ችግር ተፈጥሮአዊ መመህር ነው፡፡ ችግር የታላቅ ህይወት በር ነው፡፡ አሁን በትምህርት ቤት የምንማረው ትምህርት ሰዎች እነሱ የደረሱበትን የትምህርት ደረጃ ለመድረስ ያዘጋጀልን ፈለግ ነው፡፡ አንድ ሰው የሄደበትን ፈለግ መከተል ደግሞ የሚያደርሰው እሱ የደረሰበት ደረጃ ብቻ ነው፡፡ የተለየ ነገር ለመስራት ችግሮችን በተለየ አንግል (አቅጣጫ) መመልከት ይኖርብናል፡፡ ስለዚህ ችግር ሲደርስብን ወይም ስንመለከት የአመለካከት አቅጣጫችን በተለየ መለኩ መሆን ይኖርበታል፡፡ በዚህ ዓለም ትልቅ የምንላቸው ሰዎች ብዙሃኑን የተከተሉ ሳይሆን የራሳቸውን አቅጣጫ የተከተሉ ናቸው፡፡ ብዙሃኑን መከተል ተራ ሰው ከማድረግ ውጪ የትም አያደርስም፡፡ የተለየ ሰው ለመሆን የተለየ አመለካከት ሊኖረን ይገባል፡፡ የተለየ ሰው ማለት የተለየ ስም መያዝ ሳይሆን የተለየ አስተሳሰብና የራሳችን የግላችን የሆነ አቋም መያዝ ማለት ነው፡፡ ከስማችን ውጭ የተለየ መግለፅ የምንችለው ነገር ሊኖረን ይገባል፡፡
ከስማችን ውጭ የግላችን የምንለው የተለየ ልንጠራበት የምንችለው ነገር ሊኖረን ይገባል፡፡ ከሌላው ሰው የምንለየው በስማችን ብቻ መሆን የለበትም፡፡ የተለየን ሰዎች ነን ለማለት የተለየ የአስተሳሰብና የአመለካከት እውቀት ሊኖረን ይገባል፡፡ አንድ የተለየ ነገር ሊያስጠራን የሚችል ነገርም መስራት ይኖርብናል፡፡ ሰዎች የምንለያየውና ከፍና ዝቅ ብለን የምንታየው በስራችን ነውና፡፡ እስኪ ስለራሳችሁ አውሩ ብትባሉ ምን ያህል ደቂቃ ማውራት ትችላላችሁ? ልጆቻችሁ ስለናንተ ቢጠይቁ ደግሞ የሚያወሩት እናንት ስለራሳችሁ ከምታወሩት ባነሰ ነው፡፡ ጠቅላላ አያውቅዋችሁም ማለት ነው፡፡ የተለየ ነገር ከሌላችሁ ማለቴ ነው፡፡
- አብርሃም ሐዱሽ “ነገር በምሳሌ…” (2005)