ጉዳዮች ጥናቱን ውድቅ ሲያደርገው የታየ ሲሆን፣ ከሕገ መንግሥት ማሻሻያ በፊት  አገሪቱ ልታስቀድማቸው የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን በሰፊው ዘርዝሯል፡፡

ለውይይት መንደርደሪያ እንዲሆን እንዲሁም ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የምክክር ሥራ ግብዓት ይሆናል በሚል መንፈስ መቅረቡ የተነገረው የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ጥናት፣ በይፋ የቀረበ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሰነድ አለመሆኑ በግልጽ ሲዘገብ ሰንብቷል፡፡ ይሁን እንጂ ይህንንም ቢሆን እንደ ኦፌኮ ያሉ ኃይሎች አገር የማፍረስ አጀንዳ ነው ብለው መቃወማቸው መነጋገሪያ ነበር፡፡

በይፋ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሰነድ ነው ተብሎ ባልቀረበ ጥናት ላይ ጠንካራ ሙግት የሚነሳ ከሆነ፣ ወደ ዋናው የሕገ መንግሥት ማሻሻል ዕቅድ በምን መንገድ ሊገባ ነው? የሚል ጥያቄን ጉዳዩ አስነስቷል፡፡ በሌላ በኩል በጥናቱ ላይ የተነሳው ተቃውሞ ከዚህ ቀደም፣ ‹‹ሕገ መንግሥቱ የሚነካው በመቃብራችን ላይ ነው፤›› እየተባለ ከሚነሳው ሙግት በምን ይለያል? የሚል ሐሳብም በአንዳንዶች ዘንድ እያስነሳ ይገኛል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ግን ጥናቱ ጠንካራ ትችት የገጠመው በምን መነሻነት ነው የሚለው ጉዳይ እያወያየም ነው፡፡

ከሰሞኑ ይፋ የሆነው የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ጥናት ስለሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ በርካታ ነጥቦችን ያነሳል፡፡ ከትግራይ ክልል ውጪ ሁሉንም ክልሎች የዳሰሰ መሆኑ የተነገረለት ባለ 375 ገጹ ጥናት የሕገ መንግሥቱን መሻሻል ሐሳብ ማን እንደሚደግፍና እንደሚቃወም ዝርዝር መረጃዎች ያቀርባል፡፡ በዋናነት የብሔር ብሔረሰቦች አንቀጾችን፣ እንዲሁም ሌሎች አጨቃጫቂ የሕገ መንግሥት ነጥቦችን በተመለከተ የኢትዮጵያ ዜጎች ምን ዓይነት ዝንባሌ እንዳላቸው የሕዝብ አስተያየት  ግምገማ ይዞ ቀርቧል፡፡

በመጠይቁ ከሚካተቱት ውስጥ 75 በመቶ የሚሆኑት የሕገ መንግሥት ማሻሻል ሐሳብን ደግፈዋል ይላል ይኸው ጥናት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ 70 በመቶዎቹ በብሔር ተደራጅቶ የመንቀሳቀስ ፖለቲካ በኢትዮጵያ እንዲከለከል ይፈልጋሉም ይላል፡፡ በብሔር ፖለቲካ የመደራጀትም ሆነ ብሔርን መሠረት ያደረገ የፌዴራል መዋቅር፣ አገሪቱ ለገጠሟት በርካታ ቀውሶች መነሻ ሆነዋል ብለው የሚያምኑ በርካታ መሆናቸውንም ያወሳል፡፡

በአዲስ አበባ ጉዳይ 55 በመቶ ኢትዮጵያውያን ራሷን የቻለች ክልል ሆና እንድትኖር ይፈልጋሉ ያለው የጥናቱ ግኝት፣ ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች ደግሞ 66 በመቶዎቹ ይህን ሐሳብ ይደግፉታል ይላል፡፡ የአዲስ አበባ አወቃቀር ማሻሻያ እንዲደረግበት የሚፈልጉ ዜጎች ቁጥር 45 በመቶ መሆኑን ግኝቱ ያሳያል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ደግሞ ሃያ በመቶዎቹ በፌዴራሉ መንግሥትና በኦሮሚያ ክልል ትተዳደር ሲሉ፣ ወደ 22 በመቶዎቹ ግን የኦሮሚያ ክልል ልትሆን ይገባል ማለታቸው ታውቋል፡፡ አዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ ትጠቃለል ከሚሉ ዜጎች አብዛኞቹ (2/3ኛዎቹ) የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች ናቸውም ተብሏል፡፡

ግንቦት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ ይፋ የሆነው የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጥናት፣ በርካታ ግኝቶችና ምክረ ሐሳቦች ይዞ የቀረበ ነው፡፡ አጨቃጫቂው የሕገ መንግሥት ጉዳይ አንቀጽ 39 ይሻሻል ያሉ ዜጎች 75 በመቶ መሆናቸውን ጥናቱ ያመለክታል፡፡ አሁን ያለውን ሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች በትንሹ ከ60 እስከ 70 በመቶ እንኳ በተጨባጭ  መተርጎም ቢቻል፣ በርካታ የኢትዮጵያ ችግሮች እንደሚቀረፉ በጥናቱ የተሳተፉ መናገራቸው ተዘግቧል፡፡ ሕገ መንግሥት ማሻሻል ብቻውን የአገሪቱን ሁለንተናዊ ችግር ይቀርፋል ማለት አለመሆኑን አጥኚዎቹ ገልጸዋል፡፡ ይህ የጥናት ሰነድም ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን መሰጠቱንና በምክክር ሒደቶች እንደ ግብዓት ሆኖ እንደሚያገለግል ተጠቁሟል፡፡

ይሁን እንጂ ጥናቱን ተከትሎ የተሰሙ የባለሙያ አስተያየቶች ሲጀመር የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ይህን መሰል የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጥናት ለማድረግ መብትና ኃላፊነት ማን ሰጠው? ሲሉ ጠያቂ ሆነዋል፡፡ የሕገ መንግሥትን ማሻሻያ ያህል አንገብጋቢ ጉዳይ የማጥናት ሥራ ለመንግሥት ተቋም በብቸኝነት ሊሰጥ አይገባም ያሉም ነበሩ፡፡ አካታችና ሁሉንም የሚያሳትፍ በሆነ መንገድ ወይም በገለልተኛ አካል መጠናት እንዳለበት ተከራክረዋል፡፡

በሌላ በኩል ያለፉ ስህተቶችን በሕገ መንግሥት ጉዳይ ላለመድገም መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ የመከሩ አሉ፡፡ ከሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ በፊት መቅደም ያለባቸው የቤት ሥራዎች መኖር አለባቸውም ብለዋል፡፡ ሁሉንም ዓይነት ፍላጎት ማስተናገድ የሚችል የፖለቲካ ዓውድ መፍጠር አንዱ ሲሆን፣ ሕግና ሥርዓት ማስፈን፣ ዴሞክራሲና ተቋማትን ማጠናከር፣ እንዲሁም ሰላማዊ ከባቢን መፍጠር አስቀድሞ ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የሕገ መንግሥት መሻሻል ጉዳይ ለአገር የሚበጅ አጀንዳ ቢሆን እንኳ፣ ጉዳዩ በሰከነ ሁኔታ በጥሞና መደረጉ እንደሚጠቅም ነው የተለያዩ ወገኖች የመከሩት፡፡  ሰነድም ሆነ ጥናት ሕገ መንግሥት እጅግ አጨቃጫቂ የፖለቲካ ትኩሳት መሆኑ እየታወቀ፣ በዚህ መሰል መንገድ መቅረብ የለበትም የሚል ሐሳብ ያነሱም አሉ፡፡

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የማሻሻል ጥያቄ ፅንፍ የረገጠ ሙግት የሚያስነሳ ቢሆንም፣ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ግን ሲረቀቅ ጀምሮ ብዙ ህፀፆችና ጉድለቶች ያሉበት ሰነድ መሆኑ ተደጋግሞ ይወሳል፡፡

አሥራት አብርሃም ‹‹የሕገ መንግሥቱ ፈረሰኞች›› ብለው በ2009 ዓ.ም. ባቀረቡት መጽሐፍ፣ ሕገ መንግሥቱ የረቀቀበትን ዓውደ ከትበዋል፡፡ የማርቀቅ ሒደቱን በጊዜው የተመለከቱ ቃለ ጉባዔዎችን በመከተል ሒደቱ ምን ይመስል እንደነበር አንድ በአንድ አስነብበዋል፡፡

‹‹የሕገ መንግሥቱ መንፈስ›› ብለው ባስነቡበት ክፍል አቶ አሥራት በቃለ ጉባዔው የብሔሮች እኩልነት የተረጋገጠባት አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ የተገነባባት አገር መፍጠር ተብሎ መሥፈሩን ይጠቅሳሉ፡፡ ብሔር ብሔረሰቦች የሕገ መንግሥቱ ባለቤት እንዲሆኑ መደረጉም በቃለ ጉባዔው ተመላክቷል ይላሉ፡፡

ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥቱ የተረቀቀበት ከባቢ አየር፣ ‹‹ኢትዮጵያ ለቆመችባቸው መሠረታዊ ምሰሶች ጥላቻ ያላቸው ሰዎች የተሰበሰቡበት ሸንጎ ይመስላል›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አቶ አሥራት ሲቀጥሉም፣ ‹‹የሕገ መንግሥቱ ጉባዔ የመግባባት፣ የፍቅርና የአንድነት ጉባዔ አልነበረም፡፡ መከባበርና የሠለጠነ ውይይት አልታየበትም፡፡ ምሁራዊ ክርክር ሳይሆን የአሸናፊዎች ድንፋታ፣ የጥላቻ ንግግሮች፣ የማናለብኝነት ገለጻዎች፣ ድንቁርናና ትዕቢት የሰፈነበት፣ አሸናፊዎች ሁሉንም ነገር የሚያደርጉበት፣ ተሸናፊዎች ደግሞ ሁሉንም ነገር ለመቀበል የተገደዱበት ጉባዔ ነበር፤›› በማለት የሕገ መንግሥቱን አረቃቀቅ መንፈስ በሰፊው ተርከዋል፡፡

የአሥራት መጽሐፍ ሕገ መንግሥታዊው ጉባዔ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች ያላሳተፈ መሆኑን ያስነብባል፡፡ እንደ ኢሠፓ፣ ኢሕአፓና መኢሶን ያሉ ድርጅቶች ወደ ጎን መገፋታቸውን በምሳሌነት ያነሳል፡፡ በአቶ ክፍሌ ወዳጆ ሰብሳቢነት በሚመራውና 29 አባላት በነበሩት የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን ውስጥም ቢሆን፣ የኢሕአዴግ ውክልና የገዘፈበት መሆኑን መጽሐፉ ይተርካል፡፡ በዚህ ከባቢ አየር ውስጥ ሆኖ የተረቀቀው ሕገ መንግሥት ደግሞ የቱንም ያህል የማርቀቅ ቅደም ተከተል ቢከተል በእያንዳንዱ ጉዳይ ማወዛገቡ የሚጠበቅ መሆኑን ያክላል፡፡

በወቅቱ የነበሩ ሰዎች እንደሚገልጹት፣ ሐምሌ 15 ቀን 1983 ዓ.ም. ነበር ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የሽግግር ጊዜ ቻርተር የተባለው መዋቅር የተመሠረተው፡፡ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. ደርግን አሸንፎ ኢትዮጵያን የተቆጣጠረው ኢሕአዴግ ለአንድ ወር ተኩል የኢሕአዴግ ጊዜያዊ መንግሥት ብሎ ከመራ በኋላ ነበር ቻርተሩ የተዋቀረው፡፡ በዚሁ ቻርተር የሽግግር ፕሮግራም የተነደፈ ሲሆን፣ የሽግግር ጊዜ መመርያም በዚሁ መሠረት ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ መመርያውም የሕገ መንግሥቱን አረቃቀቅና አፀዳደቅ ሒደት አስቀምጧል፡፡

የተወካዮች ምክር ቤት የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን በመሰየም ሕገ መንግሥት እንዲረቀቅ ያዛል፡፡ አርቃቂ ኮሚሽኑ ረቂቅ ሕገ መንግሥቱን አዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ያቀርባል፡፡ ምክር ቤቱ ደግሞ ረቂቁን አፅድቆ ለሕዝብ ውይይት ይልካል፡፡ የመጨረሻው ረቂቅ በረቂቁ መሠረት በሕዝብ ለሚመረጥ ሕገ መንግሥታዊ ጉባዔ ይቀርባል፡፡ ውይይት ተደርጎ በፀደቀው ሕገ መንግሥት መሠረት የብሔራዊ ምክር ቤት ምርጫ ይደረጋል፡፡ በምክር ቤቱ አብላጫ ወንበር የሚያገኘው ኃይል/ኃይሎች መደበኛ መንግሥት ሲመሠርት/ቱ የሽግግር ጊዜ መንግሥቱ ሥልጣን ያበቃል፡፡ በዚህ መሰል ቅደም ተከተል የታጠረው የሕገ መንግሥት ማርቀቅና አዲስ መንግሥት ምሥረታ ሒደት ከሁለት ዓመት ያልበለጠ የጊዜ ገደብ የተቀመጠለት ሲሆን፣ ጊዜ ካጠረ በስድስት ወራት ብቻ ሊራዘም እንደሚችል ተቀምጦ ነበር፡፡

   በአቶ ክፍሌ ወዳጆ የተመራው አርቃቂ ኮሚሽን ነሐሴ 12 ቀን 1984 ዓ.ም. ነበር የተቋቋመው፡፡ ከየካቲት 17 ቀን 1985 ዓ.ም. ጀምሮ ዋናውን የረቂቅ ማቅረብ ሥራውን ጀመረ፡፡ ይህ ሒደት እስከ መጋቢት 1986 ዓ.ም. ድረስ መቆየቱ ይነገራል፡፡ መጋቢት 30 ቀን ሕገ መንግሥታዊ ምክር ቤት ተመረጠ፡፡ ከጥቅምት 17 እስከ ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም. ድረስ በምክር ቤቱ ውይይት ሲደረግበት ቆይቶ ሕገ መንግሥቱ በይፋ ፀደቀ፡፡ ነሐሴ 17 ቀን 1987 ዓ.ም. ደግሞ በይፋ ሥራ ላይ መዋሉን የወቅቱን ሒደት የተከታተሉ ይናገራሉ፡፡

ይህን መሰል ሒደት ያለፈው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አረቃቀቅ ላለፉት 30  ዓመታት ሳይሻሻልና ሳይለወጥ በሥራ ላይ ውሎም በተግባር ተፈትሿል፡፡ ይሁን እንጂ ከማርቀቅ ሒደቱ ጀምሮ ውዝግብ ያልተለየው ሕገ መንግሥቱ ዛሬም ድረስ፣ ቢሆን ብዙ ህፀፆችና ችግሮች እንዳሉበት ይነገራል፡፡ በሕገ መንግሥቱ ላይ ጥናት ያደረጉ ወገኖች የሕገ መንግሥቱ ችግሮች በርካታ መሆናቸውን ነው የሚናገሩት፡፡

የሕግ ባለሙያው ዮናስ ተስፋው (ዶ/ር) እንደሚናገሩት የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ሰሞነኛ ጥናት ብቻ ሳይሆን፣ በሕገ መንግሥቱ ህፀፆች ላይ እጅግ በርካታ ጥናቶች ተደርገዋል፡፡ በፍትሕ ሚኒስቴር ሥር የተደረጉ ጥናቶች ነበሩ፡፡ ከዚያ በተጨማሪም በውጭና በአገር ውስጥ ምሁራን እጅግ በርካታ ጥናቶች በሕገ መንግሥቱ ዙሪያ ተደርገዋል፡፡ ከዚህ በመነሳትም የሕገ መንግሥቱ ጉድለቶች በርካታ ናቸው ይላሉ፡፡

‹‹በሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ እንኳ የተሻለ ቢባልም በዚያም ቢሆን በእሱ ዕድሜ ካሉ የሌሎች አገሮች ሕገ መንግሥቶች አንፃር ብዙ ይቀረዋል፡፡ የኡጋንዳ፣ የዛምቢያ፣ ወይም በቅርብ ጊዜ የወጣው የኬንያ ሕገ መንግሥቶች  በሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች የተሻሉ ናቸው፡፡ የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥትማ በጣም የተራመደ ነው፡፡ የሰብዓዊ መብቶች ብሎ ከማወጅ ውጪ ሲጣስ ምን ይሆናል ብሎ የእኛ አያስቀምጥም፡፡ ወደ አንድ ሦስተኛ የሕገ መንግሥቱ ክፍል ወይም አብላጫው የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ነው ቢባልም፣ ነገር ግን ድንጋጌ ብቻ ነው፡፡ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ከቋንቋ ጀምሮ፣ አመዳደቡም ሆነ ብዙ ነገሩ ችግር አለበት፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የማስፈጸም ወሰንን በአንቀጾቹ አልያዘም፡፡ የሌሎች አገሮች ሕገ መንግሥቶች ግን አንድ የሰብዓዊ መብት አንቀጽ ሲጣስ ምን ይደረግ የሚለውን  አስቀምጠዋል፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የዳኝነት ሥልጣንን በብቸኝነት የፍርድ ቤቶች መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ይህን ድንጋጌ ግን መልሶ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ሲሰጥ ይታያል በሚል በአንዳንድ ባለሙያዎች ይተቻል፡፡ የሕገ መንግሥቱ ጉድለቶች ያልተሟላ ወይም እርስ በርሱ የሚቃረን ድንጋጌዎች ከመያዙ በተጨማሪ፣ ህፀፆቹ ብዙ መሆናቸውን ነው ባለሙያዎች የሚያወሱት፡፡

የሕግ ባለሙያው አቶ አበባው አበበ እንደሚናገሩት፣ የአንቀጾች አመዳደቡ (Classification) ችግር ያለው ነው፡፡ በግላቸው ‹‹የማሰብና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ከሁሉም የቀደመ የሰብዓዊ መብት›› መሆኑን እንደሚቀበሉ የጠቀሱት አቶ አበባው ይህ ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብቶች ቃል ኪዳን (Universal Declaration of Human Rights) ላይ ሰብዓዊ መብት ተብሎ መደንገጉን ይጠቅሳሉ፡፡

‹‹ይሁን እንጂ የእኛ ሕገ መንግሥት ይህን የሰብዓዊ መብት ዴሞክራሲያዊ መብት ብሎ ባስፈለገ ጊዜ ሊጣሱ ከሚችሉ አንቀጾች መካከል ከቶታል፡፡ በዚህ የተነሳ የሐሳብ ነፃነት በቂ ጥበቃ እንዳይደረግለት ሆኗል፡፡ ከዚህ የሚመነጨው የሚዲያ ነፃነት የሚጣሰውም ሆነ ጋዜጠኞችና ሐሳብ በነፃነት የሚገልጹ ግለሰቦች የሚታሰሩት በዚህ የተነሳ ነው፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

አቶ አበባው ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉ ሕገ መንግሥቱ የብሔር ብሔረሰቦችን እንጂ፣ የሕዝቦችን ሉዓላዊነት ዕውቅና አለመስጠቱን ይናገራሉ፡፡ ‹‹በሕገ መንግሥቱ ላይ የመጀመርያውም የመጨረሻውም አለመግባባት የሚነሳው እኛ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ብሎ ከሚነሳበት ነጥብ ጀምሮ ነው፤›› የሚሉት ባለሙያው የዜጎች ነፃነት ጉዳይ በዚህ የተዋጠ  እንደሚመስል ያስቀምጣሉ፡፡ ‹‹የተዛቡ ግንኙነቶቻችንን ለማረም›› በሚል የተቀመጠው የመነሻ ነጥብም ቢሆን ሕገ መንግሥቱ ‹‹የጨቋኝ ተጨቋኝ ወይም የበዳይ ተበዳይ›› ትርክትን ይዞ የተቀዳ ነው የሚል ውዝግብ የሚያስነሳ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

አቶ አበባው እንደሚናገሩት ሕገ መንግሥት ጥቅል ድንጋጌዎችን የሚሰጥ ነው፡፡ በማስፈጸሚያ ሕጎች ሕገ መንግሥቱ ወደ መሬት እንደሚወርድ በመጥቀስም፣ ሕገ መንግሥቱን በተግባር የመተርጎሙ ጉዳይ እጅግ ብዙ እንደሚቀረው አመልክተዋል፡፡ ‹‹ማሻሻያ ወይም ሌላ ሕገ መንግሥት ከመመኘት ይልቅ ሕገ መንግሥቱ የሰጣቸው ድንጋጌዎች በቅጡ በተግባር ቢተርጎሙ፤›› በማለት ነው ሐሳባቸውን የሚደመድሙት፡፡

የሕገ መንግሥቱ ክፍተት በተጨባጭ በበቂ ሁኔታ በተግባር ላይ ውሎ አለመፈተሹን የሕግ ባለሙያው ዮናስ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ አገራዊ ቀውሶች ሊፈጠሩ ቢችሉ፣ ሕገ መንግሥቱ እነዚያን ቀውሶች ሊፈታ የሚችልባቸው ዘዴዎች አለመቀመጣቸውን ያስረዳሉ፡፡

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ  የተወካዮች ምክር ቤትን መበተን ይችላል ይላል፡፡ ነገር ግን ምክር ቤቱ ሲፈቅድ ነው የሚበትነው ይላል መልሶ፡፡ ምክር ቤቱ በትነኝ ብሎ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈቃድ መስጠት አለበት ማለት ነው፡፡ በሌላ ሁኔታ ደግሞ ምክር ቤቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የመተማመኛ ድምፅ መስጠትም/መንፈግም ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ምክር ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከሥልጣን ተነሳ ቢል፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ በአፀፋው ምክር ቤቱን እበትነዋለሁ ሊል የሚችልበትን ዕድል ሊፈጥር ይችላል፡፡ በሌሎች አገሮች ይህንን ሚዛን አስተካክለው ሠርተውታል፡፡ እኛ ዘንድ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚበትነውን ምክር ቤት አስፈቅዶ ነው መበተን የሚችለው ተብሎ ተደንግጓል፤›› በማለት ውዝግብ ሊያስነሳ ስለሚችል አንቀጽ ያስረዳሉ፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከግማሽ በላይ ለቀው ወይም ሥራቸውን ትተው አዲስ ምርጫ ለማድረግ አገሪቱ ብትገደድ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለ ምክር ቤት ፈቃድ አባላቱን መበተን የማይችሉ እስከሆነ ድረስ መፍትሔው ምን እንደሆነ ሕገ መንግሥቱ አለመመልከቱንም ይጠቁማሉ፡፡

‹‹ከአረቃቀቁ ጀምሮ ሕገ መንግሥት አወጣጥ ሥርዓትን ያልተከተለ ሕገ መንግሥት ነው፤›› ሲሉ የሚናገሩት ዮናስ (ዶ/ር)፣ ሕገ መንግሥት የማውጣት ሥርዓት ምን የተከተለ መሆን እንዳለበትና ሙያው ምን እንደሚል አብራርተዋል፡፡

‹‹መጀመርያ ሕገ መንግሥቱ የሚቀረጽበት መሠረታዊ መርሆዎች ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ አርቃቂ ኮሚቴ የተለያዩ ብዝኃ ሐሳቦችን የሚወክል ሆኖ ይዋቀራል፡፡ አርቃቂው ኮሚቴ መሠረታዊ መርሆዎችን ተመርኩዞ ሕገ መንግሥቱን እየቀረፀ መሆን አለመሆኑን መከታተያ መንገድ ማበጀት ያስፈልጋል፡፡ የእኛ አገር ሕገ መንግሥት ቀረፃ የሽግግር መንግሥቱን ቻርተር ብቻ ታሳቢ ያደረገ ነበር፤›› በማለት ሒደቱ ከጠቀሱት ሁኔታ በምን እንደሚለይ ገልጸዋል፡፡ በትጥቅ ትግል ያሸነፉና በሽግግር መንግሥቱ የበላይነት የነበራቸው ኃይሎችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም ያክላሉ፡፡

‹‹ብዙ ጊዜ ነፃነት፣ እኩልነት፣ ፍትሕ፣ ሰብዓዊ ክብር፣ ዴሞክራሲና ብዝኃነት ተብሎ የሚቀመጡ መሠረታዊ መርሆዎችን መሠረት አድርጎም እያንዳንዱ ድንጋጌ ይረቀቃል፡፡ የእኛ አገር ሕገ መንግሥት አረቃቀቅ ግን ይህን ያልተከተለ ነው፤›› ይሉታል፡፡ ሕገ መንግሥቱ በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ዙሪያም ሆነ በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ድንጋጌዎቹ የሚነሱበት ብዙ ህፀፆች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ለምሳሌ አንድ አብላጫ ወንበር ይዞ መንግሥት የመሠረተ ፓርቲ አባላቱ ለቀው ወይ ወደ ሌላ ፓርቲ ሄደው አብላጫነቱን ቢያጣ የመንግሥቱ ዕጣ ምን ይሆናል? የሚለውን እንኳ በምርጫ ሕጉ ያላስቀመጠ ነው፤›› በማለትም ዮናስ (ዶ/ር)፣ የሕገ መንግሥቱን ቀውስ የመፍታት አቅም ጠቁመዋል፡፡

የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ሰሞነኛ ጥናት ትኩረት ይሳብ እንጂ፣ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ዙሪያ የተሠሩ ጥናቶች እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ ከሕገ መንግሥቱ በተጓዳኝ በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ላይ የሚነሱ አጨቃጫቂ ጉዳዮችም ሲጠኑ ቆይተዋል፡፡

አብኮን (ABCON) ከአፍሮ ባሮሜትር ጋር በመተባበር እ.ኤ.አ. ነሐሴ 25 ቀን 2020 የቀረበው ጥናት፣ ኢትዮጵያውያን ስለሕገ መንግሥቱ ብቻ ሳይሆን ስለፌዴራላዊ ሥርዓቱ ያላቸውን ምልከታም በሰፊው አመላክቷል፡፡ በመላ አገሪቱ የሚገኙ 300 አካባቢዎችን በናሙና በመምረጥ 2,400 ዜጎችን ስለሕገ መንግሥቱና ስለፌዴራላዊ አወቃቀሩ መጠይቅ ያቀረበው ጥናቱ፣ በእያንዳንዱ መንደር ከስምንት ያላነሱ ቃለ መጠይቆችን በማድረግ የሕዝብ አስተያየትን ሰብስቧል፡፡

ይህ ጥናት አገኘሁት ካላቸው ቁልፍ ግኝቶች መካከል ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ይሻሻል/አይሻሻል፣ ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ምን ይሁን፣ አሀዳዊ ሥርዓት ወይስ ያልተማከለ አስተዳደር፣ ሕገ መንግሥቱ በምን መንገድ ይሻሻል? ወዘተ የሚሉና ሌሎም ነጥቦችን የተመለከቱ ምላሾች ተካተውበታል፡፡

ከአሥር ኢትዮጵያውያን መካከል ስድስቱ (61 በመቶ) ከአሃዳዊ ይልቅ ፌዴራላዊ (ያልተማከለ) አስተዳደርን ይመርጣሉ ይላል ጥናቱ፡፡ ከአሥር ኢትዮጵያውያን አራቱ (37 በመቶ) ፌዴራላዊ ሥርዓት የአገሪቱን አንድነት ለክፍፍል እያደረገ በመሆኑ፣ የተማከለ አስተዳደር አገሪቱ ቢኖራት እንደሚሻል ተናግረዋል ይላል፡፡

ፌዴራላዊ ሥርዓት በኢትዮጵያ የሚቀጥል ከሆነ ምን ዓይነት ፌዴራላዊ መንግሥት እንዲፈጠር እንደሚፈልጉ በጥናቱ የተካተቱ ሰዎች ተጠይቀው ነበር፡፡ ከመላሾቹ ግማሾቹ (49 በመቶ) ብሔርን መሠረት ያደረጉ ክልሎችን ማዕከል ያደረገው የፌዴራል ሥርዓት ቢቀጥል ምርጫቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሌሎች ማለትም 48 በመቶ መላሾች ከብሔር ይልቅ ጂኦግራፊን መሠረት በማድረግ የተመሠረቱ ክልሎች በፌዴራል ሥርዓቱ እንዲፈጠሩ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡

ከተማ ቀመስ በሆኑ አካባቢዎች ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው ዜጎች መካከል ከ44 እስከ 54 በመቶዎቹ ጂኦግራፊን መሠረት ያደረጉ ክልሎች እንዲፈጠሩ ደግፈዋል፡፡ በገጠር አካባቢዎች ግን ከ47 እስከ 51 በመቶዎቹ አሁን ያለውን ብሔር ተኮር ክልላዊ መዋቅር ደግፈውታል፡፡

የሕገ መንግሥት ጉዳዮችን የተመለከቱ ግኝቶቹን የሚያስቀምጠው የአፍሮ ባሮሜትር ጥናት አስገራሚ አኃዞችን ነው ይዞ የመጣው፡፡ ከአሥር ኢትዮጵያውያን መካከል ሰባት (69 በመቶ) የሕገ መንግሥት መሻሻልን ይደግፋሉ ይላል፡፡ ወደ 18 በመቶ ኢትዮጵያውያን ሳይነካ እንዲቀጥል ይፈልጋሉ ይላል፡፡ ወደ 11 በመቶ ኢትዮጵያውያን ደግሞ አሁን ያለው ሕገ መንግሥት ተቀዶ ቢጣል ደስተኛ መሆናቸው ነው የተነገረው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ዘመን በሕግ ገደብ ሊበጅለት ይገባል የሚል ፍላጎት ያላቸው 68 በመቶ መሆናቸውን ጥናቱ ይጠቁማል፡፡ ሕግ የመተርጎም ሥልጣን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ተነጥቆ ገለልተኛ ሆኖ ለሚቋቋም ፍርድ ቤት መስጠት አለበት ያሉ መላሾች ውስጥ፣ 73 በመቶዎቹ ተጨማሪ የሥራ ቋንቋዎች በሥራ ላይ እንዲውሉ እንደሚፈልጉ ተመልክቷል፡፡

መቼና እንዴት ሕገ መንግሥቱ ይሻሻል በሚሉ ነጥቦች ላይ ጥናቱ ግኝቶችን ያቀርባል፡፡ ወደ 1/3ተኛ (34 በመቶ) የሚሆኑት ከመጪው (ማለትም በ2013 ዓ.ም. ተካሂዶ ከነበረው) ምርጫ ቀደም ብሎ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያው ቢደረግ እንደሚበጅ ተናግረው ነበር፡፡ ወደ 33 በመቶ መላሾች በምርጫው ማግሥት ቢደረግ ሲሉ ሌሎች 29 በመቶ ደግሞ ምርጫው ከተካሄደ ከዓመት በኋላ ቢደረግ ይሻላል የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡

አንኳር በሚባሉ የሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች ዙሪያ ያገኛቸውን ምላሾች በተመለከተ ደግሞ፣ በአንቀጽ 39 የተቀመጠው ‹የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል› መብት እንዲሻር የሚፈልጉ 43 በመቶ መሆናቸውን ይጠቅሳል፡፡ ይህ አንቀጽ ባለበት እንዲቀጥል የሚፈልጉ 50 በመቶ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ሰባት በመቶዎች ደግሞ ቢሻርም ሆነ ቢቀጥል ቅር እንደማይላቸው ምላሽ ሰጥተዋል ተብሏል፡፡

የአፍሮ ባሮሜትር ጥናት አረጋገጥኩት እንደሚለው 46 በመቶ መላሾች የግለሰቦች የመሬት ባለቤትነት መብት እንዲሻሻል ይፈልጋሉ፡፡ ከመላሾቹ ወደ 49 በመቶዎቹ የግለሰቦች የመሬት ባለቤት መብት ይሻሻል የሚለውን ሲቃወሙ፣ ቀሪዎቸ አምስት በመቶዎች ግን ሁለቱንም እንደማይደግፉ ነው የተናገሩት፡፡

በሰንደቅ ዓላማው ላይ ብሔራዊ ዓርማ አይኑር ያሉ 37 በመቶ ሲሆኑ፣ ዓርማው እንዳይነካ የሚሉ ደግሞ 52 በመቶ መሆናቸው ታውቋል፡፡ የአዲስ አበባ ጉዳይን በሚመለከት ደግሞ ራሷን የቻለች ክልል ትሁን የሚሉ 35 በመቶ ሲሆኑ፣ ወደ 54 በመቶ ደግሞ የአዲስ አበባን ክልል መሆን ተቃውመዋል፡፡

ከጥናቱ ግኝት ጎልቶ የተነሳው ሕገ መንግሥቱ በምን መንገድ ሊሻሻል ይገባዋል ተብሎ ለቀረበው የተሰጠው ምላሽ ነው፡፡ ወደ 92 በመቶ የሚሆኑና አብላጫ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሕገ መንግሥቱ ሲሻሻል ሁሉም ዜጋ በተዋረድ እንዲመክርበትና ሐሳቡን እንዲሰጥበት ይፈልጋሉ ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -