Friday, July 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት በግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ የመገንባት ዕቅዱን ለአጋር ድርጅቶች አቀረበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት በስድስት ክልሎች የተፈጠሩ ግጭቶች ያወደሙትንና በኢኮኖሚ ላይ ያደረሱትን ኪሳራ በዝርዝር በማቅረብ፣ ለቀጣይ አምስት ዓመታት ለመልሶ ማቋቋምና ግንባታ የያዘው ዕቅድ ለአጋር ድርጅቶች ይፋ ተደረገ፡፡

ከኅዳር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ታኅሳስ 2014 ዓ.ም. ድረስ ብቻ በትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ኮንሶ ዞን የተፈጠሩት ግጭቶች ባደረሱት ጉዳት ላይ ተመርኩዞ የተጠናውን ዳሰሳ፣ በዓለም ባንክና በሌሎች ልማት አጋሮች በመታገዝ የተካሄደ የጉዳትና ፍላጎት ግምገማ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ለአጋሮችና ዕርዳታ ድርጅቶች ይፋ የሆነው ሰነድ እንደሚያስረዳው፣ ግጭቶቹ ያደረሱት ውድመት 22.6 ቢሊዮን ዶላር የሚመደብና በኢኮኖሚው ላይ የደረሰው ኪሳራ ደግሞ ከስድስት ቢሊዮን ዶላር ከፍ የሚል እንደሆነ ያሳያል፡፡

በአጠቃላይ የ28.7 ቢሊዮን ዶላር ውድመቶችና ኪሳራዎች የደረሱ ሲሆን፣ በታቀደው የመልሶ ግንባታ ፍላጎት መሠረት ደግሞ 20 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ለአጋር ድርጅቶቹ በዝርዝር ቀርቧል፡፡ ከአገራዊ ጥቅል ምርት አንፃር ውድመትና ኪሳራዎቹ በድምርሩ 25 በመቶውን እንደሚሸፍኑ ማየት ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ መልሶ ማቋቋምና መገንባት ፕሮግራም በገንዘብ ሚኒስቴር አዘጋጅነት ባለፈው ሰኞ ሰኔ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. በሐያት ሬጀንሲ ሆቴል ለአጋር ድርጅቶች ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ የተለያዩ የመንግሥት አካላት፣ የክልል ፕሬዚዳንቶችና የልማት አጋሮች ተገኝተው ሐሳባቸውን ገልጸዋል፡፡

በማኅበራዊ ዘርፎች፣ በምርቶች፣ በመሠረተ ልማትና በተለያዩ ባለብዙ ዘርፎች ላይ በስድስቱም ክልሎች የደረሱት ጉዳቶች ናቸው በዳሰሳው የቀረቡት፡፡ በምርት ዘርፉ ላይ በርካታ ጉዳቶች የደረሱ ሲሆን፣ የውድመትና ኪሳራውን ጨምሮ በአጠቃላይ ከደረሰው የ28.7 ቢሊዮን ዶላር የምርት ዘርፉ ብቻ 19 ቢሊዮን ዶላር ይሸፍናል፡፡

እንደ ጤና፣ ትምህርት፣ ማኅበራዊ ጥበቃ፣ መኖርያ ቤትና ባህላዊ ቅርሶች ላይ የደረሱት ውድመቶችና ኪሳራዎች ከምርት ዘርፍ በማስቀጠል 6.2 ቢሊዮን ዶላር ሆነዋል፡፡ የመሠረተ ልማቶች ላይ የደረሰው ውድመትና ያመጣው የኢኮኖሚ ኪሳራ 2.4 ቢሊዮን ዶላር ተገምቶ ሌሎች የአስተዳደር፣ የአካባቢ ጥበቃና የአደጋ ሥራ አመራር ላይ የደረሱት ጉዳቶችን 902 ሚሊዮን ዶላር ይሆናል ብሎ ዳሰሳው አስቀምጧል፡፡

ከእነዚህ ጉዳቶች ተመልሶ ለመቋቋምና ለመገንባት የታቀደውን የ20 ቢሊዮን ዶላር ፍላጎት በአምስት ዓመታት ጊዜያት ውስጥ በሦስት ክፍል በተከፈሉ ዕቅዶች ነው ለማስኬድ የታሰበው፡፡ ገቢውንም መንግሥት በጀት በመያዝ በራሱ የተወሰነውን ወጪ እንደሚሸፍን ተገልጾ፣ አብዛኛውን ግን አጋር ድርጅቶችና ለጋሾች እንዲያግዙበት ነው ዕቅድ የተያዘው፡፡

በመጀመርየው ዓመት የቅድሚያ ማገገሚያ ጊዜያት ለይ 5.1 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የተገለጸ ሲሆን፣ ሰፋ ባለ ሁኔታ የማገገሚያ ፕሮግራም የሚካሄድበት በሁለተኛና ሦስተኛ ዓመት ደግሞ 9.8 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተብሏል፡፡ በመጨረሻ ደረጃ ላይ ለሚካሄደው ፕሮግራም 4.6 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ነው የዳሰሳ ጥናቱ የሚያስረዳው፡፡

አራት የሚሆኑ የፓናል ውይይቶች፣ እንዲሁም የጥያቄና መልስ ፕሮግራሞች የነበሩበት መርሐ ግብሩ፣ በተያዘላቸው ጊዜ የልማት አጋሮችና ጉዳት የደረሰባቸው ክልሎች ፕሬዚዳንቶችን ጨምሮ የመንግሥት አካላት አስተያየታቸውን ሰጥተው ነበር፡፡

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ አስተያየታቸውን ሲሰጡ፣ ከመልሶ ግንባታ በተለየ የአፋጣኝ ዕርዳታ ፍላጎት በክልላቸው ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሕፃናት ለአራት ዓመታት ትምህርት አልተማሩም›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ በምግብ ዕርዳታ ላይ ጥገኝነት የነበረው ማኅበረሰብ አሁን ዕርዳታው መቆሙም ያለውን ችግር ገልጸዋል፡፡

‹‹ትግራይ ከሌሎች በበለጠ በጦር የተጎዱ ሠራዊት ያለበት ነው፤›› ብለው በጦር ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር ከፍተኝነትን ሲገልጹ አቶ ጌታቸው፣ ‹‹በተለይ ሊድን የሚችል ትንሽ ቁስል በሕክምና ዕጦት አካለ ጎዶሎ እያደረጋቸው ነው፤›› ብለዋል፡፡

የአማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና የኦሮሚያ ክልሎች ፕሬዚዳንቶችም በክልላቸው የተከሰቱት ግጭቶች ያደረሱትን ጉዳት በዝርዝር ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች