በአዲስ አበባ ከተማ የአካል ጉዳተኞች ማኅበር ሥር የሚገኙ ስድስት የአካል ጉዳተኛ ነጋዴዎች ማኅበራት በተለያዩ አካባቢዎች ያቁቋማቸው የመሥሪያ ቤታቸው (ሱቆቻቸው) በአፍራሽ ግብረ ኃይል መፍረሱን አስመልክቶ ሰኔ 10 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰሜን ሆቴል የጠሩት ስብሰባ እንዲቋረጥና ታዳሚዎቹም አዳራሹን ለቀው እንዲወጡ ተደርጓል፡፡
ስብሰባው እንዲቋረጥና አዳራሹም ባዶ እንዲሆን የተደረገው ማኅበራቱ የሥራ ቦታቸው መፍረሱን በመቃወም ያወጡት የአቋም መግለጫ በንባብ ከተሰማና የአዲስ አበባ ከተማ አካል ጉዳተኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ንግግር ካበቃ በኋላ ነው፡፡
የሰላም ለሁሉም የአካል ጉዳተኞች ንግድ አክሲዮን ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ኢዮብ ደስታ በተለይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ስብሰባው እንዲቋረጥና ታዳሚዎቹም እንዲበተኑ ያደረጉት የሆቴሉ ሥራ አስኪያጅ ሲሆኑ፣ ለዚህም የሰጡት ምክንያት በሥፍራው ከነበሩ ፖሊሶች በተሰጣቸው ትዕዛዝና መመርያ መሠረት ነው የሚል ነው፡፡
በሆቴሉ መግቢያ ዙሪያ ለነበሩ ፖሊሶች በቅድሚያ ስብሰባ እንደሚካሄድና ብዙ ሰዓትም እንደማይፈጅ ከተገለጸላቸው በኋላ በተደረሰው መግባባት መሠረት የተጀመረ ስብሰባ እንደነበር፣ ነገር ግን ሥራ አስኪያጁ ስብሰባውን አስቁመው የኤሌክትሪክ መስመሩም እንዲቋረጥ ማድረጋቸውን አቶ ኢዮብ ተናግረዋል፡፡
የሆቴሉ ሥራ አስኪያጅ ስለዚሁ ጉዳይ ተጠይቀው በሰጡት መልስ ‹‹ፖሊሶች ተሰብሳቢዎቹ ፈቃድ ማውጣት፣ አለማውጣታቸውን ሳታጣሩ ለምን አዳራሽ አከራያችኋቸው? የሚል ጥያቄ በማቅረብ ስብሰባውን አስቁሙ ከማለታቸው በስተቀር ሌላ እክል አላስከተሉብንም፤›› ብለዋል፡፡
ስብሰባው ከመቋረጡ በፊት በንባብ ከቀረበው ባለ አራት ነጥብ የአቋም መግለጫ ለመረዳት እንደተቻለው መንግሥት በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ አካል ጉዳተኞች ችግሮቻቸውን በተዋረድና በቅደም ተከተል እንዲፈታ ጠይቀዋል፡፡
ከዚህም ሌላ መንግሥት በአፋጣኝ ከሥራ ለተፈናቀሉ አካል ጉዳተኞች ነጋዴዎች የዕለት ጉርሳቸውን ያገኙ ዘንድ ጊዜያዊ መፍትሔ እንዲሰጣቸው፣ እንዲሁም በዘላቂነት ለአካል ጉዳተኞች ችግር መፍትሔ በመስጠት የአካል ጉዳተኛውን ጥቅምና መብት እንዲያስጠብቅላቸው ማሳሰባቸውን መግለጫው አመላክቷል፡፡
የሕገ መንግሥት አንቀጽ 41/15 እንዲከበር መጠየቃቸውንና እነዚህ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ የማያገኙ ከሆነ የዓለም ኅብረተሰብና መንግሥት እንዲያውቁትና እንዲረዱ ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ እንደሚገደዱ ከወዲሁ ማሳወቅ የሚፈልጉ መሆኑን መግለጫው ሳይጠቁም አላለፈም፡፡
ቁጥራቸው ከ3000 በላይ የሚሆኑት እነዚህ አካል ጉዳተኛ ነጋዴዎች የንግዱን ዓለም የተቀላቀሉት በስድስት ማኅበራት ከተደራጁና በየአካባቢው የመሥሪያ ቦታ ከመንግሥት ከተሰጣቸውም በኋላ መሆኑን መግለጫው አመልክቶ፣ የተደራጁባቸው ማኅበራትም ሰላም ለሁሉም፣ የነገው ተስፋ፣ ጽናት ፍሬ፣ አባተ ብርሃኑ፣ መኮንን ተረፈና ሜክሲኮና ቂርቆስ አካባቢ የአካል ጉዳተኛ ማኅበራት መሆናቸውን አስረድቷል፡፡
ለንግድ ሥራ የተሰማሩባቸውም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ከረሜላ ፋብሪካ እየተባለ በሚጠራው ቦታ፣ አብዱ በረንዳ፣ አውቶቡስ ተራ፣ ወረዳ ስምንትና ዘጠኝ አካባቢዎች ባሉት ቦታዎችና በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሐራምቤ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ነው፡፡
እንደ መግለጫው ማብራሪያ አዲስ አበባን ከሸራ ሱቅ የማጽዳት ዘመቻ ላይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አካል ጉዳተኞችን ከሌላው ጉዳት አልባ ጋር እኩል በማየት ከሥራ ቦታቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ከዚህም አብዛኞቹ አካል ጉዳተኞች በአንድ ቦታ ተሰባስበው ይሠሩ ስለነበር ያለምንም ማስጠንቀቂያ የመሣሪያ ዕቃቸውን አስረው በሄዱበት ሌሊት ላይ የሚነግዱት ዕቃና ማቴሪያሎች በአፍራሽ ግብረ ኃይል ተጭኖ ተወስዷል፡፡
በዚህም አካል ጉዳተኞቹ ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ በመሆኑ የተነሳ ከአንድ ወር በላይ ያለ ሥራ መቆየታቸውን በዚህም ዓይነት መንገድ ሕይወታቸውን ሊመሩ ባመቻላቸው አብዛኞቹ ወደተዉት ልመና መግባታቸውን ነው መግለጫው የጠቆመው፡፡
በዚህ የተነሳ ማኅበሩና በሥሩ ያሉት ስድስት ማኅበራት አመራሮች ለአንድ ወር ያህል በተለያዩ የመንግሥት አካላት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ተወያይተው ጩኸታቸውንም ያሰሙ ቢሆንም ችግሮቻቸውን ለመፍታት የተደረገው ሙከራ ግን ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
የአዲስ አበባ አካል ጉዳተኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ገለታው ሙሉ በኢትዮጵያ 17.6 ሚሊዮን አካል ጉዳተኞች እንዳሉ፣ ከእነዚህም መካከል 98 ከመቶ ያህሉ ሥራ አጥ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
የአካል ጉዳተኞቹ ጥያቄዎች ብዙ እንደሆኑ፣ ከጥያቄዎቹም መካከል አንዱና ዋነኛው ከዳቦና ከህልውና ጋር የተያያዘ ጥያቄ እንደሆነና ለጥያቄውም መንግሥት ቀስ ብሎ ሳይሆን አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥበት አንገብጋቢ ጉዳይ እንደሆነ ነው ያመለከቱት፡፡