Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየተወሰኑ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱን ወቅታዊ መግለጫ በመቃወም ዛሬ መግለጫ እንደሚሰጡ...

የተወሰኑ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱን ወቅታዊ መግለጫ በመቃወም ዛሬ መግለጫ እንደሚሰጡ ታወቀ

ቀን:

የአገሪቱ የሰላም ሁኔታ የከፋ ቀውስ ውስጥ መሆኑንና አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አስመልክቶ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የሰጠውን ጋዜጣዊ መግለጫ በመቃወም፣ የተወሰኑ ፖለቲካ ፓርቲዎች በዛሬው ዕለት መግለጫ እንደሚሰጡ ታወቀ፡፡

የምክር ቤቱ ሥራ አስፈጻሚዎች ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. በተካሄደ አስቸኳይ ስብሰባ፣ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጎ በጉባዔው ውሳኔ ተደርሶባቸዋል ባሏቸው ነጥቦች ላይ መግለጫ የሰጡት፣ ዓርብ ሰኔ 2 ቀን 2015 ዓ.ም.  ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የምክር ቤቱ ሥራ አስፈጻሚ የሰጠው ጋዜጣው መግለጫ መርህን ያልተከተለ ነው ያሉ 32 ፓርቲዎች መግለጫውን በመቃወም፣ ዛሬ ሰኔ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ ተቃውሞ ካላቸው ፓርቲዎች ውስጥ አንዱ የሆነው የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ አላምረው ይርዳው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ መግለጫውን የሚሰጡ ፓርቲዎችን ስም ዝርዝር ለመግለጽ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ የሰጠው መግለጫ፣ የምክር ቤቱ የአባላትን እምነት የሚሸረሽር መሆኑን፣ ምክር ቤቱ የተሰጠውን ኃላፊነት ባለመወጣት በፓርቲዎች መካከል አለመግባባትን የሚፈጥር፣ እንዲሁም ግንኙነቶችን የሚሸረሽር እንደሆነ አቶ አላምረው ተናግርዋል፡፡

ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. የጋራ ምክር ቤቱ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ፣ በሁለት አጀንዳዎች ላይ መነጋገሩን ያስታወሱት አቶ አላምረው፣ አንደኛው ጠቅላላ ጉባዔው ሳያውቅ ወደ ውጭ አገር ስለሄዱ ሥራ አስፈጻሚዎች ሲሆን፣ ሁለተኛው በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ነበር ብለዋል፡፡

በቅርቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ወደ ኔዘርላንድስ ለሥልጠና በተጋበዙበት ወቅት፣ የጋራ ምክር ቤቱ አባላት ሳያውቁ የሥራ አስፈጻሚ አባላት ፓርቲዎችን መልምለው መላካቸውን ገልጸዋል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ ፓርቲዎቹ የመረጧቸው ሥራ አስፈጻሚ አባላት መርህ አልባ ተግባር ላይ እየተሳተፉ ነው ሲሉ አቶ አላምረው ተናግረዋል፡፡

ግንቦት 24 ቀን በነበረው ጉባዔ በአገራዊ ጉዳይ ላይ ከቀረቡት አጀንዳዎች ውስጥ ሰላምና ፀጥታ በሚለው ላይ ሁሉም ፓርቲዎች በየአካባቢያቸው ያሉ ችግሮችን አንስተው እንደነበር፣ የጋራ ምክር ቤቱ ሥራ አስፈጻሚ የተነሱ ችግሮችን አደራጅቶ ረቂቅ መግለጫ በማውጣት የጋራ ምክር ቤቱ አባላት በሚጠቀሙበት የቴሌግራም አካውንት እንዲለቀቅና ውይይት ተደርጎበት በመጨረሻ ሥራ አስፈጻሚው መግለጫውን እንዲሰጥ ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ የጋራ ምክር ቤቱ ሥራ አስፈጻሚዎች ግንቦት 24 ቀን በተደረገው ውይይት መሠረት መግለጫ ባለመስጠታቸውና አካሄዱ ትክክል አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሥራ አስፈጻሚው ሥልጣኑን ተጠቅሞ የሚሰጠው መግለጫ ቢኖርም፣ መግለጫው ግን ፓርቲዎቹ በተስማሙበት ልክ ረቂቅ ተዘጋጅቶ በቴሌግራም ግሩፑ ባለመቅረቡ፣ የበርካታ ፓርቲዎች ጥያቄ በመግለጫው አልተካተተም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

አቶ አላምረው የምክር ቤቱን መግለጫ ተቃውመው ዛሬ መግለጫ ከሚሰጡት ፓርቲዎች ጋር ብልፅግና ፓርቲ ለመካተት ሊፈልግ ቢችልም፣ ገዥው ፓርቲ ጉዳዩን እንደ ፕሮፖጋንዳ ሊጠቀምበት ስለሚችል እንዲቀላቀለን አልፈለግንም ብለዋል፡፡

‹‹ገዥው ፓርቲ ጥሩ ሲሠራ መደገፍ፣ መጥፎ ሲሠራ ደግሞ መቃወም አለብን፤›› ያሉት አቶ አላምረው፣ ‹‹ገዥው ፓርቲን ፀረ አገር አድርገን ማየት የለብንም፤›› ብለዋል፡፡ ነገር ግን አገር እየመራ በመሆኑ ስህተቶችን እንዲያርም እንደሚጠይቁ ገልጸው፣ ብልፅግና ጥፋቱን እንዲያርም ሲነገረው አላርምም ካላለ በስተቀር አይሳሳትም ተብሎ አይታሰብም ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ሰብሳቢ መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) ጉዳዩን አስመልከተው ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ የተሰጠው መግለጫ በጠቅላላ ጉባዔ መሠረት ስምምነት የተደረሰበትን ነው ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ጥቂት የተገዙ ፓርቲዎች እንደዚህ ዓይነት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹የተነሳው መሠረተ ቢስ ክስ ነው፤›› የሚሉት መብራቱ (ዶ/ር)፣ ‹‹ፓርቲዎቹ 32 ናቸው የተባለውም ከሁለት ወይም ሦስት አይበልጡም፤›› ብለው፣ ‹‹እነዚህ ፓርቲዎቸ ለገዥው ፓርቲ የሚያጨበጭቡ ናቸው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ከጅምሩ ለጋራ ምክር ቤቱ መግለጫ ገዥው ፓርቲ ፍላጎት አልነበረውም ብለዋል፡፡     

ዋና ሰብሳቢው በጠቅላላ ጉባዔው ፓርቲዎች ካነሷቸው ነጥቦች መካከል አገው በአማራ ፋኖ ተጨፍጭፏል ተብሎ እንዲወጣ ፍላጎት ያላቸው ፓርቲዎች እንደነበሩ ጠቅሰው፣ ነገር ግን ምክር ቤቱ ፋኖ አገውንም ሆነ ቅማንትን ጨፍጭፏል የሚል ምርመራና ጥናት ያልተደረገበትና ያልተረጋገጠ መግለጫ አያወጣም ብለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አንድ ሕዝብ ሌላ ሕዝብ ጨፍጭፏል ተብሎ በምክር ቤቱ መግለጫ ሊወጣ አይችልም ሲሉም አክለዋል፡፡

ፓርቲዎቹ ተቃውመው መግለጫ መስጠታቸው መብታቸው ቢሆንም፣ መግለጫው በምክር ቤቱ ላይ የሚያመጣው የተለየ ጫና እንደሌለ መብራቱ (ዶ/ር) ተናገረዋል፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ ከ60 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአባልነት እንደሚሳተፉበት ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...