Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትስለከባዱና ስለባለ ብዙ ፈርጁ የሰው ግንባታ ጥቂት ነጥቦች

ስለከባዱና ስለባለ ብዙ ፈርጁ የሰው ግንባታ ጥቂት ነጥቦች

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

1/ ሀ) የትኛውም ፅንፈኝነት ምን ያህል ፋይዳ ቢስ እንደሆነ፣ ተደርሶባት የነበረችን የኢኮኖሚና የልማት አቅምን እምሽክ አድርጎ ምን ያህል የኋሊት እንደሚያስገባ በተግባር ታይቷል፡፡ በዚህ ረገድ መላ የኢትዮጵያ ተራ ኅብረተሰብ ብዥታ የለበትም፡፡ ሁሉም የሚሻው ሰላም አግኝቶ መልማትንና መግባባትን መጨበጥ ነው፡፡ ለምን? የሁሉም ፅንፈኞች ድግስና ጠመንጃ ዝቅተኛውን የሰው ልጅ መብት እንኳ የሚነፍግ ግፍ ሠሪ መሆኑን ቀምሶ አረጋግጧል፡፡ ከዚህ አኳያ የፅንፈኞች ፖለቲካ በተግባር ከስሯል፡፡ በተለይ በትግራይ የደረሰበት ኪሳራ የከፋ ነው፡፡ እንደገና ሰውን ወደ ጠመንጃ ስቦ በሰላማዊ ኑሮው ላይ ዘራፍ እንዲል ለማድረግ፣ እጅግ ከባድ የሚሆንበትም ሥፍራ ከሁሉም በላይ ትግራይ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የፅንፈኞች ክስረት ደረጃ ቢበላለጥም ድጋፍ የሸሸው የጠመንጃ ተኩሳቸው አቅሙ እየተራገፈ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሕዝብ እታገላለሁ ባይ ጠመንጃ ተኳሽነት በጥቅሉ ወደ ማባራት እያመራ ነው፡፡ የኅብረት ትግላችን ከበረታ፣ ሙሉ ለሙሉ የመክሰሙም ውጤት በኢትዮጵያ መጪ ጉዞ ውስጥ እንደሚሳካ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል፡፡ ለዚህ መተማመኛችን የጫካ ‹‹ታጋዮች›› በጥላቻና በበቀል፣ በነፍሰ ገዳይነትና በጭፍን አራጅነት የበከቱ የገሃነም መልዕክተኞች መሆናቸው ለማንም የማይሰወር ሆኖ መውጣቱ፣ በግስጋሴና በዴሞክራሲ ውስጥ የመራመድ ተስፋ ደግሞ ከአሁኑ መንግሥት ጋር ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡ ፅንፈኞች ግን አሁንም ገና ተሸነፍን አላሉም፣ በተለይ በውጭ ያሉት፡፡ በትግራይ ፅንፈኞች ዘንድ መከፋፋል ደርሶ አሮጌና ቁልቁል ወሳጅ መስመራቸውን የጣሉ ቢኖሩም፣ አሁንም አፋቸውን አብሰው ግራና ቀኝ የሚገላመጡ፣ ተደብቀው ሸር የሚያደሩና የፖለቲካ ኡኡታ ለመፍጠር የሚሆን ነገር ለማግኘት ቋጥኝ የሚቧጥጡ አልጠፉም፡፡ በኦሮሞም በአማራም በኩል ያሉ ጠመንጃ ያዦች ለጠመንጃ ኑሮ የሚነግዱበት ነገር እያጡ፣ እያንዳንዷን የሰላም ዕለት በአግባቡ የሚጠቀምባት የኢትዮጵያ ግስጋሴ እየፈጠነ፣ በእነሱ የፕሮፓጋንዳ ውስወሳ ማስተዋል ተስኗቸው የነበሩ ዓይናቸው እየተገለጠ፣ ወስዋሾችም ራቁታቸውን እየቀሩና መከፋፈላቸው እየበረታ መሄዱ አይቀርም፡፡ ዋናው ቁምነገር ግን ዛሬ ባሉበት የዝቅጠት ደረጃ ፅንፈኞች አንድ ላይ ማኅበር ባይጠጡም ሁላቸውም ብሔሬ ለሚሉት ሕዝብ አንድም ፋይዳ የማያመጡ፣  ሕዝብን ሰላምና ትልቅ አገር አሳጥቶ የማፋጀት ግብረ አበሮች መሆናቸውን ከወዲሁ አውቀን የበኩላችንን የትግል ርብርብ መያያዛችን ነው፡፡ ለዚህም ነው እነዚህን የጥፋት ኃይሎች ከትግራዊነት፣ ከኦሮሞነትና ከአማራነት ጋር ከማዛምድ ድጥ ወጥተን፣ ሁሉንም ኢትዮጵያን ወደ ሥርዓት አልባነትና ወደ መበታተን ገሃነም በሚያስገባ ጥላቻና በቀል የነደዱ፣ በሁላችንም ህልውና ላይ የመጡ ጉግማንጉጎች አድርገን ማየት የሚያስፈልገን፡፡

የኢትዮጵያ የለውጥና የግስጋሴ ዥረት የትግል ዓይኑን ማሳረፍ ያለበት ጥፋት አጠናቆ ባነከታቸው ኃይሎች ላይ ብቻ አይደለም፡፡ ርብርባዊው የግስጋሴ ሞገድ ከድንጋይ እያላተመ ወስዶ ምድረ በዳ ላይ እንደሚጥለው የታወቀው ከጥፋት ጋር ግቢና ደጅ እያለ የቆየ (በመጨረሻ ግቡ ላይ ከጉግማንጉጎቹ ያልራቀ)፣ አፈግፍጎ ብሔርተኛ ልሂቃንን በለዘብታ እያበለዙ መራመድ የሚል ታክቲክ የያዘ ረድፈኛንም ማስተዋል አለብን፡፡ ልዝቡ ክንፍ የሚበጀን መስሎ ከውስጥ እንዲያነክተን ‹‹ፈቅደንለት››፣ የለየላቸው ጉግማንጉጎች ላይ ትኩረታችን ቢያፈጥ ልፋታችን ሁሉ አለባብሶ የማረስና እንደገና በአረም የመመለስ ይሆናል፡፡

ልዝቡን ረድፍ እየመራው ያለው ጃዋር መሐመድ በ2012 ዓ.ም. መጀመርያና መዳረሻ ግድም በተከሰቱ በውድመትና በሰዎች ጥቃት የቀለሙ ግርግሮች ውስጥ፣ ምን ያህል ኢቀጥተኛና ቀጥተኛ ሚና እንደነበረው ለኢትዮጵያ ኅብረተሰብ አላወራም፡፡ ያ ከመሆኑ በፊትም ሆነ ያ አልፎ ወጣቱ ሰው እስር ቤት ገብቶ ከወጣም በኋላ፣ ከእውነታ ጋር ታርቆ አዎንታዊ ሚና ይጫወታል ብዬ ብዙ ተስፋ ካደረግሁባቸው ሰዎች አንዱ ነበር፡፡ ይህ ተስፋዬ የእኔ ዓይነት ወይም የእከሌ ዓይነት አመለካከት ይኑረው ብሎ የመጓጓት ጉዳይ አልነበረም፡፡ የፖለቲካ ሳይንስ እንደ መማሩ ራሱም ‹‹የፖለቲካ ሳይንቲስት ነኝ›› እንደ ማለቱና የብዙ አካባቢዎችን ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች አጥንቻለሁ እንደ ማለቱ፣ ቢያንስ በትምህርቱ በኩል ያገኘው የሰው ልጆች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አዝግሞት ከሚነግረው እውነት ጋር የተስማማ ነገር ይዞ መምጣቱ አይቀርም የሚል ነበር ተስፋዬ፡፡ ለእሱ የባሰበት ጉዳይ ግን ከታሪክ እውነት ከመማር ይልቅ የከሰረ አሮጌ የፖለቲካ ቀመርን ሰዎች ህሊና ውስጥ አለሳልሶ መቀርቀር ነው፡፡

ለ) ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆኑኝ ጌታሁን ሄራሞ ከሚያዝያ 15 እስከ 22 ቀን 2015 ዓ.ም. ባለ ጊዜ በሪፖርተር ጋዜጣ ‹‹እኔ የምለው›› ዓምድ ላይ ያወጣቸው፣ በጃዋር መሐመድ ጽሑፍ ላይ የተሰነዘሩና የጃዋርን ከዚህም ከዚያም የተንቦጫረቁ (ኤክሌክቲክ) የንድፈ ሐሳብ ሥሮች ያሳዩ ጠንቃቃ ትችቶች ናቸው፡፡ ስለብሔር/ብሔረሰብ ምንነትና ስለብሔርተኝነት የምዕራቡ ሰዎች በቀነበቧቸው ንድፈ ሐሳቦች ውስጥ ገብቼ አልዳክርም፡፡ የጃዋርን ጽሑፍም እዚህ እዚያ እያልኩ የመተቸት ፍላጎትም የለኝም፡፡ የእኔ ጉዳይ የተወሰኑ የዕሳቤ ቁልፎችን ይዤ፣ አንባቢዎች ከዓለም የሰው ልጆች ታሪክና ከኢትዮጵያ የታሪክ እውነቶች ጋር አገናዝበው ለመፍረድ እንዲችሉ የሚጠቅሙ ፍሬ ነገሮችን መጥኜ በመደርደር ላይ የተወሰነ ነው፡፡

በቅድሚያ ማን አላቸው የሚለውን ትተን ቁልፎቹን ዕሳቤዎች እናገናዝባቸው፡፡ ብሔር/ብሔረሰብነት ሥጋ ዘመዳምነት (Kinship)፣ ሴመኝነት (Homogeneity)፣  መኖሪያ መሬት የእግዜር ስጦታ፡፡ የብሔር/ብሔረሰብ ሕዝብንና መኖሪያ መሬቱን (ከእግዜር የተሰጠውን) ግጥምጥም (Cngruent) ሆኖ እንዲቆይ ማድረግ፡፡

የዕሳቤዎቹ ሠልፍ እንደሚያሳየው የብሔር/ብሔረሰብነት ጥንቅር በሥጋ ዝምድና ላይ የተመሠረተ ከሆነ፣ ሴመኝነቱም ሥጋ ዝምድናው በባዕዶች አይከለስ/አይደፈራርስ ማለት መሆኑ ነው፡፡ መኖሪያ መሬትን የእግዜር ስጦታ የሚያደርግ አመለካከት፣ መኖሪያ በታሪክ ውስጥ ይለወጣል፣ ይሰፋል፣ ይጠባል የሚል ነገርን አትቀበል የሚል አንድምታ አለው፡፡ የብሔር/ብሔረሰብ ጥራትን ከእግዜር ከተሰጠ መኖሪያ ጋር መጠበቅ መልዕክቱ ግልጽ ነው፡፡ የብሔረሰብ አባልነትን በሥጋ ዝምድና ዓይን ተረድቶ ከ‹ሥጋ ዝምድና› ውጪ ያለን ሰው ባዕድ አድርጎ መቁጠር ጤናማ ነው፡፡ ለሥጋ ዘመድ ማድላትም ጤናማ (ተፈጥሯዊ) ነው ብሎ በውስጠ-ታዋቂ የሚሰብክ፣ ብሔር ብሔረሰብነት የማኅበራዊ መወራረስ ውጤት ነው የሚል ዕይታን የሚቃረን፣ መወራረስን ‹‹መጉደፍ›› አድርጎ የሚቆጥርና ‹‹ጥራትን›› የመጠበቅ ትግልን በርቱበት የሚል አመለካከት ነው፡፡ የብሔር ‹‹ጥራት›› እና ይዞታን ጠብቆ በትልቅ አገርነት ውስጥ ከተኖረም፣ ‹‹አገርን ለራስ በሚሆን መልክ መቀየር›› የሚለው ዕሳቤ ስላዘለው መርዝ እንዳትት የሚጠበቅብኝ አይመስለኝም፡፡

ይህ አስተሳሰብ ምን ያህል አሮጌ፣ ምን ያህል ከሰው ልጅ ማኅበራዊ መስተጋብርና ከታሪክ ጉዞ ጋር የተጣላ (asocial and ahistorical) እንደሆነ ለማሳየት፣ ብሔር ብሔረሰብነትን ሥጋ ዝምድናዊ አድርጎ የሚረዳው ንድፈ ሐሳብ ከአይሪሽ ብሔርተኝነት የተጣበበ ማኅፀን ውስጥ የበቀለ ነው ወይስ አይደለም የሚል ክርክር ውስጥ ገብቶ መልፋት አያስፈልገኝም፡፡ ታሪክ የሚሰጠኝ ምስክርነት በሽበሽ ነው፡፡

 • የትውልድ ዛፎችን ታሪክ በቀፎው እንዲቀር አድርጓል፡፡ የሰው ልጆች በብዙ ምክንያቶች መፍለስ፣ መቀላቀል፣ መበተን፣ መተራመስና መዘናነቅ የሞላበት ማኅበራዊ አዝግሞት (ኢቮሉሽን) ውስጥ በመጓዛቸው ምክንያት፣
 • የሰው ዘር መገኛ ከሆነው ምሥራቅ አፍሪካ ተነስተን የሰው ልጅ ከጥንተ ጥንት ጀምሮ በየአቅጣጫው ያደረገውን እንቅስቃሴ ካስተዋልን ደግሞ፣ እግዜር በቋሚነት ረግቶ እንዲኖር ለየትኛውም ሕዝብ መሬት የሰጠበት ሁኔታ እንደሌለ ማጤን አይቸግረንም፣
 • ‹‹የብሔር/ብሔረሰብ›› ንድፍ ሐሳብን አመንጪዎቹ አውሮፓውያን ከደሴቶች እስከ አውሮፓ መሀል ምድር ድረስ ከጥንት ጀምሮ ሲገላበጡና አንዳቸው ወደ ሌላቸው ሲፈሱ፣ አንዳቸው በሌላቸው ላይ ሲዘምቱ፣ አንዳቸው ሌላቸውን ሲያስገብሩ ኖረዋል፡፡ ትልልቅ ኢምፓየሮች ፈጥረዋል፡፡ አንዱ ኢምፓየር ወድቆ ሌላ ተነስቷል፡፡ ከእስያ የበቀለ ኢምፓየር አፍሪካና አውሮፓ ሲዘልቅ እንደ ጎሳዎችና ነገዶች አበቃቀል እከሌ እከሌን ወለደ…፣ ከእከሌ ትውልድ የእከሌ ጎሳ ተገኘ የሚሉ ሁሉ ከአውሮፓም የተነሱ ኢምፓየሮች እስያና አፍሪካ አሜሪካ ድረስ ሲዘረጉ በታሪክ ታይቷል፡፡ በታሪክ ውስጥ ያየነውን የዓረቦች በአፍሪካ ጠረፋማ ምድር መስፋፋት ‹‹እግዜር ሰጣቸው›› አንበል? የአውሮፓውያንን በአሜሪካ ምድሮች፣ በአውስትራሊያና በኒውዚላንድ ግፈኛ አሠረጫጨት በእግዜር ስጦታ እንተርጉመው? አፍሪካን የተቀራመቱበትን ታሪክና ዛሬ ድረስ ያለ የርዝራዦቻቸውን ድሎት በእግዜር ምርቃት እንተርጉመው? የፍልስጥኤምና የይሁዲዎችን የዛሬ ውዝግብ በእግዜር ስጦታ እንፍታው? ከናዚዎች ጭፍጨፋ በኋላ እግዜር ይሁዲዎችን ሰፋ ባለ መሬት እየሰበሰበ ፍስጥኤሞችን ደግሞ እያጣበበ በስደት እንዲበተኑ አደረገ እንበል?
 • የሰው ልጅ (ሳይንስ ‹‹ሆሞ ሳፒያን›› የሚለው ፍጡር) በደፈናው ሥጋ ዘመዳም ነው፡፡ ከዚህ በመለስ ስለ ‹ሥጋ ዘመዳምነት› ማውራት ይበልጥ ትርጉም የሚኖረው ስለዘር (Race) ካወራን ነው፡፡ ቢጫ ሕዝቦችን በጥቅሉ ወስደን ብናስተውልና ለእኛ ከቻይናና ጃፓን አንስቶ እስከ ሞንጎሊያ ድረስ ብንቃኝ አንዳቸውን ከሌላቸው መለየት ይቸግረናል፡፡ የዘር ዝምድና እንዳላቸው ማጤንም አይከብደንም፡፡ በዚህ ጥቅል የዘር ዝምድና ውስጥ አያሌ ብሔር/ብሔረሰባዊ ቅንብሮች አሉ፡፡ አያሌ የቋንቋ ተነጋሪነት አለ፣ ከአያሌም መዓት ሊባል የሚበቃ ባዕድነት አለ፡፡ ቢጫ ሕዝቦችም ሆኑ ፈረንጆች እኛን ጥቁሮችን አስተውለው በዘር ሊለዩን ቢሞክሩ አንዳንድ ጭራፊ ልዩነት ከማየት በቀር ይቸግራቸዋል፡፡ ምክንያቱም የአንድ ዘርነት (Race) ዝምድናችን ልዩነቶችን ስለሚያኮስስ፡፡ በእኛ በጥቆሮች አንድ ዘርነት/ጅምላ ‹‹የሥጋ ዝምድና›› ውስጥም በሌሎቹ ዘንድ ያየናቸው አያሌ የብሔረሰቦችና የቋንቋዎች ቅንብራዊ ስብስቦችና መዓት ባዳነቶች አሉ፡፡ በታሪክ ውስጥ አያሌ የባዳ ለባዳ መሰባጠርና መዘናነቅ ተካሂዷል፡፡ እናም ከዚህ ተነስተን በአጠቃላይ አንድ ዘርነት (Race) ውስጥ የዘሮች (Races) መካለስን ጭምር ባካተተ አኳኋን ባዕዶች የተወጠወጡበት ማኅበራዊ ቅንብር አድርጎ ብሔር/ብሔረሰብነትን መረዳት እውነታዊ ነው፡፡ በቀላል አነጋገር በብሔር/ብሔረሰብነት ውስጥ በዘመናት የመቧካት ሒደት ውስጥ እጅግ የሳሳ የሥጋ ዘመዳምነት አሻራ እንዳለ ሁሉ፣ ዛሬም በቀጠለና ነገም በሚቀጥል መዘናነቅ የሚጎለብት መዓት ባዕድነት አለ፡፡
 • ከሶሲዮ ኢኮኖሚና የፖለቲካ ልውጠት ጋር የብሔር ሥሪትና ውልደት በተከሰተበት የአውሮፓ ምድር ውስጥ የታዩት ልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪ ሆነው የወጡ አገሮች ከሥጋ ዝምድና ይልቅ በሰይፍ፣ በማኅበራዊና በባህል ሰበዞች ውጥወጣ የተገነቡ ነበሩ፡፡ ከኢምፓየሮች መፈረካከስ የወጡት አገሮችም ባለ ነጠላ ቋንቋዎች ብቻ አልነበሩም፡፡ ብዙ ቋንቋ የሚናገሩም አንድ አገር እየሆኑ ወጥተዋል ወይም መኖር ቀጥለዋል፡፡ የብሔር ዝምድናዊ ሴመኛነትና የመኖሪያ ሥፍራ ስምምነት በዓለም ታሪክ ውስጥም ሆነ ዛሬ ባሉ አገሮች ዘንድ ተፈልጎ እዚህ ጋር ተሟልቷል የሚባል አይደለም፡፡ አውሮፓን፣ ሁለቱን አሜሪካዎች፣ እስያንና አፍሪካን ሁሉ ብናስስ ድፍርስነትና ቅይጥነት ታሪካዊ ባህርይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በኢትዮጵያና በዙሪያ ጎረቤቶቿ ውስጥ ያለውን የብሔረሰቦች ሥርጭት ማየት፣ ብሔረሰብነትና የመኖሪያ ወሰን ላይገጣጠም እንደሚችል ማስረጃም ነው፡፡
 • የሰው ልጆች በሽታዎችን እየተቋቋሙ መባዛት የቻሉት የጋብቻቸውና የመዋለዳቸው አድማስ ይበልጥ ከቅርብ ዝምድና እየራቀ (ባዕድነት እያደገ) ስለሄደ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በ‹ጡት›፣ በ‹አበልጅነት›ና በመሳሰሉት፣ ወዘተ ዝምድና የሚፈጠረው ባዕድነትን የሥጋ ዝምድና-አከል ለማድረግ ነው፡፡ የክርስትና ወላጅን ልጅ ማግባት ከነውር የሚቆጠረውም ከባዕድነት የሚገኝ ወላጅነትና ልጅነት እንደ ሥጋ ስለሚከበር ነው፡፡
 • ‹ሥጋ ዝምድና› በየብሔር ብሔረሰብነት ስላለው ይዘት እናውራ ከተባለም፣ ከቤተሰብ ተነስቶ ሰፊ ቤተሰቦችን፣ ጎሳዎችንና ነገዶችን እያሸራረበ በመጣ ጥንተ አዝግሞት ውስጥ ከምናገኘው በዘመናት የተመናመነ ሐረጋዊ የሥጋ ዝምድና ይበልጥ ‹ሥጋ ዝምድና› ዝንጉርጉር የቅይጥነት ገጽታ ሆኖ ሲደረጅ እናገኘዋለን፡፡ ሐረርጌ ውስጥ ያለ ኦሮሞ ከወለጌው ይበልጥ የሶማሌና የሐረሪ ‹ሥጋ ዘመድ› ነው፡፡ የወሊሶ አካባቢ ኦሮሞ የጉራጌ ‹ሥጋ ዘመድ› ነው፡፡ የራያነት ዝምድና አማራነትን፣ ትግሬነትንና አፋርነትን፣ እያጣቀሰ እንደ ቅቤ አቅልጧል፡፡ እንዲህ ያሉ የዝምድና መወራረሶች በሌሎች ብሔረሰቦች መፋሰስ ውስጥ ይታያሉ፡፡
 • ‹‹በሥጋ ዝምድና›› ያየነውን ዝንጉርጉርነት በባህልና በጋራ ሥነ ልቦና ረገድም እናገኘዋለን፡፡ የሐረርጌ ኦሮሞ አለባበስ የምግብ ባህል፣ ልቦናዊ አቅል በአካባቢው ካሉ ማኅበረሰቦች ጋር እንጂ መሀል አካባቢ ካለው ክርስቲያን ኦሮሞ ጋር አይመሳሰልም፡፡ በሌላ አነጋገር የከረዩ ኦሮሞን፣ የጉጂ ኦሮሞን፣ የራያ ኦሮሞን፣ የሸዋ ኦሮሞን፣ የወለጋ ኦሮሞን፣ ወዘተ አንድ ላይ አገናዝቦ የጋራ ባህልና ሥነ ልቦናቸውን ለማንጠር ከመሞከር ይልቅ እያንዳንዳቸውን ከተጎራባቾቻቸው ማኅበረሰቦች ጋር ማስተያየት ይቀላል፡፡ ወሎዬነት ውስጥ፣ ጎጃሜነትና ጎንደሬነት ውስጥ ብዙ ዝንጉርጉርነት አለ፡፡ ወሰንተኛ በሆኑትና በአያሌው የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታይነት ባላቸው ጎጃሜዎችና ጎንደሬዎች ዘንድ ጎልቶ የሚታይ የሥነ ልቦና በተለይነትም አለ፡፡ ማኅበራዊ ተራክቦና መወራረስ የሚያስከትለው ውጤት መመሳሰልን የመጨመር ብቻ ሳይሆን ዝንጉርጉርነትን የማብዛትም ጭምር ነው፡፡ በጥቅሉ በኢትዮጵያ እውነታ፣ ብሔር/ብሔረሰብ የጋራ ታሪክ፣ የጋራ ቋንቋ፣ የጋራ ባህልና የጋራ ሥነ ልቦና ያለው ማኅበረሰብ ነው የሚል ድንጋጌ እውነትነት በጣም ስስ ነው፡፡
 • ከየትኛውም የአገራችን ብሔረሰቦች የልውጠት (የውጥወጣ) አዝግሞት በተለየ ኦሮሞ ሆን ብሎ ከራሱ ውጪ የሆኑ የማኅበረብ አባላትንና ቡድኖችን በጉዲፈቻና በሞጋሳ የማላላስ (ነገዳዊ ማኅበረሰቡን የማባዛትና አሠፋፈሩን የማስፋት) ታሪክ አለው፡፡ ከዚህ አኳያ ኦሮሞን በሥጋ ዝምድና ግንዛቤ ለመለሰን መሞከርና ኦሮሞን ‹‹ከላይ በተሰጠ መሬት›› ለመገደብ መሞከር ከገዳ ታሪክና ባህል ጋር መጣላት (ኢገዳዊ/ኢኦሮሟዊ መሆን) ነው፡፡ ሸኔዎች የመንግሥት ደጋፊ ኦሮሞን ከማጥቃት ባሻገር ለኦሮሞ ባዕድ ናቸው ባሏቸው ላይ በጥይት፣ በስለትና በእሳት ሲፈጽሙት በቆዩት ግፍም ኦሮሞነትን አልጠቀሙም፡፡ ጭራሽ በኦሮሞነትና በገዳዊ ታሪኩ ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ ነው የቆዩት፡፡ የዚህ ዓይነት ድርጊትንና አስተሳሰብን መደገፍም ኦሮሞ የሚታወቅበትን ገዳዊ ታሪክና የቅልቅል እሴት መቃረን ነው፡፡ ዶሮን በጋን ቢቀቅሏት ተልቃ ጋን አትሞላም፡፡ የዚህ ዓይነት ሹልዳ አስተሳሰብ ለኦሮሞም ለኢትዮጵያም አይመጥንም፡፡ የዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ዛሬ ያለ የኢትዮጵያ ተሬ ሰው ካለው አስተሳሰብ በታች ነው፡፡ በኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች ውስጥ የተስፋፉት ክርስትናና እስልምና ሃይማኖታዊ ዝምድናቸውን በየብሔር ክልል ውስጥ አጥብበው የሚሠፍሩ አይደሉም፡፡ የሃይማኖት ዘመዳቸውን ብሔሬን ታጎድፋለህ ብለው አይገፈትሩም፡፡ ያንን ቢያደርጉ የሚገፈትሩት ሁለመናዬን ይገዛል የሚሉትን እምነታቸውን ነው፡፡ የአበበች ጎበናና የዘውዲቱ መሸሻ እናትነት የሚያስተምረን ከብሔርም፣ ከቋንቋም፣ ከሃይማኖትም ያለፈ ለሰው ልጅ መንሰፍሰፍን ነው፡፡ የ‹ሥጋ ዝምድና› መሥፈርትን ወደ ኦሮሞ ማስጠጋት የአበበች ጎበናን ዕንቁነት ለመጋረድ ከመጣር አይለይም፡፡

በተለያየ አቅጣጫ ብዙ ሰበዞችን እየመዘዝኩ የደረደርኩት በተራ ወገኖቻችን ‹ደመ ነፍሳዊ› ግንዛቤ ውስጥ ያለ አስተውሎት ፈክቶ እንዲወጣ ለማገዝ እንጂ፣ ማኅበራዊ ሳይንስን የተማረ ሰው በስንት ምስቅልቅል ውስጥ የሰው ልጅ እየተቦካና እየተጋገረ እዚህ ዘመን ላይ እንደደረሰ ይጠፋዋል ብዬ ትምህርት ለመስጠት አይደለም፡፡ የሰው ልጅን የማኅበራዊ አዝግሞት ታሪክን ረግጦ፣ በዛሬው ጊዜ ‹‹ስለብሔር ሥጋ ዝምድና››፣ ‹‹ስለሴመኛነት›› እና ‹‹የብሔር ይዞታን ከሴመኛነት ጋር ስለማስማማት›› ማውራት ዓላማው ሥውር አይደለም፡፡ እነዚህን ያካተተ ቀመር የሕዝብ ህሊና ላይ አለሳልሼ እየቸከቸክሁ በ‹ዘር› የሚያስብ ብሔር ላንፅ ነው ነገሩ፡፡ ይህን ዓይነቱን ነገር ሌሎችም ከዚህ ቀደም ሞክረውታል፡፡

ብሔር ይታነፃል እውነት ነው፡፡ የሚታነፀው ግን በዘፈቀደ ወይም ላንፅ ብለው በተነሱ ሰዎች የቢሻኝ ፍላጎት አይደለም፡፡ አንድ ብሔርተኛ የሐሳብ መሐንዲስ፣ ‹‹ብሔር ላንፅ›› የሚል ዕቅድ ይዞ ሰዎችን አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ማድረግ እንደማይችል ሁሉ ‹‹የጋራ ታሪክ››፣ ‹‹የጋራ ባህል›› እና ሥነ ልቦና አመጣጥም በግለሰቦች ቀያሽነትና አናፂነት የሚከናወን አይደለም፡፡ የተፈጥሮ አደጋ፣ ጦርነት፣ ፍልሰት፣ ምርኮ መውደቅ፣ መጋዝ፣ መገበርና ማስገበር፣ መዘናነቅ የመሳሰሉ መራራና ለስላሳ ሰበዞች ሁሉ በሚስተናበሩበት አዝግሞት ውስጥ ነው የብሔር/ብሔረሰብ የጋራ ገጽታዎች የታነፁት፡፡ ከሰዎች ውጪ ያሉ ነባራዊ እውነታዎችና ሰዎች የሚያካሂዷቸው የሐሳብና የስሜት እንቅስቃሴዎች ሁሉ አንድ ላይ እየተመጋገቡ የጋራ ወደ ሆኑ እሴቶች፣ ወደ ጋራ ፍላጎቶችና የህልውና ዕጣዎች ይወስዷቸዋል፡፡ የጋራ ፍላጎቶችንና የህልውና ዕጣዎችን አዝማሚያ ከእውነታ ማንበብ የቻሉም የመሪነት ሚናን ይጫወታሉ፡፡

ቀላል ማገናዘቢያ ከዛሬያችን እንበደር፡፡ ከቅርብ ጊዜ በፊት የኮንትሮባንድ ንግድን የመታገል ጉዳይን አስታክኮ አንድ የኢትዮጵያ ልጅ (ሶማሌ)፣ ‹‹አገሬ አንድ ሳንቲም ሳልከፍል አስተምራኛለች፣ ባለ ዕዳ ነኝ›› ሲል የተሰማው የዚህ ዓይነት ነገርን የሆነ ግለሰብ ከትቦት አይደለም፡፡ አገሩ ካቋደሰችው ትምህርት ነክ የልጅነት ዕትብት የቀሰመው ነው፡፡ ብርሃኑ ነጋ የሚመራው ትምህርት ሚኒስቴር፣ የትምህርት ክንዋኔያችን ለተማሪዎች በሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያም ሆነ በኮሌጅ መልቀቂያ ላይ ተፈላጊውን ዕውቀት ስለማስጨበጡ መመዘን አለበት የሚል ውሳኔው ሰምሮለታል፡፡ ስምረቱ ግን በብርሃኑ ነጋና በባልደረቦቹ ቁርጠኝነት ላይ የተንጠለጠለ አልነበረም፡፡ የግለሰቡና የባልደረቦቹ ቁርጠኝነት ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከካቢኔው፣ ከፓርቲው፣ ከዩንቨርሲቲዎችና ከወላጆች ሁሉ ፍላጎት ጋር ስለተገጣጠመ ነው፡፡ ለእነዚህ ሁሉ ወገኖች ፍላጎት መገጣጠም መሠረት የሆነውም፣ የኢትዮጵያ ትምህርትን ከውድቀት ማንሳት ያፈጠጠ የጋራ ጉዳይ ሆኖ ፊታችን መገሸሩ ነበር፡፡ ዛሬ ኦሮሞ የገዳ ቅርስን ለ21ኛው ክፍለ ዘመን እንዲስማማ አድርጎ እየተጠቀመት ያለውና ኢትዮጵያም ለሁላችን የምትደላ ወደ መሆን የምትጓዘው፣ የአዲስ ትውልዷም ሰብዕና ብዙ ባህል ተቋዳሽነትንና ብዙ ቋንቋ ተናጋሪነትን ኅብራዊ ገጽታው ወደ ማድረግ እያመራ ያለው ዓብይ አህመድ ስለፈለገ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ይህንን ጎዳና የጠንካራ ሰላምና የጠንካራ አገርነት ካስማቸው አድርገው ስለቆጠሩት ነው፡፡ ካስማቸው አድርገው የቆጠሩትም ስለአማራቸው ሳይሆን፣ የህልውናቸው ዋስትና መሆኑ ስለታወቃቸው ነው፡፡ ክፍለ አኅጉራዊ ህልውናችንም ከኢትዮጵያ አልፈን በቀጣናችን ግቢ ውስጥ እንድንመለከት ይጣራል፡፡ አፍሪካ አኅጉራችንም በቀጣና እንዳንታጠርና አንድ አፍሪካን እንድናሰላስል ይጣራል፡፡ የዛሬው ዓለማችንም ከአኅጉር ተሻግረን ምድሪቱንና የሰው ልጅን ከጥፋት በማዳን ላይ እንድናተኩር ይጣራል፡፡

ይህ ሁሉ ጥሪ ባለበት የዛሬ እውነታ ውስጥ ስለብሔር ሥጋ ዝምድናና ሴመኝነት ከማውራትም አልፎ፣ አገርን ለጠባብ ዓላማ ስለማመቻቸት ማሰብ ምን ያህል ከ21ኛው ክፍለ ዘመን ተግባሮች ተሸቀንጥሮ ዘመነ ጥንት ውስጥ መውደቅ እንደሆነና ምን ያህል የውስጥ ሰላም ጠንቀኝነትን አቀባብሎ እንደያዘ ልብ በሉት! እናም አዘናግቶ እንዳያበልዘን ነቅቶ መታገል አስፈላጊ ነው፡፡ አለበለዚያ ‹‹ጥባ ያሉት ጥጃ ሰርሮ ይመለሳል›› ግን፣ ለዚህ ጠንቃቃ ትግል ምን ያህል የተሰናዳ አቅም አለን? የተቸነው አስተሳሰብ በኦሮሚያ አስተዳደር ልሂቃን ግድም የማበለዝ ሥራውን አልጀመረ ይሆን? እንደ እኔ ያለ ሰው ከርቀት ብዙ የስሚ ስሚ ነገሮች ጆሮው ላይ ሊንጫጩበት ይችላሉ፡፡ ቢንጫጩም ግን እነሱን ይዤ ለመቀባጠር አልደፍርም፡፡ በሚኒስትር ደኤታ ደረጃ የፌዴራል የሥልጣን ወንበር ላይ የተቀመጠው የታዬ ደንደአ ገመና ፈንጣቂ ትችት ግን በስሚ ስሚ ተቃሎ የሚጣል አይደለም፡፡ በሁሉም ሠፈሮች ውስጥ በኢትዮጵያዊነት፣ በቀጣናዊነትና በአፍሪካዊነት ማዕቀፍ የሰፋ አተያይና ተላሚነት እንዲጎለብት፣ የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታችን ዳግም የሕወሓት አመጣሽ ዓይነት ውልቃት እንዳይጎበኘው በአንድ ላይ ብልህ ትግል እናድርግ፡፡ ሙሰኞች አንዱ የሚፈሩትና የትኛውንም ቀጥተኛና ኢቀጥተኛ የውንጀላ ሾኬ ለመጥለፍ የሚያደቡት በዓብይ አህመድ ዙሪያ ያለው ሙስናንና ዘረፋን እንቢ ያለ አስኳል እንዳይስፋፋባቸው ነው፡፡ ይህ መለስተኛው ዒላማቸው ነው፡፡ የትኞቹም ብሔርተኛ ገንታሮች ሁሉንም ሲዖል ከዓብይ አህመድ ጋር አያይዘው ዓብይን ለመቁረጥ ያነጣጠሩት፣ እሱንና መሰሎቹን በመቁረጥ ኢትዮጵያ እንደ አገር የመቀጠል ማዕከል አጥታ እንድትዝረከረክ ለማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ የኅብረት ትግሉን እንወቅበት፡፡ ጊዜ የሚሰጡና የማይሰጡ ብዙ ጉዳዮችን አደራርበን አቅም ከማባከን ተጠንቅቀን፣ በየአቅጣጫው ትግላችንን ከውጤት ወደ ውጤት እናራምድ፡፡

ሐ) ከዚህ በኋላ ተስፋ የምናደርግበት የአዲስ ሕይወት መንቦግቦጊያ ዘመን ከወዲሁ ጀምሮ፣ የሰብዕና ልማትን በተመለከተ ፈርጀ-ብዙ በሆነ መልክ መዝመት ያለበት ብሔር/ብሔረሰብነትን በሥጋ ዝምድና መስሎ ከማኅበራዊ ልውጠት ውጪ ለማቆየት (ለመከተር) በሚደረግ ጥረት ላይ ብቻ አይደለም፡፡ ትግላችን ቀደም ባለ ጽሑፍ በተወሳለት በሽብር ሥልት መግደል በጀማመረ ጨለምተኝነት ላይ ጭምር የሚካሄድ ነው፡፡ እነዚህን ሁለት ረድፎች ቅርፍርፋቸውን እያወጡ ከሰዎች ላይ በማራገፍ ረገድ፣ ምሁራን በተለይ የማኅበራዊ ሥነ ሰብዕ ባለሙያዎችና የታሪክ ባለሙያዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የለውጥ ፖለቲከኞችና መንግሥት የተመጋገበ ትግል ማድረግ ይፈለግባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች በብዙ ማኅበራዊ ክሮች የተሳሰርን፣ በረዥም ታሪክ ውስጥ የተወራራስን መሆናችንን የሚያሳይ የጋራ ታሪካችን ይውጣ፡፡ ይጻፍ! ይታተም! በመድረክ ውይይትና በኮንፍራሶች ይተርተር! በሚዲያዎች ይስተጋባ!!

2/ በኢትዮጵያ ውስጥ ‹ከተሜው› ገጠሬውን፣ ቀለም የቀማመሰው ቀለም ያልቀማመሰውን ‹‹ያልሠለጠነ/ኋላቀር›› እያለ ሊንቅ አይችልም፡፡ ከ‹ተማረ› እስካልተማረና ከ‹ከተሜ› እስከ ገጠሬ ድረስ የተከተሩና ሥልጣኔ ያልዳሰሳቸው የኑሮ ዘይቤዎች እንደ ልብ ናቸው፡፡ በአስተሳሰብ፣ በግል ንፅህና፣ በመሠረታዊ የጤና ግንዛቤ፣ በአለባበስ፣ በመንገድ አጠቃቀም፣ በቆሻሻ አወጋገድ፣ በኃይል አጠቃቀም፣ በምግብ ባህል፣ በምግብ አበሳሰል፣ በምግብ አጠባበቅና በአመጋገብ፣ ወዘተ እነዚህ ሁሉ ተለይተው አኗኗርን በሚያሻሽል ልማት ይነቃነቁ፡፡ ‹‹በልማት ይነቃነቁ›› ብሎ ለማለት ዳገት የለውም፡፡ በተግባር ግን ያለው ዳገት የዋዛ አይደለም፡፡

ዕድሜያችን 70 ዓመት አካባቢ የሆንን ሰዎች በጉስቁልና የተሞላ ኑሮን ነፍስ ባወቀ ደረጃ ከተያያዝነው 50 ዓመት ግድም ሆነን፡፡ የደርግንና የኢሕአዴግን ዘመን ደፍነን አሁን ድረስ ያለንበትን ጊዜ ማለት ነው፡፡ ሃምሳ ዓመት በካድሬ ድንፋታ፣ በአዛዥ ናዛዥነት፣ በግልምጫና በማስፈራሪያ መሽቆጥቆጥ፣ በስብሰባና በመገናኛ ብዙኃን ንዝነዛና በመፈክር መቀጥቀጥ፣ ዝም ቢሉም እውነት ቢናገሩም ለለውጥ ዝግጁ ባለመሆን/በአሮጌ ሥርዓት ናፋቂነት፣ በፀረ ልማትነት፣ ወዘተ መፈረጅ ይህንን ሁሉ ኖርንበት፡፡ ከ1966 ዓ.ም. አብዮት አንስቶ ከጊዜ ወደ ጊዜ እውነተኛ ገቢን እያኮሰሰ የሚያድግ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት፣ ቀለብን ለማሟላት በየገጠር ገበያ እስከ መንጦልጦልንና ሠልፍ በታየበት እስከ መገተር አድርሶናል፡፡ የዛሬው የኑሮ ውድነት ደግሞ የበፊቱን አመናታይ ውድነት ገር የሚያሰኝ ሆኗል፡፡ በዛሬው ኑሮ አስገዳጅነት ለዓመት በዓል ከማረድ ወደ ልኳንዳ ከመሄድ፣ ሆቴል ገብቶ አለፍ ገደም ልቀናጣ ከማለት፣ ፍራፍሬ ከመግዛት ውጪ የሆንንና ለብዙ ነገር መድኃኒት አድርገን የምንጠቀምበትን ነጭ ሽንኩርት ኪሳቸው ለሞላ የተውን ጥቂት አይደለንም፡፡ መንግሥትም በቢሮክራሲ ውስጥ የሚያባክነውን ወጪ ትርጉም ባለው ደረጃ እንኳ ሳይቀንስ፣ የንብረት ግብርን ተግባራዊ ለማድረግ በመጣደፉ ምን ያህል እንደሚያስብልን ነግሮናል፡፡

ከጉርስ ቀጥተኛ ጉዳይ ውጪ በሕወሓት/ኢሕአዴግ ዘመን የነበረ ሸረኛና ቂመኛ አገዛዝ ለአገዛዙ አላጎነብስ ባልን ዜጎች ላይ ያደረሰው ጉስቁልና አይወራ፡፡ በተንኮል/አድሎ ጥቃትና ስምን በሚበክል ወሬ ተንጨርጭሮ ጨርቅ የጣለውን፣ ምርር ብሎ ራሱን ያጠፋውንና ከአገር የጠፋውን፣ በእስር ቤት አሳር የጠበሰውን ቤቱ ይቁጠረው፡፡ የእኔ ዓይነት ተንገሽጋሾች የጡረታ ጊዜያቸው ሳይደርስ አመልክቶ መውጣትማ ስንቱ የቀናበት ነው፡፡ እንደዚያም አድርገን ግን ተንኮል አልማረንም፣ መኖሪያ ቀዬአችን ድረስ ተከትሎ መጥቶ ነበር፡፡ ሱሪ በአንገት ባለ የውስጥ ለውስጥ መንገድን በጡብ ድንጋይ የማልበስ ‹‹ልማት›› በመዋጮ ድርሻና ጉድጓድ አስቆፍሮ ቱቦ እየገዙ ማስቀበር በጠየቀው የነጠቃ ዋጋ፣ በጡረታዬ ለክፉ ችግር ብትሆን ብዬ የቋጠርኳትን ለአመል ሺሕ ብር ላስ አደረገልኝ፡፡ ልማቱን ሽፋን ያደረገ ኢሕአዴጋዊ ተንኮል የአጥሬን የድንጋይ መሠረት አቃፊ መሬት በቡልዶዘር ግጦና የማይዘልቅ የውኃ መውረጃ ቦይ ፈጥሮ እንዲገረሰስ ለማድረግ ሞከረ፡፡ ሁሉን ረድፍ የሚመለከተው የመሐንዲስ ልኬት ሲመጣ ወደ እኔ አጥር ታጥፎ ሊለጠፍ አይችልምና ተንኮሉ ውሎ አድሮ ከሸፈ፡፡

ኢሕአዴግ ሄዶ የዛሬው መንግሥት ስለመጣ ወገብ ሰባሪና አዕምሮ አስጨናቂ ኑራችን ለወጥ ባለ ወዘና በረታ እንጂ አልቀለለም፡፡ የአሁኑን ብዙዎች ብንደግፍ፣ የለውጥ ተስፋን ሙጥኝ ብለንና የአገራዊ ህልውናችን ጉዳይ ከምንም ነገር በላይ በልጦብን እንጂ መመረር ርቆን አይደለም፡፡ ዙሪያ መንደሮች መብራት እያገኙ ባሉበት ሁኔታ አሥር የማይሞሉ ቤቶች ተለይተው አለፍ ገደም ለቀናት ኃይል የሚያጡበትን ኑሮ አቤት እያልንና እስኪጠገን እህህ እያልን መኖርን ከኢሕአዴግ ጊዜ ጀምሮ ለምደነዋል፡፡ ውኃ ለተወሰኑ ቀናት ጠፍቶ ለተወሰኑ ቀናት የምናገኝበትን አሠራርማ እንዳመሉ አኗኗራችንን አርቀን በአክብሮት ያለ ቅሬታ ነው የያዝነው፡፡ በየወሩ መቶ ብር ከምናምን ለጥበቃ ብናዋጣም ለአትክልት የዘረጋነው ብረት አጥር አንድ፣ አንድ በሚል ዘዴ ተሰርቆ ከማለቅ አልዳነም፡፡ አጥር ሥር የሚጣለው ቆሻሻ ከንጋቱ አሥራ አንድ ሰዓት አንስቶ እስከ ምሽት ድረስ ተገትራችሁ ካልጠበቃችሁ አንተዋችሁም እስከ ማለት የደረሰ መስሏል፡፡ ከቤት ስንወጣና ወደ ቤት ስንገባ አዲስ ቆሻሻ ዓይተን አዲስ ንዴት እንዳያበግነን ዓይናችንን ከአጥራችን እስከ መደበቅ ደርሰናል፡፡

የዛሬ ትኩስ ኃይል ሹሞች የሚሰማ ጆሮ ካላችሁ ስሙኝ! ኑሮ ቢከብድብንም አሁን የተያዘው አርዓያነት ያለው የበጎ አድራጎት ሥራ ብዙዎቻችንን ነዝሮን ከእኛም የባሰበት አለ በማለት እንደ አቅሚቲ ለማቋደስ እንሞካክራለን፡፡ ከዚያ በተረፈ ካድሬዎቻችሁ የኑሯችን አከባበድ የሚገባቸው ከሆነ ተጨማሪ ወጪ በሚያስወጣ ሥራ አያትረክርኩን፡፡ ለግማሽ ምዕት ዓመታት ያሳለፍነው በድንፋታ፣ በግልምጫና በዛቻ፣ በሸርና ሾኬ፣ በፕሮፓጋንዳና በመፈክር ቅጥቀጣ የተሞላ ኑሮ ምን ያህል መንፈሳችንን እንዳደቀቀ ለመረዳት ይሞክሩ፡፡ ቅጥቀጣው ትህትናችንንና ትዕግሥታችንን አቆርፍዶታል፡፡ ቀናነታችንን አወለጋግዶታል፡፡ ተደማምጦ ሐሳብ የመለዋወጥ ችሎታና ፍላጎታችንን አደንቁሮታል፡፡ ሁሉን ነገር ለየብቻ አሸምቆ በመሮጥና በሾላካነት ማሳደድ የኑሮ ዘዴ ሆኗል፡፡ ደግ ነገር ከመንግሥት በኩል በካድሬ ስብከት፣ በትዕዛዝ  ቢመጣ አጥቁሮ የማየትና የመፀናወት አዚም ልቦናችን ውስጥ ድሩን ሠርቷል፡፡ ምንም ቢሉን ቢወዘውዙንና ቢተነኩሱን የሚባለውን ሁሉ እንዳልተባለ ከጆሯችን እያራገፍን በድን ኑሮ የምንኖር ሞልተናል፡፡ ሌላ አመል ያወጣንም ብዙ ነን፡፡ የካድሬ ስብሰባ ውስጥ መገኘት፣ የካድሬ ደደብ ስብከት፣ ከአፍ ነጥቆ ፍረጃና ቀጭን ትዕዛዝ እክክ ክፍክፍ ያለን፣ ለማገናዘብ ጊዜ የማይሰጥ ቱግታን በአፍ በአፍጫችን የሚያመጣብን፣ ለዓመታት የተጠራቀመ ብሶት ገላ ቆዳችንን ቀድጄ ልውጣ እስከማለት የሚገተግተን ሞልተናል፡፡

የዛሬ ትኩስ ኃይሎች በእኛ ዓይነቶቹ የዘመን ወልጋዶች ላይ የሰብዕና ለውጥ ለማምጣት ከፈለጋችሁ፣ ከላይ ወደ ታች ባለመቀጮና ባለማስፈራሪያ ትዕዛዝ ከማውረድ፣ በፕሮፓጋንዳ ከመነዝነዝ፣ በአንድ ቁጭታ ስብከት ሰውን እለውጣለሁ ከሚል እኝኝና ከአፍ ጠለፋ አሮጌ ሥልት ውጡ፡፡ ትዕዛዝና ማስጠንቀቂያ የያዘች ወረቀት ወጣቶች እያስያዛችሁ በር ከመደለቅ ውጡ፡፡ የዕድሜ ባለፀግነትና ልጅ እግርነትን ለይተው አንተ፣ አንቺና አንቱ ማለትን የማያውቁ ወጣቶች እየላካችሁ ‹‹የአጥራችሁን ሥር አፅዱ… ነገ መጥተን እናጣራለን… ካልፀዳ…›› የሚል ፋታ የለሽ ትዕዛዝና የቅጣት ማስፈራሪያ ከመለፈፍ ውጡ፡፡ የበላዮቻቸው ሠርታችሁ የምታሠሩት ምን እንደሆነ በደንብ የምታውቁ ከሆነ፣ በቅድሚያ አገልጋይነት ምን ዓይነት በትሁትነት የተሞላ (ተገልጋይ ቱግ ቢል እንኳ የማይናወጥ) ወዘና እንዳለው ለወጣቶቻችሁ አስተምሯቸው፡፡ አለመናወጥን አለማምዷቸው፡፡ የነዋሪን ቅንነትና ፍላጎት የሚያሸንፍ ቀረቤታ (ራፖርት) እንዴት እንደሚገኝና ስለአመራር ጥበብ ስንቅ ብጤ ስጧቸው፡፡ ሰዎችን መለወጥ ማለት የሰዎችን ቅንነትና የውዴታ ግት እንዲሞላ የሚያደርግ ንካት ስሜታቸው ላይ መፍጠር፣ የምንለውን በጎ ነገር ወደው እንዲቀበሉና አስታዋሽ ሳይፈልጉ በውዴታ አልቀው እንዲያደርጉ የሚያበቃ ሥራ መሥራት ማለት ነው፡፡ እዚህ ደረጃ ውስጥ ለመግባት በቅድሚያ ሰዎችን ከእነ ችግራቸው ለመረዳትና የእነሱን የተከፈተ ልብ ይዞ መፍትሔን ለመመካከር መቻል አስፈላጊ ነው፡፡ የሰዎችን የውዴታ ዕትብት (ኮርድ) ይዞ ብዙ የለውጥ ሥራ የሚሠራው በዚህ አካሄድ ነው፡፡ ሜዳው ሙሉ በነውር ሠሪዎችና በሕግ ጣሾች ተሞልቶ ነዋሪዎችን ‹‹አፅዱ፣ ጠግኑ/አሠሩ›› እያሉ ማሰቃየት ከታጥቦ ጭቃነትና ከመቋሰል አያርቅም፡፡ ሰዎች ሳይወዱ ፈርተውና እየተርኮመኮሙ ያደረጉትን ነገር መልሰው በፋይዳ ቢስ እልህ ሊያጠፉት ይችላሉ፡፡ ከዚህ በታች ቢሠሩ ብዬ የጠቆምኳቸው ተግባራት ሁሉ የሚሳኩት የዜጎችን ፍላጎትና ጉጉት ለመጨበጥና ከእኛ ጋር ለማቆየት እስከቻልን ድረስ ነው፡፡

 • አሮጌና ጎጂ አስተሳሰቦችንና ዘልማዶችን ሊቀይር የሚችልና የተሻሻለ አኗኗር አብሪ ሊሆን የሚችል የጎልማሶች ትምህርት በአግባቡ ተቀሽሮ ከገጠር እስከ ከተማ ይዘርጋ፣
 • የልማቱና የጎልማሳ ትምህርቱ ውጤታማነት ወጣቶች ላይ በሚታይ ለውጥ፣ ወጣቶችን ማኮብኮቢያው አድርጎ፣ ወጣቶች በቤተሰብና በአካባቢያቸው ላይ በሚያካሂዱት ለውጥ የማለማመድና የማፅናት ሚና ይታገዝ፣
 • ‹‹ልማታችን ሰው ተኮር ነው›› የሚለውን መርሀችንን ሕገወጥነትን ለማሸነፍ ከምናደርገው ትግል ጋር ማቻቻል አለብን፡፡ ከሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ቤት ውጤት አንስቶ የሐሰት ማስረጃዎችን እየፈለፈልን አባይ ‹ባለሙያዎችን› ከሥራ እናባር ብንል መፍትሔያችን ቀውሰኛና የሥርዓት መብከት ያነቀዛቸውን ሰዎች በድፍኑ መቅጣት ይሆናል፡፡ ለዓመታት ተወዝፎ የኖረን እንዲያውም ከሕገወጥነት ወደ ሕጋዊ ባለ ሰነድነት የተሸጋገረ የቤቶች ግንባታን ታሪክ እየፈለፈልን በማፍረስና ዘወር በሉ በማለት ችግሩን እንወጣው ብንል፣ ‹‹ሰው ተኮርነታችን›› ውስጡን ለቄስ ይሆናል፡፡ ለውዝፍ ችግሮች የማያዳግም መፍትሔ ሰጥተን፣ አዲስ ውዝፍ የማይፈጠርበት ሥርዓት በሁሉም ፈርጅ እናብጅ (በብርሃኑ ነጋ የሚመራው ትምህርት ሚኒስቴር የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናን በየዩኒቨርቲዎች ውስጥ ያለ ኩረጃ ለማካሄድ በተሰናዳበት ሰዓት፣ የተወሰኑ ተማሪዎች በሆይ ሆይታ እንቢ ያሉበትና ልመናም ማስጠንቀቂያም አንሰማም ያሉበት ጊዜ ነበር፡፡ ፈተናው ተሰጥቶ እንቢኝ ባዮቹ የቅጣት ውሳኔ ሲተላለፍባቸው ርካሽ ተወዳጅነት ሊሸምት የፈለገ ፓርቲ ውሳኔው እንደገና ይታይ ማለቱ እንኳ ከቅጣት አላዳናቸውም፡፡ የ‹አዛኙ› ፓርቲ መግለጫም የቅዋሜ ሞቅ ሞቅ አላቀጣጠለም፡፡ ከዚህ መፍትሔ አሰጣጥ መማር የሚቻል ይመስለኛል)፡፡
 • የንግድ ፈቃድ አሰጣጣችን ሊጎራበቱ የማይችሉ ሥራዎችን ከማጎራበት ዝብርቅርቆሽ ይውጣ፡፡ የደንብ ማስከበር ሥራ ከአባራሪ ተባራሪ አዙሪት ወጥቶ ሥርዓት ይያዝና ሥርዓትን ዘርግቶ በማይልመጠመጥ አኳኋን ያስቀጥል፣
 • በሰው ክምችት መጨናነቅና በድህነት መባባስ ምክንያት የውስጥ ስደትን በማፍለቅ የሚታወቁ አካባቢዎች በደንብ በተጠናና ከሌሎች ጋር በተሳሰረ የልማት መርሐ ግብር ውስጥ እንዲገቡ፣ ልማትና ሥራ ከፈታ ለጉርስ ከቦታ ወደ ቦታ መሰደድን እየቀደመ ሥራ ሠሪን የሚጠራበት ሁኔታ ውስጥ ለመግባት ጥርስ ነክሰን እንገስግስ፡፡ በዚህ ጉዞ ውስጥ የተፈጥሮ ፀጋን ከመጋጥ/ከማደን ወጥቶ፣ የተፈጥሮ ፀጋን ተንከባክቦ እያራቡ/እያበለፀጉ ወደ መጠቀም መሸጋገር ትልቅ አጋዥነት አለው፡፡

ከአረንጓዴ ኢኮኖሚ እመርታ ጋር የተመጋገቡ የዚህ ዓይነት እንቅስቃሴዎች ተጋግዘው ወደ እምንፈልገው ውጤት ያደርሱናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የአዲስ ሕይወት ዘመን ውስጥ መግባት ማለት ይኼው ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...