Friday, September 22, 2023

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት መወዛገቢያ አጀንዳ የሆነ ይመስላል፡፡ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመርን መቀሌ ድረስ ያስመጣቸው አንዱ ጉዳይ፣ በጦርነት ለተጎዱ ወገኖች የተላከ የምግብ ዕርዳታ ተመዝብሯል መባሉ እንደሆነ በሰፊው ተዘግቧል፡፡

ይህ የምግብ ዕርዳታ መዘረፍ አጀንዳ ለረዥም ጊዜ ሲያወዛግብ ከርሞ፣ ከሰሞኑ ለዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ የሥራ ኃላፊዎች ሥራ መልቀቅ መነሻ ምክንያት ሆኗል፡፡ የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ክላውድ ጂቢዳርና ምክትላቸው ጄኒፈር ቢቶንዴ፣ በዚሁ የምግብ ዘረፋ ጉዳይ የተነሳ የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸው እርግጥ ሆኗል ሲባል ቆይቷል፡፡ ክልሉን የሚያስተዳድሩትና በአንድም ሆነ በሌላ ከዕርዳታ ሥርጭት ጋር ግንኙነት ያላቸው አካላት በጉዳዩ ላይ ያሉት ነገር የለም፡፡

ይሁን እንጂ የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ክሌር ኔቪል ለሪፖርተር በሰጡት መግለጫ ከሥራ የለቀቀ የቢሮ ኃላፊ አለመኖሩን አረጋግጠዋል፡፡

ኃላፊዋ በላኩት የጽሑፍ መግለጫ ‹‹የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ክላውድ ጂቢዳር ፈቃድ ላይ ናቸው እንጂ የሥራ መልቀቂያ አላስገቡም፤›› ብለዋል፡፡ ምክትላቸው ጄኒፈር ቢቶንዴም ቢሆን ከሥራ አለመልቀቃቸውን ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊዋ አረጋግጠዋል፡፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ የሥራ ኃላፊዎች ለቀዋል ተብሎ መዘገቡ የተሳሳተ መሆኑም ተመልክቷል፡፡ ይሁን እንጂ ድርጅቱ በትግራይ ሥራ ያቆመው በዕርዳታ እየቀረበ ያለ የሰብዓዊ ረድኤት በገበያ ለሽያጭ መቅረቡ በመረጋገጡ እንደሆነ አረጋግጧል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌላ ዓለም አቀፍ ውዝግብ እየፈጠረ ያለ አጀንዳ ከትግራይ ክልል የተገኘ ይመስላል፡፡ የትግራይና የአማራ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱበት የወልቃይት ጉዳይ፣ በምዕራባውያን ዘንድ ያገባኛል የበዛበት ርዕስ ሆኗል፡፡ ከሰሞኑ እየወጡ ባሉ የምዕራባዊያን መገናኛ ብዙኃንና የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ሪፖርቶች፣ በወልቃይት አካባቢ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ እንደሆነ ተዘግቧል፡፡

ሒዩማን ራይትስዎች ከመስከረም እስከ ሚያዝያ 2015 ዓ.ም. ባለው ጊዜ 35 ሰዎችን በስልክ ቃለ መጠይቅ በማድረግ ሰበሰብኩት ያለውን ሪፖርት ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል፡፡ የወልቃይት የአካባቢ ባለሥልጣናት ማለትም እነ አቶ በላይ አያሌውና ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ብሎ በስም የጠራቸው ሰዎች የሚመሩት ነው ያለው የሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ በትግራይ ተወላጆች ላይ መፈጸሙን ይዘረዝራል፡፡

ሒዩማን ራይትስዎች በወልቃይት አካባቢ በትግራይ ተወላጆች ላይ ተፈጽሟል ለሚለው ማፈናቀል፣ እስርና ሌላም የሰብዓዊ መብት ረገጣ በተለያዩ ጊዜያት እንደ ሮይተርስ ያሉ ሚዲያዎች የሠሩትን ዘገባ ማጣቀሻ አድርጎ ሲያቀርብም ነበር፡፡ በሰኔ ወር የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢ ቡድን በወልቃይት አካባቢ ጉብኝት እንደሚያደርግ ሪፖርቱ ይጠቅሳል፡፡ በዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የተቋቋመው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ኮሚቴም፣ ተመሳሳይ ቅኝት እንዲያደርግ የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲፈቅድ ይጠይቃል፡፡

ከሰሞኑ ይህን መሰል ሪፖርቶችን አከታትለው እያወጡ ያሉት ምዕራባዊያኑ፣ ወልቃይት ለትግራይ ተወላጆች መሰቃያ እንደሆነ በሰፊው ሲዘግቡ ከርመዋል፡፡ በአካባቢው የተለያዩ ማጎሪያ እስር ቤቶች መፈጠራቸውንና ከ2,000 በላይ የትግራይ ተወላጆች በእነዚህ ቦታዎች መታሰራቸውንም በሰፊው አትተዋል፡፡

ይሁን እንጂ የምዕራባዊያኑ ሪፖርቶች ‹‹ምዕራብ ትግራይ›› እያሉ የሚጠሩትን ከባድ ጦርነትና ደም መፋሰስ ያስከተለ የይገባኛል ጥያቄ፣ በሁለት ክልሎች መካከል ከ30 ዓመታት በላይ ሲነሳበት የቆየ ነው፡፡ የወልቃይት ባለቤትነት ጥያቄ ‹በግርግርና በጩኸት› ለትግራይ አሳልፎ ለመስጠት የተጠና ዘመቻ ከፍተዋል ሲሉ ነው ሁኔታውን በቅርበት የሚከታተሉ የተናገሩት፡፡

ይህ ካልሆነ ደግሞ ምዕራብ ትግራይ ወይም ወልቃይት በሚባለው ቀጣና ተፈጸመ የሚሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና ለማሳደር እየተጠቀሙበት ነው የሚል ጥርጣሬ በአንዳንዶች ዘንድ አሳድሯል፡፡

የወልቃይት የይገባኛል ውዝግብ በሕግ አግባብ መፈታት የሚችል ጉዳይ ሆኖ ሳለ፣ የምዕራባዊያኑ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርቶች የተለወሰ ዘመቻ ከየት የመጣ ነው ሲሉ የጠየቁ በርካታ ናቸው፡፡ ምዕራባዊያኑ በአንድ ሉዓላዊ አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት አልፈው፣ በአንድ አገር ውስጥ ባሉ ሁለት ክልሎች መካከል የተፈጠረ የወሰን ውዝግብን እንዳኝ የሚሉበት አንዳችም የሕግም ሆነ የሞራል አግባብ አለመኖሩን በርካቶች እየተቹም ነው፡፡

የወልቃይትን አጀንዳ ምዕራባዊያኑ ለምን ያጮሁታል ተብለው የተጠየቁት የወልቃይት ተወላጅና ማኅበራዊ አንቂ አቶ አስፋው አብረሃ፣ ውስጥ ለውስጥ የሚከናወኑ አጀንዳዎች ያሉ እንደሚመስላቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹አሜሪካም ሆነች ምዕራባውያኑ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሌላ ዓይነት ካሽሚር ለመፍጠር የፈለጉ ይመስላል፡፡ ወልቃይት የሱዳን፣ የኤርትራና የኢትዮጵያ መገናኛ ስለሆነች ልክ ምሥራቁንና ምዕራቡን ዓለም እንደምታገናኘው ዩክሬን ሌላ የውዝግብ ቀጣና የመፍጠር ፍላጎት ያላቸው ይመስላል፤›› ብለዋል፡፡

ይህ ከሚታየውና ከሚሰማው በመነሳት ለእውነት የቀረበ ነው በሚል የሚሰጥ ግምት እንጂ፣ የምዕራባዊያኑ ፍላጎት ከዚህ የተለየም ሊሆን እንደሚችል አቶ አስፋው ይናገራሉ፡፡

‹‹የፌዴራል መንግሥት አቋም በዚህ ጉዳይ ድብቅ ነው፡፡ አንድ የክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መሪ ጌታቸው ረዳ በየአደባባዩ እየወጣ በሰኔ ወልቃይትን እንይዛለን፣ ክረምት ወይ ግንቦት 20 እንይዛለን፣ ይፈጥናል ወዘተ እያለ የሚናገረው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ከጀርባ ወይ በድብቅ የተገባለት ቃል ከሌለ በስተቀር ሰው እንዲህ አይናገርም፡፡ ፌዴራል መንግሥት በዚሁ ጉዳይ አቋሙን የማያንፀባርቀው ለምንድነው? ከፌዴራል ይልቅ ሕወሓቶች በዚሁ ጉዳይ ግልጽ ናቸው፤›› በማለት ነው አቶ አስፋው የሚሰማቸውን የተናገሩት፡፡

የወልቃይት አጀንዳን ከትግራይ አስተዳደር በላይ ምዕራባዊያኑ እያረገቡ ባሉበት ወቅት፣ እሑድ ግንቦት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. የአካባቢው ነዋሪዎች በየአካባቢው የተቃውሞ ሠልፎችን ሲያካሂዱ ታይተዋል፡፡ ሰላማዊ ሠልፎቹን ተከትሎ ደግሞ ባለስምንት ነጥቦች የአቋም መግለጫ ይፋ ሆኖ ነበር፡፡

በአቋም መግለጫው እንደተገለጸው፣ ጉዳዩ በሕጋዊ መንገድ ተቋጭቶ፣ ሕዝቡ ፊቱን ወደልማት እንዲያዞር የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ሕዝቡ መጠየቁ ተመላክቷል፡፡

የዚህ አቋም መግለጫ ሁለተኛ ነጥብ ተገቢውን የሚዲያ ሽፋን የማግኘትና እውነታውን ይፋ የማድረግ ጥያቄ ያነሳል፡፡ በወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ላይ የተፈጸመው ረዥም ዘመናት ያስቆጠረው ግፍ በአፍሪካ ኅብረት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በአውሮፓ ኅብረት፣ እንዲሁም በሌሎችም ዓለም አቀፍ ተቋማት ገለልተኛና ሀቀኛ አካል ቦታው ድረስ በነፃነት ተገብቶ እውነታው እንዲጣራ ሕዝቡ እንደሚፈልግ የአቋም መግለጫው ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ ደግሞ ከሰሞኑ ሪፖርት ያቀረቡ የሰብዓዊ መብት ተቋማትን ያጠቃለለ መሆኑ ተገምቷል፡፡

በማይካድራ ብቻ 1,650 ሰዎች በሕወሓት በግፍ መጨፍጨፋቸውንና ለዚህና ለሌሎችም በወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ላይ ለደረሱ በርካታ ግፎች ፍትሕ የሚባል ተሰጥቶ እንደማያውቅ የአቋም መግለጫው አመልክቷል፡፡ በሌላ በኩል የአካባቢው ሕዝብ ከደረሰበት ግፍ በተጨማሪ፣ ከልማት ወደኋላ የቀረና በድህነት የተዘፈቀ በመሆኑ የገንዘብና የሞራል ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ይጠይቃል፡፡   

የአካባቢው ሕዝብ በደም አፋሳሽ መራር ትግል ነፃነቱን መጎናፀፉን የጠቀሰው የአቋም መግለጫው፣ አስፈላጊው የበጀትና አስተዳደራዊ ዕገዛ ሊደረግለት እንደሚገባም ያብላላል፡፡ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በተግባር እንዲተረጎም የጠየቀው መግለጫው እንደ ሒዩማን ራይትስዎች ዓይነት ተቋማት ከሀቅ ጋር እንዲቆሙ ይጠይቃል፡፡ የአቋም መግለጫው በስተመጨረሻም የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ አገራዊና ቀጣናዊ ፋይዳው ጉልህ በመሆኑ፣ በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ‹እውነትና ዕውቀትን› መሠረት ባደረገ መንገድ የሚመለከተው ሁሉ ጥረት ሊያደርግ እንደሚገባም ያሳስባል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ማክሰኖኞ ግንቦት 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ እንደ ሒዩማን ራይትስዎች ያሉ ተቋማት የወልቃይትን አጀንዳ ማራገባቸውን ተቃውሟል፡፡ ‹‹በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የነበረው ግጭት በርካታ አካባቢዎችን ለጉዳት የዳረገ ሆኖ ሳለ፣ ሒዩማን ራይትስዎች የተባለው ድርጅት ግን በልዩ ሁኔታ የተወሰነ አካባቢን መርጦ ደጋግሞ ሪፖርት በማድረግ፣ በሰብዓዊ መብት አጀንዳ ሽፋን የተለየ የፖለቲካ ተልዕኮውን ለማሳካት መሞከሩ ተቀባይነት የለውም፤›› በማለት ነው መግለጫው የተቃወመው፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ የሒዩማን ራይትስዎች ሪፖርትን፣ ‹‹ተገቢ ምርመራ ያልተደረገበትና በበቂ ማስረጃም ያልተደገፈ›› ብሎታል፡፡ ሪፖርቱ የተዛባና በአካባቢው ያለውን ሁኔታም ያላገናዘበ ከመሆኑም በላይ፣ ለዘመናት አብረው የቆዩ ሕዝቦችን አብሮ የመኖር እሴት የሚያጠለሽ፣ ለዕርቅና ለምክክር የሚደረጉ ጥረቶችንም የሚያደናቅፍ መሆኑን መግለጫው ያትታል፡፡ መግለጫው በአጠቃላይ የሒዩማን ራይትስዎች ሪፖርት ገንቢ ያልሆነና ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም ይጠቅሳል፡፡ 

ለወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት በመሟገት የሚታወቁት አቶ ተስፉ የሺወንድም በበኩላቸው፣ ከሒዩማን ራይትስዎች ጀርባ የአሜሪካኖቹ ፍላጎት መኖሩን ይናገራሉ፡፡ ‹‹አካባቢውን ለሕወሓት በማሰጠት መቆጣጠር ይፈልጋሉ፡፡ ቢቻል ደግሞ ከወልቃይት ተነስተው በጠላትነት የፈረጁትን የኤርትራ መንግሥት መቆጣጠር አሜሪካኖቹ ይመኛሉ፤›› ብለዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ሁሉንም ወገን አስደስታለሁ በሚል ራሱንም አገሪቱንም ችግር ላይ እየጣለ ነው የሚሉት አቶ ተስፉ፣ በወልቃይት ጉዳይ መንግሥት ‹‹ከሁለት ብቻ ሳይሆን ከሦስትና አራትም ያጣ እንዳይሆን ያሠጋል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ከምዕራባዊያኑ ለመታረቅ በማለት ዕርዳታና ድጋፍ ለማግኘት በሚል ሥሌት ከሕወሓት ጋር ሽር ጉድ ማብዛቱን የጠቀሱት አቶ ተስፉ፣ ‹‹ፈረንጆቹ አንዴ ጥያቄ ከጀመሩ ሱሪ ቢያወልቁላቸው እንኳ በቃኝ አያውቁም፤›› በማለት ነው የወልቃይትን አጀንዳ ምዕራባዊያኑ ከሕወሓት ጀርባ ሆነው እየጋለቡት መሆኑን በሰፊው ያስረዱት፡፡

በፕሪቶሪያው ድርድር ወቅት የመንግሥት ተደራዳሪ ቡድንን የመሩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር)፣ በአንድ ወቅት ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለድርድር ሒደቱ ገለጻ አድርገው ነበር፡፡ ሬድዋን በዚሁ ገለጻቸው አጨቃጫቂ የድንበር ጉዳዮች (ማለትም የወልቃይትና ራያ ጉዳዮች) በድርድር ሒደት የነበራቸውን ቦታም በሰፊው አንስተዋል፡፡

‹‹በድርድሩ ሒደት ስለወልቃይት ጉዳይ ወይም ምዕራብ ትግራይ በሕወሓት በኩል ምንም ነገር አልተነሳም፡፡ ሕወሓት ይህን ጉዳይ አጀንዳ አለማድረጉ ለእኛም ገርሞን ነበር፡፡ ሕወሓት ጦርነት ያደረገበትን ዋና መነሻ አጀንዳ አለማድረጉ ቢያስገርምም ዝምታው ግን ያለውን ነባራዊ ሀቅ ‹ዲፋክቶ› መቀበል ይመስል ነበር፡፡ ተቃውሞ ያልተነሳበት ጉዳይ ተቀባይነት እንዳገኘ ይቆጠራል በሚለው ዕሳቤ ሕወሓት በዚህ ጉዳይ ያለውን ሁኔታ ተቀብሎታል የሚል ነበር አቋማችን፡፡ ክርክር ቢያደርግ አንድ ነገር ነው፡፡ ሆኖም ክርክር ባለማድረጉ በወልቃይት ጉዳይ ያለውን ‹ዲፋክቶ› እንደተቀበለው ነበር የቆጠርነው፤›› ሲሉ ሬድዋን (አምባሳደር) አስረድተው ነበር፡፡

በድርድሩ መገባደጃ ወቅት ግን፣ ‹‹አንዳንድ ጉዳዩ እንዲነሳ የሚያደርጉ ነገሮች ተፈጠሩ፤›› የሚሉት አምባሳደሩ፣ በዚህ ጊዜ የምዕራብ ትግራይ ወልቃይት ጉዳይ ይፈታ የሚል ጥያቄ ሕወሓት ማቅረቡን አውስተዋል፡፡

‹‹በስተመጨረሻ ግን ከድርድሩ ብዙ ነገር ስለተገኘ በዚህ ጉዳይ ድርድሩን በሙሉ ከምናፈርሰው፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ከውጭም ከውስጥም የመጠበቅ ኃላፊነት የፌዴራል መንግሥቱ በመሆኑ፣ መከላከያ በእነዚህ አጨቃጫቂ የድንበር አካባቢዎች ይቆያል የሚል ነጥብ ላይ ተደረሰ፤›› ሲሉ ሬድዋን (አምባሳደር) አስረድተው ነበር፡፡

አምባሳደሩ አጨቃጫቂ የድንበር ጉዳዮች፣ ‹‹በሕገ መንግሥታዊ አግባብ ይፈታሉ›› የሚል መግባባት ላይ በፕሪቶሪያው ድርድር መደረሱንም በግልጽ አስቀምጠው ነበር፡፡

በወልቃይት እንዲሁም በራያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ኃይሎችም ቢሆኑ እነዚህ ከባድ ደም መፋሰስ ያስከተሉና ለረዥም ዘመናት ሲያወዛግቡ የቆዩ ጉዳዮች፣ በሕገ መንግሥታዊ አግባብና በሰላም ስምምነቱ መሠረት እንዲፈቱ ሲጠይቁ ይሰማሉ፡፡ የወልቃይት አካባቢ ነዋሪዎች ከሰሞኑ በተካሄዱ ሰላማዊ ሠልፎች ባወጡት የአቋም መግለጫ ይኼው መርህ እንዲከበር ጥያቄ ማቅረባቸው ታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ የወልቃይትን አጀንዳ ለመጥለፍ ያሰፈሰፉ የሚመስሉት ምዕራባዊያኑ፣ አጀንዳውን ዳግም ሁለቱ ክልሎችን ወደ ግጭት መክተቻ መነሻ ለማድረገ ለአንድ ወገን ባጋደለ መንገድ እያራገቡት ነው የሚሉ ድምፆች እየተሰሙ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -