Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ለቱሪዝም ታክሲ የሚያገለግሉ የኤሌክትሪክ መኪኖችን ለማስገባት የመንግሥትን ምላሽ እየጠበቅን ነው›› የቱኤምቲ ኃላፊነቱ የተወሰነ አክሲዮን ማኅበር መሥራች አባልና የማርኬቲንግ ኃላፊ አቶ ወንደሰን ለገሰ

በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች በርካታ የቱሪስት መስህቦች ይገኛሉ።  መዳረሻዎቹን ለመጎብኘት ከተለያዩ አገሮች ቱሪስቶች ወደ  ከተሞቹ ይዘልቃሉ። ምንም እንኳ የሚገኙት መስህቦች በጎብኚዎች ተመራጭና ተፈላጊ ቢሆንም፣ ዘርፉ በቂ መሠረት ልማት በማጣቱ፣ ከቱሪዝሙ መገኘት የሚገባው ገቢ ማግኘት እንዳልተቻለ ይነገራል። ከዚህም ባሻገር በኢትዮጵያ የሚገኙ መዳረሻዎች የአገልግሎት አቅርቦት ክፍተት እንደሚስተዋልባቸው ይነገራል። በቅርቡ ቱኤምቲ ኃላፊነተ የተወሰነ አክሲዮን ማኅበር፣ የቱሪዝም ታክሲ አገልግሎት ላይ የሚሰማሩ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ 3,000 ተሽከርካሪዎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል። በዘርፉ የሚስተዋለው የትራንስፖርት ችግርና ከዘመናዊ የቱሪዝም ታክሲ አገልግሎት ጋር በተያያዘ  የቱኤምቲ ኃላፊነቱ የተወሰነ አክሲዮን ማኅበር መሥራችና የማርኬቲንግ ኃላፊ አቶ ወንደሰን ለገሰን ዳዊት ቶሎሳ አነጋግሯቸዋል።

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የጀመረው መቼ ነው?

አቶ ወንደሰን፡- የድርጅታችን ዋና መነሻ ሐሳብ ዘመናዊ ትራንስፖርት አቅርቦት ላይ ነው፡፡ የሐሳቡ ጥንስስ የጀመረው ጎንደር ነው፡፡ መነሻውም በኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻዎችና ትልልቅ ከተሞች ያሉ የትራንስፖርት ክፍተቶችን ታሳቢ አድርጎ በ2012 ዓ.ም. መጨረሻ የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡ በመጀመሪያ በየመዳረሻዎች ለአሽከርካሪዎች ስለ አገልግሎቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች በመስጠት እንዲደራጁ አደረግን፡፡ ከወረዳ፣ ዞን እንዲሁም ክልል ሒደቱን ተከትለን እስከ ሚኒስቴር ጉዳዩ ደርሶ ወደ ሥራ ለመግባት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ደርሰናል፡፡

ሪፖርተር፡- የቱሪስት ትራንስፖርት አገልግሎት ለማስጀመር የተጓዛችሁበት ሒደት ምን ይመስላል?

አቶ ወንደሰን፡- የቱሪስት ትራንስፖርት አቅርቦት ላይ ለመሰማራት ከሁለት ዓመት በላይ ስንንቀሳቀስ ቆይተናል፡፡ በመላ አገሪቱ የተደራጁ የየአካባቢው ወጣቶች ነዋሪዎችና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በማኅበር አደራጅተን ወደ ዘርፉ መቀላቀል እንዲችሉ አመቻችተናል፡፡ ጥያቄያቸውን ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር አድርሰን ምላሽ እየተጠባበቅን እንገኛለን፡፡ ይኼ ምላሽ ሲያገኝ በአገር አቀፍ ደረጃ ዘመናዊ የቱሪስት ትራንስፖርት አገልግሎት እናቀርባለን፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ ወይም ቱኤምቲ ዋነኛ ተግባር ቢያብራሩልን?

አቶ ወንደሰን፡- ቱኤምቲ የተደራጁትን ማኅበራት የባንክ ብድር፣ የኢንሹራንስ እንዲሁም ተሽከርካሪ ወደ አገር ውስጥ የማምጣት ሥራ ይሠራል፡፡ ይኼ ማለት ተሽከርካሪውን ወደ አገር ውስጥ ካስመጣን በኋላ እጃችንን አጣጥፈን እንቀመጣለን ማለት ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት ያለው፣ በዘመናዊ አሠራር የተደራጀ ለጎብኚው ምቹ የሆነና የተሳለጠ አገልግሎት የመቆጣጠር ኃላፊነት አለበት፡፡ በቱኤምቲ ሥር ያሉ በቱሪዝም ሚኒስቴር፣ በትራንስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም በገንዘብ ሚኒስቴር ተቀባይነትና የድጋፍ ደብዳቤ  ያገኙ 55 ማኅበራት ተደራጅተዋል፡፡ ማኅበራቱ እያንዳንዳቸው 50 አባላት ያላቸው ሲሆን፣ በድምሩ 2,750 አባላት አቅፈው ተደራጅተዋል፡፡ ማኅበራቱ በኢትዮጵያ የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎች የተደራጁ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የማኅበራቱ ሕጋዊነት እስከ ምን ድረስ ነው?

አቶ ወንደሰን፡- ማኅበራቱ በተለያዩ ከተሞች ማለትም ጎንደር፣ ባህር ዳር፣ ባሌ ሮቤ፣ ሻሸመኔ፣ ሐዋሳና አዲስ አበባ የሚገኙ ናቸው፡፡ እነዚህ ማኅበራት ከመነሻው ከአየር ማሪፊያ፣ በቱሪስት መዳረሻና በሆቴሎች ለአገልግሎት የሚንቀሳቀሱ ዘመናዊ አደረጃጀት ያላቸው፣ የተደራጀ ግንኙነት ኖሯቸው አገልግሎት የሚሰጡ ማኅበራት ናቸው፡፡ እነዚህ የተደራጁ ተቋማት በሕጋዊ መንገድ አስፈላጊውን እንዲሁም የተቀመጠውን አሠራር ተከትለው በግል የቁጠባ ሒሳብ ደብተራቸው ገንዘብ እየቆጠቡ ይገኛሉ፡፡ በዚህም መሠረት በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ያልተነካውን አቅም ለመደገፍ የተለያዩ ባንኮች እንዲሁም የኢንሹራንስ ድጋፋቸውን ያሳዩበት ነው፡፡ በርካታ ባንኮችም ማኅበራቱ ተሽከርካሪዎችን ከቀረጥ ነፃ በሚያስገቡበት ሒደት ብድር ለማመቻቸት ፈቃደኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ይህም ዘመናዊ የቱሪዝም የትራንስፖርት አገልግሎት የአገር ቱሪዝም እንደሚያግዝ በመገንዘብ የሆነ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የቱሪስት ትራንስፖርትን በማስጀመር ያለውን የዘርፉ ክፍተት በምን መልኩ ያቀላል?

አቶ ወንደሰን፡- ፕሮጀክቱን ከከተማ ታክሲ አገልግሎት ጋር የማያያዝ ችግር አለ፡፡ የቱሪስት ታክሲ አገልግሎት ማለት ቱሪስቱ በመዳረሻ ሥፍራዎች ምቹና ቀላል የሆነ እንዲሁም ዘመናዊ አገልግሎት እንዲያገኝ ዓላማን አንግቦ የተነሳ ውጥን ነው፡፡ ለምሳሌ ለመጥቀስ ባሌ ሮቤ ትልቅ የቱሪስት መዳረሻ አለ፡፡ ትልቅ የአየር ማረፊያም አለ፡፡ ግን ከአየር ማረፊያው ወደ ሆቴል ለመምጣት ባጃጅ ወይም የጋሪ ፈረስ አገልግሎት ሊቀርብለት ነው የሚችለው፡፡ የቱሪስት ታክሲ አገልግሎት ግን የጎብኚዎችን ፍላጎት መሠረት ያደረገ፣ የራሱ አለባበስ (ዩኒፎርም) ያለው፣ ስለቱሪስት መዳረሻው በቂ መረጃ ያለው፣ ስለቱሪስት አያያዝ ሥልጠና የወሰደ ክህሎት ባለው አሽከርካሪ የተደገፈ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የቱሪስት ታክሲ አገልግሎት ለመሥራት የተገለጸው በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ነው? በኤሌክትሪክ መኪና አገልግሎት ሊሰጥ የታሰበው እንዴት ነው?

አቶ ወንደሰን፡- አሁን አገሪቱ ካለችበት ሁኔታ አንፃር አቅደን የነበረው ቶዮታና ሱዙኪ ኤርቴጋ ተሽከርካሪዎችን ለማስመጣት ነበር፡፡ ይኼም ምርጫ የቀረበው በቱሪዝም ሚኒስቴር ባለቤትነት ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ለማኅበራቱ አባላት አማራጭ ነው ያቀረብነው፡፡ ሆኖም ግን የኤሌክትሪክ መኪና ማስመጣት ሲቻል፣ ቻርጀሮች በሆቴሎች፣ በከተሞች እንዲሁም በአየር ማረፊያ አቅራቢያ ቢገጠሙ ከዋጋም አንፃር አዋጭ መሆኑን ተመልክተን ነው፡፡ መንግሥት ተሽከርካሪዎችን ከታክስ ነፃ ነው የሚያስገባልን፡፡ ከዚያም ባሻገር ከአካባቢ ብክለት አንፃር እንዲሁም በትንሽ ወጪ ብዙ ማትረፍ ስለሚቻል፣ የማኅበሩ አባላት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በመምረጥ ተስማምተዋል፡፡ በመሆናቸውም ለመደበኛው መኪናዎች ለጎብኚዎቹ ምቹ በመሆናቸው ተመራጭ ያደርጋቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበራቱ ተደራጅተው መቆጠብ ከጀመሩ ሁለት ዓመት መሻገራቸውን ያነሳሉ፡፡ ተሽከርካሪያቸውን መቼ ተረክበው ወደ ሥራ ይገባሉ?

አቶ ወንደሰን፡- እነዚህ ማኅበራት በሕጋዊ መንገድ ተደራጅተው፣ በመመርያ ታቅፈው አዲስ ተሽከርካሪ ከውጭ አገር ለማስገባት በወጣው አዋጅ መሠረት የተደራጁ ናቸው፡፡ ይኼም ሒደት የተለያዩ የእርከን ደረጃዎችን አልፎ፣ ከቱሪዝምና ትራንስፖርት ሒደቱን አጠናቅቀው ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር አስተዳደር ተመርቷል፡፡ በዚህም መሠረት አሁን ባለው በጀት የገንዘብ ሚኒስቴር ማኔጅመንት የሚሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ እየተጠበቀ ይገኛል፡፡ የሚኒስቴሩ ማኔጅመንት ምላሽ ሲያገኝ በስድስት ወር ውስጥ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ገብተው በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዘመናዊ የቱሪስት ታክሲ አገለግሎት ይጀመራል የሚል እምነት አለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም የተለያዩ ድርጅቶች የቱሪስት አገልግሎት እንደሚሰጡ ገልጸው፣ ተሽከርካሪ ከቀረጥ ነፃ ካስገቡ በኋላ ለግል ጥቅማቸው ሲያውሉ ይስተዋላል፡፡ የእናንተ የቱሪስት ታክሲ አገለግሎት ከዚህ አንፃር ምን ያህል ዝግጁ ነው?

አቶ ወንደሰን፡- ቀድሞ የግል ባለሀብት የቱሪዝም አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጾ፣ ተሽከርካሪዎችን ከተረከበ በኋላ ግን ለግል ጥቅም ሲያውል መመልከት የተለመደ ነው፡፡ አሁን የት እንዳለም አይታወቅም፡፡ በአንፃሩ የእኛ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ በአንድ ቋት ቁጥጥር የሚደረግበትና ዘመናዊ መንገድን የተከተለ ነው፡፡ ሒደቱም ከመጨረሻው ምዕራፍ ደርሷል፡፡ አገልግሎቱ የራሱ መተግበሪያ ያለውና ከየትኛውም ቦታ ማዘዝ የሚያስችል ታክሲው የት እንዳለ የአቅጣጫ ጠቋሚ ያለው ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር የአገር አቀፍና የዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ማገናኘትና ማስተሳሰር የሚያስችል ድረ ገጽ እንዲሁም የደወል ጣቢያ ያለው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዘርፉን ለማሳደግ እንደ ችግር የሚነሳ ጉዳይ አለ?

አቶ ወንደሰን፡- በኢትዮጵያ በቱሪስት መዳረሻዎችና ለቱሪስት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሻሻል የሚገባቸው በርካታ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ የግሉ ዘርፍ በቱሪዝም መስክ ቢሳተፍ መንግሥትን መርዳት ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በመንግሥት የሚስተዋለው የግንዛቤ እጥረት ሌላኛው ችግር ነው፡፡ መንግሥት በቱሪዝም ዘርፍ የግሉ ዘርፍ ሲሳተፍ ቢያበረታታ አገሪቱ የገጠማትን የገንዘብ እጥረት ሊፈታ ይችላል፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች መንግሥት እየገነባው ለሚገኘው የቱሪስት መዳረሻዎች የሚመጥነው ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ማግኘት እንዲቻል መሥራት ይገባል፡፡ በኅብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ እንዲፈጠር መሥራት ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ በቀጣይ ለመሥራት ያቀደው ምንድነው?

አቶ ወንደሰን፡- በአሁኑ ሦስት ሺሕ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር አስመጥተን አሁን ለተመዘገቡት የማኅበር አባለት የምናስረክብ ይሆናል፡፡ አገልግሎቱ በእነዚህ ማኅበራት ብቻ ይቆማል ማለት አይደለም፡፡ በቀጣይ ክፍተቶችን ተመልክቶ ባልተዳረሱ የቱሪስት መዳረሻዎች በተለይ የአገር ውስጥ ቱሪዝም ዙርያ ለመሥራት ዕቅድ አለን፡፡ ይህም በአገር ውስጥ ቱሪዝም የተለያዩ ተቋማትንና ተማሪዎችን ጨምሮ በቱሪዝም መዳረሻዎች ለማንቀሳቀስ ሐሳብ አለን፡፡ በዚህም መሠረት 1.2 ሚሊዮን የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን ለማጓጓዝ አቅደናል፡፡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹ ከ25 እስከ 60 ተሳፋሪዎች መያዝ አቅም አላቸው፡፡ ለራይድ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችንም በማስመጣት ለግለሰቦች በሽያጭ መልክ እያቀረብን እንገኛለን፡፡ በቅርቡም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በአገር ውስጥ ገጣጥመን ለማቅረብ ሒደት ላይ ነን፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...

የልጅነት ሕልም ዕውን ሲሆን

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተር አባባል አለ፡፡ አባባሉ የተጎዳን ሰው ለመርዳት፣ የወደቁትን ለማንሳት፣ ያዘኑትን ለማፅናናት፣ ከገንዘብ ባሻገር ቅንነት፣ ፈቃደኝነት፣...

በርካታ ሐኪሞችን የሚፈልገው የጨቅላ ሕፃናት ሕክምና

በኢትዮጵያ የጨቅላ ሕፃናት ሞትን ለመቀነስ ባለፉት አሠርታት የተሠሩ ሥራዎች ለውጥ አምጥተዋል፡፡ ሆኖም በጨቅላ ሕፃናት ሕክምና ዘርፍ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ከነበረው ቢሻልም፣ የጨቅላ ሕፃናት...