- እኔ ምለው?
- እሺ… አንቺ የምትይው?
- የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ አባላት እንዲያወሩ ወይም እንዲጠይቁ አይፈቀድም እንዴ?
- እንዴት ይከለከላል?
- ታዲያ ለምንድነው ፕሬዚዳንቱ ብቻ የሚያወሩት?
- እያወሩ አይደለም፣ ገለጻ እያደረጉ ነው።
- ቢሆንም አንድም አባል ሲጠይቅ ወይም ሐሳብ ሲያቀርብ አይቼ አላውቅም፡፡
- አጋጣሚ ይሆናል።
- ዛሬ ብቻ እኮ አይደለም፡፡
- ቆይ ይህ ጉዳይ ለምን አሳሰበሽ?
- እንዴት አገር የሚመሩ ሰዎች በሐሳብ አይሟገቱም የሚል ጥያቄ ተፈጥሮብኝ ነው፣ ግን ትሟገታላችሁ?
- ለምን እንሟገታለን? የአንድ ድርጅት አባላት አይደለን አንዴ?
- እሱማ ነው፣ ቢሆኑም የተለያየ ምልከታ ያላቸው አባላት የተሰባሰቡበት ድርጅት ነው ብዬ ነው፣ ያልገባችሁንስ ትጠይቃላችሁ?
- ግልጽነት የሚሻ ጉዳይ ካለማ እንጠይቃለን።
- እንደዚያ ከሆነ ጥሩ፣ በል እስኪ አሁን ሲተላለፍ ከሰማሁት ያልተረዳሁትን ልጠይቅህ?
- ጠይቂኝ… ምንድነው ያልገባሽ?
- የወል እውነት መፍጠር ያስፈልገናል ያሉት ገብቶኛል፣ ግን ቀጥሎ የተናገሩት ምን ማለት እንደሆነ ልረዳው አልቻልኩም።
- የትኛውን ነው?
- የወል እውነት ካልተፈጠረ የአንዱ ኢትዮጵያዊና የሌላው ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያ መስማማት አይችሉም ያሉት ነገር ግልጽ አልሆነልኘም።
- ቆይ ቃል በቃል ያሉትን ልንገርሽ?
- እሺ…
- ‹‹የአንተ ኢትዮጵያ ዕውን የምትሆነው፣ የሌላው ኢትዮጵያዊም ኢትዮጵያ መሆን ስትችል ብቻ ነው፤›› ነው ያሉት፣ ቃል በቃል የተናገሩት ይኼንን ነው።
- እኮ ምን ማለታቸው ነው?
- እሳቸው የተናገሩትን ትንሽ ቀየር አድርጌ ባስቀምጠው የሚገባሽ ይመስለኛል።
- እስኪ አስቀምጥልኝና ልረዳው።
- በሌላ አነጋገር ምን ማለታቸው መሰለሽ?
- እህ…?
- ያንቺ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ሆና የምትቀጥለው፣ የሌላው ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያ ዕውን መሆን ስትችል ነው ማለታቸው ነው።
- የሌላው ኢትዮጵያዊ?
- አዎ፡፡
- ሌላው ኢትዮጵያዊ ማነው? የሌላው ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያ እንዴት ያለች ነች?
- የምጠይቅሽን ከመለስሽ ሌላው ኢትዮጵያዊ ማለት ማን እንደሆነ ይገባሻል።
- እሺ ጠይቀኝ፡፡
- አንቺ ኢትዮጵያን እንዴት ትገልጫታለሽ? ኢትዮጵያ ለአንቺ ማናት?
- ከአበው የተረከብናት የጥንቷ የጠዋቷ፣ ቃል ኪዳን የተገባላት ባለ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቋ ኢትዮጵያ ናታ፡፡
- ይኸውልሽ ገና በአበው ላይ እንኳን የወል ዕውነት አልፈጠርንም፡፡
- እ… ምን ማለት ነው?
- እሱ ውስብስብ ታሪክ ስለሆነ እንተወውና ሰንደቅ ዓላማውን ምሳሌ አድርገን ብናወራ ይሻላል።
- ሰንደቅ ዓላማው ደግሞ ምን ይወጣለታል?
- አንቺ እንደዚያ ብታምኚም፣ የማይቀበሉትና አምርረው የሚቃወሙት አሉ።
- ማነው የሚቃወመው?
- ሌላው ኢትዮጵያዊ።
- ሌላው ኢትዮጵያዊ የምትላቸው በሕገ መንግሥቱ ደስተኛ አይደሉም?
- ደስተኛ አይደሉም ማለት?
- አይቀበሉትም?
- እንዲያውም ሕገ መንግሥቱ ያጎናፀፋቸው መብት እንዲከበር ነው የሚጠይቁት።
- ታዲያ እኮ ሕገ መንግሥቱ የአገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ እንዳለ ተቀብሎ የሚያስማማ ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡
- አዎ፣ ምን ነበር ድንጋጌው የሚለው?
- የሰንደቅ ዓላማው ቀለሞች አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ነው። መካከል ላይ ያለው ዓርማ ደግሞ የሕዝቦችንና ሃይማኖቶችን እኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቅ ነው ይላል።
- ቢሆንም ሌላው ኢትዮጵያዊ ሰንደቅ ዓላማውን አምርሮ ይቃወማል።
- ምክንያታቸው ምንድነው?
- የአንድ ወገን ባህልና እምነት፣ ትውፊትና ማንነት በሌሎች ላይ መጫኑን የሚያስታውስ ምልክት ነው ይሉታል።
- እህ… ከስንት ሺሕ ዘመን በፊት የነበረ የማንነታችን መገለጫ ሆኖ ለሌሎች አፍሪካዊያን ነፃ መሆን ጭምር ተስፋ የፈነጠቀ ምልክት አይደለም እንዴ?
- እሱማ ልክ ነሽ።
- እና ለሌላው ኢትዮጵያዊ ሲባል የሌላው ኢትዮጵያ መፍረስ አለባት?
- ትፍረስ ሳይሆን ጥያቄው መመለስ አለበት ነው።
- ቆይ አንተ የትኛው ኢትዮጵያዊ ነህ?
- በግሌ ነው ወይስ በድርጅት ማንነቴ?
- አንተን ባለቤቴን ነው የጠየቅኩት።
- በቤተሰብ ደረጃማ አንለያይም።
- ግልጽ አድርገህ መልስልኝ፡፡
- ሁለት ኢትዮጵያማ በአንድ ቤት ውስጥ ልትኖረን አትችልም።
- የትኛው ነህ ማለት ነው? ግልጽ አድርገህ መልስልኝ።
- የአንቺ ኢትዮጵያ የእኔም ኢትዮጵያ ናት፣ ግን እንዳልኩሽ በቤተሰብ ደረጃ ነው።
- በድርጅት ደረጃስ?
- በድርጅት ደረጃ የአባላት ውሳኔ ገና አልተጠየቀም።
- ሲጠየቅስ?
- ሁኔታውን ዓይቼ እወስናለሁ።
- ወይ ጉድ?
- ምነው?
- የራሳችሁን ሳትይዙ በአገር ደረጃ አልቸኮላችሁም?
- የራሳችሁን ሳትይዙ?
- እህ…?
- ምንድን ያልያዝነው?
- የወል እውነት!
- Advertisment -
- Advertisment -