Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያን የአኅጉራዊ የነፃ የንግድ ቀጣና ተሳታፊ ለማድረግ ድርድር እየተደረገ መሆኑ ተነገረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ወደ ትግበራ ለማስገባት ዘግይታበታለች ተብሎ የሚነገረውን የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ዕውን ለማድረግ፣ ድርድር እየተደረገ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ እንዳለው መኮንን ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በንግድ ቀጣናው ላይ ተሳታፊ እንድትሆን ድርድር እየተደረገ ነው፡፡ ‹‹የሚቀርቡት አገልግሎትና ምርቶች ምን ይሁኑ? እንዴት እንለዋወጥ? የታክስ ምጣኔው እንዴት መሆን አለበት?›› የሚሉ ጉዳዮችን ይመለክታል ብለዋል፡፡ የድርድር ሁኔታው ሲያልቅ የንግድ ልውውጡ ወደ ሙሉ ትግበራ እንደሚገባ አቶ እንዳለው አክለዋል፡፡

ሚኒስቴር ዴኤታው እንዳስረዱት፣ የአፍሪካ ነፃ የንግድና ቀጣና በዓለም ትልቁ ገበያ ሊባል የሚችልና ከ55 የአፍሪካ አገሮች ውስጥ 54 አገሮች ስምምነት የተፈራረሙበት ነው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ44 በላይ አገሮች ወደ ራሳቸው ሕግ አካተው አፅድቀዋል፡፡ ከዚህ በኋላ የሚቀረው ሙሉ በሙሉ ትግበራ ሲደረግ፣ በየትኛውም የገበያ መዳረሻ በአገሮች ስምምነት መሠረት የገበያ ልውውጥ መከናወኑ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ከአምስት ዓመታት በፊት በሩዋንዳ ኪጋሊ በአፍሪካ አገሮች መሪዎች ተፈርሞ ከፀደቀ በኋላ፣ በጋና አክራ ቢሮ ተከፍቶ ሠራተኞች ተመድበው ሥራውን መጀመሩ የሚታወቅ ነው። ስምምነቱ በአኅጉሩ ተደራራቢ ቀረጦችን በማስቀረት የአፍሪካውያንን የእርስ በርስ የንግድ ዝምድና ያቀላጥፋል የሚል ትልቅ ግምት ተሰጥቶታል። 

ከሁለት ዓመት በፊት በ34 የአፍሪካ አገሮች ስምምነት የፀደቀው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራ፣ የዚህ ዓመት የአፍሪቃ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ዋነኛ መወያያ እንደነበር ይታወሳል።

በየካቲት ወር ተደርጎ በነበረው ጉባዔ አዲሱ የኅብረቱ ሊቀመንበር የኮሞሮሱ ፕሬዚዳንት አዛሊ አሶማኒ የነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራው ‹‹የተለጠጠ ዕቅድ ቢሆንም›› እናሳካዋለን ሲሉ ተደምጠው ነበር።

የኢትዮጵያ አምራቶች፣ ላኪዎችና አስመጪዎች ለአኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና በቂ ዝግጅት ማድረግ ይጠብቃቸዋል ያሉት አቶ እንዳለው፣ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ የተመረቱ ምርቶች  በኡጋንዳ፣ በሩዋንዳና በኬንያ፣ እንዲሁም በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ድንበር ተሻጋሪ በሆነ ገበያ ተሳታፊ መሆን ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡

አፍሪካ ከ1.3 ቢሊዮን በላይ ሕዝብ፣ ከ3.4 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ልውውጥ ያላት ትልቅ አኅጉር ናት ያሉት አቶ እንዳለው፣ ይህንን ከመጠቀም አኳያ ኢትዮጵያ ትልቅ አቅም አላት ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የአፍሪካ አገሮች የፈረሟቸውን ስምምነቶች የመተግበር ችግር ያለባቸው መሆኑ፣ በአኅጉሩ የሚመረቱ ብዙ የኢንዱስትሪ ምርቶች አለመኖራቸው፣ የሰላምና ፀጥታ መደፍረስ ለአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ዕቅድ መተግበር ፈተና እንደሚሆን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል።

በተያያዘም በአፍሪካ ኢንቨስትመንት ማዕከል (Investment Center of Africa Ltd-ICOA) አዘጋጅነት በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተሰናዳው የአፍሪካ ንግድና ኢንቨስትመንት ሰሚት ግንቦት 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በስካይ ላይት ሆቴል ተከናውኗል፡፡

ዓመታዊ መድረኩ በንግድ፣ በኢንዱስትሪ በኢንቨስትመንት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ አተኩሮ በአፍሪካ አስተማማኝ የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ለማሳደግና አኅጉራዊ የቢዝነስ ግንኙነት ለመፍጠር ያለው አበርክቶ ተገልጿል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ደኤታ አቶ ሐሰን አህመድ እንዳስታወቁት፣ የስብሰባው ዋና ዓላማ የኢትዮጵያን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን መስህብን ማስተዋወቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አባል በሆነችበት የነፃ ንግድ ቀጠና ስምምነት፣ በአፍሪካ ደረጃ ምን ያህል ለውጥ እንደሚመጣ ለመግለጽና ከተሳታፊዎቹ ጋር በመተባበር የሥራ ዕድል፣ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ማምጣትን ዓላማው ያደረገ ስብሰባ እንደሆነ አቶ ሐሰን አክለዋል፡፡

አቶ እንዳለው በበኩላቸው፣ በአኅጉር አቀፍ ደረጃ የተዘጋጀው ስብሰባ ለኢትዮጵያ ይዞት የሚመጣው መልካም አጋጣሚ ተጨማሪ፣ የኢንቨስትመንት ዕድል መፍጠሩ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ከተለያዩ አገሮች የመጡ ኢንቨስተሮች፣ በዲፕሎማቶችና በርካታ ጉዳዩ የሚመለታቸው ዲፕሎማቶች በመሳተፋቸው፣ ንግድና ኢንቨስትመንት ከማስፋፋት አኳያ ብዙ መልካም አጋጣሚዎችን ይዞ መጥቷል ብለዋል፡፡

በአንድ አገር ኢንቨስትመንትን ከመሳብና ከማስተዋወቅ አንፃር ከሚነሱ ጉዳዮች አንፃር የሰላምና የፀጥታ ጉዳዩ ተጠቃሹ ሲሆን፣ ከዚህ አኳያ የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ደኤታው ገለጻ አድርገዋል፡፡

‹‹የሰላምና የደኅንነት ጉዳይ ለአንድ ተቋም ወይም ለመንግሥት ብቻ የሚተው አይደለም፤›› ያሉት አቶ እንዳለው፣ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ አገር የሚደርሰውን ኃላፊነት ማረጋገጥ እንደሚገባና መንግሥት ይህንን ማድረግ የሚችሉ ተቋማት ላይ የአቅም ግንባታ ሥራዎች እየሠራ እንደሆነ፣ የፍትሕ አካላት በሚባሉት የመከላከያና የደኅንነት ተቋማት ላይ የተሠሩትን ሥራዎች በአስረጅነት አቅርበዋል፡፡

በተቋማቱ እየተሠሩ ያሉ የሪፎርም ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ወደ መሬት ሲወርዱ የሰላምና የደኅንነት ጉዳይ አሳሳቢ የማይሆንበት ደረጃ ይኖራል ብለው እንደሚያምኑ አቶ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኢንቨስትመንት ፕሮሞንሽና ማርኬቲንግ ዳይሬክተር ወ/ሪት ሐረገወይን ሚራቶ፣ መንግሥት ከፖሊሲ አቅጣጫ ጀምሮ ለኢንቨስትመንት አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የተለያዩ የፖሊሲ ሪፎርሞች እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ ከዓመት በፊት አዲስ የኢንቨስትመንት ሕግ እንደተዘጋጀ፣ ከ60 ዓመት በላይ የቆየው የንግድ ሕግ እንደተሻሻለና ሌሎች አገልግሎቶችም ዲጂታይዝ እየተደረገ መሆኑን ዳይሬክተሯ አክለዋል፡፡

‹‹እንዲህ ዓይነት ሁነቶች ተካሄደው ብቻ መተው ሳይሆን ተከታትሎ አሳምኖ መምጣት ያስፈልጋል፣ ሥራ ይፈልጋል፡፡ እሱን ደግሞ እየሠራን ነው፤›› በማለት ወ/ሪት ሐረገወይን ተናግረዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች