Sunday, October 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየጣሊያኑ ሲሊቪዮ ቤርሉስኮኒ (1936 - 2023)

የጣሊያኑ ሲሊቪዮ ቤርሉስኮኒ (1936 – 2023)

ቀን:

የጣሊያን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ በ86 ዓመታቸው መሞታቸው ተሰምቷል፡፡ እኝህ ሰው ለአራት የሥልጣን ዘመን የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል፡፡

የጣሊያንን ፖለቲካ በመድረክ እንደሚተመን ጥበብ አጣፍጠውታል የሚባሉትና በጣሊያውያኑ ዘንድ ኤልካቫሊ ሬ (ዘ ናይት) ወይም ጀብደኛ የሚባሉት ቤርሉስኮኒ፣ በፎርብስ ሜጋዚን የቢሊየነሮች ሰንጠረዥ ስድስት ቢሊዮን ዶላር በማካበት በ169ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ናቸው፡፡

በሕይወት ዘመናቸው ለኢትዮጵያ ካደረጉት ደግሞ የአክሱም ሐውልት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ማስወሰናቸውና መተግበራቸው የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል፡፡

ኢትዮጵያን በ1928 ዓ.ም. የወረረው የቤኒቶ ሞሶሎኒ መንግሥት፣ በዓመቱ ከኢትዮጵያ ከዘረፋቸው ቅርሶች መካከል 24 ሜትር የሚረዝመው የአክሱም ሐውልት የሚገኝ ሲሆን፣ ሐውልቱም በጣሊያን ሮም ከተማ ለ63 ዓመታት ያህል ተተክሎ ቆይቷል፡፡

ሐውልቱን ለማስመለስ በኢትዮጵያ የነበሩ መንግሥታት ተደጋጋሚ ጥያቄ ማንሳታቸውም ይታወሳል፡፡ በጣሊያን በኩል ከቤርሉስኮኒ በፊት የነበሩ የተለያዩ መሪዎች ሐውልቱን ለመመለስ ቃል ቢገቡም፣ ተግባራዊ ያደረጉት ግን እኝህ ሰው ናቸው፡፡

ቤርሉስኮኒ የአክሱም ሐውልት እንዲመለስ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ኢትዮጵያ ከመላኩ በፊት ዕድሳት እንዲደረግለትም በካቢኔያቸው ያስወሰኑ ነበሩ፡፡

እ.ኤ.አ. በ1936 በጣሊያን ሚላን የተወለዱት ቤርሉስኮኒ፣ በፖለቲካው ዓለም  የአውሮፓን ፖለቲካ ለሁለት ከፍለዋል ከሚባሉባቸው አንዱ ፖፒሊስት (ሕዝበኛ) መሆናቸው ነው፡፡

ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወዲህ ጣሊያንን ዙር ለረዥም ዓመታት ያገለገሉት ቤርሉስኮኒ፣ በቆነጃጅት ሚስቶቻቸውና በሴት ጓደኞቻቸው የሚታወቁ ነበሩ፡፡

የጣሊያን መከላከያ ሚኒስትር ‹‹ቤርሉስኮኒ ራሱን እንደ ጥሩ ወይን አድርጎ መቁጠር ይወዳል፤›› ሲሉ የሚገልጻቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በፆታዊ ቅሌትና በሙስና ጉዳዮች በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት ቀርበው የተከራከሩም ናቸው፡፡

በጣሊያን ሚዲያ ዘርፍ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸውና በስፖርቱም የሚታወቁት እኝህ ሰው፣ በተለይ ሚዲያውን በሀብት በመቆጣጠር የፈጠሩት ተፅዕኖም ቀላል አልነበረም፡፡

በጣሊያን ፖለቲካ ብቻም ሳይሆን በስፖርቱ ዘርፍ ይታወቃሉ፡፡ የኤሲሚላን የቀድሞ የበላይ ኃላፊ ሆነውም አገልግለዋል፡፡

ቢሊየነሩ ቤርሉስኮኒ፣ በጠቅላይ ሚኒስትርነት እስካገለገሉበት 2011 ድረስ፣ በጣሊያን ታሪክ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ መሪዎች እንደሚመደቡ ጣሊያንን ከ2022 ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትርነት እየመሩ የሚገኙት ሚስ ጆርጅያ ሚሎኒ ገልጸዋል፡፡

በ1970ዎቹና 80ዎቹ በሪልስቴት፣ በእግር ኳስና በቴሌቪዥን ዘርፍ በመግባት ራሳቸውን ካስተዋወቁ በኋላ ወደ ፖለቲካው የተቀላቀሉት እኝህ ሰው፣ ከፓርቲያቸው ‹ሴንተር ራይት ፎርዛ ኢታሊያ› ጋር በተያያዘና በሌሎችም ክስ ተመሥርቶባቸው በነፃ የተለቀቁባቸውና በዕግድ የቆዩባቸው ጊዜያት ነበሩ፡፡

ሮይተርስ እንደሚለው ደግሞ፣ በአንድ የክስ ሒደት ላይ እያሉ ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት፡፡

በጣሊያን ፖለቲካ ውስጥ ለሃያ ዓመታት ያህል ያገለገሉት ቤርሉስኮኒ፣ በአከራካሪና በአወዛጋቢ ፖለቲካቸው የታወቁ፣ በሕዝብ ዘንድ ደግሞ ተወዳጅነትን ያተረፉ ነበሩ፡፡

በአገራቸውና በውጭ ዓለም ሚዲያ የሚታወቁ፣ በተለይ ደግሞ ከሩሲያ ጋር በነበራቸው ወዳጅነት የሚነሱም ናቸው፡፡

የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ‹‹እውነተኛ ወዳጅ›› የሚሏቸው ቤርሉስኮኒ፣ በሩሲያና ዩክሬን መካከል በተቀሰቀሰው ጦርነት ከምዕራባውያኑ በተቃራኒ ከሩሲያ ጎን የቆሙ ነበሩ፡፡

የጣሊያንን የፖለቲካ ባህል እንደቀየሩም ይነገርላቸዋል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ጣሊያንን ባሽመደመደበት ወቅት በቫይረሱ ከተያዙ ዜጎች አንዱ ሲሆኑ፣ የፕሮስቴት ካንሰር፣ የልብ ሕመም እንዲሁም የደም ካንሰር ታማሚ እንደነበሩም ሮይተርስ አስፍሯል፡፡

ቤርሉስኮኒ ሁለት ሚስቶችን የፈቱ ሲሆን፣ እስካረፉበት ጊዜ ድረስ ከ33 ዓመቷ ‹‹ሚስታቸው›› ጋር ይኖሩ ነበር፡፡ አምስት ልጆች፣ ከአሥር በላይ የልጅ ልጆችና አንድ የልጅ ልጅ ልጅ ነበራቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...