Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየዘሪሁን አስፋው ስሙር ምርምሮች

የዘሪሁን አስፋው ስሙር ምርምሮች

ቀን:

‹‹…በአንድ ጥራዝ ታትመው እንዲወጡ ያደረግሁት ለሥነ ጽሑፍ ተማሪዎች ስለደራሲዎችና ድርሰቶቻቸው የተወሰኑ ገጽታዎችን ያሳያሉ፣ ለጥናትም እንዲፈልጓቸው ያግዛሉ ብዬ ነው፡፡ በተጨማሪም የሒሳዊ ንባብን አንድ አቅጣጫ ያመለክታሉ፡፡ ለአፍቃርያነ ሥነ ጽሑፍና ወደ ጽሕፈት ተግባር ለሚገቡ ሰዎችም አንዳንድ ሥነ ጽሑፋዊ እሳቤዎችንና ብልሃቶችን ያሳውቃሉ ብዬ ስላመንኩ ነው፡፡››

በወርኃ መጋቢት ዜና ዕረፍታቸው የተሰማው የሥነ ጽሑፍ መምህሩ ዘሪሁን አስፋው (ፕሮፌሰር) በ2013 ዓ.ም. ባሳተሙት ‹‹ከበዓሉ ግርማ እስከ አዳም ረታ›› የተሰኘ የመጣጥፎች መድበል ላይ፣ መድበሉ ለምን እንደተዘጋጀ በመግቢያው የገለጹት ኃይለ ቃል ነው፡፡  

በኖሩበት የማስተማርና የምርምር ዘመን ውስጥ ከአንድ መቶ ስድሳ በላይ ሥነ ጽሑፋዊና ባህላዊ ገለጻዎች እንዲሁም የአርትኦት አገልግሎቶች እንደሰጡ በመድበሉ ጠቁመዋል፡፡ ከእነዚህ ሥራዎች ውስጥ 44 ያህሉን ማሳተማቸውን ሌሎቹ በተከታታይ ሊታተሙ እንደሚችሉ ተስፋቸውን ገልጸውም ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ተኮር የሆኑ 21 የምርምር መጣጥፋቸውን ከማረፋቸው ከጥቂት ወራት በፊት ለኅትመት ቢያዘጋጁም የኅትመቱን ብርሃን ለማየት አልታደሉም፡፡ 

ቢሆንም ‹‹ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር፣ ስሙር ምርምሮች›› የተሰኘው መጽሐፉን ባለቤታቸውና ልጆቻቸው በፍጥነት እንዲታተም አድርገው ለምረቃ አብቅተውታል፡፡

‹‹ስሙር›› በአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ አተረጓጐም ያማረ፣ የበጀ፣ ያፈራ፣ ፍሬያማ ወፍራም ማለት ነው፡፡

ለመጽሐፉ ‹‹ማስተዋወቂያ›› የጻፉት ጓደኛቸውና የሥራ ባልደረባቸው አቶ ደረጀ ገብሬ (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ ስለታተመው ምርምራዊ መጣጥፎች ይዘት እንደሚከተለው ገልጸዋል፡፡  

‹‹የአጭር ልብ ወለድን ጥቅል ምንነትና ዝርዝር ባህሪያት የሚያሳዩ አራት መጣጥፎች ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉም በየራሳቸው አስረጂነትና ትምህርት ሰጪነታቸው በወጥነት የሚታዩ ናቸው፡፡ ስለሴቶችና በሴቶች ስለተሠሩ ሥነ ጽሑፋዊ ሥራዎችም እንዲሁ በአንድ ምድብ ሊታዩ የሚችሉ መጣጥፎች አሉ፡፡

‹‹ሌላው በወሎና በወሎ ባህል ላይ የሚያጠነጥኑት ሥራዎቻቸው ናቸው፡፡ ስለወሎ በተለያዩ ተመራማሪዎች፣ በጋዜጦች፣ በደራሲዎች የፈጠራ ድርሰቶች ውስጥ ስለቀረቡ የባህል፣ የትምህርት፣ የቋንቋ፣ የልማት እርምጃዎችና በመሳሰሉ ርእሰ ጉዳዮች ያቀረቧቸው መጣጥፎቹ ተካተዋል፡፡

‹‹በበዓሉ ግርማ ላይ ከሠራቸው ሥራዎች ውስጥም (በቀደመው ያልተካተቱ) ሁለት መጣጥፎች አሉ፡፡ በልጆች ሥነ ጽሑፍ ላይ ያደረጓቸው ምርምሮች እዚህ መድበል ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ሌሎቹ ራሳቸውን ችለው በተናጠል የቀረቡ መጣጥፎች ናቸው፡፡

‹‹እያንዳንዱን መጣጥፍ ለማዘጋጀት የተጠቀሙባቸውን ማመሳከሪያዎች በየመጣጥፎቹ መጨረሻ ላይ በጥንቃቄ አሥፍረዋል፡፡ የአንዳንዶቹን መጣጥፎች መቼትና ሰበበ ጥናት በየቀረቡበት ገጽ መጀመርያ ላይ ወይም በግርጌ ማስታወሻነት ጠቁመዋል፡፡ የአንዳንዶቹ አልተጠቆሙም፡፡ ምናልባት በቀደመው መጽሐፍ ላይ እንዳደረጉት በመጨረሻ ላይ ይጠቁሙን ነበር ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ በታወቀ ምክንያት ይህ አልሆነም፡፡

ፍኖተ ዘሪሁን

‹‹አቶ ዘሪሁን አስፋው (1944 – 2015) ገና በጠዋቱ በመምህርነትና በሥነ ጽሑፍ አድባር የተጠራ ሰው ነበር፡፡ በልጅነቱ በትምህርት ቤት የኪነ ጥበብ ክበብ የጀመረውን ንቁ ተሳታፊነት ቀስ በቀስ እያሳደገና እያጠናከረ የሕይወቱ ድርና ማግ ያደረገ፣ በጥልቅ ተመልካችነትም ሥነ ጽሑፍን የተጠበበ፣ የመረመረ፣ የሔሰ፣ የአገራችን አንጋፋና ወጣት ተመራማሪዎችም ሆኑ ጎምቱ ፈጣሪዎች በረቂቅ የአስተሳሰብ መንገድና የአሠራር ብልሃታቸው ያስገኙትን ትሩፋት አንጥሮ ለማሳየት ዘወትር የተጋ ነበር፡፡››

ይህ ኃይለ ቃል አቶ ዘሪሁን ባረፉ በ71ኛው ቀን በዋቢ ሸበሌ ሆቴል በተዘጋጀው ‹‹ዝክረ ዘሪሁን›› በሰመረው መጽሐፍ ምረቃ ላይ የተስተጋባ ነው፡፡

ከ1976 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ እስካረፉበት ዕለት ድረስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቀድሞ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ (በአሁኑ ስሙ የአማርኛ ቋንቋ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር) ክፍለ ትምህርት ውስጥ በተለያዩ ማዕረጎችና የኃላፊነት ደረጃ (በትምህርት ክፍል ሊቀመንበርነትና በተቋም ዲንነት) ያገለገሉት አቶ ዘሪሁን፣ ተማሪዎችን በምርምር ከማገዝም አልፈው በግላቸው ሠርተው ያቀረቧቸውና ለኅትመት ያዘጋጇቸው ብዙ ሥራዎች አሏቸው፡፡ ከእነዚህም መካከልም አምስቱን አሳትመዋል፡፡

እነርሱም የሥነ ጽሑፉ መሠረታውያን፣ ልብ ወለድ አዋጅና የቀደምት ደራስያን አጫጭር ትረካዎች፣ ሥነ ጽሑፍ ለማኅበራዊ ለውጥ (ከፖፑሌሽን መገናኛ ማዕከል ጋር)፣ ከበዓሉ ግርማ እስከ አዳም ረታ ሥነ ጽሑፋዊ ተሀዝቦት፣ በሥነ ጽሑፍና በፎክሎር ላይ የተሠሩ ዲግሪ ማሟያ ጥናቶች አጠቃሎዎች ስብስብ ናቸው፡፡

እሙሩ ባለሙያ

በአካዴሚያዊና ማኅበራዊ አገልግሎትና ለሥነ ጽሑፍ ባበረከቱት አስተዋጽኦ እሙሩ (ታዋቂው) ባለሙያ ዘሪሁን አስፋው በልዕልና ግንቦት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ታስበው ነበር፡፡ በዕለቱ የአቶ ዘሪሁን ሦስቱ ምሰሶዎች እንዲህ ተገልጸው ነበር፡፡

ዘሪሁንና የምርምር ሥራዎቻቸው

በአማርኛ የፈጠራ ሥራዎችም ሆነ በምርምር ውጤቶች ላይ ማን ምን አቅርቧል? በምን ያህል መጠንና ትኩረት? በማለት፣ ጥቃቅን የሚመስሉ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ነጥቦችን አኃዛዊ መረጃዎችን ጭምር በማቅረብ፣ ያለንን የሥነ ጽሑፍ ሀብት በዝርዝር እንድናውቅ የሚያስችሉንን በርካታ የምርምር ሥራዎች ለንባብ አብቅተዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን መጠናዊ (ኳንቲቴቲቭ) የምርምር ዘዴ መጠቀማቸው በተለይ ለአዳዲስ የመስኩ ተመራማሪዎች የመረጃ ቋትና የምርምር አቅጣጫ ፈላጊ እንዲሆኑ አስችለዋል፡፡

ዘሪሁን አስፋው ራሳቸው ያሳተሟቸው መጻሕፍቱ ብቻ ሳይሆኑ፣ የምርምራቸው ውጤት የሆኑ መጣጥፎቻቸውም ከሥነ ጽሑፍ ሙያ ውጪ ያሉ ሰዎች እንኳን ከሥነ ጽሑፍ ጋር እንዲተዋወቁና ራሳቸውን እንዲያላምዱ የሚያደርጉ ሥራዎች ናቸው፡፡ ለዚህም የሥነ ጽሑፍ መሠረታውያንና የልብ ወለድ አዋጅ ለዚህ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከዚህም በላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ሆነ በክልል ዩኒቨርሲቲዎች እጅግ በርካታ የሆኑ የፒኤችዲና የማስተርስ ዲግሪ ማሟያ ጽሑፎችን በማማከርና በመፈተንም ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

ዘሪሁን በአርታኢነት የተሳተፋባቸው በርካታ አካዴሚያዊ መጽሔቶች ያሉ ሲሆን፣ የልብ ወለድ መጻሕፍት ላይም ተመሳሳይ ሥራዎችን አከናውነዋል፡፡ የተቆለፈበት ቁልፍ የተሰኘው ልብ ወለድ ለዚህ ዋነኛ ምሳሌ ነው፡፡

የሕፃናት ሥነ ጽሑፍም እንደ አንድ የሥነ ጽሑፍ ዘውግ ትኩረት እንዲሰጠውና እንዲጠና ግንባር ቀደም ሚና ነበራቸው፡፡

ዘሪሁንና ሴት ደራስያን

ሌላው የዘሪሁን አስተዋጽኦ የሴት ደራስያን የፈጠራ ውጤቶች እንዲበረታቱና በሥራዎቻቸውም ከጾታ አኳያ ያነሷቸው ጉዳዮች ትኩረት እንዲያገኙ ማድረጋቸው ነው፡፡ ሴት ደራስያን በጻፏቸው መጻሕፍት ብቻ ሳይሆን በፈጠራ ሥራዎች ውስጥ ሴቶች  ምን ዓይነት ሚና አላቸው የሚለውም ዋነኛው አቅጣጫቸው ሲሆን፣ ‹‹Stories of Women in the Novels of Selected Ethiopian Women Writers›› እና ‹‹Women in the Works of Ethiopian Short Story Writers›› የተባሉት አካዴሚያዊ ጽሑፎች ከጾታ አኳያ ያለውን የማኅበረሰቡን አተያይ ከሚያሳዩ ሥራዎቻቸው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ዘሪሁንና ወጣት ደራስያን

ከዚህ በተጨማሪ ወጣት ደራስያን እንዲበረታቱና ሥራዎቻቸውን ለሕዝብ እንዲያቀርቡ በማረምና በማበረታታት ሙያዊ እገዛም በማድረግ ጭምር ያበከረከቱት አስተዋጽኦ በቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ ከ12 በላይ የኅትመት ውጤቶችን ከፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር ጋር በመሆን ለፍሬ አብቅተዋል፡፡ በተለያዩ የመጻሕፍት ምረቃዎችም ላይ በመገኘት ሙያዊ አስተያየቶችን ለወጣት ደራስያን ሰጥተዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...