Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበታራሚዎች ላይ የሚፈጸም ድብደባ በሕገ መንግሥቱ መሠረት መታረም እንዳለበት ኢሰመኮ አሳሰበ

በታራሚዎች ላይ የሚፈጸም ድብደባ በሕገ መንግሥቱ መሠረት መታረም እንዳለበት ኢሰመኮ አሳሰበ

ቀን:

መንግሥት በታራሚዎች ላይ የሚፈጸም ድብደባን በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሊያርም እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ፡፡

ኮሚሽኑ ይህን መሳሰቢያ የሰጠው፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙ አሶሳና መተከል ዞን ማረሚያ ቤቶች በ2015 ዓ.ም. የሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ሁኔታን በተመለከተ አደረኩት ባለው የክትትል ግኝቶችና በተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ዙሪያ፣ በባምባሲ ከተማ ሰኔ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ከሚመለከታው አካላት ጋር አደረኩት ያለውን ውይይት አስመልክቶ ዓርብ ሰኔ 9 ቀን 2015 ይፋ ባደረገው መረጃ ነው፡፡

በክትትሉ በተለይ አንድ ታራሚ ላይ በካቴና በማሰር ድብደባ እንደተፈጸመ ማረጋገጡን የገለጸው ኢሰመኮ፣ በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶችም ሆነ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሠረት ኢሰብዓዊ አያያዝና ፈጽሞ የተከለከሉ ድርጊቶች በመሆናቸው ሊታረሙ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

የኢሰመኮ የክትትል ሪፖርት የሚያስረዳው፣ በአሶሳ ዞን ማረሚያ ቤት ጭካኔ ከተመላበት፣ ኢሰብዓዊና አዋራጅ ከሆነ አያያዝና ቅጣት የመጠበቅ መብትን በተጻረረ መልኩ አንድን ታራሚ በካቴና አስሮ የማቆየት ቅጣት እንደተወሰደ፣ አልፎ አልፎ በታራሚዎች ላይ በማረሚያ ፖሊስ አባላት የሚፈጸም ድብደባና ማሸማቀቅ መኖሩንና አሳሳቢ ጉዳይ ተብለው መጠቀሳቸውን ነው፡፡

ከመሠረታዊ ፍላጎት አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ በመተከልና አሶሳ ዞን ማረሚያ ቤት የታራሚ ክፍሎች ጥበትና ከፍተኛ የሆነ የንጽህና ጉድለት መስተዋሉን፣ የመኝታ አልጋና ፍራሽ አቅርቦት እጥረት መኖሩን፣ ከሕክምና አገልግሎት የመድኃኒትና ላብራቶሪ እጥረቶች በመኖራቸው የማስተካከያ ዕርምጃ እንደሚያስፈልግ በክትትሉ ተለይወተው ለውይይት መቅረባቸውን፣ በጊዜ ቀጠሮ ላይ በማረሚያ ቤት የሚገኙ ዜጎች የተፋጠነ ፍትሕ እያገኙ አለመሆናቸው በክትትሉ ተለይተው ለውይይት ቀርበዋል ተብሏል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የእምነት ነፃነት፣ የፆታ እኩልነት በማረሚያ ቤቶቹ የተደራጀና ወጥ የሆነ የቅሬታ ማቅረቢያ ሥርዓት አለመዘርጋት ጋር የተያያዙ ችግሮች ቀርበው ውይይት እንደተደረገባቸው ኢሰመኮ በሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡

የውይይቱ መድረኩ ተሳታፊዎች በማረሚያ ቤቶቹ የሚስተዋሉ ችግሮች በመሠረታዊነት ከበጀት እጥረት ጋር የተያያዙ እንደሆኑ፣ የክልል ፍትሕ ቢሮ በበኩሉ ኮሚሽኑ ባካሄደው ክትትል ተለይተው ቀረቡ የተባሉት ግኝቶች የክልሉን ማረሚያ ቤቶች ነባራዊ ሁኔታ የሚያመለክቱ መሆናቸውን ገልጸዋል ተብሏል፡፡

‹‹ፖሊሲ አውጭዎችና የፍትሕ አካላት በፍርድ ቤት ጥፋተኛ የተባሉ ታራሚዎችና ከእስር ይልቅ የማኅበረሰብ አገልግሎቶችን ጨምሮ አማራጭ የቅጣት ፖሊሲ በመተግበርና አማራጭ የግጭት መፍቻ ዘዴዎችን በመጠቀም በአጠቃላይ በፍትሕ ሥርዓቱ በተለይ በማረሚያ ቤቶች የሚስተዋለውን ጫና መቀነስ ይቻላል፤›› ሲሉ የኢሰመኮ የሰብዓዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል የክልል ዳይሬክተር ዓለሙ ምሕረቱ (ዶ/ር) በውይይቱ ማጠቃለያ መናገራቸው ተጠቅሷል፡፡

በሪፖርቱ በአሶሳ ዞን ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር መምሪያ የታራሚዎች ማረፊያ ክፍል ጥበትን ለመቀነስ የሚያስችል የማስፋፊያ ግንባታ መጀመሩ፣ ታራሚዎች የተለያዩ የእጅ ሙያዎችን እንዲለምዱና ከማኅበረሰቡ ጋር ሲቀላቀሉ ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያግዛቸው የብረትና የእንጨት ሥራ እንዲሠሩ መደረጉ፣ በማረፊያ ክፍሎች ተጨማሪ አልጋና ፍራሽ መግባቱ፣ አዲስ የዳቦ መጋገሪያ ማሽን መተከሉና የታራሚዎች ምግብ ዝግጅት ላይ ለሚቀርብ ቅሬታ ባለሙያዎች እንዲመደቡ መደረጉ በማረሚያ ቤቱ የተስተዋሉ አዎንታዊ መሻሻሎች መሆናቸውን ኢሰመኮ አስታውቋል፡፡

በውይይቱ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኮሚሽነርና የፍትሕ ቢሮ ኃላፊን ጨምሮ ከምክር ቤት፣ ከሕዝብ ዕንባ ጠባቂ አሶሳ ጽሕፈት ቤት፣ ከአሶሳ ዞን ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር፣ ከመተከል ዞን ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር መምሪያ የተውጣጡ ተወካዮችና ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል ኃላፊዎች መሳተፋቸው በሪፖርቱ ተካቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...