Sunday, October 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለቅድመ ማጣሪያ ውድድር ለ14 አትሌቶች ጥሪ አቀረበ

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለቅድመ ማጣሪያ ውድድር ለ14 አትሌቶች ጥሪ አቀረበ

ቀን:

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዘንድሮ የዓለም ሻምፒዮና በ10 ሺሕ ሜትር የሚወክሉ አትሌቶችን ለመምረጥ ለቅድመ ማጣሪያ ውድድር ለ14 አትሌቶች ጥሪ አቀረበ፡፡

በሃንጋሪ ቡዳፔስት ለሚከናወነው የዓለም ሻምፒዮና ብሔራዊ ቡድኑን ወክለው የሚካፈሉ አትሌቶች ለመለየት፣ በስፔን የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ለማድረግ ከውሳኔ የደረሰው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለሰባት ወንዶችና ለሰባት ሴቶች ጥሪ አቅርቧል፡፡

ግንቦት 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በማስታወቂያ ይፋ ያደረገው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ፣ አትሌቶች ከግንቦት 28 ቀን ጀምሮ ፓስፖርታቸውን በመያዝ በፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት እንዲቀርቡ ጥሪ አድርጓል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2023 በተለያዩ አገሮች በ10 ሺሕ ሜትር ተካፍለው የራሳቸውን ምርጥ ሰዓት ያመጡ አትሌቶች ስም ዝርዝርም ይፋ አድርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ከሁለቱም ፆታዎች ስድስት ስድስት አትሌቶች በቀጥታ ሲመረጡ አንድ አትሌት በተጠባባቂነት ተይዟል፡፡

ለንደን በሴቶች በ10 ኪሎ ሜትር በተደረገ ውድድር 29፡59 የሮጠችው ሚዛን ዓለም፣ በአሜሪካ ዩጂን በተከናወነ 10 ሺሕ ሜትር በ30፡12 የገባችው እጅጋየሁ ታዬና በ30፡17 በሆነ ጊዜ ያጠናቀቀችው ቦሰና ሙላቱ በቅደም ተከተል ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ምርጥ ሰዓት መያዝ የቻሉ አትሌቶች ናቸው፡፡

በሌላ በኩል ዘንድሮ በጀርመን በተከናወነው የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር ላይ ተካፍለው 30፡24 እስከ 30፡34 በሆነ ሰዓት መግባት የቻሉት፣ ፋንታዬ በላይነህ፣ ፎቴን ተስፋይ፣ ጽጌ ገብረሰላማ እንዲሁም በተጠባባቂነት የተያዘችው ሰናይት ጌታቸው በቅድመ ማጣሪያው የሚሳተፉ አትሌቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በወንዶች በስፔን በተከናወነው የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር 26፡33 ማጠናቀቅ የቻለው በሪሁ አረጋዊ በስፔኑ ቅድመ ማጣሪያ ውድድር ላይ ከሚካፈሉ አትሌቶች መካከል በቀዳሚነት ስሙ ሠፍሯል፡፡ በዘንድሮ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በ29፡26 ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቅ የቻለው በሪሁ፣ በዓለም ሻምፒዮና በወንዶች 10 ሺሕ ሜትር ከፍተኛ ግምት ካገኙ አትሌቶች መካከል ይጠቀሳል፡፡

አትሌቱ እ.ኤ.አ. በ2021 ባርሴሎና በተካሄደ የ5 ኪሎ ሜትር ሩጫ 12፡49 በመግባት የዓለም ክብረ ወሰን መጨበጥ መቻሉ ይታወሳል፡፡

የ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ የአሥር ሺሕ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤቱ ሰለሞን ባረጋ፣ በ2022 ኔዘርላንድ ባደረገው ውድድር 26፡44 መግባቱን ተከትሎ በሁለተኝነት ለቅድመ ማጣሪያ ውድድሩ ስሙ ይፋ የሆነ አትሌት ነው፡፡

ሌላው በኔዘርላንድ ውድድር ተሳትፎ 26፡45 የገባው ታደሰ ወርቁ ሦስተኛውን ምርጥ ሰዓት ያስመዘገበ አትሌት ሆኖ በመለያ ውድድሩ ይሳተፋል፡፡

ሌሎቹ ተሳታፊዎች ዮሚፍ ቀጄልቻ በ10 ሺሕ ሜትር 26፡49 ኔዘርላንድ (2022)፣ ያሲን ሃጂ 10 ኪሎ ሜትር 27፡00 በፈረንሣይ (2022)፣ ጨምዴሳ ደበሌ 10 ሺሕ ኪሎ ሜትር 27፡10 በስፔን (2022) ሲሆኑ፣ ገመቹ ዲዳ 10 ኪሎ ሜትር በፈረንሣይ (2023) በተደረገ ውድድር 27፡12 በመግባት በተጠባባቂነት የተያዘ መሆኑን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡

ለዓለም ሻምፒዮናው ተሳታፊ አገሮች የተወዳዳሪ አትሌቶች ስም ዝርዝር ይፋ ከማድረግ ባለፈ ዝግጅት መጀመራቸውም ታውቋል፡፡

በቅርቡም ኬንያ አትሌቲክስ በዓለም ሻምፒዮናው አገራቸውን ወክለው የሚሳተፉ የ10 ሺሕ ሜትር አትሌቶችን ስም ዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡

በአንፃሩ የኢትዮጵያው ፌዴሬሽን የመጨረሻዎቹን አትሌቶች ስም ዝርዝር የቅድመ ማጣሪያ ውድድሩን በስፔን ኔርጃ ሰኔ 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ከሚያደርገው ውድድር በኋላ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ፌዴሬሽኑ የማሟያ ውድድሩን በሐዋሳ ሲያደርግ እንደነበር ሲነገር ቢቆይም፣ በጉዳዩ ዙሪያ ከአሠልጣኞችና ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ጋር ከመከረ በኋላ፣ ሐሳቡን ቀልብሶ የማጣሪያ ውድድሩን በስፔን ለማድረግ ዝግጅት መጀመሩ ተጠቅሷል፡፡

ለቡዳፔስቱ የዓለም ሻምፒዮና ላይ ለመካፈል አትሌቶች በስፔን በሚያደርጉት የማጣሪያ ውድድር ሴቶች 30፡40፡00 መግባት የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ ወንዶች ከ27፡10፡00 ሰዓት በታች ማጠናቀቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከነሐሴ 13 እስከ 21 ቀን 2015 ዓ.ም. በሐንጋሪ ቡዳፔስት የሚከናወነው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሊካሄድ 74 ቀናት ቀርተውታል፡፡ በሻምፒዮና ከ200 በላይ አገሮች የተውጣጡ ከሁለት ሺሕ በላይ አትሌቶች ይጠበቃሉ፡፡

ዓምና በአሜሪካ ዩጂን ተካፍለው አሸናፊ የሆኑ አትሌቶች በዘንድሮው ሻምፒዮና በቀጥታ የማለፍ መብት ይዘው ይሳተፋሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...