Saturday, July 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቴሌኮምና ፋይናንስ ተቋማት በአገር ውስጥ መረጃ የሚለዋወጡበት አገልግሎት ለመጀመሪያ ጊዜ ቀረበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የቴሌኮምና ፋይናንስ ተቋማት የተለያዩ መረጃዎችን ለመለዋወጥ በውጭ አገር መሠረተ ልማት ይጠቀሙበት የነበረውን አሠራር፣ በአገር ውስጥ እንዲለዋወጡ የሚያስችል የዳታ መሠረተ ልማት አገልግሎት ለመጀመሪያ ጊዜ ‹‹ዊንጉ አፍሪካ›› በተባለ የግል ተቋም መቅረብ ጀመረ፡፡

“Internet Exchange Point- IXP” በመባል የሚታወቀው የኔትወርክ መሠረተ ልማት አገልግሎት በዋናነት፣ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎች እርስ በርስ መረጃዎችን እንዲለዋወጡ የሚያስችል መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

በአይቲ ፓርክ ኮርፓሬሽን ውስጥ በ50 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ዊንጉ አፍሪካ በተሰኘው ዓለም አቀፍ የግል ዳታ አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት አማካይነት የቀረበው ይህ አገልግሎት፣ የተለያዩ የቴሌኮም ኩባንያዎች አንዱ የሌላኛውን መረጃዎች ለማግኘት የሚያስችል ሲስተም ነው ተብሏል፡፡

የአይኤክስፒ አገልግሎትን ከዚህ ቀደም ተቋማቱ ለማግኘት ሲፈልጉ ሲስተሙ በቀጥታ ውጭ አገር ሄዶ ተመልሶ መጥቶ ይገኝ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በአገር ውስጥ መቅረብ መጀመሩ ተቋማቱ በፍጥነትና በቀላሉ ተገናኝተው እንዲለዋወጡ የሚያደርግ ይሆናል ተብሏል፡፡

ልውውጡ ከአገር ውጭ መደረጉ መዘግየቶች ያሉበት፣ ተገልጋዮች ተጨማሪ የብሮድባንድ ክፍያ እንዲክፍሉ የሚያደርግ ሲሆን፣ የውጭ ዳታዎችን ፍለጋ ካልሆነ ለአገር ውስጥ ዳታዎች ተቋማቱ ወደ ውጭ የሚያደርጉትን አሰሳ እንደሚያስቀር የዊንጉ አፍሪካ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚና ቺፍ ኦፕሬቲንግ አፊሰር ዴሞስ ኪሪያኩ ገልጸዋል፡፡

ዊንጉ አፍሪካ ይህን አገልግሎት ማዘጋጀቱ ከቴሌኮም ተቋማት ባሻገር ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት የሚዲያ አውታሮች ጭምር በቀላሉ እርስ በርስ ተደራሽ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን አስታውቋል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ውስጥ የዳታ ሴንተር አገልግሎቶችን ሲያቀርብ እንደቆየ ያስታወቀው ዊንጉ አፍሪካ፣ 24 ወራት በፈጀ ግንባታ ለአገልግሎት ያበቃው የዳታ ማዕከል የኢትዮ ቴሌኮም፣ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ጨምሮ ሌሎች ግዙፍ ተቋማትን ለማስተናገድ የሚችል አቅም ያለው መሆኑን ትናንት ሰኔ 6 ቀን 2015 ዓ.ም. በአይቲ ፓርክ በተደረገ የምርቃት ሁነት ላይ ተገልጿል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) የዊንጉ አፍሪካ ዳታ ማዕከል ዕውን መሆን አገሪቱ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ሽግግር የባለሀብቶችን ተሳትፎ አጥብቃ እንደምትሻ ማሳያ ነው ብለዋል።

የዜጎችን ሕይወት ከማሻሻል ባሻገር ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የውጭ ምንዛሪ ክምችት፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በመስኩ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማረጋገጥ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የግል ዘርፉን በማሳተፍ በትብብር እየተሠራ ነው ብለዋል።

የዊንጉ አፍሪካ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አንቶኒ ቮስካሪደስ በበኩላቸው፣ ዊንጉ አፍሪካ ዘመናዊ የመረጃ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀሙ በሶማሊ ላንድ፣ ጂቡቲና ታንዛኒያ አገሮች አገልግሎት የሚሰጡ የመረጃ ቋት ያለው መሆኑን ገልጸው፣ በኢትዮጵያ አስተማማኝና ደኅንነቱ የተጠበቀ የመረጃ አገልግሎት የሚሰጥና ለአፍሪካውያን ተጨማሪ አቅም የሚሆን መሠረተ ልማት የተገነባ መሆኑን አስታውቀዋል።

የአይቲ ፓርክ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሔኖክ አህመድ እንደገለጹት፣ እንደ ዊንጉ አፍሪካ ሁሉ የተለያዩ ተቋማትም በአይ ቲ ፓርክ ኢንቨስት እያደረጉ ሲሆን፣ ዊንጉ አፍሪካ ከአሁኑ ደንበኞች እያፈራ ያለ ተቋም እንደሆነና ፓርኩም በድምሩ አራት የሚሆኑ የዳታ ማዕከላት በውስጡ የያዘ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች