Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልምሥጋና እና ዝየራ ለልማት አርበኛው ገራድ ስርጋጋ ዳሪ

ምሥጋና እና ዝየራ ለልማት አርበኛው ገራድ ስርጋጋ ዳሪ

ቀን:

በአበበ ፍቅር

‹‹መልካም ሥራ ከመቃብር በላይ ትውላለች›› የሚለውን አባባል ብዙ ጊዜ ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው የሚሠሩትንና ሠርተው ያለፉትን ሕያው የሆነ ሥራቸውን ለመዘከር ወይም ለማስታወስ የሚያገለግል አባባል ነው፡፡

ብዙ ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው በሠሩት መልካም ሥራቸው ቀሪው ትውልድ ሲያመሠግናቸው፣ አሊያም በሠሩት ክፋት የክፉ ነገር ምሳሌ ሲደረጉ ይታያል፡፡

በመልካም ሥራቸው ስማቸው የሚነሱ ሰዎች ብዙ ጊዜ የኅልፈት ዜናቸው ከተሰማ በኋላ ከመቃብራቸው ላይ ነው፡፡ ይህ ዓይነት ሙገሳ ግን ብዙ ጊዜ በተለይ በኢትዮጵያ ሊቀረፍ ያልቻለ አካሄድ ነው የሚል ትችት ይቀርብበታል፡፡

ለአገር ታላቅ ውለታን ለዋሉ ሰዎች፣ የአገርን ዳር ድንበር ላላስደፈሩ፣ ለሰንደቅ ዓላማቸውና ለድንበራቸው ውድ ሕይወታቸውን ለሰዉ ጀግኖች አፈር ሳይጫናቸውና ሞት ሳይቀድማቸው ሥራቸውን በዓይናቸው ማሳየት፣ ሲሞቱ ከማልቀስ የተሻለ ተግባር ነው የሚሉት ብዙዎች ናቸው፡፡

በሌላ በኩል በመልካም አስተዳደርና በአመራር ጥበብ ትውልድን ያሻገሩ ባለውለታዎች የዕውቀት ጮራን በመፈንጠቅ ለትውልድ ብርሃን የሆኑ አባቶችን በልማትና በንቁ ተሳትፏቸው አይቻልም የተባለን ነገር በ‹ይቻላል› መንፈስ ተክተው በማኅበረሰቡ ልብ ውስጥ ሆነው በጀግንነት ሲወደሱ ይኖራሉ፡፡ በሕይወት እያሉ አባቶችን ስለሠሩት መልካም ሥራና ስላደረጉት የለውጥ እንቅስቃሴ ከማለፋቸው ቀደም ብሎ ማመሥገን፣ የመልካምነት ተሞክሯቸውንና የስኬት መንገዳቸውን ለቀጣዩ ትውልድ ያለመሰሰትና ያለመሰልቸት እንዲያካፍሉ ያደርጋል፡፡

ለዚህም ይመስላል የሙጎና አካባቢ ሕዝብ ‹‹ዕድሜያቸውን በሙሉ ለአካባቢና ለአገር ልማት የሰጡ የአገር ባለውለታ አባቶችን ማመሥገን፣ ለቀጣይ ትውልድ የሚፈጥረው በጎ ሚና ወደር የለውም፤›› በማለት ለሐጂ ስርጋጋ ዳሪ የምሥጋናና የዝየራ ፕሮግራም በማዘጋጀት ለሠሩት መልካም ሥራ ለሐጂ ስርጋጋ  ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

ስርጋጋ ገና በሕፃንነታቸው ምቹ ባልሆነና ከአካባቢያቸው ማኅበረሰብ ዘንድ ትችት በሚቀርብበት፣ በሚነቀፍበት እንዲሁም ሃይማኖታቸው በማይፈቅድላቸው መንገድ ተጉዘው ወደ ቄስ ትምህርት ቤት በመግባት ቀለምን የቀሰሙት፣ ታዲያ ከቀለምም አልፈው ‹‹አባታችን ሆይ! በሰማያት የምትኖር…›› የምትለውን የየኔታን ጸሎት እንደዋዛ ማነብነብ እንደጀመሩ፣ የሐጂ ስርጋጋን የሕይወት ታሪክ በሚያትተው ዶክመንተሪ ላይ ተነግሯል፡፡

ታዲያ ይህንን የሰሙ የአካባቢው ሰዎች የስርጋጋ አባት፣ ‹‹ልጅህን አስጠመቅከው እንዴ?›› ሲሉ ጥያቄ አቀረቡላቸው፡፡ አባቱ ዳሪም ከልጃቸው አንደበት፣ ‹‹አባታችን ሆይ! በሰማያት የምትኖር…›› የሚለውን ጸሎት ሲያነበንብ በመስማታቸው ሕፃኑ ስርጋጋን ከየኔታ ዘንድ ድርሽ እንዳይል አደረጉት፡፡

ይሁንና ለወራት ከየኔታ የቀሰመው ትምህርት ውሎ አድሮ የስርጋጋን የሕይወት አቅጣጫ ቀይሯል፡፡

በጊዜው በአካባቢያቸው የተማረ ይቅርና ስለትምህርት ጠቀሜታ የማያውቀው ማኅበረሰብ ደብዳቤ ሲላክላቸው ወደ ስርጋጋ መምጣታቸው አልቀረም፡፡ ማንበብ ብቻ ሳይሆን ፊደላትን ገጣጥሞ፣ ቃላትን መሥርቶ ለደብዳቤው መልስን ይጽፉ ነበር፡፡ ሲውል ሲያደር ግሩም የሆነ ክህሎቱን የተረዳው የአጥቢያው ፍርድ ቤት ለከሳሽና ለተከሳሽ የሚቀርብ ጽሑፍን እንዲያዘጋጅ ተደረገ፡፡ በሒደትም ስለከሳሽና ስለተከሳሽ ለሁሉም የሚሟገት የልምድ ነገረ ፈጅ ለመሆን እንዳበቃው ተነግሯል፡፡

ተወልደው ያደጉበት በሥልጤ ዞን የበርበሬ ወረዳ የሙጎ ቀበሌ አካባቢ ኅብረተሰብ ባለመማሩ የእግር እሳት የሆነባቸው ወጣቱ ስርጋጋ፣ በ1950ዎቹ ገደማ ወደ አዲስ አበባ መጥተው በሚኖሩበት ወቅት ከበርበሬ ተወላጆች ጋር በመተዋወቅና መዋጮ ቢጤ በማሰባሰብና ተሳትፎ በማድረግ፣ በማይምነት ውስጥ የሚኖረውን ኅብረተሰብ በትምህርት ለማበልፀግ ከላይ ታች ሲሉ ቆይተው፣ በዕድር አባላትና በሌሎችም ቀና ትብብር ትምህርት ቤት በአካባቢው እንዲመሠረትና ልጆች እንዲማሩ በ1958 ዓ.ም. መሠረትን ጣሉ፡፡

በወቅቱ ፈተና የነበረው ነገር የአካባቢው ኅብረተሰብ የእስልምና እምነት ተከታይ በመሆኑ፣ ‹‹ዘመናዊ ትምህርት የክርስቲያኖች ትምህርት ነው››፣ ሃይማኖታችን አይፈቅድም በማለት፣ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት መላክ አለመቻላቸው እንደነበር ሐጂ ስርጋጋ ያስታውሳሉ፡፡

በወቅቱ የነበረውን የቤተክህነት ትምህርት ሥጋት ለመቅረፍ ትምህርት ቤቱን ጠንስሰው ለፍሬ ያበቁት የበርበሬ መረዳጃ የዕድር አባላት ልጆቻቸውን በግንባር ቀደምትነት ትምህርት እንዲማሩ በማድረግና ለአካባቢው አርዓያ ለመሆን ቢሞክሩም ኅብረተሰቡ፣ ‹‹ትምህርት ሃይማኖትን ያረክሳል›› በሚል ግንዛቤ በወቅቱ ማንም ሰው ልጁን ለመላክ አልደፈሩም ነበር፡፡

ዋነኛው ምክንያታቸውም በወቅቱ በአካባቢው የቤተክህነት ትምህርት ይሰጥ ስለነበር ዘመናዊ ትምህርት ‹‹ያካፍራል›› ወይም ‹‹ሃይማኖት ያስክዳል›› በሚለው ነበር፡፡

በወቅቱ በመረዳጃ ዕድር አባል የነበሩት እንዲሁም በአካባቢ በሃይማኖታቸው የሚከበሩት ሼህ ኑረዲን የተባሉ የበጎ ፈቃድ መምህር ስለነበሩ፣ ለሕፃናት ተማሪዎች ሃይማኖታዊ መዝሙሮችንና ግጥሞችን በማስናዳት ሕዝብ ለሶላትና ለሌሎች ጉዳዮች በሚሰበሰብበት ወቅት እነዚህን መዝሙሮች እንዲቀርቡ በማድረግ በኅብረተሰቡ ላይ ያለውን አመለካከት በአንድ ጊዜ የቀየረና ውጤት ያስገኘ ነበር፡፡

የአካባቢው ሙስሊም ቦታ እስኪጣበብ ድረስ ሕፃናትን ወደ ትምህርት ቤት መላክ ጀመረ፡፡ ከዚህም አልፎ ለትምህርት ቤቱ ገንዘብ በማሰባሰብ በ1958 ዓ.ም. የተጀመረው ግንባታ በ1961 ዓ.ም. ተጠናቀቀ፡፡

በዚህ መልኩ የጀመረው የሙጎ አካባቢና በአጠቃላይ የሥልጤ ዞን የልማት እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ አሁን ላይ ለደረሰበት ደረጃ እንደበቃ ተነግሯል፡፡

በ1970ዎቹ አጋማሽ ‹‹የአዘርነት በርበሬ የመረዳጃ ማኅበር የዕድገት ምንጭ›› ወደሚል ስያሜ ተቀይሯል፡፡ በዚህ ወቅትም ሐጂ ስርጋጋ የዕድሩ ዋና ሰብሳቢ ነበሩ፡፡

ሐጂ ስርጋጋም በወረዳው የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲስፋፋ ኅብረተሰቡን በማስተባበርና ባለቤት በማድረግ፣ እንዲሁም ከዞን ጀምረው እስከ ትምህርት ሚኒስቴር ድረስ በብርቱ በመንቀሳቀስ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ያጠናቀቁ ተማሪዎች ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተሸጋግረው ይማሩ ዘንድ በአካባቢው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሠራ አድርገዋል፡፡

በሐጂ ስርጋጋ የሚሠራው ሥራ በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ደስታና መነቃቃትን በመፍጠሩ፣ ለከፍተኛ ልማት ከኅብረተሰቡ ገንዘብ በሚጠይቁበት ወቅት ከወተት ላም እስከ ፈረሳቸው ድረስ ይሰጡ እንደነበር ሐጂ ስርጋጋ ያስታውሳሉ፡፡

በዚህ መልኩ በሚሰበሰበው ገንዘብ በዞኑ ብዙ ትምህርት ቤቶችና የጤና ጣቢያዎችንም ለማስገንባት በቅተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከሌሎች ረጂ ድርጅቶች ገንዘብ በማሰባሰብ በሙጎ አንድ ዘመናዊ የጤና ማዕከል፣ ጤና ጣቢያ እንዲሁም የእንስሳት ጤና ኬላ ለማስገንባት ችለዋል፡፡

የንፁህ ውኃ መጠጥ እንዲያገኙና የመብራት አገልግሎትን፣ የአካባቢን ማኅበረሰብ በማስተባበር የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ሥራ እንዲሠራም ያደረጉት ሐጂ ስርጋጋ፣ ከዚህ ባሻገር ኅብረተሰቡ ከኋላቀር አስተሳሰብ ተላቆ የቁጠባ ባህልን እንዲያዳብርና የተሻለ ኑሮን እንዲኖር አሻራቸውን ያስቀመጡ የአገር ባለውለታ ናቸው ሲሉ ብዙዎች መስክረውላቸዋል፡፡

‹‹ስርጋጋ ባሉበት ሁሉ ልማት አለ፤›› ሲሉም ያደንቋቸዋል፡፡ ንብ ባንክን በማቋቋም ሒደት በአደራጅነትና በመሥራች አባልነት ጉህል አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ የባንኩ የቦርድ አባል በመሆንም አገልግለዋል፡፡

ያላቸውን የሕይወት ተሞክሮ ለወጣቱ ሲያካፍሉ ‹‹ኅብረተሰቡን ማገልገል የፈለገ ሰው በቅድሚያ የማንቃት ሥራን መሥራት ይገባዋል›› ይላሉ፡፡ ከልማቱ ምን ሊጠቀም እንደሚችል ማስረዳት፣ ማንቃትና ማደራጀት፣ የተደራጀውን ማኅበረሰብ በብቃት ሊመራው የሚችል መሪን መፍጠር ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

ቀጣዩ ትውልድም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ወደ ዩኒቨርሲቲ፣ ጤና ጣቢያዎችን ወደ ሆስፒታል በመቀየር የራሱን አሻራ ሊያስቀምጥ ይገባዋል ብለዋል፡፡

‹‹እዚያ ማዶ ያለው ካልለማ እዚህ የሠራነው መበላሸቱ አይቀርም፤›› የሚሉት ሐጂ ስርጋጋ፣ ታላላቆች ለማኅበረሰባቸው ልማት የከፈሉትን መስዋዕትነት ተገንዝቦ በሕይወት እያሉ ዕውቅና መስጠት፣ ማመሥገን፣ ከአዲሱ ትውልድ ጋር ማስተዋወቅና ማስተማሪያ ማድረግ ራሱ ታላቅነት ነው በማለት አወድሰዋል፡፡

ሐጂ ስርጋጋ አገራቸውንና ሕዝባቸውን ከነበረበት ኋላቀርነት እንዲላቀቁ የሕይወት ዘመናቸውን ከገጠር እስከ ከተማ ሕዝብ በማስተባበር ለሠሩት የበጎ አድራጎትና የልማት ሥራ፣ ስላስመዘገቡት ደማቅ አገልግሎት ግንቦት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. በኢሄው ላዴ የበጎ አድራጎት ማኅበር ‹‹የአገር ባለውለታና የልማት አርበኛ›› በማለት የምሥጋናና የዝየራ ሥነ ሥርዓት አድርገውላቸዋል፡፡

ሐጂ ስርጋጋ ዳሪ ላበረከቱት በጎ አስተዋጽኦ በሥልጤ ባህል ‹‹ገራድ›› የሚል የክብር ስያሜ በአገር ሽማግሌዎች ተበርክቶላቸዋል፡፡

‹‹ገራድ›› በሥልጤ ባህል በሕይወት ዘመናቸው መልካም ሥራን ለሠሩ ትልልቅ ሰዎች የሚሰጥ የክብር ስም እንደሆነ ማዕረጉን የሰጡ አባቶች ተናግረዋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...