Saturday, September 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየግሉ የጤና ዘርፍ አገልግሎት ከኅብረተሰቡ የመክፈል አቅም በላይ እየሆነ መምጣቱን ኢሰመኮ አስታወቀ

የግሉ የጤና ዘርፍ አገልግሎት ከኅብረተሰቡ የመክፈል አቅም በላይ እየሆነ መምጣቱን ኢሰመኮ አስታወቀ

ቀን:

የግሉ የጤና ዘርፍ የአገልግሎት ክፍያ ከኅብረተሰቡ የመክፈል አቅም በላይ እየሆነ መምጣቱን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡ የግሉ የጤና ዘርፍ ከኅብረተሰቡ የመክፈል አቅም ጋር የተመጣጠነና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት አቅርቦት ላይ ባተኮረው የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ­­­ሪፖርቱ ነው ይህንን ያስታወቀው፡፡ 

ኮሚሽኑ ዓርብ ሰኔ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ ያደረገው ባለ 39 ገጽ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ የግሉ የጤና ዘርፍ አገልግሎት ከመንግሥት የጤና ዘርፍ አገልግሎት ጋር ሲነፃፀር፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከኅብረተሰቡ የመክፈል አቅም በላይ እየሆነ ነው፡፡ ለዚህም የሕክምና ግብዓቶች አቅርቦት እጥረትና ዋጋ መናር፣ የግዴታ ግዥ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረትና ቁጥጥር አናሳ መሆን፣ ከሙያ ሥነ ምግባር ውጪ የሆኑ ተግባራትና በመንግሥት ተቋማት የተሟላና አመርቂ አገልግሎት አለመኖር ምክንያት ናቸው ብሏል፡፡

በግሉ የጤና ዘርፍ የሚሰጡ አገልግሎቶች ለኅብረተሰቡ በፋይናንስ ተደራሽ እንዲሆኑ የአሠራር፣ የፖሊሲና የሕግ ማሻሻያ ያስፈልጋል ያለው ኮሚሽኑ፣ በመንግሥት የጤና ተቋማት ላይ የአገልግሎትና የአቅርቦት ማሻሻያና ተገቢ ቁጥጥር በማድረግ፣ ኅብረተሰቡ አማራጭ እንዲያገኝ ማድረግ፣ መሠረታዊ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የጤና መድን አገልግሎት ማስፋፋትና የግል የጤና ተቋማትም የሚሳተፉበትን አሠራር መዘርጋት ያስፈልጋል ሲል ምክረ ሐሳብ ሰጥቷል፡፡

ለጤና አገልግሎት አስፈላጊ ለሆኑ አቅርቦቶች ከቀረጥ ነፃ አገልግሎትን ማፋጠንና ማሻሻል፣ የመንግሥትና የግል የጤና ተቋማት ሽርክናዎችን ማጠናከር፣ በአስመጪዎች በኩል ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ መቆጣጠር፣ በሕክምና መሣሪያዎች ግዥ ላይ አመቺ አሠራር በመዘርጋት ተገቢ የሆነ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግም፣ በአተገባበር ደረጃ ሊሻሻሉ ይገባል ተብለው በሪፖርቱ ከተቀመጡት ምክረ ሐሳቦች ይጠቀሳሉ፡፡

ከፖሊሲና ከሕግ ማሻሻያዎች አኳያም፣ ለሕግ ባለሙያዎች ተግባራዊ የተደረገው ነፃ የሕግ አገልግሎት ተሞክሮ ላይ በመመሥረት፣ በግል ዘርፍ የተሰማሩ የጤና ባለሙያዎች፣ በሰዓት የተገደበ ነፃ የሕክምና ሙያዊ አገልግሎትና የግል የጤና ተቋማቱም በየደረጃቸው ዝቅተኛው መጠን የተወሰነ ድርጅታዊ፣ ማኅበራዊ ኃላፊነት በነፃ ለማኅበረሰቡ እንዲሰጡ የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት፣ በጤና ዘርፉ በተለይም ለጤና አገልግሎት የመክፈል አቅም የሌላቸውና ለጉዳት ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት በማድረግ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ማስፋፋትና ማጎልበት የሚሉትን ምክረ ሐሳቦችን አካቷል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአብዛኛው በመንግሥት ሲቀርብ በነበረው የጤና አገልግሎት ላይ የግሉ ዘርፍ በሰፊው መሰማራቱ ሊበረታታ እንደሚገባው ገልጸው፣ ተቋማቱ ካላቸው የፋይናንስ ተደራሽነት አንጻር ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ አስታውቀዋል፡፡   

የጤና መብት ተገኝነት፣ ተደራሽነት፣ ተቀባይነትና ጥራት ላይ ያተኮሩ አራት ዋና ዋና ይዘቶች ያሉት ሲሆን፣ ሪፖርቱ የተጠናከረው፣  በተደራሽነት ሥር ከተጠቃለሉት ንዑስ ይዘቶች በገንዘብ ተደራሽነት ላይ ትኩረት አድርጎ ነው፡፡

 ሪፖርቱን ለማዘጋጀትም በአጠቃላይ ከ218 የባለድርሻ አካላት (80 የግል የጤና ተቋማት ኃላፊዎች፣ ከስምንት መንግሥታዊ ያልሆኑ የጤና አገልግሎት ተቋማት ተጠሪዎች፣ ከ20 የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች፣ ከ80 የግል የጤና ተቋማት ተጠቃሚዎች/ተገልጋዮችና ከ30 የምክክር መድረክ ተሳታፊዎች) ከሐዋሳ፣ ከባህር ዳር፣ከአዲስ አበባና ከጅማ ከተሞች መረጃዎች መሰባሰባቸውን የኮሚሽኑ መግለጫ ያሳያል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...