የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በቅርቡ ከፓርቲው አባልነት ለቀናል ብለው በይፋ ካሳወቁ አባላት መካከል ግማሽ ያህሉ፣ የዲሲፒሊን ችግር ያለባቸውና አለቃቀቃቸው ምክንያታዊና መርህን የተከተለ አይደለም አለ፡፡
የፓርቲው የሥራ ኃላፊዎች ማክሰኞ ግንቦት 29 ቀን 2015 ዓ.ም. የፓርቲውን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፓርቲው ውስጥ የዲሲፒሊን ችግር ተንሰራፍቷል ብለዋል፡፡
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የፓርቲው የቀድሞ አመራሮችን ጨምሮ በርካታ የኢዜማ አባላት ከአባልነት መልቀቃቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡
የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት መምርያ ኃላፊ ሙሉዓለም ተገኝ (ዶ/ር)፣ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች አንዳንድ የኢዜማ አባል የሆኑ ሰዎች ፓርቲውን እንደሚሳደቡና እንደሚያጥላሉ ተናግረዋል፡፡
በዚህም የተነሳ ፓርቲው ይህ ችግር ሥርዓት መያዝ አለበት በሚል እንቅስቃሴ መጀመሩን፣ ፓርቲው እንቅስቃሴ ሲጀምር አሁን ከለቀቁት መካከል፣ ‹‹ግማሾቹ የዲሲፒሊን ችግር ያለባቸውና በአደባባይ እየወጡ የሚሳደቡ፣ ተገቢ ያልሆነ ቃል የሚጠቀሙ፣ ጨዋ ያልሆኑ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳ ሁሉም የወጡት አባላት ዘንድ ችግር አለ ባይባልም፣ በአንድ ፓርቲ አባልነት ውስጥ የአባልነት ክፍያ ግዴታ ሆኖ እያለ ይህን ግዴታ የማይወጣ፣ በድርጅቱ ተገኝቶ ሥራ ለመሥራት የማይፈልግ ሰው፣ በማኅበራዊ ሚዲያ እየወጣ ማጥላላቱን አግባብ ነው ብሎ ፓርቲው እንደማያስብ ጠቅሰው፣ የአባልነት ግዴታቸውን ያልተወጡ አባላት ደግሞ፣ ‹‹ኢዜማን የመክሰስ መብት አላቸው ብለን አናምንም ምክንያቱም አባል ስላይደሉ›› ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ፣ የሚዲያ ተቋማት ያልተጣራ መረጃ ማሠራጨታቸውን ጠቅሰው ወቀሳ አቅርበዋል፡፡ አቶ ዋሲሁን ከፓርቲው በርካታ ቁጥር ያላቸው አባላት ለቀቁ የተባለው ዘገባ ትክክል አለመሆኑን ገልጸው፣ ከአመራርነትና ከአባልነት ሰባት ሰዎች ብቻ መልቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡
ከለቀቁት አባላት መካከል ፓርቲው በ2014 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ለአመራርነት ተወዳድረው፣ ነገር ግን በጉባዔ አባላት ያልተመረጡ ናቸው ብለዋል፡፡ በመሆኑም በምርጫ ለአብላጫ ድምፅ መገዛት የማይችል አመራርም ሆነ ግለሰብ፣ መንግሥት ቢሆን በአገር ደረጃ ዴሞክራሲን ለማስረፅ የሚችል አይደለም ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ኢዜማን ከለቀቁት የፓርቲው አባላት ጋር ያለው ልዩነትም፣ የጉባዔውን ውጤት በመቀበልና ባለመቀበል መካከልና አመራር ከመሆንና ካለመሆን ጋር ያለ ልዩነት ነው ብለዋል፡፡
የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት እንዳሉት፣ ከፓርቲው ለቀው ወጥተዋል የተባለው ቁጥር የተጋነነ ነው፡፡ የፓርቲው መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) የብልፅግና ፓርቲን ሐሳብ ይደግፋሉ ተብሎ ለቀረበው ሐሳብ እውነታ ግን፣ የኢዜማ መሪ አንድም የብልፅግና ሐሳብ ደግፈው አያውቁም ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ኢዜማ ከመንግሥት ጋር በመሥራቱ ‹‹ለአገራችን አትርፈናል›› ሲሉ አክለዋል፡፡
አገር በትብብርና በፉክክር ነው የሚገነባው ያሉት ሙሉዓለም (ዶ/ር)፣ ‹‹መተባበር ያለብን ጉዳይ ላይ መተባበር፣ መፎካከር ያለብን ጉዳይ ላይ መፎካከር እንጂ፣ በተለመደው የፖለቲካ አስተሳሰብ በተቃርኖና በቅራኔ ጠላትና ወዳጅ ሁለት ዕይታ ብቻ ይዘን መቀጠል አንችልም፤›› ብለዋል፡፡
አገሪቱ የገባችበት አሁናዊ ውስብስብ ሁኔታ በአንድ ፓርቲ የሚፈታ ባለመሆኑ ብዙ ኃይል ተሰብስቦ መሥራት አለበት ብለው፣ ‹‹በመሆኑም እኛ አክራሪ ፖለቲከኞች አይደለንም፣ ለሚነሳው አሉባልታ ሁሉ እየተነሳንም መልስ አንሰጥም፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡