በአበበ ፍቅር
ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ የተሰቃዩበት ነው፡፡ ችግሮቹ እየተባባሱ ነው፡፡ በትግራይ ያለው ጦርነት አበቃ ሲባል፣ በአማራ ክልል ሌላ ግጭት ተፈጥሯል፡፡ በኦሮሚያም ቢሆን ግጭቱ እንዳለ ነው፡፡ ዛሬ ሰው ከከተማው ወጥቶ ለመሥራት፣ ለመነገድ፣ ለመታከምም ሆነ ለመዝናናት ሥጋት ውስጥ ገብቷል፡፡ ግጭቶቹና መፈናቀሎቹ ሞትን ጨምሮ የተለያዩ ቀውሶችን ማስከተላቸውም አልቀረም፡፡
በግጭት ቀጣና ውስጥ የነበሩ ሰዎች ሕይወታቸውን ለማቆየት ወደ ተለያዩ አቅጣጫ ማማተራቸው ግዴታ ነው፡፡ በእነዚህና ሌሎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ገፊ ምክንያቶች በተለይ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረጉ ፍልሰቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ስለመምጣታቸው አመላካቾች ሲነሱ ቆይተዋል፡፡
በአገሪቱ ተባብሶ በቆየው የሰላም ዕጦት ምክንያት ከተፈናቀሉ በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች አብዛኞቹ ወደ ከተማ በተለይ ደግሞ ርዕሰ መዲና ወደሆነችው አዲስ አበባ እንደሚፈልሱ ሕፃናትና ልጆቻቸውን ይዘው በየጎዳና የሚታዩ አባቶችና እናቶች ምስክር ናቸው፡፡
ገፊ በተባሉ ምክንያቶች ፈልሰው ወደ አዲስ አበባ ከሚገቡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ሠርተው ራሳቸውን ለመለወጥ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በአካባቢያቸው በሚከሰተው የሰላም ዕጦት ተረጋግተው መሥራት ስላልቻሉና የነበራቸው ጥሪት በመዘረፍ አልያም በጦርነት ወቅት እንደወደመባቸው ይገልጻሉ፡፡ በተሳሳተ መረጃ በአጭር ጊዜ ሠርተው የመለወጥን ህልም አንግበው የሚመጡ እንዲሁም ልመናንም ተስፋ አድርገው ከቀዬአቸው የሚነጉዱም አሉ፡፡
በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ወደ መዲናዋ የሚገቡ ዜጎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱ፣ ከተማዋን አጨናነቁ ከመባል አልፈው ‹‹በትረ መንግሥትን እስከ መነቀቅ ደርሰዋል›› ተብለው ተፈርጀው በመጣ እግራቸው ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ የሚያደርጉ ድርጊቶች እየተፈጸሙ መሆኑንም የሚናገሩ አልታጡም፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በመጋቢት 2015 ዓ.ም. ‹‹መንግሥትን በኃይል ለመጣል ከአንዳንድ ክልሎች ከፍተኛ ፍልሰት›› እየተደረገ መሆኑን ማንሳቱም ይታወሳል፡፡
የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አዲስ አበባን ‹‹የሁከት አውድማ›› ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን፣ ይህም ለፀጥታ ሥጋት እንደሆነና ‹‹ሥርዓት አልበኝነትና የመሬት ወረራ›› እንደተስፋፋም ገልጸው ነበር፡፡
ምንም እንኳን ወደ መዲናዋ የሚገቡ ዜጎች ጥበቃና ቁጥጥር እየተደረገባቸው ቢቆይም፣ በከተማ አስተዳደሩ ከላይ የተገለጸው ሐሳብ ከቀረበ ጀምሮ ቁጥጥሩ ተጠናክሮ ከነአካቴውም የአዲስ አበባ መታወቂያ ከሌላችሁ መግባት አትችሉም ተብለው እንደነበር በወቅቱ ሲዘገብ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ባሻገር እህልና መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች እንዳይገቡ ሲደረጉ እንደነበርም ይታወሳል፡፡
ይህም በመዲናዋ ላይ በተለይም የጤፍና የስንዴ ዋጋ በእጥፍ እንዲጨምር አድርጓል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የአዲስ አበባ መታወቂያ ካልያዛችሁ አትገቡም በሚል የነበረው ገደብ አንፃራዊ መሻሻል ቢኖረውም፣ አሁንም የአዲስ አበባ ኬላዎች ከመቼውም በላይ ተጠናክረው እየተጠበቁ ነው፡፡ በተለይ ከሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ተነስተው ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ ወገኖች በኬላ በሚገኙ ኃይሎች ድብደባና እንግልት ይደርስባቸው እንደነበር መግለጻቸውም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡
ይህ ሁሉ እንቅስቃሴ ታልፎ በአሁኑ ወቅት በመዲናዋ ጎዳናዎች ‹‹ሠርተን መብላት ስለማንችል እርዱን፣ ቤታችን ፈርሶብን መጠጊያ አጥተን ነው ተባበሩን›› የሚሉ ሕፃናት፣ አረጋውያን፣ እናቶችና ወጣቶች እየተበራከቱ ነው፡፡
‹‹አዲስ አበባ እንደተወጠረ ፊኛ ሆናለች፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን የሚሰነዝሩ አሉ፡፡ በተለይ አንዳንድ ጎዳናዎቿ ጠጠር መጣያ እስከሚያጡ በሰዎች ሲጨናነቁ ይስተዋላል፡፡
የመንገድ ዳርቻዎቿም ከጊዜ ወደ ጊዜ መደበኛ ባልሆኑ የጎዳና ነጋዴዎች ሲጨናነቁ፣ በደንብ አስከባሪዎችና በእነዚህ ሕገወጥ በተባሉ ነጋዴዎች መካከል ግጭት ሲፈጠር ነበር፡፡
በ1990ዎቹ ማብቂያ የተቋማትን ጥጋ ጥግ ይዘው የተሠሩ የአርከበ ሱቆችን ጨምሮ በየጎዳና ያሉና ለከተማዋ ውበት፣ ለመንገድና ለትራንስፖርት እንዲሁም ለፀጥታ ችግር ሆነዋል የተባሉ ሱቆች በአሁኑ ወቅት እየተነሱ ነው፡፡
እነዚህና በትልልቅ ሕንፃዎች ሥር፣ በተለያዩ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ አካባቢዎች እንዲሁም በተለያዩ ጥጋጥጎች ሸራን በመወጠር መደበኛ ባልሆነና የከተማዋን ገፅታ በሚያበላሽ መልኩ ሥራቸውን የሚያከናውኑ ሰዎች ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
ከእነዚህ ውስጥም ቀደም ሲል መንግሥት ‹ሕገወጥ ከምትባሉ ሕጋዊ ሆናችሁ በጋራ ተሰባስባችሁ ለመንግሥት ግብር ከፍላችሁ ሥሩ› ብሏቸው ፈቃድ ተሰጥቷቸውና ሪቫን ተቆርጦላቸው ሲሠሩና የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን ሲገፉ እንደነበር የነገሩን አሉ፡፡ በተጠየቁት መሠረትም በሠሩበት ልክ የግብር ግዴታቸውን ሲገብሩ መቆየታቸውን ያስረዳሉ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ያሉ የመኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ ጥቃቅን የንግድ ተቋማት ‹‹ሕገወጥ ናችሁ›› ተብለው እየፈረሱና ብዙ ሰዎች ከጎዳና እየወጡ እንደሆነ ይስተዋላል፡፡
እነዚህ አሁን ላይ ‹‹ሕገወጥ›› ናችሁ ተብለው እየፈረሱ ካሉ ንግድ ቤቶች በአንድ ወቅት በከተማዋ ከንቲባ ሕጋዊ ዕውቅና ተሰጥቷቸው እንደነበርና አሁን ግን ‹ያኔ በስህተት ነው የሰጠናችሁና መልሳችሁ ትለቃላችሁ› ተብለው ወደ ቀደመ የተጎሳቆለ ኑሮ ለመመለስ እንደተገደዱ ይናገራሉ፡፡ ይህ ዕጣ ፈንታ ከደረሰባቸው ነጋዴዎች መካከል አንዱ፣ ከሦስት ዓመት በፊት እሱና 250 የሚሆኑ መሰል ጓደኞቹ በወቅቱ የከተማዋ ከንቲባ በነበሩት ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ጥሪ ተደርጎላቸውና ‹‹መገናኛ ተርሚናል የገበያ ማዕከል›› በሚል አቋቁመው እንዲሠሩ ተፈቅዶላቸው እንደነበር ይናገራል፡፡
በተፈቀደላቸው ሥፍራ የተለያዩ የአዋቂና የልጆች አልባሳት በመሸጥ ኑሯቸውን ሲገፉ እንደነበር የሚናገረው ወጣቱ፣ ሳምንት ባልሞላው ማስጠንቀቂያ በእጃቸው ያለውን በርካታ ልብስ ገንዘባቸውን እንደያዘ ያለ ዋስትና ቦታውን ለቀው እንዲወጡ መደረጋቸውን ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡
ሥራ ከመጀመሩ በፊት በከፋ ሕይወት ውስጥ ሲኖር እንደነበር የተናገረው ወጣቱ፣ ቀደም ሲል መንግሥት ባደረገው መልካም ተግባር ወደ ሥራ ተሰማርቶ በመሥራት ሁለት ልጆችንና ዕርዳታ የሚሹ ወላጆቹን እስከ መደገፍ ተጉዞ እንደበር ተናግሯል፡፡ እየሠራ ባለው ሥራም በየዓመቱ የተጠየቀውን የገቢ ግብር ለአገሩ ገቢ እያደረገ እንደነበር ተናግሮ፣ በአሁኑ ወቅት ግን ‹‹ምንም ባላወቅነው ሁኔታ ዕቃችሁን ነገ ካላነሳችሁ አፍራሽ ኃይሎች መጥተው እንዳይወርሷችሁ ነው የተባልነው፤›› ብሏል፡፡
‹‹እንድናፈርስ ትዕዛዝ የሚሰጠን ሌላ ለማፍረስ የሚመጣው አካል ደግሞ ሌላ ነው›› ያለው ወጣቱ፣ ዕቃው ከመወረሱ በፊት በአንድ ጀምበር ከቦታው አስለቅቆ ግማሹ፣ ወደ መኖሪያ ቤት የወሰደ ሲሆን፣ ኑሮውን ለመደጎም ከደንብ አስከባሪዎች ጋር እየተሯሯጠ በመሸጥ ላይ እንደሆነ ተናግሯል፡፡
‹‹ማን እንደሚያፈርሰውና ለማን አቤት እንደሚባል አላወቅንም›› የሚለው ወጣቱ፣ አፍርሱ ብለው ለሚመጡ ሰዎች ጥያቄ ብናቀርብም መጀመርያ አፍርሱና እንነጋገራለን የሚል ምላሽ እንደሚያቀርቡላቸው ለሪፖርተር ገልጿል፡፡
‹‹ምናልባት የከተማዋን ውበት ባልጠበቀ መልኩ ነው የተሠራው ብላችሁ ከሆነ እናንተ በምትፈልጉት መልኩ እንሥራው ወይም ቦታው ለሌላ ልማት ተፈልጎ ከሆነ ምትክ ቦታ ስጡን በማለት ጠይቀን ነበር፤ ነገር ግን ማንም ሊሰማን ፈቃደኛ አይደለም፤›› ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
የሚሸጡበት ጊዜያዊ ቦታ እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም፣ ምላሽ አለማግኘታቸውን፣ ወቅቱ ዝናባማና መጭውም ክረምት እንደመሆኑ እንዲሁም የኑሮ ውድነቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ በመምጣቱ መኖሪያ ቤትንና የንግድ ቦታን ‹‹ሕገወጥ ናችሁ›› በሚል ምክንያት ከቤት ንብረት ማፈናቀሉ ችግሩን ሊያባብሰው ይችላል እንጂ ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን አይችልም፣ መንግሥት መፍትሔ ቢያስቀምጥ የተሻለ ይሆናል ሲል ሐሳቡን ሰጥቷል፡፡
አቶ አባተ ኃይሉ በአዲስ አበባ ኮተቤ አካባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ በከተማዋ እየተከናወነ ያለውን የጎዳና ንግድ ማስነሳትና ፈረሳ አስመልክተው ‹‹ጥሩ ጎንም መጥፎ ጎንም›› እንደሚታያቸው ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ጥሩ ጎን ነው›› ያሉትን ሲያብራሩ፣ አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫና ዋና ከተማ እንደመሆኗ በየቦታው ያሉ የሸራ ቤቶች፣ ጩኸትና ግርግር የሚፈጥሩ የመንገድ ዳር ግብይቶች አቅጣጫ ሊቀመጥላቸው ይገባል ይላሉ፡፡
አቶ አባተ አሁን ላይ እየታየ ላለው የተቀናጀ ቤት ፈረሳና የዜጎች መንገላታት መንግሥትን ‹‹ተጠያቂ›› ነው ይሉታል፡፡ አመክንዮአቸው ደግሞ የብልፅግና መንግሥት ወደ ሥልጣን በመጣ ማግስት ከተማዋ የተወረረች ያህል ሁሉም በጉልበቱ ያገኘውን ቦታ ሲያጥር፣ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሕገ ወጥነት ሲስፋፋ በወቅቱ ዕርምጃ አለመወሰዱ አሁን ለተፈጠረው ችግር መነሻ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡
‹‹መንግሥት በወቅቱ ሕገወጥ የሆነ አካሄድ የትም አያደርስም ማለት ሲገባው፣ በዝምታ ሲመለከት ነበር፤›› የሚሉት አቶ አባተ፣ ምርጫ በተቃረበበት ወቅት አሁን ላይ የፈረሰባቸው ግለሰቦች ብዙዎቹ በመንግሥት ተደራጁ ተብለው ሲሰጣቸው እንደነበር በማስታወስ ተናግረዋል፡፡
መንግሥት ምርጫ ሲቃረብ ማባበያ የሚመስል ነገር ማቅረብ፣ ምርጫ ሲያልፍ እንደ ሕፃን ልጅ የሰጠውን መቀማት ተገቢ ያልሆነና ዘላቂ መፍትሔን ሊያስገኝ የማይችል መሆኑንም ያክላሉ፡፡
እንደ አቶ አባተ አስተያየት ቤት ማፍረስ ወይም አለማፍረስ ብቻ ላይ ማተኮር ተገቢ አይደለም፡፡ የመኖሪያ ቤታቸውና የመንግሥት ግብር ሲገብሩበት የነበረ የንግድ ተቋም ለፈረሰባቸው ዘላቂ ምትክ ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል ባይ ናቸው፡፡
በየመንገድ ዳሩ ሸራ ዘርግተው የሚሠሩት መነሳታቸውን ባይቃወሙም፣ ሲሠሩ መቆየታቸው ለሥራ ያላቸውን ተነሳሽነት አመላካች በመሆኑ፣ አማራጭ የሥራ ዕድል ቢፈጠርላቸው የተሻለ እንደሚሆንም ይጠቁማሉ፡፡
‹‹በነበረው አካሄድ ቢቀጥል ሙሉ አዲስ አበባ በሸራ መሸፈን ነበር የሚገጥማት፤›› ያሉት አስተያየት ሰጪው፣ መንግሥት እያደረገ ያለው ነገር ለከተማዋ ውበት ተመራጭ ቢሆንም፣ አሠራሩ ግን ጥድፊያ የበዛበትና በመንግሥት በኩል በቂ ዝግጅት ያልተደረገበት እንደሚመስል ይስተዋላል ብለዋል፡፡ ‹‹ቤትን ያህል ነገር ሲፈርስ፣ ሥራን ያህል ነገር በአንድ ቀን ሲታጣ ለሚመጣው ችግር ቀድሞ መፍትሔ አለመበጀቱን›› ያሳያል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ ዝናቡ መበርታቱን፣ መጪው ክረምት መሆኑን፣ በከተማዋ በአጠቃላይም በአገሪቱ የኑሮ ውድነት መኖሩን በመግለጽም፣ መሥሪያ ቦታቸውም ሆነ መኖሪያ ቤታቸው የፈረሰባቸው ዜጎች በቀላሉ ቤት ተከራይተው ለመኖር ሆነ ለማሰብ እንደማይችሉም አስተያየታቸውን ለሪፖርተር አጋርተዋል፡፡
ሌላኛዋ ባለታሪክ ወ/ሮ ሥራው ድንቅ (ስም ተቀይሯል)፣ ፒያሳ አካባቢ ሸራ ዘርግታ ቡናና ሻይ በመሸጥ ቤተሰቧን ለዓመታት ትመራ እንደነበር ተናግራለች፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ትሠራበት የነበረው ሸራ ተነስቶ ዝናብና ፀሐይ እየተፈራረቀባት እንደሆነ ሪፖርተር ለመታዘብ ችሏል፡፡
ሕገወጥ ስለሆንሽ ነው የተነሳሽው? ስንል ላቀረብንላት ጥያቄ ወ/ሮ ሥራው ድንቅ ‹‹እስከማውቀው ድረስ ሕገወጥ አይደለሁም፣ ምክንያቱም ቦታውን በ2014 ዓ.ም. የወረዳው ጥቃቅንና አነስተኛ ነበር የሰጠን፤›› ትላለች፡፡
ጥቃቅንና አነስተኛ ለንግድና ኢንዱስትሪ እንዳስረከበ እንደነገራቸውና የንግድ ፈቃድ አውጡና ሥሩ ተብለው ለማውጣት በሒደት እያሉ እንደፈረሰባቸው ትገልጻለች፡፡
ወ/ሮ ሥራው ድንቅ፣ ከመፍረሱም በላይ ቀደም ብለው ቢነግሩዋቸው የተሻለ እንደነበር ተናግራ፣ ደንቦች ናቸው የተባሉ አፍራሾች ጧት መጥተው ከሰዓት ከላያቸው ላይ ሸራውን ገፈው እንደሄዱ አብራርታለች፡፡
‹‹ከዚህ በኋላ ምን እንደሚፈጠር አላውቅም›› የምትለው ወይዘሮዋ፣ ቀደም ሲል ወደ አደራጇቸው አካላት ቢሄዱም ‹‹ተመዝገቡ›› እያሉ ስማቸውን በየጊዜው በመመዝገብ፣ ለምንድነው ብለው ሲጠይቁ ‹ለክፍለ ከተማ ልናስተላልፍ ነው› እንደሚሏቸው ተናግራለች፡፡
ሌላኛዋም ስሜን አትጥቀሱ ያለችው ደግሞ፣ በቦታው ከአሥር ዓመት በላይ ኮንቴይነር ተሰጥቷት ስትሠራ እንደነበር ተናግራ፣ በዚህ ወቅት የኮንቴይነሩ ግማሽ ክፍል ተነስቶ በቀረችው ቦታ ላይ ዕቃዎቿን በመሸጥ ላይ ነበረች፣ ከምታገኘው ገቢም የሚጠበቅባትን ግብር ገቢ ስታደርግ እንዲሁም በምትሠራው ሥራ ቤተሰቧን ታስተዳድር እንደነበር ተናግራለች፡፡
እንደ ወ/ሮ ሥራው ድንቅ ሁሉ እሷም ወደ መንግሥት መሥሪያ ቤት እንደሄደች፣ ነገር ግን ምንም ዓይነት ምላሽ እንዳላገኘች ተናግራለች፡፡
የኮንቴይነሯን ግማሽ ክፍል ያላፈረሱት መጪው የግብር መክፈያ ወቅት ስለሆነ ግብር እስኪሰበስቡ ሊሆን እንደሚችል ሥጋቷን ታስቀምጣለች፡፡
በሌላ በኩል ወረዳው በየጊዜው ተሰብሰቡ እያለ የራሳቸውን ጉዳይ እንጂ የእኛን ጉዳይ አጀንዳ አድርገው አያወያዩንም፣ ከዚህ ይልቅ የብልፅግና አባል እንዲሆኑ፣ በቀጣይ ጉዳያሁ ይታይላችኋል በማለት እንደሚነግሯቸውና እሷም ይህንን ተስፋ አድርጋ እየኖረች መሆኑን ትገልጻለች፡፡ ‹‹ይህ ደግሞ አሁን ላለንበት ፈታኝ ወቅት አፋጣኝ ምላሽ አይሆንም›› ያለችው ወይዘሮዋ፣ መንግሥት በአፋጣኝ ምላሽ ካልሰጠ ብዙ ሰው ጎዳና እንደሚወጣ፣ ሰው ቤቱ ከፈረሰ ሜዳ ላይ መውደቅ እንጂ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ታክላለች፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለጉዳዮች አብዛኞቹ ቤታቸውና የንግድ ቦታቸው ‹‹ደንቦች ናቸው›› ከሚል ውጪ በማንና ለምን እንደሚፈርስ ግልጽ የሆነ መረጃ እንደሌላቸው ለመገንዘብ ችሏል፡፡
ደንቦች ናቸው የሚባሉትም እኛ ‹‹አፍራሽ ኃይል›› ነን አፍርሱ ተብለን ነው ከማለት የዘለለ ምላሽ እንደማይሰጧቸው ተናግረዋል፡፡
ጉዳዩ ወደሚመለከተው የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ቢሮ ማብራሪያ ለማግኘት በደብዳቤ የጠየቅን ቢሆንም ምላሽ አልሰጡንም፡፡