- ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል
በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት እየሰፋና እየተጠናከረ ስለሚሄድ ተመሳሳይ ዓላማ ያለባቸው ባንኮች ተዋህደው ለመሥራት ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ገለጹ፡፡
አቶ አህመድ ይህንን የገለጹት ባለፈው እሑድ በኢትዮጵያ አራተኛው ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመው ራሚስ ባንክ የምረቃ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው፡፡
እንደ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርቶች እየተጠናከሩ የሚሄዱ ከመሆኑም በላይ መንግሥት የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ስለሚያደርግ ለሚጠብቃቸው ውድድር ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡
ባንኮች ራሳቸውን ለማጠናከር ደግሞ ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸው ባንኮች እርስ በርስ በጥምረት በርትቶ መሥራት አንዱ አማራጭ በመሆኑ ከወዲህ ለዚህ መዘጋጀት እንዳለባቸው ሚኒስትሩ ገልጸዋል። አክለውም፣ የገለጹት ባንክ ለማቋቋም ጠንከር ያለ መሥፈርት እንደሚወጣና በቀጣይ ዓመታት ውስጥ ተግባራዊ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም እንደ ዋና መሥፈርት የሚጠየቀው የካፒታል መጠን ነው፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕግ ከአንድ ዓመት በፊት በወጣው መመርያ አንድ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው የተከፈለ ካፒታል አምስት ቢሊዮን ብር እንዲሆን ተወስኗል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት እመርታ እየታየበት ቢሆንም ከተሰበሰበው አጠቃላይ ተቀማጭ ውስጥ ለብድር የዋለው 40 በመቶ ብቻ በመሆኑ ተጨማሪ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ በዚሁ ፕሬግራም ላይ ገልጸዋል፡፡
እንደ ምክትል ገዥው ገለጻ በሒሳብ ዓመቱ አሥራ አንደኛ ወር ላይ በመስኮትና ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ ባንኮች የተሰበሰበው አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 171 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ሆኖም ከዚህ ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ በብድር መልክ ለተጠቃሚዎች የተላለፈው 40 በመቶው ወይም 68.8 ቢሊዮን ብር ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ከወለድ ነፃ አስቀማጮች ቁጥር ደግሞ 15.60 ሚሊዮን ደርሷል፡፡
ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት ብድር የወሰዱ ተጠቃሚዎችም ቁጥር 39.9 ሺሕ ብቻ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ሰለሞን በጥቅል ሲታይ ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች የሰበሰቡትን ያህል ተቀማጭ ገንዘብ ብድር እየሰጡ አለመሆናቸው የሚያመላክት ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት በመስኮት ደረጃ አገልግሎቱን እየሰጡ ካሉት ባንኮች ሌላ ዘጠኝ ማክሮ ፋይናንሶችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከወለድ ነፃ የባንክ አገለግሎት በመስኮት ደረጃ እየሰጡ በመሆኑ በዚህ ዘርፍ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ቁጥር 21 መድረሳቸው ተገልጿል፡፡
ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ባሻገር ተካፉል ወይም ከወለድ ነፃ የኢንሹራንስ አገልግሎትም በኢትዮጵያ እየተተገበረ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ሰለሞን ከወለድ ነፃ የኢንሹራንስ አገልግሎት የሚሰጡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አራት ደርሰዋል፡፡
እስካለፈው ሳምንት መጨረሻ እነዚህ አራት ከወለድ ነፃ የኢንሹራንስ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋሙት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ያሰባሰቡት የዓረቦን መጠን 48.41 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በመሆኑም ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱም ሆነ ከወለድ ነፃ የኢንሹራንስ አገልግሎት ያለው ከተደራሽነት አንፃር ብዙ የሚቀረው ስለመሆኑ አመላካች ነው ተብሏል፡፡ አቶ ሰለሞን እንደገሉጸትም በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት እመርታ እየታየበት ቢሆንም ከተሰበሰበው አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ ለብድር የዋለው 40 በመቶ ብቻ በመሆኑ ተጨማሪ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው የሚያሳይ ነው፡፡
ከዚህ አንፃር ገና ብዙ የሚቀረው በመሆኑ ይህንን ክፍተት ለመድፈን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እየሠራ መሆኑን ግን ገልጸዋል፡፡
‹‹ለብድር የዋለው 40 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ይህም 60 በመቶው በፋይናንስ መልክ ያልቀረበ መሆኑን እናያለን፤›› ያሉት አቶ ሰለሞን ይህም ከተደራሽነት አንፃር ገና ብዙ የሚቀረው በመሆኑም በፋይናንስ እውቀት በደንበኞች ጥበቃና በሕግ ማዕቀፍ ዙሪያ ተጨማሪ ሥራ ይጠይቀናል፡፡ ብሔራዊ ባንክም ይህንን ክፍተት ለመድፈን የፋይናንስ አማራጮችን በማስጠናት ሥራ ላይ ማዋል የሚያስፈልግ መሆኑን በማመን የተለያዩ ሥራዎችን መጀመሩን አመልክተዋል፡፡
በተለይ በቂ የሕግ ማዕቀፍ የለም በሚል የሚነሱ አስተያየቶች ትክክል ስለመሆኑ የገለጹት ምክትል ገዥው ሕግ ማዕቀፎች ላይ ብሔራዊ ባንክ እየሠራ መሆኑን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡
የራሚስ ባንክን በተመለከተ አቶ አህመድ አሁን ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ከተቋቋሙት ባንኮች አንዱ የሆነው ራሚስ ባንክም ከሌሎቹ ባንኮች ጋር በመቀናጀት ለአገር ብቻ ሳይሆን በምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ አገልግሎት የሚሰጥ እንዲሆን አደራ ብለዋል፡፡
የአገሪቱ የፋይናንስ ተደራሽነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የገለጹት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ የፋይናንስ አካታችነቱን ለማሳደግ የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ውስጥ ራሱን የቻለ ሸሪአን መሠረት ያደረገ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት መጀመሩን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡
በተለይ በእምነቱ ምክንያት ወደ ባንክ መምጣት ሳይችል ቀርቶ የነበረው የኅብረተሰብ ክፍል ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋሙ ባንኮች በርካታ ጠቀሜታ ያሳየ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
ይህ አገልግሎት መጀመሩ ለዘመናት ሲጠየቅ የነበረውን ጥያቄ ከመመለስ ባለፈ ጉዳዩ የመብት ጥያቄ በመሆኑ በዚህ ረገድ የተገኘው ውጤት አበረታች እንደነበርም በዚሁ ንግግራቸው አመልክተዋል፡፡
የራሚስ ባንክ ወደ ሥራ መግባት የአገሪቱን የባንክ ተደራሽነት ለማሳደግ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ያመለከቱት አቶ ሰለሞን ደግሞ ባንኩ የሸሪአ ሕግን ተመሥርቶ የሚሠራ ቢሆንም የሁሉም እምነት ተከታዮች የሚገለገሉበት እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል፡፡
ራሚስ ባንክ ባለው ዕቅድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት ለዋና መሥሪያ ቤትነት በገዛው ሕንፃ ላይ በይፋ ሥራ ጀምሯል፡፡ ባንኩ ኢንዱስትሪውን የተቀላቀለው ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ የተከፈለና ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ በተረፈመ ካፒታል ነው፡፡