‹‹የዛፍ ምስጢሩ ውበቱ ብቻ ሳይሆን፣ ተስፋን ማጫሩ ሕይወትን ማደሱ ነው›› እንዲሉ የሥነ ሕይወት ሳይንቲስቱ ለገሰ ነጋሽ (ፕሮፌሰር)፤ ዕጽዋት ማብቀል ዛሬን አለፍ፣ ትውልድ ጠቀስ ቁም ነገር ነው። ሰው ችግኝ የሚተክለው ነገን ተስፋ አድርጎ ነው። ተስፋው ዕውን ሲሆን ደግሞ ሕይወቱ በመንፈስም፣ በቁስም ይታደሳል በሚል አምኖ ነው። ዛፍ ተከላ፣ ደን ድነና ደግሞ ተቋማዊ ሲሆን ትርጉሙ የትየለሌ ይሆናል።
‹‹አሳሳቢው የደን ጉዳይ›› በሚል ሐተታ ደን የከተበው ታዬ ፈቃደ፣ የደን ልማትም ሆነ የአካባቢ ጥበቃ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው ሲል ይገልጸዋል፡፡ ደን የሰውና እንስሳት ህልውና መሠረት ነው ለማለትም በሥዕላዊ ድርሰት እንዲህ አብራርቶታል፡፡
‹‹አረንጓዴ ገጽታ የገነት ምሳሌ ነው፤ ሐመልማላዊ ደን እስትንፋስ ነው፤ ደን ፋይዳው አካባቢያዊ ነው፤ ለድርቅ ክትባት ነው፤ ደን ለገጸ ምድርና ከርሰ ምድር ውኃ ፍሰት ዘላቂነት ዋስትና ነው፤ ደን ለአፈር መሸርሸር ደጀን ነው፤ ደን ልማት ለተራቆቱት መልክዓ ምድሮች ገመና ልብስ ነው፤ ደን ከሠሩበትም እንጀራ ነው።››
በወርኃ ሰኔ ዋዜማ የዓለም ዓይንና ጆሮ ወደ አንድ ትኩረት የሚያመጣው ይኸው የአረንጓዴ ገጽታ ጉዳይ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የማስገንዘቢያ ቀን ከፈጠረላቸው ሁነቶች አንዱ ጁን 5 (ግንቦት 28) የሚከበረው የዓለም የአካባቢ ቀን ነው፡፡
የዓለም የአካባቢ ቀን መከበር ከጀመረ ዘንድሮ 50ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ የዘንድሮ መሪ ቃሉ ‹‹የላስቲክ ብክለትን ድል መንሳት›› የሚል ሲሆን፣ በዓሉ በዓለም ዙርያ ከባህልና ሥነ ጥበብ ጋር ተያይዞ መከበሩ ተዘግቧል፡፡
በዓለም ዙሪያ በከፍተኛ ጉጉት መከበሩ የተነገረለት የዓለም የአካባቢ ቀን፣ የፕላስቲክ ቆሻሻ አሳሳቢነትን በማወጅ የኅብረተሰቡ ግንዛቤ ከፍ እንዲል በፕላስቲክ የሚደርሰውን ብክለት ማሸነፍ እንደሚገባ ላሳሰበው ተመድ ሥነ ጥበባዊ ምላሽ የሰጠው ሕንዳዊው በአሸዋ ላይ ጥበባዊ ሥራ የሚሠራው አርቲስት ሱዳርሳን ፓትናይክ ነው፡፡
በኦዲሻ በፑሪ የባሕር ዳርቻ ሁለት ሺሕ ሦስት መቶ ሃያ የፕላስቲክ ጠርሙሶች በመጠቀም አስደናቂ የሆነ የዔሊ ቅርጽ ፈጥሯል። ሥነ ጥበባዊ ሥራው የሥነ ጥበብ ችሎታ እንዳለው የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ የፕላስቲክ ብክለትን ስለ መዋጋት ጠንካራ መልዕክት ማስተላለፉ ዘኢንዲያን ታይምስ ዘግቦአል።
ቀኑ በኢትዮጵያ
የዘንድሮው የዓለም አካባቢ ቀን፣ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር (ኢቅባማ) እና የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማኅበር ‹‹የላስቲክ ብክለትን ድል መንሳት›› በሚል መሪ ቃል ሐሙስ ሰኔ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በሁለት ክፍሎች እንደሚያከብሩት አስታውቀዋል፡፡
ሪፖርተር ከኢቅባማ ባገኘው መረጃ መሠረት፣ ቀኑ በተለይ በቅርቡ ያረፉት ታዋቂው የአካባቢ ጥበቃ ሳይንቲስት ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር) ይዘከራሉ፡፡ ኢቅባማ በሚስተዳድረው የእንጦጦ የተፈጥሮ ፓርክ ፕላስቲክ በማፅዳት ተጀምሮ ከሰዓት በኋላ በግዮን ሆቴል ዶ/ር ተወልደ ብርሃንን በመዘከር የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡
የሥነ አካባቢ ሳይንቲስቱን በጨረፍታ
«የአፍሪካ አገሮችን አስተባብረው የተሟገቱ ተሟግተውም ያሸነፉ፣ በመጨረሻም አፍሪካ የራስዋን ብዝኃ ሕይወት እንድትጠብቅ ያደረጉ ሰው ናቸው፤ በኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ላይ ብዙ ሕጎች እንዲወጡ፣ በአየር ለውጥ ኢትዮጵያ ታዋቂ ሆና አቅሟ እንዲጎለብት ያደረጉ ትልቅ ሰው ነበሩ፡፡»
ይህን ዓቢይ ኃይለ ቃል በምስክርነት ለሥነ አካባቢ ሳይንቲስቱ ነፍስ ኄር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር) የሰጡት የጄኔቲክስ ፕሮፌሰሩ እንዳሻው በቀለ ናቸው፡፡ ‹‹ተቋምን ብቻ ሳይሆን አብረው ሰውን የመሠረቱና ያፈሩ ትልቅ ሰው፣ በአገራችን ይሁን በአህጉር ደረጃ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ናቸው፡፡››
ተወልደ ብርሃን (ዶ/ር) በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ በብዝኃ ሕይወት ሀብት፣ በደኅንነተ ሕይወት ጭምርና በማኅበረሰብ የፈጠራ መብት ባለቤትነት በመልማት ላይ የሚገኙ አገሮችን በማስተባበር ዋና ተደራዳሪ ሆነው አፍሪካውያን በዚህ ረገድ ግንዛቤ እንዲጨብጡ በማድረግ ያገለገሉ ታላቅ ምሁር ናቸው። ከስድስት በላይ ዓለም አቀፍ ድርድሮች ላይ አገራቸውን፣ አፍሪካንና በመልማት ላይ የሚገኙ 77 አገሮችን ወክለዋል። በእነዚህና በሌሎች ዓለም አቀፍ አስተዋፅኦዎቻቸው በ1993 ዓ.ም. የአማራጭ ኖቤል ሽልማት ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላም የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ መርሐ ግብር /ዩኔፕ/ ‹‹የምድራችን ጀግና›› (Champions of the Earth) የሚል ሽልማት ሰጥቶአቸው በሲንጋፖር ተገኝተው ተቀብለዋል።
ዘጋርዲያን የተባለው ዕድሜ ጠገብ አንጋፋ ጋዜጣ እ.ኤ.አ 2008 ዓ.ም. የዓለማችን ሃምሳ ምርጥ ሰዎች ብሎ እውቅና ከሰጣቸው ሰዎች መካከል አንዱ ዶ/ር ተወልደብርሃን ነበሩ፡፡