Friday, July 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የወጪ ንግድ ምርቶች በከፍተኛ ዋጋ እየተገዙ ለዶላር ሲባል ከዋጋ በታች ኤክስፖርት እየተደረጉ መሆኑ ተጠቆመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ አሁንም ከችግር የተላቀቀ አይደለም፡፡ ቀጣይነት ያለው ዕድገት እያሳየ አለመሆኑም በግልጽ እየታየ ነው፡፡ በየበጀት ዓመቱ በዕቅድ የተቀመጠውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማግኘት እየተቻለ አይደለም፡፡ በ2014 የበጀት ዓመት አገሪቱ ከፍተኛ የሚባለውን የውጭ ምንዛሪ ያገኘችበት ወቅት ተደርጎ ብዙ የተባለለት ቢሆንም፣ ዘንድሮ ግን የዓምናውን ያህል ዕድገት ያስገኛል ተብሎ አይጠበቅም፡፡

የ2015 የዘጠኝ ወራት የወጪ ንግድ አፈጻጸም የሚያመለክተውም ይህንኑ ነው፡፡ በዘጠኝ ወር ከአጠቃላይ የወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ 2.6 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡ በበጀት ዓመቱ በዘጠኝ ወራት ለማግኘት ታቅዶ የነበረው ግን 3.72 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ይህም የዘጠኝ ወሩ አፈጻጸሙ 71 በመቶ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን፣ ከዕቅዱ አንፃር ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ዝቅ ያለ አፈጻጸም መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡

የአገሪቱን የወጪ ንግድ አፈጻጻም ላይ ለሚታየው ጉድለት የተለያየ ምክንያት የሚሰጥ ቢሆንም፣ በዘርፉ ከሚታዩ በርካታ ችግሮች ውስጥ አሁን ላይ እጅግ አሳሳቢ ነው ተብሎ የሚጠቀሰው አገሪቱ የወጪ ንግድ ምርቷን በኪሳራ እየሸጠች ነው የሚለው በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ 

የኢትዮጵያ ላኪዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤዳኦ አብዲ እንደሚገልጹትም፣ የአገሪቱ የወጪ ንግድ ምርት በኪሳራ እየተሸጠ ነው በሚለው ጉዳይ ላይ ይስማማሉ፡፡ 

አንድን የወጪ ንግድ ምርት ከዓለም አቀፍ ዋጋው በላይ ከአገር ውስጥ በመግዛት ለውጭ ገበያ ማቅረብ በኪሳራ እየሸጡ መቀጠል እያስከተለ ያለው ችግር የአገሪቱን የወጪ ንግድ ከመጉዳቱም በላይ ለዋጋ ንረትም ምክንያት እየሆነ መጥቷል የሚል እምነት አላቸው፡፡ 

ይህንንም በምሳሌ ሲያስረዱም በአሁኑ ወቅት በዓለም ገበያ አንድ ቶን ሰሊጥ የሚሸጥበት ዋጋ 1,900 ዶላር ወይም በኩንታል 190 ዶላር ነው፡፡ ይህ አሁን ባለው የባንኮች የምንዛሪ ዋጋ አንድ ኩንታል ሰሊጥ 10,300 ብር አካባቢ እንደማለት ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ውጭ ገበያ መቅረብ ያለበት ሰሊጥ ከአገር ውስጥ ገበያ ሲገዛ ከ10,300 ብር ባነሰ ዋጋ መገዛት እንደነበረበት የሚያመለክት ነው፡፡ አሁን የሚታየው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው፡፡ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ምርት ገበያ አንዱ ኩንታል ሰሊጥ በጨረታ የሚሸጥበት ዋጋ ግን 13 ሺሕ ብር መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይህም ማለት አንድ ላኪ በ13 ሺሕ ብር የገዛውን ሰሊጥ ለውጭ ገበያ እየሸጠ ያለው በ10,300 ብር ወይም በ190 ዶላር ነው የሚሉት አቶ ኤዳኦ፣ ላኪዎች ምርቱን የሚልኩት በኪሳራ እንደሆነ ያስረዳሉ። እንዲህ ያለው ጉዳይ በሰሊጥ ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የወጪ ንግድ ምርቶች ላይ እየታየ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ኤዳኦ፣ አገሪቱ ከወጪ ንግድ ገቢ ዋጋ እንዲህ እያከሰረች መቀጠልዋ አደጋ መሆኑን ይጠቀማሉ፡፡  

‹‹በዓለም ደረጃ ተፈላጊ የሆነ የሑመራ ሰሊጥ እያመረትን በኪሳራ የምንሸጥ አገር እኛ ነን፤›› ያሉት አቶ ኤዳኦ፣ ይህ አካሄድ አደገኛ እየሆነ መምጣቱንም አመልክተዋል፡፡ ለምሳሌ ሰሊጥ በቶን ከ200 እስከ 300 ዶላር ኪሳራ ለዓለም ገበያ እየቀረበ በቂ የውጭ ምንዛሪ እየተገኘበት አለመሆኑ የሚያሳዝን ነው ይላሉ፡፡ 

‹‹የኢትዮጵያ ባንኮች አሁን በአብዛኛው እያበደሩ ያሉት ለኤክስፖርት ዘርፍ ሆኖ እንኳን ኤክስፖርቱ ከኪሳራ መውጣት አልቻለም፤›› የሚሉት አቶ ኤዳኦ፣ አሁንም ይህ ዘርፍ በትክክለኛው የቢዝነስ ሕግጋት እንዲመራ ካልተደረገ ችግሩ ሊቀጥል ይችላል የሚል ሥጋት አላቸው፡፡ ላኪዎች ኪሳራ በጻፉ ቁጥርም መጨረሻ ላይ ችግሩ የሁሉም ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡  

እንደ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፣ የወጪ ንግድ ምርቶች ሊያገኙ ከሚገባው ዋጋ በታች የሚሸጡበት ዋና ምክንያት ደግሞ የወጪ ንግዱ ዶላር ማስገኛ ተደርጎ በመወሰዱ ነው ብለዋል፡፡ ብዙዎች የወጪ ንግዱን የመረጡት ከወጪ ንግዱ በቀጥታ አትራፊ እንሆናለን ብለው ሳይሆን፣ በኪሳራም ቢሆን ምርቱን ልከው የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሪ ሌሎች ምርቶችን በማስገባት ለማካካስ ስለሚጠቀሙበት መሆኑን አቶ ኤዳኦ አስረድተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ትክክኛ የሆነ የቢዝነስ አሠራር ባለመሆኑ ኤክስፖርትና በኪሳራ የሚሠራ ቢዝነስ እየሆነ መምጣቱን ይጠቅሳሉ፡፡ ቡና፣ ሰሊጥ፣ ቅመማ ቅመም፣ ቦሎቄና የመሳሰሉት የወጪ ንግድ ምርቶች ከዋጋ በታች የሚሸጡበት፣ በአንፃሩ ደግሞ የአገር ውስጥ ዋጋቸው ከፍተኛ የሆነበት ምክንያት ዶላር ለማግኘት የሚደረግ ጥረት በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡  

ለውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ተብሎ ወደ ኤክስፖርት ንግድ እየተገባ መሆኑ ደግሞ ከዓለም ጋር ተወዳድሮ የመሸጥ ያለውን አቅም እየተገዳደረው እንደሚገኝም ያመለክታሉ፡፡ ለውጭ ገበያ በጥሩ ዋጋ ልንሸጣቸው የሚችሉ ምርቶቻችንን ከዋጋ በታች እየተሸጡ መቀጠሉ በልዩ ትኩረት ሊሠራበት ባለመቻሉም ችግሩ ጎልቶ እንዲወጣ እንዳደረገው ከአቶ ኤዳኦ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በተለይ ነጋዴው እየከሰረ በመሸጥ ዘርፉን የውጭ ምንዛሪ ማግኛው ማድረጉ በሰሊጥ ከስሮ ሌላ ምርት አምጥቶበት በማትረፍ ላይ የተመሠረተው አካሄድ ትክክለኛ የቢዝነስ መንገድ ባለመሆኑም መለወጥ እንደሚኖርበት አምኖ በዚህ ረገድ ሊሠራ እንደሚገባ አቶ ኤዳኦ ያምናሉ፡፡ 

በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ችግር በተለይም ማደግ ያለበትን ያህል አለማደጉና እየቀነሰ መጥቷል፡፡ አንዱ ምክንያት ይኼው እየከሰሩ የመሸጥ ልምዱ ማደጉ ሲሆን፣ ሌለው እንደ መሠረታዊ ችግር ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ኢትዮጵያ የኤክስፖርት ስትራቴጂ ዶክመንት የሌላት መሆኑ ነው፡፡ ይህም ባይኖር እንኳን ዘርፉ ይህንን ዘርፍ የሚመራ ትክክለኛ ተቋማትን መለየት ያስፈልገው ነበርም ይላሉ፡፡ የባለቤትነት ችግርም የዚህ ዘርፍ አንድ ማነቆ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ የኤክስፖርቱ ችግር ምንድነው? ተብሎ መንግሥት ራሱ ከኤክስፖርተሮች ጋር ቆም ብሎ ያለ መወያየቱም ሌላው የዘርፉ ችግር ነው ብለዋል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት የወጪ ንግድ እየቀነሰ መምጣቱና በኪሳራ እየተሸጠ መሆኑ ከታወቀ እንደ ማኅበር ምን እያደረጋችሁ ነው ለሚለው ጥያቄ አቶ ኤዳኦ፣ አብዛኛውን ጊዜ ማኅበራት ግንዛቤ መስጠት የገበያ ስፔስኩሌሽን በሚኖርበት ጊዜ የገበያ መረጃ መስጠት ጥንቃቄ አድርገው ንግዳቸውን እንዲያካሂዱ ማድረግ እንጂ፣ ከዚህ የዘለለ ሥራ ብዙ የሌላቸው መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ጠንካራ የንግድ ኅብረተሰብና ማኅበር የሚያሻ መሆኑን ግን ያምናሉ፡፡ በሌሎች እንዳሉ ማኅበራት መጠንከር የሚያስገኘው ውጤት ከፍተኛ ይሆን ብለው የወጪ ንግዱን በተመለከተ ግን እየሠራን ያለነው ሥራ አለ ብለዋል፡፡  

የኬንያ መንግሥት ከኢትዮጵያ መግዛት ፈለገና መንግሥት ላኩ ብሎ መረጠን፡፡ የኬንያ ነጋዴዎች ግን እኛ ንግድ ፈቃድ ያወጣነው ልንነግድ ነው እንጂ አንተ እንድትነግዱ አይደለም ብለው ፍርድ ቤት ከሰውት አሳገዱት፡፡ ይህ የነጋዴውን ፍላጎት ስለነካ መንግሥት ተጠያቂ የሚሆንበት አሠራር አለ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለ ተፅዕኖ ማድረግ የሚችል አቅም ያለው ማኅበር ኢትዮጵያ ውስጥ ያለመኖሩ አንድ ክፍተት መሆኑን ያሳያል፡፡ 

‹‹እንዲህ ያለው ልምድ የሚመጣው ማኅበራት ሲጠነክሩ ነው፤›› ያሉት አቶ ኤዳኦ፣ የመንግሥት የወጪ ንግድ ሕጎች ያለው ግንኙነት ጠንካራ እየሆነ ሲሄድ መስተካከል ይችላል፡፡ አሁን ባለው ደረጃ ግን የማኅበራቸው አቅም ውስን ነው ይላሉ፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከወጪ ንግድ ጋር ያሉ ችግሮች ለአንድ ወገን የሚተው ያለመሆኑንም አስረድተዋል፡፡ በንግዱ ኅብረተሰብ በኩል ያለም ችግር ከፍተኛ ሊባል የሚችል መሆኑን የጠቀሱት አቶ ኤዳኦ፣ ለምሳሌ ለቻይና አኩሪ አተር ለመላክ የአንድ ሚሊዮን ኮንትራት እንፈርምና ዲፎልት ሲደረግ ዕርምጃ አይወሰድም፡፡ ይህ ነጋዴ የአገርን ገጽታ ለምን የሚያጠለሽ ይሆናል? የሁለቱን አገሮች የንግድ ግንኙነት የሚያበላሽ ለምን ይሆናል? ነጋዴዎችን በከፍተኛ ደረጃ ዲፎልት ያደርጋሉ? ብሎ ተከታትሎ ዕርምጃ መውሰድንም ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ነው አብዛኛው የእስያ ገበያ ኢትዮጵውያን ዲፎልተርስ ብለው ጥራጥሬ ምርቶቻቸውን ላለመግዛት በመወሰን ፊታቸውን ወደ ታንዛንያና ወደ ኡጋንዳ  እየሄዱ ለመሆኑ አንዱ ምክንያት የኮንትራት ውሎች ላይና እያጋጠሙ ባሉ ችግሮች በመሆኑ የወጪ ንግድን እናሳድግ ከተባለ እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን መመልከት ግድ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ከፍተኛ ውድድር ያለ በመሆኑ ነዳጅ የሌላቸው አገሮች መሬታቸውን በእርሻ ትራንስፎም እያደረጉ የህንድና የቻይና ገበያዎች እያጥለቀለቁት ነው፡፡ ኢትዮጵያም ያላትን የወጪ ንግድ ምርቶች በአግባቡና በተሻለ ዋጋ ለመሸጥና የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ተናብቦ መሥራት የግድ መሆኑንም ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡ 

የወጪ ንግድን ለማሳደግ በዓለም ላይ የተለያዩ ሥራዎች የሚሠሩ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ኤዳኦ፣ በቅርቡ በአውስትራሊያና በህንድ መካከል የተደረሰውን ስምምነት በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ መንግሥት፣ ለመንግሥት ተነጋግረው የተመረተውን ከፍተኛ ምርት ህንድ እንድትረከብ እስከመነጋገር መድረሳቸው የሚያመለክተው የወጪን ንግድን ለማሳደግ እንዲህ ያሉ ሥራዎች መሠራት ያለባቸው ጭምር መሆኑን ነው ይላሉ፡፡  

ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ ደግሞ የሰሊጥ ምርት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ነው፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት የነበረ ምርት ዛሬ የለም፡፡ ምርት እያሽቆለቆለ እየመጣ ነው፡፡ ለምን ተብሎ ኢንተርቬሸን አይደረግም፡፡ ትልቅ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ እንደመሆኑ መጠን ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ በመሆኑ አንፃር ችግሩ አውቆ መፍትሔ ማስቀመጥ ተገቢ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ 

ከዚህ አንፃር ሌላው ሊጠቀስ የሚችለው ጫት ነው፡፡ ዛሬ ወደ ሶማና ሶማሌላንድ የሚላከው ጫት ቆሟል፡፡ ይህ ሲቆም ለምን ቆመ ተብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ እንዴት ይቆማል ችግሩ ለምን ተፈጠረ ተብሎ የልዑካን ቡድን ሁሉ መላክ ነበረበት፡፡ እንዲህ ያሉ ክፍተቶች የወጪ ንግዱ ላይ ተፅዕኖ እያሳረፉ ነው፡፡ 

በኪሳራ ከመሸጥ ጋር ተያይዞ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ቁጥጥር ማድረግ አይገባውም ወይ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ኤዳኦ፣ መንግሥት ከዓለም አቀፍ ዋጋ በታች እንዳይሸጥ የዋጋ ቦርድ አውጥቶ ይሠራል፡፡ ከዓለም አቀፍ ዋጋ በላይ ተገዝቶ የሚሸጥበት ሁኔታ ላይ ግን አሁንም ብዙ ሥራ ሊሠራበት የሚገባ ነው ይላሉ፡፡ መንግሥት ይህንን ማድረግ የሚቻልበት ዕድል እንዳለ ግን ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡፡ የዋጋ ቦርዱም የተቋቋመው ካፒታል ፍላይቱን ለማስቀረት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ስኬታማ ሥራ ተሠርቷል ብለው ያምናሉ፡፡ 

ከዚህ ቀደም የዋጋ ቦርድ አልነበረም፡፡ የመሸጫ ዋጋ ጣሪያ የማይቀመስ ስለነበር ችግር ፈጥሯል፡፡ የዋጋ ቦርድ የወጣው በምክንያት ነው፡፡ ለምሳሌ 1,700 ዶላር መሸጥ የነበረበትን ሰሊጥ 1,500 ዶላር እየተሸጠ መሆኑ ሲታወቅና በዚህ ምክንያት ካፒታል ፍላይት የበዛ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የተወሰነ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ከምርቶች ማግኘት የሚገባውን ገቢ እንዳያጣ የኮንትራት አስተዳደር በማዋቀር የወጪ ንግድ ኮንትራቶች ይመዘገባል፡፡ ኮንትራቶቹ በግልጽ ሲስተም ላይ ተመዝግበው ቁጥጥር እየተደረገባቸው ማኔጅ ማድረግ ተቻለ፡፡ ቦርዱ ከግል ዘርፍና ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ ከምርት ገበያ፣ ከጉምሩክና የመሳሰሉት ባለድርሻ አካላትን የየዘ ነው፡፡ እነዚህ ባለድርሻ አካላት ዓለም አቀፍ የገበያ ሁኔታን በአካባቢው ያለውንም ገበያ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውንም የአቅርቦትና የሽያጭ ሁኔታ ይመለክቱና ዋጋ ሴት ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ነጋዴ በዚህ ዋጋ እንዲያወጣ ይገደዳል፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር ካፒታል ፍላይት እንዳይኖር ያገዘ ቢሆንም፣ ከዋጋ በላይ ተገዝቶ ወደ ውጭ የሚላከውን የሚመለከት እንዳልሆነ አቶ ኤዳኦ ያስረዳሉ፡፡ 

አንድ ነጋዴ የዓለም ዋጋ 10,300 ብር የሆነን ሰሊጥ በ13 ሺሕ ብር እየገዛ ከሰሮ እየሸጠ ለመሆኑ የመንግሥት ቁጥጥር ማነስ ብቻ የፈጠረው ያለመሆኑን ግን አቶ ኤዳኦ ይስማሙበታል፡፡ ትልቁ ችግር ያለው በዚህ ዋጋ እየገባ ዶላር ለማግኘት እየጣረ ያለው ላኪ ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ የሰሊጥን ዋጋ ማውረድ እየተቻለ ላለመውረዱ አንዱ ምክንያት ይኼው ዶላር የማግኘት አባዜ ያመጣው ጣጣ ነው፡፡ 

‹‹መንግሥት ሁል ጊዜ የሬጉላቶሪ ሥራ ነው የሚሠራው፡፡ ነጋዴ ደግሞ በተመሳሳይ የራሱን ወጪዎች ጌሩሌት ማድረግ አለበት፡፡ ይህንን አያደርግም ምክንያም ይህንን ኪሳራ 20 በመቶ በሚያገኘውን የውጭ ምንዛሪ ያጣጣል፤›› ያሉት አቶ ኤዳኦ፣ መንግሥት ግን የኪሳራ የወጪ ንግድን ላለማስቀረት ማስገደድ ይችላል ይላሉ፡፡ አሁን ባለው አካሄድ ብዙ ላኪዎች ከወጪ ንግድ ኪሳራ እየጻፉ ነው፡፡ ከባንክ በተበደረው ገንዘብ የገጠመው ኪሳራ ነው፡፡ ኤክስፖርተሩ እንዲህ በኪሳራ የሚሠራ ከሆነ አካሄዱ ጥሩ አይሆንም፡፡ እንዲህ ያለው ችግር መዘዙ ብዙ መሆኑን የሚጠቅሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ በኪሳራ የሚላክ ምርት ከባንክ የተገኘ ብድር ለመመለስም አደጋ ይሆናል፡፡ አብዛኛዎቹ ብድሮች እየተከፈሉ ላለመሆናቸው አንዱ ምክንያት በቀጥታ የወጪ ንግዱ ትርፍ እየተገኘበት ባለመሆኑ ነው፡፡ በተለይ ኢክስፖርተሮች ለቅድመ ጭነት ብለው የወሰዱት ገንዘብ እየተከፈለ አይደለም፡፡ የተበላሸ ብድር ውስጥ እንዳይገባ ተብሎ ወለዱ ብቻ እየተከፈለ መሆኑ አንድ ማሳያ ነው ይላሉ፡፡ ሌሎች አስተያየት የሰጡን የዘርፉ ተዋንያኖች በበኩላቸው፣ በኪሳራ የሚደረግ የወጪ ንግድ እንዲሰፋ ያደረገው ከምርት ገበያው ውጪ የሚደረጉ ግብይቶች በመስፋፋታቸው ነው ይላሉ፡፡ በተለይ በቡና አካባቢ ይህ ጎልቶ የሚታይ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡  

ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ደግሞ፣ ከዋጋ በላይ ግብይት እንደማይካሄድ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የወጣ ደንብ ስላለ በምርት ገበያው ውስጥ የዓለም ዋጋ 10 ሺሕ ብር ሆኖ 13 ሺሕ ብር ሊገበያይ የማይችል መሆኑን ነው፡፡ ለዚህም ደንብ ወጥቶ እየተሠራበት በመሆኑ በምርት ገበያው እንዲህ ያለ ሁኔታ እንደሌለ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ግን እንዲህ ያሉ ችግሮች ይታዩ ስለነበር የደንቡ መውጣት ይህንን አስቀርቷል፡፡

የሰርቪላንስ መቆጣጠሪያ ስላለም ከዋጋ በላይ ግብይት እንዳይፈጸም ስለሚያግዝ በምርት ገበያው በዚህ ደንብ መሠረት እየሠራ መሆኑን አመልክቷል፡፡ 

ነገር ግን ከምርት ገበያው ውጪ የሚፈጸም ግብይት ስላለ በዚያ በኩል ያለ ችግር ሊሆን እንደሚችልበት ዕድል ስለመኖሩ ግን ይኼው የምርት ገበያው መረጃ ያመለክታል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው አንዳንድ ተዋናዮች ደግሞ በኮንትራት ፋርሚንግ የሚደረግ ግብይት ለምርት ገበያው በኩል የሚያልፍ ባለመሆኑ በኮንትራት ፋርሚንግ አስመርተው ምርት እጃቸው ያሉ ሰዎች ከአቅም በላይ ዋጋ ሰጥተው ካስመረቱ በኋላ ከዓለም ገበያ የበለጠ ዋጋ ሆኖባቸው ችግሩ ሊያጋጥም ይችላል ይላሉ፡፡ 

ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው ቡና ነው፡፡ ቨርቲካል ኢንተግሬሽን አሠራር ይተግበር ተበሎ በምርት ገበያው ከሚገበያይበት ዋጋ በላይ እየተገበያየ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ከዋጋ በላይ እየተደረገ ያለው ግብይትና በኪሳራ ምርትን መሸጥ ጎልቶ የሚታየው በኮንትራት ፋርሚንግ በኩል እየተደረገ ያለው አሠራር ሊሆን እንደሚችል የሚጠቅሱም አሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያረግነው ሙከራ ባይሳካም፣ ሚኒስትሩ ከዋጋ በላይ የሚደረጉ ግብይቶችን የሚቆጣጠርበትን አሠራር ስለመዘርጋቱ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሆኖም ከአሁንም በኪሳራ የሚዳረጉ የወጪ ንግዶች በስፋት እየታዩ ነው፡፡  

እንደ አቶ ኤዳኦ ገለጻ ከሆነ ደግሞ እንዲህ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ማኅበራቸው ጥናት በማስጠናት ለመንግሥት ለማቅረብ የባለሙያ ቅጥር ፈጽመዋል፡፡ በዚህ  ጥናት ያሉ ችግሮችን በመለየት በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥናቱን በማጠናቀቅ ለመንግሥት በማቅረብ መፍትሔ እንዲኖረው ይደረጋል የሚል እምነታቸውንም አንፀባርቀዋል፡፡ 

 

   

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች