‹‹የገንዘብ እጥረት የሚገጥመው ያለውን ሀብት የማስተዳደር ችግር ስላለ ነው››
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በስተቀር ሁሉም የንግድ ባንኮች ሊባል በሚል ደረጃ ከፍተኛ የጥሬ ገንዘብ እጥረት ጣሪያ ላይ መሆናቸውን እየገለጹ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመርያ መሠረት አንድ ደንበኛ በቀን ወጪ ማድረግ የሚችለው እስከ 50,000 ብር ቢሆንም፣ በመርካቶና በሌሎች የገበያ ማዕከላት የሚገኙ ነጋዴዎች፣ ከተለያዩ ባንኮች ጥሬ ገንዘብ ማውጣት የቻሉት ከአሥር እስከ ሃያ ሺሕ ብር ድረስ ብቻ መሆኑን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በተለያዩ የባንክ ቅርንጫፎች ለአንድ ሰው እየተሰጠ ያለው ከተፈቀደው በግማሽ ያነሰ መሆኑን ሪፖርተር በመርካቶና በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ነጋዴዎች ተናግረዋል፡፡
የገንዘብ እጥረት በባንኮች መታየት ከጀመረ ሦስት ወራት ማስቆጠሩን፣ ለዚህ እንደ ምክንያት ሲነሳ የቆየው ደግሞ የግብርና ግብዓቶች በብዛት መግዛት ተያይዞ የመጣ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ይህ ችግር ለወራት ይስተካከል ቢባልም ሪፖርተር በቅኝቱ ያረጋገጠው ግን የጥሬ ገንዘብ እጥረቱ መኖሩን ነው፡፡
በመርካቶ ገበያ አመዴ ተራ አካባቢ በጫማ ማከፋፈል ንግድ ላይ የተሠማሩት አቶ እንዳለ አስቻለው እንደተናገሩት፣ የጥሬ ገንዘብ እጥረቱ ከተከሰተ ወራት በማስቆጠሩ፣ ‹‹እንደ እኔ ያሉ ነጋዴዎች ሥራችንን ለማቀላጠፍ እንቅፋት ሆኖብናል፤›› ብለዋል፡፡
የጥሬ ገንዘብ እጥረቱ እንዳለ ሆኖ ከባንክ ወደ ባንክ የሚደረገው የገንዘብ ዝውውርም ከሳምንት በላይ በመውሰዱ ችግሩን አባብሶታል ብለዋል፡፡ ‹‹ደንበኞቻቸው በፈለጉት የባንክ አማራጭ ክፍያ ለመፈጸም›› እንደተቸገሩ የሚገልጹት አቶ እንዳለ፣ ጥሬ ገንዘብ በማውጣት ክፍያ ለመፈጸም እንደተገደዱ ገልጸዋል፡፡
ባንኮቹ የጥሬ ገንዘብ እጥረት ስለገጠማቸው ደንበኞቻቸውን ‹‹ኮኔክሽን የለም›› በማለት ምላሽ እንደሚሰጡ በመጠቆም፣ የችግሩ መባባሱን ያስረዳሉ፡፡ በግዙፍ የገበያ ማዕከል በንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ አያልሰው ቢሆን፣ ስለጥሬ ገንዘብ እጥረት ስለመኖሩ ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡
ሪፖርተር በተለያዩ ንግድ በባንኮች ተዘዋውሮ ቅኝት አድርጓል፡፡ በቅኝቱም በብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት አንድ ሰው በቀን ማውጣት የተፈቀደለት 50 ሺሕ ብር ቢሆንም፣ 10,000 ብር እንኳን ማግኘት እንዳልተቻለ ደንበኞች ሲማረሩ ተመልክቷል፡፡
ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በቅርንጫፎቹ ለደንበኞች መስጠት ያለበት በቀን የ50 ሺሕ ብር ቢሆንም፣ ገሚሱንና ከዚያ በታች እየሰጠ መሆኑን ሪፖርተር ለመታዘብ ችሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተመሳሳይ ሁኔታ የጥሬ ገንዘብ እጥረት ባለባቸው ባንኮች፣ ለአገልግሎት የሚገቡ የደንበኞች ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑን ሪፖርተር አስተውሏል፡፡ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ የአቢሲኒያ ባንክ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ከዚህ ቀደም የገንዘብ እጥረት ከአንድ እስከ ሦስት ወራት ብቻ ይቆይ ነበር፡፡ የአሁኑ እጥረት ግን ከፍተኛ መሆኑንና ከየካቲት 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ችግሩ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡
ለተከታታይ ወራት በተለያዩ ባንኮች ከፍተኛ የጥሬ ገንዘብ እጥረት በመኖሩ፣ የቁጠባ እንቅስቃሴያቸው ማሽቆልቆሉን ተናግረዋል፡፡ ባጋጠመው የጥሬ ገንዘብ እጥረት ሳቢያ አብዛኛዎቹ ቅርንጫፎች ያቀዱትን በቁጠባ የሚቀመጥ የገንዘብ መጠን ማሳካት አልተቻለም፡፡
በአሁኑ ጊዜ 100,000 ብር የሚይዙ ቅርንጫፎች መኖራቸውን በመጠቆም፣ ከእጥረቱ አኳያ ከ50,000 ብር እስከ 100,000 ብር የሚያሳድሩ ባንኮች መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡
የጥሬ ገንዘብ እጥረት ባንኮች ብድር አሰጣጣቸውን ሊያስተጓጉል እንደሚችል የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፣ የደንበኞች አመኔታንም ሊቀንስ እንደሚችል ሥጋታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከሌሎች ባንኮች የሥራ ባልደረቦቻቸው የሰሙትን ያጋሩት ሥራ አስኪያጁ፣ አንዳንድ ባንኮች አምስት ሺሕ ብር እንኳን የመክፈል አቅም እንደሌላቸው አስረድተዋል፡፡
እጥረቱ የተከሰተው ለምንድነው? ተብለው ሲጠየቁም፣ የገንዘብ እጥረቱ የመጣው ጤናማ ያልሆነ ብድር አሰጣጥ በመኖሩና ብድሩ በወቅቱ ሳይመለስ ሲቀር የሚገጥም ችግር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ባንኮች በገጠማቸው የገንዘብ እጥረት ሳቢያ የደንበኞች የቁጠባና ገንዘብ የማስቀመጥ ሁኔታን ሸርሸሮታልም ሲሉ አክለዋል፡፡ ምክንያቱም ደንበኞች በፈለጉበት ጊዜና ሰዓት ገንዘባቸውን ማውጣት ስላልቻሉና፣ ያላቸውን የገንዘብ ዝውውር በመገደቡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
እንደ ምክንያት ያነሱት ሌላኛው ችግር ከባንክ ወደ ባንክ ያለው የገንዘብ ዝውውር ላይም ችግር በመኖሩ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ደንበኞች ጥሬ ገንዘብ እንዲፈልጉ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰሎሞን ደስታ፣ ባንኮች መያዝ ያለባቸውን የገንዘብ መጠን መስፈርቶች ማሟላታቸውን ተናግረው፣ ነገር ግን ባንኮቹ ገንዘብ የሚያጎሉባቸው ችግሮች (መስፈርቶች) ካሉ አንድ ባንድ እንደሚታዩ ገልጸዋል፡፡ ችግሮቹ እንደየቅርንጫፎቹ ሊለያዩ እንደሚችልም ይጠቁማሉ፡፡
አንድ የባንክ ቅርንጫፍ ችግር አለበት ማለት ሁሉም የፋይናንስ ሲስተም ላይ ችግር አለባቸው ማለት አይደለም ሲሉም ተናግረዋል፡፡ የገንዘብ እጥረት የሚገጥመው ያለውን ሀብት የማስተዳደር ችግሮች ስላለ መሆኑን የገለጹት አቶ ሰሎሞን፣ ባንኮቹ ይህንንም እንዲፈቱና እንዲያስተካክሉ ተናግረዋል፡፡
በብሔራዊ ባንክ በኩል፣ ባንኮቹ ጤናማ ናቸው? አይደሉም? የሚለው መታየት እንዳለበት በመግለጽ፣ ይህ ማለት ግን ፍፁም ናቸው ማለት እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡