Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የመጪው ዓመት አገራዊ በጀት ሁለት በመቶ አድጎ ለፓርላማ ተመራ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ2016 ዓ.ም. በጀት እየተጠናቀቀ ካለው በጀት ዓመት አንፃር በሁለት በመቶ ብቻ በማሳደግ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መራው፡፡

ማክሰኞ ግንቦት 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በተካሄደው 21ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ በተላለፈው ውሳኔ መሠረት፣ መንግሥት የመጪው ዓመት በጀት 801.65 ቢሊዮን ብር መሆኑን አስታውቋል፡፡

ይህም በ2015 ዓ.ም. መድቦት ከነበረው 786.61 ቢሊዮን ብር በጀት ከሁለት በመቶ ባነሰ ያደገ ሲሆን፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከዓመት ዓመት ይታይ ከነበረው ከፍተኛ የሆነ የበጀት ዕድገት አንፃር በተለየ ሁኔታ ዝቅ ብሎ ታይቷል፡፡

እየተጠናቀቀ ላለው የ2015 በጀት ዓመት ፀድቆ የነበረው 786.61 ቢሊዮን ብር ከ2014 በጀት ዓመት አንፃር ከ40 በመቶ በላይ ዕድገት እንደነበረው የሚታወስ ነው፡፡ የ2014 በጀት ዓመት 561.7 ቢሊዮን ብር ቀድሞ ከነበረው በ18 በመቶ ይበልጥ የነበረ ሲሆን፣ የ2013 ዓ.ም. በጀት 476 ቢሊዮን ብር በ2012 ዓ.ም. ፀድቆ ከነበረው 386.9 ቢሊዮን ብር ወይም በ23 በመቶ ይበልጥ እንደነበረ አይዘነጋም፡፡ ከዚያ በፊት በነበሩት ዓመታትም ከአሥር በመቶ ባላነሰ እያደገ የየዓመቱ በጀት ይፀድቅ እንደነበር  ይታወቃል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የመጪውን ዓመት በጀት 801.65 ቢሊዮን ብር አድርጎ ሲያፀድቅ፣ ለፌዴራል መንግሥት መደበኛ ወጪዎች 369.6 ቢሊዮን ብር መድቧል፡፡ ለካፒታል ወጪዎች ደግሞ 203.9 ቢሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን፣ ለክልሎች ድጋፍ እንዲሆን ደግሞ 234 ቢሊዮን ብርና ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ የሚውል ደግሞ 14 ቢሊዮን ብር መድቧል፡፡

ለካፒታል ወጪዎች የሚውለው 203.9 ቢሊዮን ብር በጀት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ15 ቢሊዮን ብር የሚያንስ ሲሆን፣ ለፌዴራል መንግሥት መደበኛ ወጪ የተመደበው ደግሞ ከባለፈው ዓመት አንፃር በ24 ቢሊዮን ብር ከፍ ይላል፡፡

በያዝነው ዓመት ለሠራተኞቻቸው ደመወዝ መክፈል እስኪያቅታቸው ከፍተኛ የሆነ የበጀት እጥረት ገጥሟቸው እንደነበር የሚነገርላቸው ክልሎች፣ ለመጪው ዓመት የተመደበላቸው የበጀት ድጋፍ በ25 ቢሊዮን ብር ከፍ ብሏል፡፡  

የበጀት ዕቅዱን ያፀደቀው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች የተፈናቀሉ ዜጎችን መደገፍና በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረው ጦርነት የወደሙ መሠረተ ልማቶች መልሶ ማቋቋምን ጨምሮ፣ ከበርካታ ዓላማዎች አኳያ በማየት በጀቱ እንደተዘጋጀ ባወጣው መግለጫ አሳውቋል፡፡

ምክር ቤቱ የበጀት ዕቅዱን በዝርዝር የያዘ ረቂቅ አዋጅ ከተወያየበት በኋላ፣ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩንም በመግለጫው አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች