- ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ የንብረት ጉዳት ደርሷል
በአበበ ፍቅር
ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2,783 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ማጣታቸውን፣ የመንገድ ደኅንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
ፈንዱ ትናንት ማክሰኞ ግንቦት 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ሕይወታቸውን ካጡት በተጨማሪ 4,456 ዜጎች ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ጀማል አባሶ ተናግረዋል፡፡
በ2014 ዓ.ም. ከተመዘገበው የሞት መጠን ጋር ሲነፃፀር የ2015 ዓ.ም. ዘጠኝ ወራት 13 በመቶ ጭማሪ ያሳየ መሆኑን፣ በአንፃሩ የአካል ጉዳት በሁለት በመቶ መቀነሱን አቶ ጀማል ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከሰው ሞትና ከአካል ጉዳት በተጨማሪ፣ ከ1.7 ቢሊዮን በላይ የሚሆን የንብረት ጉዳት መድረሱን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አክለዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ በ6.3 ሚሊዮን በላይ ተሽከርካሪዎች ላይ በተደጋጋሚ ድንገተኛ የቴክኒክ ፍተሻ የተደረገ መሆኑን፣ እንዲሁም 235,199 አሽከርካሪዎች ልዩ ልዩ የደንብ መተላለፎች በመፈጸማቸው ቅጣት ተጥሎባቸዋል ብለዋል፡፡ በዚህም ግማሽ ቢሊዮን ብር ተሰብስቦ ለመንግሥት ገቢ መደረጉን አቶ ጀማል አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የሞት አደጋ ያደረሱ 90 አሽከርካሪዎች ለአንድ ዓመት ከሥራ የታገዱ መሆናቸውን ገልጸው፣ 432 ከባድ ጉዳት ያደረሱ አሽከርካሪዎች ለስድስት ወራት ከሥራ እንዲታገዱ መደረጉን አብራርተዋል፡፡
የሦስተኛ ወገን ሽፋንን በተመለከተ 93 ሺሕ ተሽከርካሪዎች ላይ በተደረገ ቁጥጥር 117 የመድን ሽፋን እንደሌላቸው፣ 650 ያህሉ ደግሞ ዕድሳት ሳያደርጉ መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የተሽከርካሪ ቁጥር ካላቸው አገሮች ውስጥ አንዷ ስትሆን በትራፊክ አደጋ ሞትና የንብረት ውድመት ቀዳሚ ናት ያሉት አቶ ጀማል፣ በየዓመቱ የሚከሰተውን አደጋ ለመቀነስ ተቋሙ ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት እየሠራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
‹‹በየጊዜው የሚከሰተው የሞት አደጋና የአካል ጉዳት አምራችና ምሁራን ዜጎችን እያሳጣን ነው፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ሞትንና የአካል ጉዳትን ለመቀነስ በርካታ ሥራዎችን እየሠራን ነው፤›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ‹‹ነገር ግን አሁንም አደጋ ውስጥ ነው ያለነው፤›› ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ የሞት አደጋ እየጨመሩባቸው ያሉ አካባቢዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ መጪው ክረምት እንደመሆኑ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ከፍ በማድረግ ካልተሠራ አደጋው አስከፊ ሊሆን ይችላል ሲሉ አክለዋል፡፡
አደጋውን እያደረሱ ያሉት አሽከርካሪዎች በብዛት ወጣቶች እንደሆኑና ከአምስት ዓመት በታች የማሽከርከር ልምድ ያላቸው እንደሆኑ የጠቆሙት አቶ ጀማል፣ አደጋ አድራሹም ወጣቱ ሲሆን ሟቹም ራሱ ወጣቱ የማኅበረሰብ ክፍል ነው ብለዋል፡፡
የመንግሥት ተቋማት የንብረት አስተዳደር ሥምሪት ክፍሎች ተሽከርካሪው አገልግሎት የመስጠት ቴክኒካዊ ብቃት ላይ ካልሆነ ሥምሪት እንዳይሰጡ ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ችግሩ በመንግሥት ተቋማት ላይ ባሉ ተሽከርከሪዎችም የሚታይ መሆኑን፣ ተሽከርካሪው ችግር እንዳለበት እየታወቀ በሥራ ላይ እየዋለ ከሆነም ይህንን ችግር ኃላፊዎች መቆጣጠር ይኖርባቸዋል ሲሉ አቶ ጀማል አሳስበዋል፡፡
የትራፊክ አደጋን ትርጉም ባለው መጠን ለመቀነስ ከግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለ25 ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የግንዛቤ ማስጨበጥና የቁጥጥር ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
በተቋሙ አስተባባሪነት የሚደረገው አገር አቀፍ የቁጥጥር እንቅስቃሴ በተመረጡና አደጋ በተደጋጋሚ በሚከሰትባቸው የመንገድ ኮሪደሮች ላይ እንደሚሆን የተናገሩት አቶ ጀማል በዚህም በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋና በሸገር ከተማ በአምስቱም መውጫ በሮች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በክልሎች ደግሞ በደቡብ፣ በሲዳማ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝና በሐረሪ ክልሎች በተመረጡ መንገዶች ላይ ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል፡፡