የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) መንግሥታዊ ተቋማት ሰብዓዊ ዕርዳታዎችንና ድጋፎችን የዜጎችን ነፃነት በሚነጥቅ ሁኔታ ለገዥው ፓርቲ የፖለቲካ ትርፍ ማስገኛ አድርገው እየተጠቀሙበት ነው ሲል ከሰሰ፡፡
ፓርቲው ይህንን ያለው ሰኔ 9 ቀን 2015 ዓ.ም.፣ ‹‹መንግሥት ከታረዙ ዜጎች ጉሮሮ የሚነጥቀው ሰብዓዊ ዕርዳታ አገራችን ያለችበትን የከፋ የሌብነት፣ ሙስናና ኢሰብዓዊነት ደረጃ የሚያሳይ ነው፤›› በሚል ርዕሰ ባወጣው መግለጫ ላይ ነው፡፡
‹‹በተደጋጋሚ እንደታዘብነው መንግሥታዊ ተቋማት ሰብዓዊ ዕርዳታዎችንና ድጋፎችን ዕርዳታ የሚደርሳቸውን ዜጎች ነፃነት በሚነጥቅ ሁኔታ ለገዥው ፓርቲ የፖለቲካ ትርፍ ማስገኛ አድርገው ይጠቀሙበታል፤›› ያለው ኢዜማ፣ ‹‹ለዚህም ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ብልፅግና ፓርቲ ከኢሕአዴግ በወረሰው መጥፎ ፀባይ ባለፈው አገራዊ ምርጫ ‹‹ብልፅግናን ካልመረጣችሁ የሴፍቲኔት ድጋፉን እናቋርጣለን፤›› በሚል ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ማስፈራሪያ፣ እንዲሁም ለሴፍቲኔት ፕሮግራም የተመደቡ በጀቶችን ለምርጫ ቅስቀሳ ጥቅም ላይ የማዋል ተግባራት ሲፈጸሙ እንደነበር የአደባባይ ሀቅ ነው፤››› ብሏል፡፡
ከሰሞኑ የመንግሥት የሞራል ማጣት ልጓም እጅጉን በመክፋቱ የአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት (USAID) እና የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) የሚያቀርቧቸው ሰብዓዊ ዕርዳታዎች በመንግሥት ኃይሎች እየተዘረፉ ለችግሩ ተጠቂዎች ከመድረስ ይልቅ ለሌላ ዓላማ እየዋሉ መሆኑን ጠቅሰው፣ በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን የዕርዳታ መርሐ ግብር ማቋረጣቸውን እንዳስታወቁ ኢዜማ በመግለጫው አስታውሷል።
ፓርቲው መንግሥት በቂ የሆነ ምርት እንዲኖር የማስቻል ሥራውን በተገቢው ሁኔታ አለመወጣቱ አገሪቱን ለዕርዳታ መዳረጉና በዜጎች ላይ የተረጂነትና ጥገኝነት መንፈስ እንዲሰፍን ማድረጉ ሳያንስ፣ ችግር ላይ የወደቁ ዜጎችን ሕይወታቸውን ማቆያ የሚሆንን የዕርዳታ እህል መዝረፍና እንደ አገር መከላከያ ያሉ ተቋማትን ስም በሚያጠለሽ ሁኔታ እንዲነሳ ማድረግ የመንግሥት የሞራል ዝቅጠትን ጥግ ያሳያል ሲል ገልጿል፡፡
ድርጊቱ በምፅዋት የሚሰጥን ፍጆታ ከዜጎች ጉሮሮ የመንጠቅ ከፍተኛ የሆነ የሞራል ዝቅጠትና ወንጀሉ የማኅበረሰቡን እሴት እጅጉን የሚፈታተን አፀያፊ ተግባር እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል ሲል ኢዜማ አክሏል።
ስለሆነም መንግሥት በአገሪቱ በተለያዩ ምክንያቶች አስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሚቀርብ ድጋፍን ከብልሹ አሠራር በፀዳ መንገድ እንዲያከናውን፣ የተጣለበትን ግዴታን እንዲሁም በረዥም ጊዜ ሒደት አገሪቱን ከተመጽዋችነት የምትላቀቅበትን ምርታማነትን የማሳደግ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ፓርቲው ጠይቋል፡፡ አክሎም መንግሥት በየትኛውም ደረጃ የሚደረግን ሰብዓዊ ዕርዳታ ለፖለቲካ ፍጆታ፣ ለምርጫ ቅስቀሳና ለገጽታ ግንባታ የመጠቀም አባዜን በአስቸኳይ እንዲያቆም አሳስቧል፡፡
ዓለም አቀፍ የተራድዖ ድርጅቶችም ‹‹በስግብግብ መንታፊ መንግሥታዊ አሠራር ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ንፁኃን ዜጎችን የሚጎዳ ውሳኔ ማሳለፋቸውን ተገንዝበው፣ ከመንግሥት ጋር በጋራ የጀመሩትን እነዚህን ወንጀለኞች ሕግ ፊት የማቅረብ ጥረት ማጠናከርና የዕርዳታው ተደራሽነት ላይ ቀደም ካለው ጊዜ በበለጠ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ፣ ዜጎችን ከእርዛትና መከራ እንዲያወጡ፤›› ሲል ፓርቲው በመግለጫው ጠይቋል፡፡