ህንድ በሚገኘው ሲባዮሲስ ዩኒቨርሲቲ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል፡፡ በአሜሪካ በሆቴል ማኔጅመንት ተመርቀዋል፡፡ ለስምንት ዓመታት በአሜሪካ፣ ለሦስት ዓመት በህንድ መኖሪያቸውን አድርገው ቆይተዋል አቶ ቢንያም ተስፋዬ፡፡ በአሜሪካ በሚኖሩበት ወቅት መኖሪያ ቤታቸው በአስተማማኝ የቴክኖሎጂ ውጤት በሆነ የአላርም ሲስተም (የማንቂያ ደወል) ጥበቃ ይደረግለት እንደነበር ይናገራሉ፡፡ የማንቂያ ደወሉ ለቤታቸው የነበረውን አስተማማኝ ጥበቃ በመገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት የራሳቸውን ‹‹ኮፓ ስማርት ሴኩሪቲ›› የሚባል ድርጅት ከፍተው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ከ200 በላይ ድርጅቶችና መኖሪያ ቤቶች ቴክኖሎጂውን በማስገጠም እየተጠቀሙ ሲሆን፣ ከ13 እስከ 14 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ንብረት በኮፓ ስማርት ሴኩሪቲ ጥበቃ እየተደረገለት ነው፡፡ አበበ ፍቅር ከድርጅቱ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢንያም ተስፋዬ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
ሪፖርተር፡- ኮፓ ስማርት ሴኩሪቲ በዋናነት ስማርት ሴኩሪቲ ላይ ይሠራል፡፡ ስማርት ሴኩሪቲ ምንድነው?
አቶ ቢኒያም፡- ድርጅታችን ስማርት ሴኩሪቲ ላይ ይሠራል፡፡ ይህ ማለት ከተለመደው የደኅንነት ካሜራ አገልግሎት ወጣ ያለ ሆኖ የማንቂያ ደወል (አላርም) ሲስተም ነው፡፡ አገልግሎቱም መኖሪያ ቤቶቸ፣ ሱቆች፣ መጋዘኖች እንዲሁም ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል በተባሉ የግልና የመንግሥት ተቋማት ውስጥ በመግጠም ደኅንነትን ማስጠበቅ ነው፡፡ የአላርም ሲስተሙ በተገጠመባቸው ቦታዎች ሁሉ ማንኛውም ሰው በሚጠጋበት ጊዜ ከፍተኛ ድምፅ በማውጣት ስርቆትን ያስቀራል፡፡
ሪፖርተር፡- እናንተ በምን ዓይነት መንገድ ነው ሌባውን የምትከታተሉት ስለመዘረፉና አለመዘረፉ የሚደርሳችሁ መረጃ አለ?
አቶ ቢኒያም፡- ለ24 ሰዓት የመከታተያ ጣቢያ አለን፡፡ ይህ ጣቢያ በአዲስ አበባ ከተገጠሙ ደወሎች ጋር ተገናኝቶ ይሠራል፡፡ አላርሙ መጮኸ ሲጀምር ቢሮአችን ውስጥ እንቅስቃሴውን ሁሉ የሚከታተሉ ኦፕሬተሮች ስላሉ ወዲያው ለአደጋ ጊዜ ሠራተኞች መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡ ኦፕሬተሮቻችን በሙያው አስፈላጊውን ሥልጠና ወስደዋል፡፡ በሙያቸውም የአሜሪካ ሞኒተሪንግ ማረጋገጫን ያገኙ ናቸው፡፡ ኦፕሬተሮቻችን ሰው ስለተጠጋ ብቻ አይደውሉም፡፡ እውነት ነው ወይስ ውሸት የሚለውን አጣርተው ነው የሚደውሉት፡፡ ስልክ ከመደወል ባሻገር ስልካቸው ላይ መልዕክት እንዲደርሳቸው ተደርጎ ነው የተዘጋጀው፡፡ መጋዘን ወይም ቤት ውስጥ ያለው አላርም ሲጮህ ጩኸቱ ከዋናው ቢሮአችን ይደርሳል፡፡ ያለምንም ኢንተርኔት ነው የሚደርሰው፡፡ ንብረቱ ከመዘረፉ በፊት እዚህ ላሉ ኦፕሬተሮች መልዕክቱ በሚደርስበት ተመሳሳይ ሰዓት ለባለንብረቱም መልዕክቱ ይደርሰዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የማሳወቂያ መልዕክቱ ለማን ነው የሚደርሰው?
አቶ ቢኒያም፡- ብዙ ጊዜ አንድ ወይም ሁለት መቆጣጠሪያው (ሪሞት ኮንትሮል) ነው የምንሰጣቸው፡፡ ይህንን የሚቆጣጠረው ደግሞ ከቤተሰቡ ወይም ከድርጅቱ አንዱ ሰው ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የመተግበሪያ ሲስተም ስልካቸው ላይ ተጭኖላቸው ልክ እንደ መኪና ሪሞት ኮንትሮል የአላርም ሲስተሙን ጭነው ማዘዝ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ አባት ከሆነ የሚቆጣጠረው ልክ ልጆቹ ከገቡ በኋላ መጋዘንም ከሆነ ሠራተኞቹ ቆልፈው ሲወጡ ሲስተሙን ተጠቅመው አላርሙን ያበሩታል፡፡ ከዚህ በኋላ በበርም ሆነ በአጥር ዘሎ ለመግባት የሚሞክር ማንኛውም ሰው ላይ ይጮሃል፡፡
ሪፖርተር፡- ይህንን የቴክኖሎጂ ውጤት ለየት የሚያደርገው ምንድንነው?
አቶ ቢኒያም፡- ሲስተሙን ለየት የሚያደርገው ሰውን ብቻ ለይቶ የሚጮህ መሆኑ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቅድመ መከላከል ላይ ነው የሚሠራው፡፡ ንብረቱ ከመዘረፉ በፊት ለባለቤቶቹ ቀድሞ ንብረታችሁ ሊዘረፍ ነው በማለት ያሳውቃቸዋል፡፡ ሰውን ብቻ ለይቶ መጮኸ ደግሞ ደንበኞቻችን ንፋስ ነክቶት ይሆን አይጥ ወይም ውሻ ነክቶት ይሆን ወይስ ሌባ ሊገባ ነው ብለው እንዳይጠራጠሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ደወሉ ከጮኸ ያለምንም ጥርጣሬ ሰው ነው ብለው ይደመድማሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ምን ያህል ተደራሽ እየሆናችሁ ነው?
አቶ ቢኒያም፡- አገልግሎቱን ከጀመርን ሁለት ዓመት ሆኖናል፡፡ በእርግጥ የመጀመርያውን ዓመት ሥልጠናና አንዳንድ ዝግጅቶችን በማድረግ ነው የጨረስነው፡፡ ወደ ሥራ ከገባን አንድ ዓመት ሆኖናል፡፡ በዚሁ አንድ ዓመት ውስጥ ከሁለት መቶ በላይ ተቋሞችና የግል መኖሪያ ቤቶች የአገልግሎታችን ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በዚህም ደንበኞቻችን በመኖሪያ ቤታቸው፣ በድርጅታቸውና በመጋዘናቸው ተገጥሞላቸው ወርኃዊ ክፍያ እየከፈሉ በመገልገል ላይ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ሌብነት እየተስፋፋ በመምጣቱ ሲስተሙን የሚያስገጥሙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች ወደ እኛ የሚመጡት ንብረታቸው ሲዘረፍ ወይም የመዘረፍ ሙከራ ሲደረግባቸው ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ማኅበረሰባችን ቴክኖሎጂን ለመጠቀም ብዙ አይደፍርም፡፡
ሪፖርተር፡- ሰው አዲስ የሚመጣ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ቀድሞ በድፍረት የመጠቀም ልምዱ አነስተኛ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ዋጋው ምን ያህል ተመጣጣኝ ነው?
አቶ ቢኒያም፡- ሲስተሙን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ በሚል ዋጋውን ተመጣጣኝ ለማድረግ እየሞከርን ነው፡፡ ለዚህም የመገጣጠም ሥራው በአገር ውስጥ እንዲሆን እየሠራን ነው፡፡ ከዚህ በፊት ግን ተገጣጥሞ ያለቀውን ነበር የምናስመጣው፡፡ ሲስተሙ የዴንማርክ ቴክኖሎጂ ይሁን እንጂ፣ ሥሪቱ የቻይና ነው፡፡ እኛ ወኪል በመሆን ነው ወደ አገር ውስጥ እያስገባን ያለነው፡፡ አሁን ያለው ክፍያ ከጥቅሙ አንፃር ሲታይ ዝቅተኛ ቢሆንም፣ ሲስተሙን ለመግዛት መነሻው ከ60 ሺሕ ብር ጀምሮ ነው፡፡ በቤቱ አልያም ከድርጅቱ ዙሪያ እንደሚያስገጥምባቸው ብዛት ዋጋው እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ለምሳሌ በቤቱ ወይም በድርጅቱ ዙሪያ ሌባን ሊከላከል የሚችል አስተማማኝ አጥር ወይም ትልልቅ ሕንፃዎች ካሉ ከደንበኞቻችን ጋር ከተነጋገርን በኋላ እኛም የምንጠብቀውን ቦታ ለይተን በማወቅ በክፍያው እንስማማለን፡፡ በቀጣይ ዋጋውን ለማስተካከልና ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ እየሠራን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ለቤቶችና ለትልልቅ ድርጅቶች የሚገጠሙት መሣሪያዎች ልዩነት አላቸው ወይስ ተመሳሳይ ናቸው?
አቶ ቢኒያም፡- ለመኖሪያ ቤቶችና ለመጋዘኖች የምንጠቀምባቸው ‹ኮንትሮል ፓላኖ› የሚባሉ ሲሆኑ፣ ለባንኮች ተብለው በልዩ ሁኔታ የሚገጠሙ አሉ፡፡ ለባንኮች የሚገጠሙት ኤሌክትሪክ ባይኖር ሦስት ቀን ተኩል በባትሪ መሥራት ይችላሉ፡፡ ስለዚህ መብራት ቢጠፋ ሦስት ቀን አያሳስባቸውም ማለት ነው፡፡ ያለምንም መቆራረጥ ሥራውን ይሠራል፡፡ ሲስተሙን በባንኮች ለመግጠም ከተለያዩ ባንኮች ጋር ከስምምነት ደርሰናል፡፡ ሁሉንም ባንኮች ወደ ሲስተሙ ለማስገባት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራን እየሠራን ነው፡፡ በሌላ በኩል ለመኖሪያ ቤትና ለመጋዘኖች የሚገጠሙት ኤሌክትሪክ ባይኖር ለስምንት ሰዓት የሚያገለግል ባትሪ የተገጠመላቸው ናቸው፡፡ በቤት ውስጥ የሚገጠሙ ሲስተሞች በቤት ውስጥ የሚደረግን እንቅስቃሴ የሚያሳይ ነው፡፡ በቤት ውስጥ የተለኮሰን ተቀጣጣይ ነገር እንደ ቡታ ጋዝ የመሳሰሉት ኃይላቸው ከሚፈለገው መጠን በላይ ከሆነ፣ ተለኩሰው ከተረሱና ተቀጣጥለው ለአደጋ የሚያጋልጡ ከሆኑ ሴንሰሮቹ መጠኑን በሽታ በመለካት ከመጠን በላይ መሆኑን በማረጋገጥ በመጮህ ሪፖርት ያደርጋል፡፡
ሪፖርተር፡- ከሁለት መቶ በላይ ደንበኞች በመኖሪያ ቤታቸውና በመጋዘኖቻቸው የእናንተን ስማርት ሴኩሪቲ አላርም በመግጠም ንብረታቸውን እያስጠበቁ እንደሆነ ገልጸውልናል፡፡ በዚህ ውስጥ በማስገጠማቸው ንብረታችን ተረፈ ወይም ብናስገጥምም ከመዘረፍ አልዳንም ብለው ሪፖርት ያደረጉ ደንበኞች አሉ?
አቶ ቢኒያም፡- መቶ በመቶ ነው የምንቆጣጠረው፡፡ ደንበኞች ያስረከቡንን ንብረት ለ24 ሰዓት በንቃት በመቆጣጠር ብዙ የመዘረፍ ሙከራዎችን ማስቀረት ችለናል፡፡ በዚህም በድርጅቶችና በመኖሪያ ቤቶች ዙሪያ አጥር ዘለው ሊገቡ ሲሉ የተያዙና በጩኸቱ ደንግጠው የተመለሱ ዘራፊዎችን በምሥል አስቀርተን ለመመልከት ችለናል፡፡ ከዚህ በፊት በወር አንድ ጊዜ የመሰረቅ ሙከራዎች ሪፖርት ሲያደርሰን ነበር፡፡ አሁን ግን የደንበኞች ቁጥርና ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ በሳምንት አንድ ጊዜ የመሰረቅ ሙከራዎች በቤትና በድርጅቶች ሲደረግ ማየት እየቻልን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የጋራ መኖሪያ ቤቶች የሴኩሪቲ አላርም ሲስተም በምን መልኩ ነው የሚጠቀሙት?
አቶ ቢኒያም፡- አፓርትመንቶች ያን ያህል የደኅንነት ሥጋት የሌለባቸው ቢሆኑ፣ ከዕለታት ባንዱ ቀን መሞከራቸው ስለማይቀር ተመጣጣኝ የሆነ፣ ዋጋውም ቀነስ የሚያደርግ ሲስተም እያዘጋጀንላቸው ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ደንበኞቻችሁ የደኅንነት መጠበቂያቸውን ካስገጠሙ በኋላ የቴክኒክ ችግር ቢገጥመውና ቢበላሽ የጥገና አገልግሎት ማን ሊሰጣቸው ይችላል? ባለሙያስ አለ ወይ?
አቶ ቢኒያም፡- በአገልግሎታችን ዙሪያ ብልሽት ቢገጥም የጥገና አገልግሎት የምንሰጠው ራሳችን ነን፡፡ በፊትም ወርኃዊ የጥገና አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ ለምሳሌ አንድ ድርጅት 60 ቅርንጫፎች ቢኖሩት ሁሉንም ቅርንጫፎች ለ24 ሰዓት የምንቆጣጠረው እኛ ነን፡፡ ደወሉን ረስተው ቢያጠፉት እኛ ተከታትለን እናበራለን፡፡ በአጋጣሚ ቁልፍ ቢጠፋባቸውና ከዚህ ሰዓት እስከዚህ ሰዓት በቤትም ሆነ በድርጅት ማንም ሰው እንዳይገባ ወይም እንዳይወጣ ብለው ደንበኞቻችን ካዘዙን እስከተባለው ጊዜ ድረስ ቤቱ መከፈትም ሆነ መዘጋት አይችልም፡፡ የሚከፍተውም ባለቤቱ ደውሎ የሚስጥር ቁጥሩን ሲናገር ብቻ ነው፡፡