Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ሕገ መንግሥቱም ቢሆን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በንፁህና በጤናማ አካባቢ የመኖር መብት እንዳለው ይደነግጋል›› ገሰሰ ደሴ (ዶ/ር)፣ የአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ ባለሙያ

ገሰሰ ደሴ (ዶ/ር) ከወንዶ ገነት ደን ትምህርት ቤት ከተመረቁ በኋላ በኔዘርላንድስና በስዊድን ተጨማሪ የከፍተኛ ትምህርቶችን ተከታትለዋል፡፡ በሥራ በኩል በደብረ ብርሃን ማገዶ ተክል ተቋም የሠሩ ሲሆን፣ በዩኒቨርሲቲ መምህርነትም አገልግለዋል፡፡ ከአገር ውጪም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዩኒቨርሲቲ (ዩኤንዩ) ውስጥ ሆነው በጋና ሲያስተምሩ ቆይተዋል፡፡ ከዚያ ተመልሰው በአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የአየር ንብረት ጉዳይ አማካሪ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ ወደ ኤስኤንቪ ተቋም አማካሪነት በሒደት ገብተዋል፡፡ አሁን ደግሞ በዚሁ ተቋም ከብክለት የፀዳ አበሳሰል ሥርዓት ሥራ ክፍልን በማኔጂንግ ዳይሬክተርነት እየመሩ ይገኛሉ፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባው ሲሟገቱ የኖሩት ገሰሰ (ዶ/ር)፣ ከምንም በላይ የምግብ ማብሰል ሥራን ማዘመን ለዚህ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባም ይመክራሉ፡፡ ዮናስ አማረ የምግብ ማብሰል ጉዳይ ትልቅ የፖሊሲ ጉዳይ ሊሆን ይገባል ሲሉ ሰፊ ማብራሪያ ካቀረቡት ገሰሰ ደሴ (ዶ/ር)  ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- የሚበላ ነገር በሚፈለገው መጠን ማግኘት ችግር በሆነበት አገር ስለምግብ አበሳሰል ማውራት ቅንጦት አይሆንም? አበሳሰሉ የሚመጣው የሚበላውን ነገር ከማግኘት በኋላ ነውና ምግቡ እስከተገኘ በተገኘው ነገር ቢበስል ችግር የለውም ማለት አይቻልም ስለዚህ ምን ይላሉ?

ገሰሰ (ዶ/ር)፡- ጉዳዩ ቅንጦት አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ሳይመገብ አይኖርም፡፡ ሲመገብ ደግሞ በአብዛኛው ያበስላል፡፡ ማብሰል ከዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር የተቆራኘ ጉዳይ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች 63 በመቶ ሕዝብ በሦስት ጉልቻ በእንጨትና በኩበት ነው የሚያበስለው፡፡ ወደ 90 በመቶ ሕዝብ ከእንጨትና ከከሰል ኢነርጂ ማብሰያ ገና አልተላቀቀም፡፡ የተሻለ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ባለባቸው የኢነርጂ አማራጭ በሰፋባቸው እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች፣ ሕዝቡ ከእንጨትና ከሰል ገና ነፃ አልወጣም፡፡ ለምሳሌ በዓመት ወደ አዲስ አበባ የሚገባው ከሰል ከ537 ሺሕ ቶን በላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የማብሰያ ጉዳይን ቅንጦት ላለማለት የምትገደድባቸው ሌሎችም በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ በየዓመቱ በማብሰያ ጭስ የተነሳ እስከ 2,000 ሰዎች በኢትዮጵያ ይሞታሉ፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ትራኮማ ባሉ ሕመሞች ከዓለም ቀዳሚ ናት፡፡ በኢትዮጵያ ያለ ዕድሜ መሞትን ከሚያስከትሉ ችግሮች ቀዳሚው የቤት ውስጥ ጭስ አንዱ ነው፡፡ እንጨት ለቀማው፣ ማብሰያ ፍለጋው፣ ከሰል መግዛቱ፣ በጭስ መጨናበሱና ከማብሰያ አጠቃቀም ጋር የሚመጣ ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የጤና ቀውስ ኢትዮጵያውያን ይሸከማሉ፡፡ በኢትዮጵያ እንደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ላሉ ፕሮጀክቶች መላው ኅብረተሰብ ትኩረት የሰጠውና ከፍተኛ ድጋፍም እያደረገ ያለው፣ ፕሮጀክቱ ብዙ ቤተሰቦችን ከጭስ የሚገላግል የኃይል ምንጭ ይሆናል ብሎ ተስፋ በማድረጉ ነው፡፡ የማብሰያ ጉዳይ ከእያንዳንዱ ቤት ተነስቶ እስከ ግዙፍ ሜጋ ፕሮጀክት የሚደርስ ቁርኝት ያለው ጉዳይ እንጂ፣ ከምግብ በኋላ ለወሬ ይቅረብ የሚባል የቅንጦት አጀንዳ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ንፁህ አበሳሰል ወይም ከብክለት የፀዳ አበሳሰል ይባላል ጽንሰ ሐሳቡ በዋናነት፡፡ ምን ማለት ነው?      

ገሰሰ (ዶ/ር)፡– አምስት መለኪያዎች አሉት፡፡ ንፁህ አበሳሰል ሲባል መታጠቡ፣ መፅዳቱና የመሳሰሉ ነገሮች ቀድመው ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ንፁህ የአበሳሰል ሥርዓት ግን ከአበሳሰል ሒደቱ ጋር በቀጥታ የተገናኘ ነው፡፡ ምን ዓይነት የማብሰያ ቴክኖሎጂ ወይም ምን ዓይነት የኃይል አማራጭ ይጠቀማል የሚለው ነው በእኛ የሚታየው፡፡ ያለ ጭስ ወይም ያለ አየር ብክለት ነው ወይ የሚበስለው? አበሳሰሉ ኃይል ቆጣቢ ነው ወይ? አበሳሰሉ ምቹና ደህንነቱ የተጠበቀ ነው ወይ? እንዲሁም ተደራሽነት ያለው ዘመናዊ የማብሰያ ቴክኖሎጂ አለ ወይ? የሚሉ ነገሮች ናቸው የሚታዩት፡፡ ተደራሽነት፣ ደኅንነትና ጤናማነት ያለው የአበሳሰል ሒደት መኖር አለመኖሩ ነው የሚለካው፡፡ አስተማማኝ ጭስ የሌለው የኃይል አቅርቦት መኖሩ፣ እንዲሁም ተስማሚ ቴክኖሎጂ መኖሩም ይፈተሻል፡፡ አሁን ባለው ባለሦስት ጉልቻ የአበሳሰል ሥርዓት እሳቱ በየአቅጣጫው እየተበተነ ብዙ ኃይል ይባክናል፡፡ የምንጠቀመውን እንጨት፣ ኩበትም ሆነ ከሰል የመሳሰሉ የኃይል አቅርቦትንና ፍጆታንም ይጨምራል፡፡ በዚህ ዘዴ ማብሰል ጭሱም በየቦታው ስለሚሠራጭ ከባድ የጤናና የአካባቢ ጉዳት ያስከትላል፡፡

አንድ ቤተሰብ ማገዶም ሆነ ኃይል የሚቆጥብ ማብሰያ ባለማግኘቱ ብዙ መስዋዕትነት ሊከፍል ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ በማኅበራዊ፣ ከኢኮኖሚያዊና በጤና ሊገለጽ የሚችል ጉዳት ነው፡፡ ለምሳሌ በአሥር ብር ከሰል ወይ ማገዶ የዕለት ምግቡን ማብሰል የሚችል ቤተሰብ ዘመናዊ የአበሳሰል ሥርዓት አገልግሎት ስለሌለው፣ የከሰል ወይ የኃይል አቅርቦት ወጪው በእጅጉ ይጨምራል፡፡ ከማብሰያ ወጪ በተጨማሪ እንጨት ለቀማና የኃይል ፍላጎትን ለማሟላት ብዙ የጊዜና የጉልበት ድካምም ይጠይቃል፡፡ ይህን ከባድ ኃላፊነት የሚሸከሙት ደግሞ ቤተሰብን ለማቆም ወሳኝ መሠረት የሆኑት ሴቶችና እናቶች ናቸው፡፡ ለጭስ የተጋለጠ አበሳሰል አንደኛ በቀጥታ ለካርቦን ሞኖክሳይድ ጭስ ያጋልጣል፡፡ ሌላው ደግሞ ከጭሱ ጋር ተቀላቅለው ወደ መተንፈሻ አካላችን ብዙ ዓይነት ብናኞች እንዲገቡ ያደርጋል፡፡ ይህ ለጭስ የመጋለጥ ሁኔታ የሚፈጠረው ደግሞ መስኮት በሌለውና በታፈነ ቤት ውስጥ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ለካንሰር፣ ለሳንባ፣ ለልብና ለሌሎችም ሕመሞች ይዳርጋል፡፡ ሕመም መፈጠሩ ደግሞ የአንድን ቤተሰብ የሕክምና ወጪም የሚጨምር ነው፡፡ ከማኅበራዊ፣ ከኢኮኖሚያዊ፣ ከጤና፣ እንዲሁም ከአካባቢ ችግር ጋር የተሳሰረ ቀውስ የሚፈጥር ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ንፁህ የአበሳሰል ሥርዓት ለማንም ሰው በሚመጥን የመግዛት አቅም የማብሰያ ቴክኖሎጂዎችን ማዳረስም የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ ቴክኖሎጂዎችን ማለትም ኃይል ቆጣቢ፣ ከጭስ የፀዱ፣ ውጤታማና ጤናማ የሆኑ ማብሰያዎችን በበቂ ሁኔታ ለገበያ ማቅረብ አንዱ ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች መቅረባቸው ብቻ ሳይሆን፣ ማኅበረሰቡ በሚመጥነው ዋጋ ሊገዛቸው የሚችላቸው ሆነው መቅረብም መቻል አለባቸው፡፡ ንፁህና ከብክለት የፀዳ የአበሳሰል ሥርዓት ይህን ሁሉ ሒደት የሚጠይቅ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አገራዊ አሳሳቢ ችግር ያልሆነው በግለሰብ ምናልባትም በቤተሰብ ደረጃ የተወሰነ ችግር በመሆኑ ነው?

ገሰሰ (ዶ/ር)፡- በግለሰብ ወይም በቤተሰብ የተወሰነ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ በየሠፈሩ ካሉ ዳቦ ቤቶች፣ ጠላና ጠጅ መጥመቂያዎች ጀምሮ ማብሰልን መሠረት ያደረጉ ንግዶችና ኢንዱስትሪዎች መታየት አለባቸው፡፡ ትልልቅና ዘመናዊ የሚባሉ ሆቴሎች ገብተህ ወደ ጀርባ ዞር ስትል፣ ማብሰያው በፍልጥና በከሰል የሚካሄድ ሆኖ ነው የምታገኘው፡፡ ዘመናዊና ውድ ምግብ ቤቶች ሳይቀር ዛሬም ከጭስና ከእሳት አልተላቀቁም፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቻችን በምን እንደሚያበስሉ እናውቃለን፡፡ በቅርቡ ከተጀመረው ከትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ጋርም አያይዘን ልናየው እንችላለን፡፡ ማብሰል ከቤተሰብና ከግለሰብ አልፎ ከብዙ ተቋማትና ከኢንዱስትሪዎች ጋር የተገናኘ ጉዳይ ነው፡፡   

ሪፖርተር፡– ከብክለት የፀዳ የአበሳሰል ሥርዓት በአገር ደረጃ ለመተግበር በቂ ትኩረት አለመሰጠቱ ይነገራል፡፡ ይህ ለምን የሆነ ይመስልዎታል?

ገሰሰ (ዶ/ር)፡- ይህ ጥናት የሚፈልግ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ትኩረት ሊሰጥ የሚገባው አካል ማን ነው ከሚለው ጀምሮ ለምን ትኩረት አልተሰጠውም የሚለው ጉዳይ መጠናት አለበት፡፡ ከብክለት የፀዱ የማብሰያ ቴክሎጂዎች መስፋፋታቸው፣ እንዲሁም የማኅበረሰቡ የመግዛት አቅምም ሊታይ ይገባል፡፡ ጉዳዩ ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን መዋቅራዊም ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ ጎኑ ደግሞ ባህላዊና ልማዳዊ መሠረትም ሊኖረው ይችላል፡፡ መዋቅራዊ ስንል ለጉዳዩ ቅድሚያ ከመስጠት ጀምሮ የፖሊሲ፣ የተቋማትና የአሠራር ችግሮችን የተመለከተ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ሁሉ በአጠቃላይ ተጠንቶ ነው ዘርፉ ትኩረት ለምን ተነፈገው የሚለው መፈተሽ ያለበት፡፡ አንድ ቤተሰብ አበሳሰልህን፣ አመጋገብህን ወይም የምግብ አቅርቦትህን አሻሽል ከምትለው የትኛውን ነው የሚቀድመው የሚለው በመሠረታዊነት መታየት አለበት፡፡ የምግብን ዋስትና ከማረጋገጥ ቀጥሎ ነው የምግብ አበሳሰል ጉዳይ የሚመጣው፡፡ የምግብ አበሳሰል ጉዳይ ሲመጣ ደግሞ ብዙ አማራጭ ያለው ጉዳይ መሆኑ ሊታይ ይገባል፡፡ ምግብ አበሳሰል ላይ ሲገባ በሦስት ጉልቻ በጭስ እየተጨናበሱ፣ ጤናን፣ አካልን፣ አካባቢንም ሆነ ኪስን እየጎዱ ኋላቀር አበሳሰልን ከመከተል ይልቅ የዘመነና የተሻሻለ አበሳሰልን ብዙዎች እንደሚመርጡ ይገመታል፡፡

ዘርፉ አላደገም በምንልበት ጊዜ እስካሁን በኢትዮጵያ ከ80 በመቶ በላይ ማኅበረሰብ የተሻሻሉ የማብሰያ ቴክሎጂዎችን አይጠቀምም የሚል ግምት እናገኛለን፡፡ በአማካይ በያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ አምስት ሰው አለ ተብሎ እንኳን ቢታሰብ 120 ሚሊዮን ሕዝብን ለአምስት በማካፈል፣ በአገሪቱ ወደ 20 ሚሊዮን ቤተሰብ አለ እንደ ማለት ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ከወጪ ቀሪ 80 በመቶውን እንውሰድ ብንል እንኳን 15 ሚሊዮን ቤተሰብ አለ የሚል ቁጥር ላይ እንደርሳለን፡፡ ለእያንዳንዱ 15 ሚሊዮን ቤተሰብ በአማካይ አንድ ዘመናዊ ምድጃ (ምጣድ) እናድርስ ቢባል ዘርፉ እጅግ ግዙፍ የገበያ ዕድል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ አንዳንድ ቤተሰብ ደግሞ ከአንድ በላይ ምድጃ ይፈልጋል፡፡ ለእንጀራ ለብቻው፣ ለወጥ ለብቻው፣ ለቡና ለብቻው ይኑረኝ የሚልና መግዛት የሚችል ቤተሰብ አለ፡፡ በሌላ በኩል ምድጃዎቹ የአገልግሎት ዘመናቸውን ሲጨርሱ መተካት አለባቸው፣ ሲበላሹም መጠገንና መለዋወጫ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የምድጃ ጉዳይ ልክ እንደሌላው ነገር ሁሉ ትልቅ የእሴት ሰንሰለት ያለው ኢንዱስትሪ ሊፈጥር ይችላል የምንለው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን በመሠረታዊነት የምድጃና የአበሳሰል ጉዳይን ትኩረት ስንሰጥ ነው፡፡

ጭስ የሌለውና ከብክለት የፀዳ ዘመናዊ ምድጃ በማምረት ሥራ ላይ ብዙ ሰው ሊሰማራ ይችላል፡፡ ምድጃውን ብቻ ሳይሆን የኢነርጂ አማራጮችንም በማቅረብ ረገድ ብዙ ኢንዱስትሪዎች ሊስፋፉ ይችላሉ፡፡ ባዮፊውል የመሳሰሉ ምርቶችን በማቅረብ አገርን ከብዙ ወጪ መታደግ ይቻላል፡፡ ከስኳር ፋብሪካዎች ተረፈ ምርት ብዙ የኢነርጂ አማራጮችን ማምረት ይቻላል፡፡ በየአካባቢው ከሚጣሉ ቆሻሻዎችና ተረፈ ምርቶች ለማብሰያ የሚያገለግሉ ከሰልና ማገዶዎችን በማምረት፣ አካባቢንም ሆነ ጤናን መጠበቅ የሚችል ሰፊ የእሴት ሰንሰለት ያለው ኢንዱስትሪ መገንባት ይቻላል፡፡ ይህን መሰል ሰፊ የገበያ ዕድል ያለው መስክ ግን በሚፈለገው ልክ ኢንቨስተሮችንና ባለሀብቶችን መሳብ አልቻለም፡፡ ዘርፉ የኢንቨስትመንት መስክ መሆን ያቃተው በምን ምክንያት ነው ተብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ የተሻሻሉ ምድጃዎችን ወይም ከብክለት የፀዱ ከሰልና ማገዶዎችን የሚያመርቱ ሰዎች፣ በአነስተኛ ደረጃ የሚገኙ በትንሽ መሥሪያ ቦታዎች ላይ የተገደቡና ወደ ግዙፍ ኢንዱስትሪነት ገና ያላደጉ ናቸው፡፡

ይህ ብቻም አይደለም፣ ኢንዱስትሪው የኅብረተሰቡን የአመጋገብና የአበሳሰል ልማድና ባህል የተከተለ ነው ወይ የሚለውም መጠየቅ አለበት፡፡ እንጀራ ተመጋቢ ማኅበረሰብ እንዳለው ሁሉ፣ አንዱ ማኅበረሰብ ገንፎ የሚያገነፋ፣ ሌላው ድንች መቀቀል የሚያዘወትር፣ አንዳንዱ ደግሞ ክትፎ መክተፍ የሚያዘወትር ማኅበረሰብ ያለበት አገር ነው፡፡ ዘመናዊ የማብሰያ ቴክኖሎጂ መጠቀምን ከመስበክ በፊት ለኅብረተሰቡ ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ አማራጮችን ይዞ መምጣትና በአቅሙ ተደራሽ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ መረሳት የለበትም፡፡

ዘርፉ መሻሻልና ማደግ ያለበት ነው ቢባልም፣ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ ግን ብዙ ሥራ መሥራት ይጠይቃል፡፡ በየቴክኒክና ሙያው ተቋሙ፣ በየኮሌጁና በየዩኒቨርሲቲው መሠረታዊ ዕውቀትና ክህሎትን የጨበጠ የሰው ኃይል አሰልጥኖ ማስመረቅ ይጠይቃል፡፡ ሰፊ የተመረቀ የሰው ኃይል ቢኖር እንኳን ዘርፉን በልዩ ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራና የዕውቀት ሽግግር መሠረት የሚሆን አካል ግን ያስፈልጋል ተብሎ ይታመናል፡፡ ሚዲያው ስለኃይል ልማት፣ አጠቃቀምና ቁጠባ ሲነሳ በአብዛኛው ለትልልቅ የኃይል ልማት ፕሮጀክቶች ነው ትኩረት የሚሰጠው? ወይስ በየቤቱ የእያንዳንዱን ሰው ሕይወት ለሚነካው የማብሰያ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም? የሚለውም መታየት አለበት፡፡ እንደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ከሚያገኙት የሚዲያ ትኩረት ጥቂቱን እንኳ ዘመናዊ የማብሰያ ጉዳይ ያገኘ አይመስልም፡፡

ሪፖርተር፡- ዘመናዊ ማብሰያን ማስፋፋት የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ነው ይባላል፡፡ ዘርፉን ከሌሎች ዘርፎች ጋር አስተሳስሮ መደገፍስ አይቻልም?

ገሰሰ (ዶ/ር)፡- ትኩረት የማጣቱ ችግር ስንል ከፖሊሲ ጋር በቀጥታ ይገናኛል፡፡ ፖሊሲ ደግሞ ከስትራቴጂ፣ ስትራቴጂ ደግሞ ከመመርያ፣ ከዚያም ከተቋማት ጋር እየተያያዘ ታች ድረስ ይሄዳል፡፡ የማብሰያ ጉዳይ ከቤተሰብ፣ ከጤና፣ ከአካባቢ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከኢነርጂና ከሌላም ጋር የተቆራኘ በመሆኑ የዘርፉ ዕድገት ከሌሎች መስኮች ጋር ተያይዞ መታየቱ አስፈላጊና ጠቃሚ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአንዳንድ ሁኔታዎች በሌሎች ጉዳዮች ተጋርዶ የሚዘነጋበትና ትኩረት የሚያጣበት ሁኔታ እንዳይፈጠር መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የአየር ንብረት ለውጥን የተመለከተ ስትራቴጂ በአገራችን አለ፡፡ ያ ስትራቴጂ ከብክለት የፀዱ የተሻሻሉ ምድጃዎችን በአገሪቱ ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ ያስቀምጣል፡፡ የማብሰያ ጉዳይ በዚህ ውስጥ ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ መንገዶችን ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ የጤና ሚኒስቴር በበኩሉ ማንኛውም ቤተሰብ ባልተበከለና ጤናማነቱ በተጠበቀ አካባቢ መኖር አለበት ይላል፡፡ ይህም ለዘርፉ ትኩረት ማግኘት አንዱ በጎ ዕድል ሆኖ ሊታይ ይችላል፡፡

ሕገ መንግሥቱም ቢሆን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በንፁህና በጤናማ አካባቢ የመኖር መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ ከብክለት የፀዳ የማብሰያ አገልግሎት የማግኘት ጥያቄ ከዚህ ተነስተን ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና ያገኘ ጉዳይ ነው ልንል እንችላለን፡፡ ጉዳዩ በብዙ አቅጣጫ ከብዙ ዘርፎች ጋር ይተሳሰራል፡፡ ከሌሎች ዘርፎች ጋር ተሳስሮ ብቻ ሳይሆን እንደ ሌሎቹ ራሱን ችሎና በቂ ትኩረት አግኝቶ መነሳትም ይችላል፡፡ ንፁህና የተሻሻለ የማብሰያ ቴክኖሎጂ መጠቀምን የሴቶች ጉዳይም ያነሳዋል፣ ግብርናም ያነሳዋል፣ ደን ልማት፣ አካባቢ ጥበቃ፣ ጤና ጥበቃ፣ ውኃና ኢነርጂ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሌሎችም ጉዳዬ ብለው ያነሱታል፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉም ቢያነሳውም ባለቤት የማጣት ችግር ሲገጥመው ይታያል፡፡ ይህ ሊታሰብበት የሚገባ ችግር ነው፡፡ ከብክለት የፀዳ ማብሰያ ጉዳይን በዋናነት በባለቤትነት የያዘው ውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሲሆን፣ በተቋሙ ራሱን በቻለ አንድ የሥራ ክፍል የሚመራ መስክ ነው፡፡ ይህ አደረጃጀት የበለጠ እየተጠናከረ መሄድ እንዳለበትና ዘርፉን ከእስካሁኑ በላይ ትኩረት እንዲያገኝ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ነው የሚታመንበት፡፡

ሪፖርተር፡- በአዲሱ የውኃና ኢነርጂ ፖሊሲ ውስጥ ዘርፉ ተካቶ መቅረቡ ከዚህ ቀደም የነበረውን የፖሊሲ ክፍተት ይደፍናል እየተባለ ነው፡፡ ዘርፉ የፖሊሲ ትኩረት ማግኘቱ ብቻውን ግን እየገጠሙ ያሉ መሰናክሎችን ያቀላል?

ገሰሰ (ዶ/ር)፡- ፖሊሲው ገና አላለቀም፣ ገና በመረቀቅ ሒደት ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ሆኖም ጉዳዩ በፖሊሲ ተካቶ ይቀርባል መባሉ በራሱ የሚሰጠው ትኩረት እያደገ መምጣቱን አንድ ጠቋሚ ነጥብ ነው፡፡ ይህ አንድ ዕርምጃ ወደፊት ሊባል የሚችል ጠቃሚ ጉዳይ ነው፡፡ ፖሊሲ ብቻውን ሳይሆን ግን ማስፈጸሚያ በጀትን ጨምሮ፣ መዋቅር፣ መመርያ፣ ተቋምና ሌላም ያስፈልገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከብክለት የፀዳ የማብሰያ ዘዴ በኢትዮጵያ አለመስፋፋቱና ኋላቀር ደረጃ ላይ ለመገኘቱ በዋናነት ችግር የሆነው ምን ዓይነት ምክንያት ነው?

ገሰሰ (ዶ/ር)፡- የተጠናና በተጨባጭ ዳታ የተደገፈ መረጃ ሳይኖር ይህን ጥያቄ ለመመለስ መሞከር ትንሽ ከባድ ነው፡፡ ለምሳሌ ሞባይል ስልክ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ 20 ዓመቱ ነው ይባላል፡፡ አሁን ያለው ተጠቃሚ ቁጥር ከ60 ሚሊዮን በላይ መድረሱም ይነገራል፡፡ የተሻሻለና ዘመናዊ የማብሰያ ቴክኖሎጂ ጉዳይ እ.ኤ.አ. በ1970ዎቹ የመጣ አጀንዳ ነው፡፡ እስካሁን በኢትዮጵያ ንፁህ የማብሰያ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሆነው ኅብረተሰብ ቁጥር ግን ከ15 በመቶ የማያልፍ ነው፡፡ ይህ የአኃዝ ዕድገትም ከኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ጋር በአብዛኛው የተቆራኘ ነው፡፡ የሁለቱን ማለትም የሞባይል ስልክና የንፁህ ማብሰያ ቴክኖሎጂ ዕድገት ልዩነትን እናነፃፅረው፡፡ የማብሰል ጉዳይ ምግብ ነው፣ ጤና ነው፣ በአጠቃላይ የእያንዳንዱን ሰው የየዕለት ሕይወት የሚነካ ጉዳይ ነው፡፡ ሞባይል ደግሞ መረጃ ማግኛና የመገናኛ አውታር ነው፡፡ የሰዎች ፍላጎት ከመሠረታዊው የማብሰያ ጉዳይ ወደ ሞባይል ለምን አዘነበለ የሚለው ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡  

ከብክለት የፀዳ ማብሰያን መጠቀም በተመለከተ በኅብረተሰቡ ዘንድ በቂ ግንዛቤ መፍጠር ተችሏል ወይ የሚለው መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ በበቂ ሁኔታ ንፁህ የማብሰያ ቴክኖሎጂ አማራጮችን ማቅረብ መቻል አስፈላጊ ነው እንደሚባለው ሁሉ ሰዎች የሚቀርቡ የቴክኖሎጂ አማራጮችን ፈልገውና ፈቅደው የመግዛት አቅም አላቸው ወይ የሚለውም አብሮ መታሰብ አለበት፡፡ ከመግዛት አቅም ውጪ ለአንድ ሰው የማብሰያ ጉዳይ አሳሳቢ ላይሆንም ይችላል፡፡ ሰዎች ምግብ በስሎ መቅረቡን እንጂ በምን በሰለ ብለው የመጨነቅ ዝንባሌ ብዙም ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ገጠር የሚኖሩና ምርጫ ያጡ ሰዎች ጭምር የተሻለ፣ ከጭስ የፀዳ፣ ወይም ኃይል ቆጣቢ ምጣድና ምድጃ መጠቀም እንደሚጠቅማቸው በሚገባ ያውቃሉ፡፡ አሁን የግብርና፣ የጤናም ሆነ የወረዳ መዋቅሮች ታች ድረስ ገብተው ይሠራሉ፡፡ በዚህ የተነሳ በኋላቀር ማብሰያዎች መገልገል ያለውን ጉዳት ኅብረተሰቡ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የሚሰማበት ዕድል አለው፡፡ ዘመናዊ የማብሰያ ቴክኖሎጂ በኅብረተሰቡ የሚፈለግ ከሆነና ጥቅሙ ከታወቀ፣ ለምንድነው በሰፊው መሰራጨት ያልቻለው ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ደግሞ የግንዛቤው ችግር ያለው ታች ኅብረተሰቡ ጋር ሳይሆን፣ ከላይ ፖሊሲ አውጪዎች ዘንድ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ሊያደርስ ይችላል፡፡ ዘመናዊ የማብሰያ ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ያልተስፋፋውም ሆነ ኅብረተሰቡ ከአስቸጋሪ የሦስት ጉልቻ አበሳሰል መላቀቅ ያልቻለው፣ በዚህ መነሻነት ነው ብሎ አንድ ዓይነት ምላሽ መስጠት ወይም አመክንዮ ማበላለጥ አይቻልም፡፡ በሁሉም አቅጣጫ ጉዳዩ ትኩረት ተነፍጎታል ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ በሁሉም ወገን የግንዛቤ ችግር አለ፡፡ በሁሉም አቅጣጫ ጉዳዩ ቅድሚያ አይሰጠውም  ማለት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ጉዳዩን አጀንዳ ለማድረግ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

ገሰሰ (ዶ/ር)፡- ትልቁ ነጥብ ዘርፉ ድምፅ ሊኖረው ይገባል፡፡ ጉዳዩን በባለቤትነት የሚይዙና የሚቀሰቅሱ ወገኖች ያስፈልጋሉ፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ በየአካባቢው መንገድ፣ ትምህርት ቤት፣ ጤና፣ ወይም የውኃ ፕሮጀክት አልተሠራም ብለው ድምፅ የሚያሰሙ ተመራጮች አሉ፡፡ እስከ ዛሬ ግን አንድም የፓርላማ አባል በጭስ ምክንያት ሰዎች እየሞቱ ነው ብሎ ድምፅ ሲያሰማ ታይቶ አይታወቅም፡፡ እናቶችና ሴቶች በኋላቀር አበሳሰል እየተጎዱ ነው የሚል ጠያቂም አጋጥሞ አያውቅም፡፡ ዘመናዊ የማብሰያ ዘዴዎችን ማስፋፋት ከጭስ ተጋላጭነት ባለፈ ለኢኮኖሚና ለአካባቢም ጠቀሜታ ያለው ነው ብሎ የሚናገር ወገን አይታይም፡፡ ይህ ጉዳዩ ገና የፖሊሲ አጀንዳ አለመሆኑንና ጠያቂ እንደሌለው የሚያሳይ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ዘርፉ እንደ ሌሎች ጉዳዮች ድምፅ የሚሆንለት ወገንም የለውም፡፡ ለምሳሌ የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ጉዳይን በሰፊው መቀስቀሻ ያደረጉ በርካታ ሰዎችና ተቋማት አሉ፡፡ በኩላሊት ሕመምና ሕክምና ችግር ጉዳይ የሚንቀሳቀሱ አርቲስቶችና ታዋቂ ሰዎች በርካታ ናቸው፡፡ በልብ ሕክምና ጉዳይና በሌሎች ማኅበራዊ ችግሮች ላይም ችግሮች ጎልተው እንዲሰሙ የሚያደርጉ፣ የሚቀሰቅሱና ግንዛቤ የሚፈጥሩ ግለሰቦች ብዙ ናቸው፡፡ ከብክለት የፀዳ የማብሰያ ሥርዓት አለማስፋፋት መሠረታዊ የአገር ችግር መሆኑን ተገንዝቦ ለጉዳዩ ድምፅ የሚሆን ወገን መፍጠር እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የእናንተ ድርጅት በዚህ ጉዳይ ላይ ምንድነው የሚሠራው?

ገሰሰ (ዶ/ር)፡- ኤስኤንቪ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሲሆን በግብርናና በውኃ አቅርቦት ላይ ይሠራል፡፡ ሌላው ደግሞ በኃይል አቅርቦት ይሠራል፡፡ የገጠር ኃይል አቅርቦት፣ በተለይም በግብርናውና በማብሰያው ዘርፍ ባሉ የኢነርጂ አቅርቦትና አጠቃቀም ጉዳዮች ላይ አተኩሮም ይንቀሳቀሳል፡፡ በዚህ የተነሳ ዘመናዊ የአበሳሰል ሥርዓት ለመገንባት ቅድሚያ ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- በመርካቶና በተለያዩ ቦታዎች ዘመናዊ ምድጃዎች ይሠራሉ፣ ኅብረተሰቡም በሰፊው እነዚህን ይጠቀማል፡፡ ውኃና ኢነርጂ የሚመራውም ሆነ የእናንተን የተሻሻለ ምድጃ የማሠራጨት ዕቅድ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ለማስተሳሰር ለምን አልተቻለም?

ገሰሰ (ዶ/ር)፡- የጥራትና የገበያ ጉዳይ ትልቁ ችግር ነው፡፡ መርካቶ ምናለሽ ተራ ትልቅ የምሕንድስናና የፈጠራ መናኸሪያ ሊባል ይችላል፡፡ እንዲህ ባሉ አካባቢዎች በዲዛይንም ሆነ በውበትና በዋጋ የተሻሉ ሊባሉ የሚችሉ ምድጃዎች በሰፊው ይመረታሉ፡፡ ችግሩ መርካቶ እየተመረተ በየቀኑ በአይሱዙ እየተጫነ በመላ አገሪቱ የሚሠራጨው ምድጃ በአብዛኛው የሚፈለገው ጥራት የለውም፡፡ ጉዳዩ በሰፊው የተጠና ሲሆን፣ ከ90 በመቶ በላይ እንደ መርካቶ ካሉ አካባበዎች የሚመረት ምድጃ ጥራት የሌለው መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ እነዚህ ለገበያ የሚመረቱ ምድጃዎች በአሠራርም በአገልግሎትም በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚተገበሩና በሙከራ ተረጋግጠው የተቀመጡ የጥራት መሥፈርቶችን አብዛኞቹ አያሟሉም፡፡ አንድ ሰው ላቀች ከሰል ምድጃን ከገበያ በርካሽ ሊገዛ ይችላል፡፡ ነገር ግን ላቀች ምድጃ መጀመሪያ ዲዛይን ተደርጎ ጥቅም ላይ ሲውል የተቀመጠ የአሠራር መሥፈርት አለ፡፡ የብረቱ ብቻ ሳይሆን የሸክላው ቁመትና አቀማመጥ የተቀመጡ የልኬት መሥፈርቶችን ያሟላ መሆን አለበት፡፡ የምድጃው አየር መሳቢያ ቀዳዳና የሸክላው ብሶች ተለክተውና ተቆጥረው ነው የሚሠሩት፡፡ ምርጥ ምድጃ ወይም የምጣድ ምድጃ እየተባለ ሲገነባም በዘልማድ ሳይሆን፣ በትንሹም ቢሆን ምሕንድስናና የጥራት መሥፈርት ወጥቶለት ነው የሚሠራው፡፡

ሰዎች ምድጃ መሥራታቸውና የወዳደቁ ቁሳቁሶችን መልሰው ጥቅም ላይ በማዋል ጭምር ሰፊ ግብይት ያለው ሥራ ፈጠራ በማካበታቸው ሊደነቁ እንጂ ሊኮነኑ አይገባም፡፡ ነገር ግን የማብሰያ ቴክኖሎጂዎች ሲሠሩም ቢሆን ጥራቱንና መሥፈርቱን ባሟላ መንገድ መሆን አለበት፡፡ የቴክኒክና ሙያዎች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ውኃና ኢነርጂን የመሳሰሉ ተቋማት በየጊዜው የተሻሻሉ ምድጃዎች ያፈልቃሉ፡፡ እነዚህን ምድጃዎች ደግሞ በላብራቶሪ አስፈትሸውና ጥራታቸው አስገምግመው ነው የሚያቀርቡት፡፡ ይሁን እንጂ ቴክኖሎጂዎቹን ማሠራጨት ላይ ሁሌም እንቅፋት ሲገጥማቸው ይታያል፡፡ ጥራቱን የጠበቀ የተሻሻለ ምድጃዎች መርካቶ ከሚመረቱት ጋር ተወዳዳሪ በሆነ ዋጋ ማቅረብ ከባዱ ፈተና ይመስላል፡፡ መንግሥት ጥራት መፈተሻ ላብራቶሪ በአዲስ አበባ ገንብቷል፡፡ ላብራቶሪው በየክልሉ መሠራጨቱ አስፈላጊ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ማንደጃ ማምረት ላይ በግል የተሰማሩ ነጋዴዎች ይህንን አንድ ላብራቶሪ በአግባቡ እየመጡ ሲጠቀሙበት አይታይም፡፡ ሌላው ጥራት ባለው መንገድ ሠርቼ ባቀርብ ወጪ ስለሚጨምር ምርቱን ያስወድድብኝና ፈላጊ አጣለሁ የሚል ሥጋት አምራች ነጋዴዎች ዘንድ ያለ ይመስላል፡፡ እነሱ የሚያመርቱትን ምርት ለገበያ ሲያቀርቡ የጥራት መሥፈርቶችን አሟልቶ፣ የተመረተውንም ምርት ጎን ለጎን ቢያከፋፍሉና ቢሸጡ ገበያውን ለማላመድ እንደሚረዳ ግንዛቤው እየመጣ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ዘርፉ እንዲያድግ በአጠቃላይ ከዚህ በላይ ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደሚጠይቅ መረሳት የለበትም፡፡

በኢትዮጵያ 20 ሚሊዮን ቤተሰብ ምድጃ ያስፈልገዋል ካልን፣ ለዚህ ሁሉ ቤተሰብ ጥራቱን የጠበቀ ምድጃ አምርተው የሚያቀርቡ ብዙ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት አለባቸው ማለት ነው፡፡ ለእነዚህ ሥራ ፈጣሪ ኢንዱስትሪዎች ደግሞ የፋይናንስ አቅርቦት፣ የቴክኒክ ድጋፍና ሌላም ማበረታቻዎች መቅረብ አለባቸው፡፡ በኢትዮጵያ በ11 ዓመታት 17 ሚሊዮን ዘመናዊ ምድጃዎች ቢሠራጩም፣ ከእነዚህ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ግን ከሥር ሚሊዮን እንደማይበልጡ ይታመናል፡፡ የዘመናዊ ምድጃዎች ተደራሽነት በገጠርም ሆነ በከተሞች ገና ታች ያለ ነው፡፡ ዘርፉ ትኩረት ካገኘ ገበያውንም ሆነ ሥራ ፈጠራውን በዚህ ረገድ ማሳደግ ይቻላል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የአጎራባች ክልሎች የሰላም ዕጦት በእኛ ላይ ሸክምና ጫና ፈጥሮብናል›› ከአቶ ባበከር ሀሊፋ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ

አቶ ባበከር ሀሊፋ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወንዶ ገነት ኮሌጅ በፎረስትሪ ሠርተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረው አጠናቀዋል። ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም....

‹‹ሥራችን ተከብሮ እየሠራን ነው ብዬ አስባለሁ›› ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር

ቀደም ሲል በተለያዩ ተቋማት በኃላፊነቶች ሲሠሩ የቆዩትና በ2014 ዓ.ም. የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን በዋና ኦዲተርነት እንዲመሩ የተሾሙት  ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ በኦዲት ክፍተቶች ላይ...

‹‹ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማስተላልፈው መልዕክት የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ያለበቂ ምክክርና ውይይት እንዳይፀድቅ ነው›› አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም፣  የሕግ ባለሙያ

አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም በዳኝነትና በጥብቅና ሙያ ለረዥም ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከአምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ በሕገ መንግሥትና አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ  ጠበቆች ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ...