Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአካል ጉዳተኞች የሚፈልጉት ድጋፍ እስከ ምን?

አካል ጉዳተኞች የሚፈልጉት ድጋፍ እስከ ምን?

ቀን:

በአበበ ፍቅር

‹‹ሰዎች በእኔ ላይ እንደነበራቸው ግንዛቤ ቢሆን ኖሮ ከቤቴ ባልወጣሁ ነበር፡፡ ነገር ግን በእልህና በአሸናፊነት፣ በይቻላልና በይሆናል ወኔ በመነሳት በብዙ ፈተናዎችና ቁጭቶች ውስጥ ሆኜ ማንኛውም ሰው ከደረሰበት መድረስ ችያለሁ፡፡ ነገም ከዚህ በላይ ተሻግሬ ስኬትን ለመቆናጠጥ እታገላለሁ፤›› የምትለው ትዕግሥት ነገሠ ናት፡፡

ትዕግሥት ብዙ አካል ጉዳተኞች እየደረሰባቸው ያለው ከባድ ጫና በእርሷ ላይም ደርሶባታል፡፡ ‹‹አትችልም›› የሚለውን ቃል ከቤተሰብ እስከ አካባቢ በተደጋጋሚ ሰምታዋለች፡፡ ትዕግሥት ግን አንድ እግሯ አሟልቶ መርገጥ ባይችልም ዊልቸር በመጠቀም ሰው ያደረገውን ሁሉ ማድረግ እንደምትችል በተግባር ማሳየት ምኞቷ ነበር፡፡

ሐሳቧን ለማሳካት ብዙ ፈተናዎች ቢገጥሟትም፣ ፈተናዎችን ወደ ጥንካሬ በመቀየር ይወረወሩባት የነበሩ ቃላት ከዓላማዋ ሊያስቆሟት እንዳልቻሉ ትናገራለች፡፡

ለአካል ጉዳተኞች ፈታኝ ከሆኑ ተግባራት መካከል ወደ ትምህርት ቤት ገብቶ መማር አንዱ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ትምህርት ቤቶች ሲመሠረቱ ብዙ ጊዜ የአካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ አለመሆናቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ማኅበረሰቡ ለአካል ጉዳተኞች ካለው አመለካከት ጋር ተዳምሮ አካል ጉዳተኞች ወደ አደባባይ እንዳይወጡ ያደርጋቸዋል፡፡

ችግሩ በትምህርት ቤት ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በተለያዩ ተቋማት ውስጥም በስፋት ይታያል፡፡ ሆኖም እነዚህን ውስብስብ ችግሮች በጥንካሬ አልፈው የማኅበረሰቡን እይታ የሰበሩ፣ አይችሉም የተባሉትን ሠርተው ያሳዩ በርካታ ናቸው፡፡

ከእነዚህ መካከል ወጣት ትዕግሥት አንዷ ነች፡፡ ትዕግሥት በብዙ ውጣ ውረድ እስከ አሥረኛ ክፍል ትምህርቷን እንደተከታተለች ትናገራለች፡፡

‹‹ከቤት እስከ ትምህርት ቤት አቀበት አለ፡፡ አብረውኝ ያሉ እኩዮቼ አቀበቱን ሩጠው ሲወጡ፣ ፈጣሪዬን ምን ነበር እንደ እነሱ ብታደርገኝ ብዬ ውስጤ በሐዘን ይቆጭ ነበር፡፡ ደግሞ ወዲያው መለስ ብዬ የባሰ አለና ተመስገን ብዬ አመሰግነዋለሁ፤›› በማለት ራሴን በራሴ አጽናናለሁ የምትለው ትዕግሥት፣ ቦርሳዋን በመያዝ የሚረዷት አይዞሽ በርቺ እያሉ የሚያፅናኗት እንዳሉም ትገልጻለች፡፡ በዚህ ሁሉ የሕይወት ውጣ ውረድ እስከ አሥረኛ ክፍል ተምራ ወደ ቀጣይ የክፍል ደረጃ መሸጋገር አልቻለችም፡፡

ነገር ግን ‹አልችልም› የሚለውን አባዜ የጣለችው ትዕግሥት፣ ከዛሬ ሦስት ወር በፊት ከአሜሪካ የልማት ተራድዖ ድርጅት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ፣ የወላይታ ሶዶ ሙያና ቴክኒክ ማሠልጠኛ ኮሌጅ ከቴክኒካል ቮኬሽናል ትሬዲንግ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ባመቻቸው የአካል ጉዳተኞች ሥልጠናን እንደተከታተለች ተናግራለች፡፡ ግንቦት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን በቦሌ ማኑፋክቸሪነግ ቴክኒካልና ቮኬሽናል ኮሌጅ ሲመረቁ፣ ወጣት ትዕግሥትም ከተመረቁት 110 ተማሪዎች አንዷ በመሆን ሥልጠናዋን አጠናቃለች፡፡

‹‹ምን ይሉኛል፣ አልችልም ከዚህ በኋላ እኔ ተምሬ የት ልደርስ ነው? እያሉ በቤት ውስጥ በር ተዘግቶባቸው የሚውሉ አካል ጉዳተኞች አሁንም አሉ፤›› የምትለው ወጣት ትዕግሥት፣ ባላት አቅም ሁሉም አካል ጉዳተኞች ወጥተው ከተማሩና ወደ ሥራ ከገቡ ከማንኛውም ሰው ጋር እኩል የመሥራት አቅም አላቸው በማለት ትመክራለች፡፡

ኮሌጁ የሙያ ሥልጠና ከሰጠ በኋላ ወደ ሥራ ለመግባት ፈታኝ የሚሆንባቸው የገንዘብና የቦታ ችግር እንደሆነ የገለጸችው ተመራቂዋ፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችም ሆነ መንግሥት ሁኔታዎችን ካመቻቸላቸው ለመሥራት ፈቃደኛ እንደሆኑ ተናግራለች፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ጌታሁን ስምâን (ዶ/ር)፣ ከአሜሪካ የልማት ተራድዖ ድርጅት በተገኘ የገዘብ ድጋፍ 1,200 ተማሪዎችን ለማስተማር ታሰቦ 710 ተማሪዎች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ከሦስት ወር እስከ አምስት ወር ሥልጠናውን መከታተላቸውን ገልጸዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ ከመላው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከፍተኛ ውጤት ያመጡ 110 ተማሪዎች በዕለቱ መመረቃቸውን ጌታሁን (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ ተመራቂ ተማሪዎችም በቀጣይ በተለያዩ የግል ድርጅቶችና የመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው መንገዶችን እናመቻቻለን ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የተግባር ሥልጠናውን ወስደው ለተመረቁ ወጣቶች የገንዘብና እንዳስፈላጊነቱ የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው አብራርተዋል፡፡

ምንም እንኳን ፕሮጀክቱ ለሦስት ዓመት ብቻ የሚቆይ ቢሆንም፣ ባለው ጊዜ የተለያዩ አካላዊና ሞራላዊ ድጋፍ በማድረግ ለኅብረተሰቡም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራን በመሥራት በአካል ጉዳተኞች ላይ እየደረሰ ያለውን ጫና ለመቀነስ ይሠራል ሲሉ ጌታሁን (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

መንግሥትና የተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ለአካል ጉዳተኞች ልዩ ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይኖርባቸዋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በተለይ መንግሥት የመሥሪያ ሼዶችን በመስጠት በጎ አድራጊዎችም በገንዘብ በመደገፍ መተባበር እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል፡፡

ጌታሁን (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ሥልጠና ወስደው ወደ ሥራ ለሚገቡ ወጣቶች ከብድርና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በቀጥታ እንዲገናኙ በማድረግ የጎደላቸውን በብድር እንዲሞሉ የሚያደርግ ሥርዓት ይመቻችላቸዋል፡፡

ተመራቂ ተማሪዎች በበኩላቸው፣ ማንኛውም አካል የመሥሪያ ቦታና የብድር አገልግሎት ካመቻቸላቸው የትኛውንም ሥራ በብቃትና በውጤታማነት ለመሥራትና ለመለወጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህ ካልተመቻቸ እንደ አብዛኛው ተማሪ ተመርቀው ሊቀመጡ እንደሚችሉ ሥጋታቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...