Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ምን ሆነናል?

ሰላም! ሰላም! ‘እንደገና ፍቅር እንደገና፣ እንደገና አይገኝምና’ ይሉት ዘፈን እንደ እውነቱ ለፍቅር ቢሠራም ለእኔና ለእናንተ ግን አልሠራም። እንዴት ሰነበታችሁ? ቀኑን እየገፋነው ይሁን ወይ እየገፋን ይኼው በሰንበት አንተጣጣም። በዚያም ተባለ በዚህ ዘመኑ የገፊና የተገፊ ነዋ፣ ምን ይደረግ? ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ጋሽ መሐሙድ አህመድ ‹ከልብ አመሠግናለሁ› ብሎን ማይኩን ከማስቀመጡ በፊት፣ ይህንን የእንደገና ዜማ ርዕሰ ጉዳይ እየለዋወጠ ደጋግሞ ቢጫወተው እንዴት ሸጋ ነበር? አንበርብር ሁሉም ነገር ብትል እንደ ትናንቱ መቼ ይገኝና?›› ሲለኝ ነበር። ‹‹እንዴት?›› ብዬ ማብራሪያ መጠየቅ በእውነቱ ድካም ሆነብኝ። እያወቅኩት? እያወቅነው? ከአቋም እስከ ጥራጥሬ በነበረበትና በትናንትና ሥፍራው ዋጋው አልገኝ ማለቱን እያየሁ ለምን ብዬ ላድክመው? እናንተዬ ዘመኑና ሰው ትናንት እንደምናውቀው አልገኝ ብሎ አሻፈረኝ እንዳለ ምን አስረጂ ያስፈልገዋል ትላላችሁ? ሰው ብትሉት እንደ ቃሉ፣ እንደ አለባበሱ፣ እንደ ተቀመጠበት ወንበር (ሹመት) ክብደት የመገኘቱ ነገር በተጠያቂነትና በግልጽነት አሠራር ብቻ የሚመለስ እንቆቅልሽ አልሆነም። ታማኝነት፣ ቀናነት፣ ሰው አክባሪነትና ትሁትነት የሚባሉ እሴቶች ምን እንደዋጣቸው የታወቀ ነገር የለም። እኔስ አፋልጉን ብለን አደባባይ እንውጣ ይሆን እላለሁ የምለው ሳጣ። ‘የጨነቀው እርጉዝ ያገባል’ ሲሆንብኝ። አሁን አሁንማ ሆን ብሎ አስረግዞ የሚያገባው በዛ እንጂ። ተመልከቱ ተረትና አባባሉም ለትናንት እንጂ ለዛሬ አልሠራም እያለ መጥቷል። ‹‹ወይ ጊዜ…›› አሉ ባሻዬ በስንት ልመናና ምልጃ የቀጠሉት ዕድሜ ጉድ እያሳየ ቢያስቸግራቸው፡፡ ይቻሉት እንግዲህ!

ስለዘመን ካነሳን አይቀር ማለቂያ ባይኖረውም አንድ አንድ እንበል እስኪ። እንግዲህ የዘንድሮ ነገር ከአየር ንብረቱ የባሰ አይደል እንዴ ያስቸገረን? ታዲያ እንጫወታ። በረባ ባረባው በሚያልቀው ዘመናችን የዘመኑን ነገር ማማት እንደሆነ ሲወርድ ሲዋረድ የተቀበልነው የአያት የቅድም አያቶቻችን ወግ ነው። በተለይ የአሁኑ ትውልድ ባይኖረውም ይትብሃሉን ለመጠበቅ ደፋ ቀና ሲል እታዘበዋለሁ። ታዲያ ሰሞኑን ነው አየሩም ጠዋት እንዳረፈደው በማያመሽበት በዚህ ጊዜ አንድ ጎልማሳ ወዳጄ ድንገት ደርሶ፣ ‹‹አንበርብር?…› አለኝ። እኔ ደግሞ ምን ገጠመው ብዬ፣ ‹‹አቤት ወዳጄ…›› ስለው፣ ‹‹…አንድ ሰሞን ካስተዋወቅኩህ የከንፈር ወዳጄ ጋር ልንጋባ ቆርጠናል…›› ሲለኝ ‹‹ማለፊያ፣ እንኳን ደስ አለህ…›› ብዬ አቀፍኩና የወዳጅነት ደስታዬን ገለጽኩለት። ‹‹እና ምን ልርዳህ?›› ስለው፣ ‹‹ቤተሰቦቿ ዘንድ ሽማግሌ አድርጌ ልልክህ ነው…›› አለኝ። ‹‹በዚህ ዕድሜያችሁ እንጋባ ብላችሁ ራሳችሁ ቆርጣችሁ ስታበቁ ልክ እንደ ወጣቶቹ የሚያደርጋችሁ የምን ድራማ ነው?›› ልለው አሰብኩና ከአፌ መለስኩት። በወግና በልማዱ ውስጥ ጣልቃ ገብቼ ባልፈተፍትስ? ‹‹አሁን እኔ ትልቅ ሰው ነኝ። አንተም አርባዎቹን ጨርሰህ ሃምሳዎቹን እየጀመርክ ነው፡፡ እኔ ምን ብዬ ነው ባለቀና በአዛውንት ጉዳይ ሄጄ ‘ልጃችሁን ለልጃችን’ የምለው?›› ብለውም ሊሰማኝ አልቻለም። እንዲህ ያለውን ድፍረትና ወኔ ስለማላውቀው በጣም ተጨነቅኩ። በኋላ ማንጠግቦሽን፣ ‹‹እንዲያው ምን ይሻለኛል?›› ብላት፣ ‹‹ነገር ማጥበቅ ስትወድ? ደረስ ብለህ ብትመጣ ምን እንዳይቀርብህ ነው? እንዲያው ያንተስ ነገር…›› ብላ አታማርርብኝ መሰላችሁ? እኔ እሷን በወጣትነታችን ሳገባ በሽማግሌ መላክ ምክንያት ያየሁትን አሳር ትናንት ዋጋ ሰጥታ ስታሞጋግሰኝ እንዳልነበር፣ አሁን ለይስሙላ የሚሠራው ሥራና ዕቅድ ሁላ ደጋፊ ሆናልኝ ቁጭ። እንዲህ እውነትን በአደባባይ ‘ዓይንሽን ላፈር’ ብሎ ሕይወትን ቴአትር ያደረገበት ዘመን ይሁን ግን? ‘የምንኖረው አርቴፊሻል’ አለች ያቺ ድምፀ መረዋ፡፡ ምን ታድርግ!

እንደምታውቁት እዚህ አገር ሥራ ላይ ብቻ አተኩሮ መኖር ከባድ ነው። ማኅበራዊ ሕይወቱ ራሱ ራሱን የቻለ ሥራ በሉት። መቼስ ምን ይደረግ በዚህ ቀውጢ የኑሮ ማዕበል በራስ ላይ ድራማ ለመሥራት ሥራ አልፈታም ብዬ ሰላሜን አላጣ እያልኩ እየተነጫነጭኩ ወደ ሙሽሪት ቤተሰቦች። በሩቅ የማውቃቸው ሦስት ጎልማሶችም አሉበት። ‹‹ሲጋቡ ሸምግለን ሲጣሉ ሸምግለን›› እያለ ከመካከላችን አንዱ አንዲት ቀልድ አወጋን። ‹‹ሚስት ‘እንዲህ በጠጅ የምትጨርሰውን ገንዘብ ብትቆጥበው ዓለምን ትዞርበት ነበር’ ትለዋለች ባልን። ባል ሲመልስ ምን ቢል ጥሩ ነው? ‘አምስት ብርሌ ጠጅ ስጠጣ ራሷ ትዞር የለም ወይ? እኔ ምን አደከመኝ?’ አላት…›› ሲለን ሳቅ በሳቅ። ነገ ፍቅር እንደ ጫጉላና የእጮኝነት ጊዜ አልሆን ሲል ሥራ ፈተን ‘ተው!’ ‘ተይ!’ ስንል የምንውለውን እንተወው፣ ማሟረት ይሆንብናል። ብቻ በተቀመጠበትና በተተከለበት ሥፍራ የሚገኝ ነገር እየጠፋ ነው። እንደተዋችሁት የምታገኙት ሰው አለ ከተባለ ግን ምናልባት ታክሲ ጥበቃ የተሠለፈ ሰው ብቻ መሆን ይገባዋል። እውነቴን አይደል? ‘ካልተሳፈሩበት ቶሎ ተሽቀዳድሞ፣ ጊዜ ታክሲ አይደለም አይጠብቅም ቆሞ’ እንዳልተባለ ዛሬ ተለውጦ ታክሲ ቆሞ እንዳልጠበቀን ቆመን ጠባቂዎቹ እኛ ሆንን። ‹‹ዘ ይገርም ሻሸመኔ›› ያለው ማን ይሆን? እንጃ!

ስለታክሲ ጥበቃ ሳነሳ ባለፈው ሰሞን አንድ ወዳጄ፣ ‹‹እነሱ ተመችቷቸው በ‘ቪ8’ ይንፈላሰሳሉ፣ እኛ እዚህ እንደ ድንጋይ ተገትረን እንውላለን…›› ሲል ብሰማው፣ ‘ጓደኞችህ ተመችቷቸው በመርስዲስ ይንፈላሰሳሉ አንተ እዚህ ቆመህ ቀረህ፣ ድንጋይ’ እያለ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ሥር ቆሞ ይሳደብ ስለነበረው ‘ጀብራሬ’ አንድ መጽሐፍ ውስጥ ያነበብኩት ትዝ ሲለኝ ነበር። የእኛ ኑሮ በትዝታ ሆኗል። ‹‹ማርጀታችን የሚታወቀው በተስፋ ቀርቶ በትዝታ መኖር ስንጀምር ነው›› ያለው ሰው እንዴት ያለ ሊቅ ነበር? የሕዝቡ የትራንስፖርት ችግር ፈጽሞ የገባው የማይመስለው ፀሐዩ መንግሥታችን ምን መፍትሔ እያሰበልን እንደሆነ በእውነቱ እኛም አላወቅንም፣ ቃል አቀባዩ ‘ኢቲቪ’ም አልነገረንም። ድሎትና ቅምጥል ኑሮ አሳዳጅ የሆኑ አንዳንድ ባለሥልጣኖቻችንንና እኛን ላነፃፀረ ግን ወዳጄ ለማለት የፈለገው ነገር በደንብ የሚገለጽለት ይመስለኛል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ለሕዝብና ለእውነት፣ ለማተባቸው ብለው መስዋዕትነት የከፈሉትንና በሕዝብ ሀብት ዕንቁላል መስለው የሚንፈላሰሱብን ስታስቡ እንዴት ያለ ኅሊና እንዳላቸው ማወቅ አያሰኛችሁም? ሙስና የአፍሪካ የበኩር ልጅ ይመስል የዘራነውን ሁሉ እየወረሰን እስከ መቼ እንደምንኖር እንጃ፡፡ እስከ መቼስ በራስ ላይ መቀለድ ተቀናቃኝ የሌለው ሀብታችን ሆኖ ይኖራል? ማንም አያውቅም!

ታክሲ ጥበቃ በተሠለፍንበት ነው ብያችኋለሁ። አንዱ ‘ወይ ሐረር ወይ ሸገር ነይና አጫውችኝ’ በሚለው ዜማ ማፏጨቱን ገታ አድርጎ፣ ‹‹ኤድያ ፍቅር ድሮ ቀረ ታክሲ በሽ በነበረበት ዘመን፡፡ አሁን ነይ ቢሏት እሷስ ልምጣ ብትል በምን ትመጣለች?›› ሲል ፈገግ ያሰኘዋል ሰውን። ሌላው ተቀብሎ፣ ‹‹ኧረ እውነትህን ነው፣ ‘ከትልቁ ሾላ ከሥሩ ደርሼ ያለ ዕድል አይበሉ መጣሁ ተመልሼ’ አይደል የሚለው የአገሬ ሰው። ስም ያተረፈብን ዘመን፡፡ ባዶ ኪስን ማን ይጠጋል?›› ይላል። ‹‹እንዲህ የትራንስፖርት ፖለቲካ ከራሳችን አልወርድ ብሎ እንዴት አድርገን ነው አሉ አገር በቀሉን የኢኮኖሚ ዕድገት ዕቅድ የምናሳካው?›› ይለዋል ሌላው። ‹‹መልሱ አልተሰጠም…›› እየሳቀ ይመልሳል ሦስተኛው። ‹‹ውይ ፈጣሪ ሲወዳቸው እኮ…›› ትላለች ደግሞ አንዷ ቀዘባ ሠልፈኛ። ‹‹ማንን?›› ይጠይቃታል (ወዳጇ ነው መሰል አብረው ናቸው)፣ ‹‹የበፊቶቹን የአገር መሪዎች ነዋ። እንኳን እንዲህ ስንሆን አላዩን…›› አለች የአንጀቷን መንሰፍሰፍ ፊቷ በማጨማደድ ለመግለጽ እየሞከረች። ‹‹ቢያዩን ዝም የሚሉ ግን ይመስልሻል?›› ከማለቱ ሦስተኛው ሠልፈኛ፣ ‹‹እንዴት ዝም ይላሉ? ‘መንግሥት ለእያንዳንዱ ዜጋ መኪና ማደል አይችልም፣ አቅም የለንም’ ይላሉ እንጂ እንዴት ዝም ይላሉ?›› ብሎ ፈገግ። ‹‹እንዴት?! መቼ ለእያንዳንዳችን መኪና ይሰጠን አልን?›› ሲለው ሌላው ሠልፈኛ ተናዶ የልጁ መልስ ከአንጀቱ መሳቅ ነበር። ቅኔው ገባኝ ያለ አብሮት ይስቃል፡፡ ሰምና ወርቁን መለየት ያልቻለ ሁሉ!

ሙቀትና ቅዝቃዜውን ችዬ በታክሲ ዕጦት እየተንገላታሁ ሥራ መፈለጌን መቼም አልተውኩትም። ቆይቼ አንድ ሥራ አግኝቻለሁ። ‘የማታ ማታ’ እንዲሉ፣ ሥራው ዘመናዊ የሆነ ባለሦስት ደርብ ቪላ ሻጭን ከገዥ ጋር ማገናኘት ነው፡፡ ሻጭ ይህንን ዘመናዊ ቪላ ጆሮውን ብሎ በላሦስት መኝታ ኮንዶሚኒየም ለመብዛት አስቧል፡፡ ስለዚህ ሌላም ሥራ ይጠብቀኛል ማለት ነው፡፡ ወጥቼ ወርጄ ያገኘሁት ገዥ ግን ሥጋት ገብቶታል፡፡ ሰሞኑን የተጀመረው የንብረት ታክስ ጉዳይ ሁሉንም ነገር የሚያጦዝ መስሎታል፡፡ ለምሳሌ እሱ እንደነገረኝ ሻጭ አጋጣሚውን በመጠቀም ዋጋ እንደሚቆልል፣ እሱ እንደ ምንም ብሎ ቢገዛ ደግሞ ታክሱ ከአቅሙ በላይ ሊሆንበት እንደሚችል ነው ሥጋቱ፡፡ በተጨማሪም የንብረት ታክስ አዋጅ ሳይወጣ አፈጻጸም መጀመሩም የጤንነት አልመሰለውም፡፡ ደግነቱ ሻጭ ደግሞ ቶሎ በአገር ዋጋ ሸጦ መገላገል በመፈለጉ በፍጥነት ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡ አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ሽያጭ ተጠናቆ ኮሚሽኔ በአካውንቴ ሲላክልኝ የነገዎቹ ግብይቶች እያሳሰቡኝ መንገዴን ቀጠልኩ፡፡ የሆነስ ሆነና ይህ ሁሉ ጥድፊያና ሁካታ ለምን ይሆን ብዬ ብጠይቅ ምን ይመስላችኋል ለማለት ያህል ነው፡፡ እስቲ ተነጋገሩበት!

በሉ እስኪ እንሰነባበት። የእኔ ነገር ለካ የሽምግልናውን ጨዋታ አልጨረስኩትም? አሁን እኔ ሰው ነኝ? ምን ሆነ መሰላችሁ ‘አሁን ማን ነው የሚጀምረው? ምን ብሎ ነው የሚናገረው?’ ስንባባል ሳለን የሙሽሪት እናት በቤት ሠራተኞቻቸው ታጅበው ጠጁን፣ ጠላውን፣ ሽንጡን፣ ዳቢቱን ከፊታችን አስቀረቡና ‘በሉ!’ ይሉን ጀመር። አባወራው ደግሞ ‘አሞራው በሰማይ ሲያሽ ዋለን’ ከፍተው ጆሯችንን አደነቆሩት። ‹‹እንዲያው ትንሽ እንኳ ሳንጫወት?›› ሲላቸው ከመሀላችን አንደኛው ሁለቱም የፌዝ ሳቅ ስቀው፣ ‹‹ብሉና ይደርሳል፣ ምን የሚያስቸኩል ነገር ኖረና ለወሬው?›› ብለው በነገር ወጉን። ኃፍረት ቢያሽመደምደንም የመብሉ አጋጣሚ የሚታለፍ አልነበረም። ‹‹ይታይህ እንግዲህ ይኼ ዘመን? ወይ አልሠለጠነ ወይ አንደኛውን ወደኋላ አልቀረ?›› ብዬ ግሮሰሪ ስንገናኝ ለምሁሩ የባሻዬ ልጅ አጫወትኩት። ‹‹እናንተስ ስንት ሽማግሌ የሚያስፈልግበት ሥፍራ እያለ…›› ብሎ በእንጥልጥል ተወው። ‹‹ማለት?›› ስለው፣ ‹‹መንግሥት ነዋ፣ በዚህ ጊዜ ሽማግሌ የሚያስፈልገው እኮ ለመንግሥት ነው። የሚሠራውና የሚያስበው መልካም ነገር ሊኖር ቢችልም፣ አልፈታቸው ያሉ ችግሮች ከዕለት ወደ ዕለት በዝተዋል። ቢነገር ቢዘከር አልሰማ ብሏል። ‘ለችግሮቻችን መፍትሔ ዳርልን’ ብለን በሽማግሌዎች ደጅ መጥናት አለብን። በሕግ ካልሆነ በሽምግልና መሞከር…›› ብሎኝ፣ ‹‹ቢራውን ድገመኝ!›› አለው ወደ አሳላፊው ዞሮ። ጉድ እኮ ነው!

ከእሱ ጋር እየተሳሳቅን ሳለ አንድ ድምፅ ከባንኮኒ አካባቢ ይሰማ ነበር፡፡ ‹‹ጎበዝ እስቲ እየተደማመጥን፡፡ ለአቅመ ግሮሰሪ ጠጪነት ያልበቃችሁ ጎረምሶች እስኪ ድምፃችሁን ቀንሱ…›› እያለ ማሳሰቢያ ሲሰጥ ሁሉም ተስተናጋጆች ፀጥ አሉ፡፡ ሰውዬው ትኩረት ማግኘቱን ካረጋገጠ በኋላ፣ ‹‹ጎበዝ እኛ ግን ምን ነክቶን ነው እንዲህ እንደ አውሬ እርስ በርስ ጎራ ለይተን የምንነካከሰው… ለመሆኑ መሀላችን ምን ቢገባ ነው በብሔርና በሃይማኖት የምንናጀሰው… ፈጣሪን ምን ብንበድለው ነው ለምለም አገር ውስጥ ፈጥሮን ረሃብተኛ የምንሆነው… ዙሪያችንን የታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪዎች እያንዣበቡብን ምን ሆነን ነው አንድነት የምናጣው… ልዩነቶቻችንን በወጉ አስተናግደን በሠለጠነ መንገድ መነጋገር ያቀተን ምን ሆነን ነው… ለሁሉም ነገር መፍትሔው ጠመንጃ ብቻ ይመስል ለምን ይሆን ለውይይት ቅድሚያ መስጠት ያቃተን… ምን ያህል ከንቱዎች ብንሆን ነው የጨዋዎቹን አገር የሌቦች መፈንጫ ያደረግናት… እነዚህንና ሌሎች አንገብጋቢ ችግሮቻችን ታቅፈንስ እስከ መቼ ነው የምንቆዝመው….›› እያለ የችግራችንን ብዛት ሲዘረግፈው ደነገጥን፡፡ እኔ በበኩሌ ምድር ተከፍታ ብትውጠኝስ እያልኩ ነበር ውስጤ የታመሰው፡፡ እንዲያው የግሮሰሪ ወግ ስለሆነ ሳይሆን እኛ ግን ምን ነክቶን ነው እንዲህ የምንሆነው ያሰኛል፡፡ እስቲ ሁላችንም ከራሳችን፣ ከቤተሰባችን፣ ከማኅበረሰባችን እየጀመርን መላ አገራችንን በዓይነ ህሊና ብንዳስስ ሁኔታችን ያስፈራል፡፡ የስንትና ስንት ጀግኖችና ጠቢባን አገር የነበረችው ኢትዮጵያ እንዲህ የዓለሙ ሁሉ መዘባበቻ ስትሆን አያሳፍርም እንዴ? የሆነስ ሆነና ምን ሆነናል? መልካም ሰንበት! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት