የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን እ.ኤ.አ በ2024 በሚካሄደው የፓሪስ ኦሊምፒክ ጨዋታ ማጣሪያ ለመካፈል ዝግጅቱን ጀመረ፡፡ የማጣሪያ ጨዋታ ለማድረግ አሠልጣኝ ፍሬው ወልደ ገብርኤል ለ34 ተጫዋቾች ጥሪ አቅርቧል፡፡
የ2024 የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሴቶች እግር ኳስ አፍሪካ ዞን የመጀመርያ ዙር ማጣሪያ ድልድል ይፋ ሆኗል፡፡
የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) የመጀመርያ ዙር ማጣሪያውን ከቻድ አቻው ጋር የሚያደርግ ሲሆን፣ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ከሐምሌ 3 እስከ 11 ባሉት ቀናት ይካሄዳል፡፡
የሁለቱ አገሮች አሸናፊ በሁለተኛው ዙር ማጣሪያ ከናይጄሪያ ጋር የሚጫወት ይሆናል፡፡
አሠልጣኝ ፍሬው ለ34 ተጫዋቾች ጥሪ ካደረገ በኋላ ማክሰኞ ሰኔ 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ልምምድ ጀምረዋል፡፡
በሌላ በኩል በኬንያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የሴቶች ከ18 ዓመት በታች የሴካፋ ውድድር የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን መጀመሩን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
በአሠልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ፣ ውድድሩን ለማካሄድ ለ34 ተጫዋቾች ጥሪ ያደረገ ሲሆን፣ ከግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ማረፊያቸውን በቱሊፕ ኦሊምፒያ ሆቴል በማድረግ ዝግጅታቸውን መጀመራቸው ተገልጿል፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ ከመጨረሻው ስብሰብ ውስጥ ዘጠኝ ተጫዋቾችን በመቀነስ 25 ተጫዋቾችን መልምሎ ዝግጅቱን እያደረገ ነው፡፡
ዝግጅቱንም በኢትዮጵያ ስፖርት አካዴሚ እያከናወነ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን በቦታው በመገኘት ልምምዱን መመልከታቸው ጠቅስዋል፡፡
በኬንያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የሴካፋ ከ18 ዓመት በታች ሴቶች ውድድር ከሰኔ 17 ጀምሮ እንደሚካሄድ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ ወደ ሰኔ 22 መሸጋገሩን ሴካፋ ለአባል አገሮች አሳውቋል። በዚህ ውድድር ላይ እንደሚሳተፉ ያረጋገጡ አገሮችም አዘጋጇ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ታንዛንያ፣ ኡጋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ጂቡቲና ዛንዚባር መሆናቸውን ሴካፋ አስታውቋል።