Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አዳማጭ ጠፋ እንጂ…!

ሰላም! ሰላም! ውሎና አዳሩ፣ እርሻው፣ ንግዱ፣ ትምህርቱ፣ መውጣትና መውረዱ፣ ጨብጦ መበተኑና አፍስሶ መልቀሙ እንዴት ይዟችሁ ሰንብቷል? አንዳንዴ ሰላምታ ስትሰጥ ታዳላለህ የሚሉኝ ሰዎች ቁጥር ከጨመረ ወዲህ፣ ሳይሠራ የሚያካብተውንና ለፍቶ የማያልፍለትን እኩል ለማስተናገድ ጥረት ማድረግ ጀመርኩላችሁ። ደግሞ ለሰላምታ? አይከፈልበት ምን ይጨንቀኝ ብላችሁ ነው? ስንት ለሚያስጨንቀን ኑሯችንና ለታይታ ያህል ስለአኗኗራችን ለሚጨነቀው መንግሥታችን ይብላኝ እንጂ፣ በሰላምታ ብቻ ስንወጣ ስንገባ የሚያጋጥመንን የሰውን ኩርፊያስ ከተገላገልነው እሰየው ነበር። የሚገርማችሁ ግን አንዳንዱ የዘንድሮ ሰው ቁጭ ብሎ መብላቱ ሳያንሰው ስገዱልኝ ሲላችሁ አላፍር ማለቱ ነው። ለነገሩ ድሮ ከቀሩት ብዙ ነገሮች ውስጥ አንዱ ማፈር አይደል? ለዚህም እኮ ነው ሥልጣን ላይ፣ ፍቅር ላይ፣ እምነት ላይ እኩይ ነገርን የሚያሳስብ ድፍረት የበዛው። ‹‹ድፍረት ማፈርን በተካበት ፍጥነት ዕድገትን ቢተካው አሁን ምን ነበረበት?›› ብዬ ብጠይቀው ምሁሩን የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ምንም ከማለት በቀር የምለው ምንም የለኝም…›› ብሎ ኩም አደረገኝ። እኔ ደግሞ በኑሮ ውድነት ምክንያት ብሩ አልበረክትልን እያለ እሱን ብቻ ያጣን መስሎኝ ነበር። ለካስ ለአንኳር ጥያቄዎችና ትዝብቶቻችንም መልስም ጭምር ነው ያጣነው። ልብ ካላችሁ እንግዲህ፣ ‹‹እንዲህ መልስ ከኑሮ እኩል በተወደደበት ጊዜ እንዴት ይሆን የዘንድሮ ተማሪ ፈተና እያለፈ ተመራቂ የሚበዛው?›› ብላችሁ ትጠይቃላችሁ። መልስ የሌለው ጥያቄና መልስ የማይሰጥ የእኔ ብጤ ከበዛባችሁ ነው፡፡ ለነገሩ ነጋዴው፣ አርሶ አደሩ፣ ወዝአደሩ፣ የቢሮ ሠራተኛው፣ ኢንቨስተሩ፣ ወዘተ በርካታ ጥያቄዎች ታቅፈው ተቀምጠዋል፡፡ አዳማጭ ግን የለም!

እኔና ማንጠግቦሽ ሰሞኑን መንደር ውስጥ እየተወራ ስላለው የሙስና ወሬ ስንጨዋወት ነበር። ከዕድር ገንዘብ ላይ 40,000 ብር ጠፋ በመባሉ እነ ባሻዬ በከባድ የሐሜት ማዕበል እየተናጡ ነው። እንዳለ መንደርተኛው ባሻዬንና በአጠቃላይ የዕድሩ ተጠሪዎችን ከገንዘቡ መጥፋት ጋር አያይዟቸዋል። አንድን ጉዳይ ማጣራት ሞቱ የሆነው የመንደሬ ሰው ብዙ ነገር እያለ ነው፡፡ ‹‹መንግሥት ለልማት ተደራጁ ቢል ለመዝረፍ የሚደራጅብን እኮ እየጨመረ ነው…›› እያለ የአካባቢው ሰው እነ ባሻዬን ሲያንገዋልላቸው ብሰማ የሐሜቱ መነሾ ምን ይሆን እያልኩ ተብሰለሰልኩ። ማንጠግቦሽ አገር ሰላም ብላ፣ ‹‹ቆይ ግን ሰው ከሠርቶ አዳሪነት ይልቅ ሰርቆ አዳሪነት እንዲህ የባሰበት ለምን ይሆን?›› ስትል አዛውንቱ ባሻዬ ከተፍ አይሉ መሰላችሁ፡፡ ‹‹አይ ማንጠግቦሽ! ከሠርቶ በላተኛነት ይልቅ ሌብነት አዋጪና ጠያቂ የለሽ ሆኖ ሲገኝስ?›› ብለዋት፣ ‹‹…የሚሮጠው ብዙ ቢሆንም የሚሰበስበው ጥቂቱ እንደሆነ እያየን አይደለም ወይ?›› ብለው እኔኑ ጠየቁኝ። ‹‹እውነት ነው…›› አልኳቸው እኔም ፈጠን ብዬ። ‹‹እሱ የከፈተውን ጉሮሮ እሱ ሳይዘጋው አያድርም ሆኖ ይህችን ታህል እንተነፍሳለን…›› አሉ ትንሽ ዝም ብለው ቆዩና በረጅሙ እየተነፈሱ። ነገር ገብቷቸዋል ማለት ነው!

‹‹ባሻዬ ለመሆኑ ጠፋ ስለሚባለው ገንዘብ ምን ይላሉ?›› አለቻቸው ማንጠግቦሽ ነገር መቋጠር አላስችል ብሏት። ‹‹ኧረ ምንም የጠፋ ገንዘብ የለም ልጄ። ዕድሩ ሁሉንም በአግባቡ እንደተጠቀመበት በኦዲት ተረጋግጦ ሒሳብ መዝገቡ ላይ በትክክል ሠፍሯል። ቁምነገር ጠፍቶ ቀልድ በበዛበት ዘመን ሰው ስለአገሩና መንደሩ በፈጠራ ወሬ መከበቡን ላስታውስሽ ይሆን?›› ብለው ፈገግ አሰኙን። ወዲያው ከጉያቸው ላጥ አደረጉና የዕድሩን ሒሳብ መዝገብ ቢያሳዩን እንዳሉት ሆኖ አየነው። ‹‹መቼም ጊዜው የሚያሳየን ብዙ ነውና የወሬ ፈጠራ ውድድር እንደ ቶክሾው ተዘጋጅቶ እንዳንመለከት እፈራለሁ…›› ያለው ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነበር፡፡ ሳልነግራችሁ ከባሻዬ ጋር ስለኑሮ ስንጫወት ምን አሉኝ መሰላችሁ? ‹‹ልጄ እኔ የማዝነው እንደ እናንተ ላለው ነው እንጂ ለአንድ ለራሴ በቂ ነኝ…›› አሉኝ። እኔ ደግሞ በቃ እኚህ ሰው በደህና ቀን ቋጥረዋል ማለት ነው እያልኩ ስጠብቅ፣ ‹‹ለመሆኑ የሽንብራው ጥርጥር የዛፎቹ ፍሬ፣ የትም የትም ዞሬ ትዝ አለኝ አገሬ…›› የሚለውን ዘፈን ታስታውሰዋለህ? አሉኝ። ‹‹አዎን ባሻዬ…›› አልኳቸው እኔ ነኝ ሊሉኝ ይሆን እያልኩ እየተጠራጠርኩ። በዚህ ዘመን መሆን ሳይሆን መምሰል በቂ ነው ተብሏል መሰለኝ አርቲስት ነኝ ባዩ በዝቶብናል። ባሻዬ፣ ‹‹ምንም ቢሆን አገርንና ወገንን መበደልና መዝረፍ ተገቢ አይደለም…›› ነው ያሉኝ። ልክ ናቸው!

ከባሻዬ ጋር ተለያይተን ወደ ጉዳዬ ሳመራ አንድ ልጅ እግር ሲበር መጣና በራሪ ወረቀት ሰጥቶኝ ከነፈ። ቆም ብዬ ሳነበው፣ ‹‹እንዳትቀሩ ብትቀሩ ይቀርብዎታል…›› ብሎ ሲጀምር ምን ይሆን በማለት ጓጓሁ። ግን ገና ከሥሩ ያለውን ጽሑፍ ሳይ አዲስ የሚከፈት ዘመናዊ ሥጋ ቤት ማስታወቂያ መሆኑ ገባኝ። በነፃ ያበላ ይመስል የዘንድሮ ነጋዴ ማስታወቂያው ማስፈራሪያ እየሆነ መምጣቱ አስገርሞኝ ነበር። በነገራችን ላይ አንድ ጡረታ የወጡ ደላላ ወዳጄ ስለጊዜው ሠርግ አጠራር ያጫወቱኝን ልንገራችሁ። ‹‹አንበርብር ማግባትስ አሁን ነበር…›› አሉኝ ድንገት የቆጫቸው በሚመስል ሁኔታ። ‹‹እንዴት?›› ብላቸው፣ ‹‹ኧረ አንድ ቦታ የሆነውን ሰምቼ ገርሞኝ ነው፡፡ ወጣት ተጋቢዎች ናቸው አሉ። ሠርጋቸውን በሥራ ቀን ያደርጉትና ለ100 ሰው የሚሆን ቦታና ምግብ አዘጋጅተው ለአንድ ሺሕ ሰው የጥሪ ካርድ ይበትናሉ፡፡ ስለመጡ እናመሠግናለን ከሚል ተጨማሪ ካርድ ጋር አርፍዶ ለሚመጣ ቦታ የለንም ብለው ያስታውቃሉ። ለካ ዘጠኝ መቶው በእርግጠኝነት ሠርጋቸው ላይ እንደማይገኝ ያውቁታል። የሥራ ቀን ነዋ፡፡ እንግዲህ አልጠሩም እንዳይባል መሆኑ ነው እኮ። ተመልከት የዘመኑን ሥራ…›› ብለው አጀብ ያሰኙኝ ታወሰኝ። ያለ ገቢ ግብርና ቫት የሚበላበት ዋናው ሥፍራ ሠርግ ቢሆንም፣ እሱም መቆጠብ ተጀመረበት ማለት ነው። ቁጠባን አዲስ የሚወለድ ሕፃን ሳይቀር እያወቀው እያየን ሰው ካለው ላይ መቆጠቡ ለምን ይገርመን ይሆን? እንጃ!

ያው እንደምታውቁት አሁን የምንሰማው ክፉ ወሬና ዜና ዓይነትና መልኩን እየለዋወጠ ጉድ ማስባሉን ቀጥሏል። በቅርቡ በአሜሪካ በጦር መሣሪያ በሰዎች ላይ ስለሚፈጸመው ጭፍጨፋ ከባሻዬ ልጅ ጋር ስናወራ፣ ‹‹ሁላችንም በአሜሪካ ስለደረሰው በሰብዓዊነት ልባችንም ቢያዝንም፣ የእኛም አገር ሁኔታ በጣም እያሳሰበን ወዴት እየሄደች እንደሆነ ለመረዳት ያቃተን መስለናል…›› አለኝ። ‹‹እዚያም እዚህም ሰብዓዊነት ጠፍቶ ሞት ከበረከተ እንዴት ልንሆን ነው?›› ስለው፣ ‹‹ወዳጄ የደም ነጋዴዎች እኮ አንዴ በሥልጣን፣ ሌላ ጊዜ በንግድ ውስጥ፣ ሲላቸው ደግሞ እምነት ውስጥ ተደብቀው ነው የሚፈጁን…›› ሲለኝ ግር ያለኝ ነገር በዛ። ‹‹እንዴት?›› አልኩት ግራ መጋባቴን በሚመሰክር ስሜት። ‹‹እንዴት ማለት ጥሩ ነው፡፡ ወዳጄ ካፒታሊስቶቹ የመሣሪያ አምራቾች የፖለቲከኞችን እጅ ጠምዝዘው ከአቅም በላይ የሆኑ ጠመንጃዎችን እንደ ብስኩት በየመደብሩ ያስቸበችባሉ፡፡ እኛ ዘንድ ደግሞ በሕገወጥ የጦር መሣሪያ አዘዋዋሪዎችና ተባባሪ ሹማምንት አማካይነት ታጣቂዎች በዘመናዊ መሣሪያዎች ይፈጁናል…›› ሲለኝ ነገሩ ገባኝ። ባሻዬ በበኩላቸው፣ ‹‹እግዚኦ ጊዜ! እግዚኦ ዘመን!›› እያሉ ዘመኑን እንደ እርኩስ መንፈስ ሲገስጹት ይውላሉ። ማንጠግቦሽ በበኩሏ፣ ‹‹አሁን በዚህ ጊዜ ሰው እንዴት ይወልዳል?›› እያለች ስትብሰለሰል ካልወለድን ብዬ መቆሚያ መቀመጫ ያሳጣኋት ታስመስለኛለች። ለነገሩ አንድስ ቢሆን ዘር መተካቴ የት ሊቀር ነው? እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ዓይኔን በዓይኔ ካላየሁ ምን የሚታይ ነገር አለኝና እንዲሁ እቀራለሁ? ዕድሜ ይስጠን!

የልጅን ጉዳይ ካነሳን ላይቀር በዚህ ዘመን ወልዶ ስለማሳደግ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ያወራሁትን ባጫውታችሁ አይከፋኝም። ለመሆኑ ሳምንት እየተቀጣጠርን የምንገናኘውስ ለዚህ አይደል? አንድ ጠና ያሉ ሰው ቤታቸውን እንዳከራይላቸው ጠርተው አሳይተውኝ ካበቁ በኋላ፣ ‹‹ይኖርበት የነበረው ልጄ ነበር። ምን ዋጋ አለው አገሩን በአጭር ጊዜ አጥለቅልቆ ትውልድ እየቀጨ ያለው ሐሺሽ አሳብዶ ገደለብኝ። መቼም የወለደ መከራው ብዙ አይደል? እንዳይሆን ሆኖ ከቀረበት አንስቼ ቀበርኩት። አሁን ቤቱን ማንም እንዲኖርበት ስለማልፈልግ ማከራየቴ ነው…›› ሲሉኝ ዕንባቸው ንግግራቸውን ቀድሞ ዱብ ዱብ አለ። እኔም ክፉኛ ስላሳዘኑኝ በዕለቱ ላከራይላቸው ስማስን አንድ ጎልማሳ ተከራይ አገኘሁና ስለወልዶ ማሳደግ አጀንዳ ተነጋገርን። መቼም ደላላ በየሥራው መሀል የማይከፍተው ኅብረተሰባዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አጀንዳ የለም። እኔማ ደላሎች የተደራጁ ቀን የመንግሥትን ተወያይቶ የማወያየት ደካማ ባህል ክፉኛ ማስተቸታቸው አይቀርም እያልኩ የማልነግረው ሰው የለም። ለራስ ሲቆርሱ የሚለኝ ይበዛል እንጂ። በነገራችን ላይ የቲቪ ላይ ውይይቶችን አያችሁ? ‹‹አንተ ቅድም እንዳልከው፣ ቀደም ሲል እንደ ጠቀስከው…›› የሚሉ ፖለቲከኞች በጣም ሲያሳዝኑ? ምን ማሳዘን ብቻ ያናድዳሉ እንጂ!

እናም ጎልማሳው ተከራይ ሰውየው የነገሩኝን ታሪክ አጫውቼው ሳበቃ በጣም አዝኖ፣ ‹‹የሚገርምህ ትምህርት ቤት፣ ሠፈር ውስጥ፣ በየመዝናኛ ቦታው የምናየው ነገር እኮ ችላ መባል የለበትም፡፡ የትኛውን ማስቀደም እንዳለብን አላውቅ ብለን እስከ መቼ እንደምንዘልቅ አይገባኝም…›› ካለኝ በኋላ፣ ‹‹በነገራችን ላይ ሦስት ጊዜ የሚከራዩ ቤቶችን አግኝቼ ምን እንደተባልኩ ታውቃለህ?›› አለኝ። ‹‹ምን ተባልክ?›› ስለው፣ ‹‹አሁን ተከራየ እየተባልኩ ተመለስኩ…›› ብሎኝ የተከራዩ ቁጥር መጨመርና የቤት ኪራይ ጡዘት እንዳስገረመው አብራራልኝ። ‹‹ይገርምሃል ይኼ ኮንዶሚኒየም የሚባለውማ የኢንቨስተሮች መኖሪያ ከሆነ ቆየ። ባለአንድ ክፍል ቤት እስከ 15,000 ብር መከራየት ጀምሮልሃል። ለነገሩ ከመሬት ተነስቶ አይደለም አሉ እንዲህ እየሆነ ያለው?››› ሲለኝ እኛ ላይ ስለሚወራው ያላግባብ የኪራይ የማናር ሐሜት ሊመጣ መስሎኝ ደነገጥኩ። ዓይጥ በበላው ዳዋ ከመመታቱ በፊት ስንቴ ደንግጦ ይሆን? ‹‹እስኪ ንገረኝ?›› ስለው፣ ‹‹ሁለትና ሦስት ቦታ መቅበጥ የሚያምረው ለቅምጡ ሲል አጉል ክፍያ አከራዩን እያስለመደ ስላስቸገረ ነው የሚል ወሬ ሰምቻለሁ…›› ሲለኝ፣ ‹‹ነው?›› አልኩና ጭጭ አልኩ። ላይጨርስ የሚጀምር በበዛበት ጊዜ የማያልቅ ነገር መጀመር ትርፉ ድካም አይደል? በጣም እንጂ!

መሰነባበቻችን እየደረሰ ነው። ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር ቆሜ የተከራይ ቁጥር መጨመሩ አስደንቆኝ ሳወራው፣ ሳለሁ ሦስት ጎረምሶች በሩቁ ሰውን እየተሰናበቱ ቅልና ጨርቅ ሳይዙ ሲጓዙ አየን። የጎረምሶቹን ሁኔታ ስንከታተል ሳለን፣ ‹‹ዓለም ልትጠፋ ስለሆነ ደህና ሁኑ…›› እያሉ የሚያውቁትንም የማያውቁትንም ሰው ሲሰናበቱ ሰማን። ‹‹ጉድ ፈላልህ ምፅዓት እንዲህ በቆምንበት ሊመጣ ይሆን?›› አልኩት። ‹‹ኧረ ተወኝ አንበርብር። እኔስ አሁን ምን ታከተህ ብትለኝ ሰው መኖር ሲደብረው እየፈጠረ ለሕይወት ማድመቂያ የሚነሰንሰው ቅመም አዘል ወሬ ነው…›› ከማለቱ ጎረምሶቹ አጠገባችን ደርሰው እኛንም ደህና ሁኑ ይሉን ጀመር። ‹‹አንበርብር እንዲህ እያሉ ሽብር የሚነዙ ሰዎችን ቻይና ማሰሯን ነግሬሃለሁ?›› ቢለኝ፣ ‹‹ታዲያ ምነው የእኛ ፖሊሶች እነዚህን ዝም ብለዋቸው አለፉ?›› ብዬ በሩቁ ሁለት ፖሊሶችን ጠቆምኩት። ‹‹አይ አንበርብር! እዚህ አገር በነገ እመን አትመን ማንም ጉዳዩ አይደለም። ዋናው ነገር በሕገ መንግሥቱ ማመንህ ነው። መንግሥትንና ሕገ መንግሥትን ካልተተናኮስክ ስለነገ ሰበክ አልሰበክ ማን ግድ አለው? ነፃነት ከዚህ በላይ ከየት ይምጣልህ?››› ብሎኝ እየተሳሳቅን ወደ ግሮሰሪያችን ጉዞ ጀመርን። ምን ይደረግ ታዲያ!

ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ከቀልደኛነቱ ባሻገር በነገር ወጋ ማድረግ ስለሚወድ እኔም ወደዋለሁ፡፡ ዕውቀቱን የሚፈልግ ካለ ለማጋራት ወደኋላ የማይል በመሆኑም አከብረዋለሁ፡፡ ስንቱ ከእነ ዕውቀቱ ማጀት ውስጥ ተደብቆ የቆረፈደ ፖለቲካ ውስጥ ተዘፍቆ ከሐሜት አልወጣ ሲል፣ እሱ የትም ቦታ የመሰለውን ይናገራል፡፡ ያልተጨበጠና መሬት ያልረገጠ ነገር ሲገጥመውም በፅናት ይጋፈጠዋል፡፡ ላለፉት በርካታ ዓመታት ሳውቀው ለግል ጥቅም፣ ክብር፣ ዝና ወይም ለርካሽ ተወዳጅነት ደንታ የለውም፡፡ ከስንት ምሁራን ጋር ውሎ ማምሸት እየቻለ የእኔ ደላላው ወዳጅነትም ያስደስተዋል፡፡ ‹‹ማን ከየት ይምጣ፣ ከማን ይወለድ፣ ምን ዓይነት አስተሳሰብ ይኑረው፣ የትኛውን አቋም ያራምድ እኔ የማከብረውና የምጠጋው በሰውነቱ ብቻ ነው…›› ስለሚለኝ ሁሌም ባርኔጣዬን በአክብሮት አነሳለታለሁ፡፡ የሰው ልጅ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት እየተዳፈሩ የማግለልና የማናናቅ ዘመቻ ውስጥ ለሚገቡ ከንቱዎች ትልቅ ምሳሌ ነው እላለሁ፡፡ ግሮሰሪያችን ገብተን ያላበው ቢራ ካዘዝን በኋላ፣ ‹‹ምነው ሁሉም ሰው እንዳንተ በሆነ?›› አልኩት፡፡ ሳቅ ብሎ እያየኝ፣ ‹‹ውድ ወዳጄ አንበርብር ምንተስኖት ሁሉም ሰው አንድ እንዲሆን አትጠብቅ…›› አለኝ፡፡ ‹‹ለምን?›› አልኩኝ ኮስተር ብዬ፡፡ የባሻዬ ልጅ አሁንም በፈገግታ እያየኝ፣ ‹‹ለምን መሰለህ? ሰዎች ስንባል በተፈጥሮ የተለያዩ ፍላጎቶች አሉን፡፡ ለምሳሌ አንተ ከውበት ጠይም ዘለግ ያለች፣ ከሙዚቃ ትዝታን፣ ከቀለም የካፖርትህንና የባርኔጣህን ዓይነት ግራጫ ትወዳለህ፡፡ እኔ ደግሞ በተቃራኒው ነኝ፡፡ የምንግባባው ግን ለልዩነቶቻችን ክብር ስንሰጥ ነው…›› ሲለኝ ከሚገባው በላይ ገባኝ፡፡ ወገኖቼ ‹‹ከእኔ ወዲያ ላሳር›› እያሉ የሚፎክሩብንን ማን ያስተምርልን? አዳማጭ ጠፋ እንጂ ብዙ የምንለው ነበር፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት