Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርዴሞክራሲን ትቶ ስለለውጥ መደስኮር ከንቱ መወራጨት እንዳይሆን!

ዴሞክራሲን ትቶ ስለለውጥ መደስኮር ከንቱ መወራጨት እንዳይሆን!

ቀን:

በያሲን ባህሩ

    በሠለጠነው የዓለም አቀፍ ሁኔታም ሆነ በየትኛውም የተነቃቃ ማኅበረሰብ ዕሳቤ ውስጥ ካለ ዴሞክራሲ ለውጥ አይደለም ራሱ ሥርዓተ መንግሥት አይኖርም፡፡ ፈላጭ ቆራጭ፣ ጨቋኝም ሆነ አሻባሪ ሥርዓት አለ ሳይሆን የሚባለው አገር እየናደና ሕዝብ እያተራመሰ መውደቂያውን በመጠባበቅ ላይ ነው ብቻ ነው፡፡ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ወደ ኋላ ከመመለስ ያውጣን፡፡

     በመሠረቱ ዴሞክራሲ ማለት የሕዝብ ለሕዝብና በሕዝብ የቆመ ሥርዓት ነው፡፡ ዴሞክራሲ የአማራጭ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው ደግሞ በሕዝባዊ ምርጫ በመሆኑ ምርጫም የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ምርጫ የሚካሄደው በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ነው፡፡ ፓርቲዎች ዓላማቸውን ማስረፅ የሚችሉት ደግሞ በሐሳብ ነፃነት መርሆና በመሣሪያዎቹ ነው፡፡

     ሕዝብም ቢሆን ጠቀመውም ጎዳውም ካለ ምርጫ በየትኛውም መንገድ ሕጋዊ መንግሥትን ለማውረድ መመኘትም ማድረግም አይችልም፣ ሕገወጥነትም ነው፡፡ አሁን ባለው የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ግን ነገሮች ባልተከፈተላቸው ቦይ ሲጎርፉ እየታየ ስለሆነ፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ረገድ መታየት ያላባቸውን አንዳንድ ነጥቦች በማንሳት መወያያ ነጥብ ለማድረግ እሞክራለሁ፡፡

የፓርቲዎች ጉዳይ

       የፖለቲካ ፓርቲዎች (ገዥና ተቃዋሚ ሳይባሉ) ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ዋነኛ መሠረቶች ናቸው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሌሉበት ሁኔታ የሚደረግ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ሊያስገኝልን አይችልም፡፡ በምርጫ የሚመሠረት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲኖረን ከፈለግን የፖለቲካ ፓርቲዎችን አስፈላጊነት ማመንና መቀበል ግዴታችን የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡

   መንግሥት የሰላማዊና የዴሞክራሲ ምኅዳር እንዳይጠብ ሕግና ሥርዓት እንዳይጣስ፣ የሕዝብ ደኅንነት ለአደጋ እንዳይጋለጥ ተግቶ መገኘት ያለበት በዋናነት ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ አገረ መንግሥት ለመገንባት ነው፡፡ ዳቦም ሆነ ብልፅግና የሚመጣው በሁለተኛ ደረጃ ነው፡፡ አሁን በምንገኝበት አገራዊ ሁኔታ ግን ለውጥ እየተባለ ያለው በጨነገፈ ዴሞክራሲ ውስጥ የሚውተረተረው አስተሳሳብ እየሆነ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከንቱ መታከት ከመሆን አለማለፉ ብቻ ሳይሆን፣ አገር ቀደም ሲል በነበረችበት መረጋጋት ውስጥ እንኳን መቀጠል እንዳትችል ነው የሚያደርገው፡፡

      ስለሆነም በቀዳሚነት የፖለቲካ ውይይትና የሕጋዊ ፓርቲዎች ሚና የሚጎለብትበት መንፈስ ይፈጠር፡፡ በአገር ላይ ፓርቲዎች ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸው ሚና ኃያል ነው፡፡ ፓርቲዎቹ ‹‹ቆመንለታል›› የሚሉትን ሕዝብ/ቡድን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችሉ አማራጭ ሐሳቦችን ያመነጫሉ፡፡

    እየተጠናከሩ ሲሄዱም ሐሳቦቻቸው ለቆሙለት ኅብረተሰብ/ቡድንና በጠቅላላው ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ይታገላሉ፡፡ ሐሳቦች በዴሞክራሲያዊ አኳኋን ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚቻላቸውን ሁሉም ያደርጋሉ፡፡ ሕዝብን ወክለውም ይሳተፋሉ (ይህም አሁን ያለውን ሁሉም አውቃለሁ፣ ልደመጥ ባይነትን አደብ ያስይዛል)፡፡ ይህንን ለማድረግ ግን ፓርቲዎች ህልውናቸው ተከብሮ ሊንቀሳቀሱ ግድ ይላል፡፡ በሕዝብም ሆነ በመንግሥት ዋስትና ማግኘትም አለባቸው፡፡

     አሁን ባለው አገራዊ ሁኔታ ግን የፓርቲ ፖለቲካ ከተፎካካሪና ከተወዳዳሪነት መንፈስ ወጥቶ በሥርዓቱ ተለጣፊነት፣ አልያም በኃይል አማራጭና ነውጥኝነት የተበከለ ሆኗል፡፡ እንኳንስ በክልሎች በአዲስ አባባም የሰላማዊና የዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ ትግል ወሬ ማውረት የማይቻልበት ደረጃ ተፈጥሯል፡፡ ፍርኃትና አለመተማማንም ነግሷል፡፡ ከሁሉ በላይ ይህን ጥበቃ በመፈጸም የዴሞክራሲ ተቋማትን ያጎለብታሉ የተባሉ ሕጋዊ አካላት ድምፃቸው ሰሏል፡፡ ግን የት ለመድረስ፣ ምንስ ለማምጣት?

     መንግሥትን ተቃውሞ መጻፍ፣ መናገር፣ መሰብስብና ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግ ይቅርና በኪነ ጥበብ ሥራዎች ቅሬታን መግለጽ ፍፁም ወንጀል እየመሰሉ ነው፡፡ ተጣርቶም ሆነ ሳይጣራ በፖለቲካ አመለካካቱና ሐሳብን በመግለጽ ዴሞክራሲያዊ መብት ትግበራው ብቻ የሚታሰረው ሰው የትየለሌ ነው፡፡ እንዴትና ለምን ባይም ያለ አይመስልም፡፡ ይህ ነባራዊ ሀቅ ደግሞ የዴሞክራሲ ዕድሉንም ሆነ የአገር ግንባታውን ክፉኛ የሚያዳክምና ወደኋላ የሚመልስ ነው፡፡ ለአገራችንም ፈፅሞ ሊበጅ አይችልም፡፡

      እቅጭ እቅጩን እንነጋገር ከተባለ በብሔር ላይ የተመሠረተው የፖለቲካ ሥረወ መንግሥት ዋና ዋና የአገሪቱ መሪዎች የወጡበትን ማኅበረሰብ ‹‹የአንተ ወቅት ነው›› በሚል ቅስቀሳ ሥርዓቱን የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን፣ የህልውና ትግል መነሾ ለማድረግም ሲሞከር በመታየት ላይ ነው፡፡ 

     እሱ ብቻ ሳይሆን ‹‹ቀደም ባሉት ጊዜያት ተገፍተሃል፣ የሕዝብ ቁጥርህም ከፍተኛ ነው›› በሚል ሥሌት ብቻ ቢመጥንም ባይመጥንም በየሹመቱና በየአዳዲሱ የመንግሥት ሥራ መደብ ላይ እየገባ ያለው የብሔር መረጣ ፍፁም አግላይ አካሄድን የሚያሳብቅ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የዴሞክራሲ ግንባታ ሕልሙን ወደ መቀመቅ የሚያወርድ ብቻ ሳይሆን፣ አብሮ መኖርንም የሚያውክ ነው፡፡ ‹‹በምን ታመጣለህ›› አገር እንደ መምራትም ይቆጠራል፡፡

         እንኳን አንድነትን ሊያቀነቅን የሚሞከረው ገዥው ፓርቲ ብልፅግና ቀርቶ፣  የአገራችን ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካካል ብቃት ያለው አመራር አግኝተው መብትና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚችሉበት ሁኔታ በተግባር ማሳየት ነበር ያለባቸው፡፡ በማንነትና በቤተሰብ እየተሰባሰቡ ስለሰፊ አገርና 120 ሚሊዮን ሕዝብ ማሰብ ግን አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ አሁን እንደ አገር ያቆጠቆጠው ደግሞ  ነፍጥ መነቅነቅና ቡራ ከረዩ ማለት መሆኑ ነገሩን በቦሃ ላይ ቆረቆር እያደረገው ነው፡፡ በአገሩ በሰለጠነ መንገድ መኖርና መሥራት የሆነ ማኅበረሰብ ቀና ብሎ እንዳይራመድና እንዳይደመጥ በመሆንም ላይ ነው፡፡

        በመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምንላቸው አንድን የፖለቲካ ዓላማ ለማራመድ፣ በዚያ ዓላማ ዙሪያ መሰባሰብና መታገል የሚፈልጉ ዜጎችን ለማሰባሰብ የሚሠሩና መነሻና መድረሻቸውን በያዙት የፖለቲካ ዓላማ ላይ ብቻ ያደረጉትን የዴሞክራሲ ተዋናዮችን ነው፡፡ ዓላማቸውን በሚገባ የተረዱና ያወቁ፣ የተነሱለትን ዓላማ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ አማራጮችን ለመተንተን፣ ለማቀናበርና ለሕዝብ ለማቅረብ ፍላጎትና አቅም ያላቸው ብቻ ሳይሆን አቃፊነታቸው በገቢር የተረጋገጡትን ነው፡፡ አፍራሹና ዱለኛውማ ምን ፓርቲ ይባላል ፀረ ዴሞክራት ጥገኛ  እንጂ፡፡

     በዚህ መሠረት ፓርቲዎችና የዴሞክራሲ ተቋማት የአገሪቱን ሕገ መንግሥት አክብረው የሕግ ማዕቀፉን ጠብቀው፣ ዴሞክራሲያዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ተደራጅተው እንዲንቀሳቀሱና እንዲነቃቁ መደረግ አለባቸው፡፡ እንዲህ ያሉ ፓርቲዎች ከትናንቱም  በላይ ይፈለጋሉ፣ ያስፈልጉናልም፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን በእኛ አገር እየታየ ያለው መዳከም ነው፡፡ ግን አንሞኝ መሰባሰብ ኃይል ነውና እንጠቀምበት፣ ዴሞክራሲያችንንም ከመውደቁ በፊት እንታደግ፡፡ መንግሥትንም በሰላማዊ መንገድ እንገዳደር፡፡

የሐሳብ ነፃነት ጉዳይ

       በየትኛውም የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ታሪክ ውስጥ ዋነኛው የትግል መሣሪያና ሰላማዊ መንገድ የሐሳብ ትግል ነው፡፡ ሐሳብ ደግሞ ያለ ገደብና በነፃነት መንሸራሸር ያለበት ብቻ ሳይሆን፣ ትግል የሚደረገውም በሓሳብ ብቻ እንደሆነ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ያስቀምጣሉ፡፡ በእኛም አገር ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 29 መሠረት የፕሬስና የሐሳብ ነፃነት ጉዳይ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ ይህ ድንጋጌ ደግሞ በቀጥታ እ.ኤ.አ. በ1948 ይፋ ከተደረገው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ አንቀጽ 19 ቃል በቃል የሠፈረ ነው፡፡

    ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የሚዲያና የኮሙዩኒኬሽን አማራጩ ወደ ማኅበራዊ ድረ ገጽና ዘመን አመጣሹ የኢንተርኔት መረብ በመስፋቱ የዜጋ ጋዜጠኝነት (ሁሉም ሰው መረጃ የሚያመነጭበት፣ የሚያሠራጭበትና የሚቀበልበት ዕድል) የተሰፋፋበት ሆኗል፡፡ እናም ከማጀት እስከ አደባባይ፣ ከቤተ መንግሥት እስከ መሸታ ቤት የሚደበቀው ነገር ጠፍቷል፡፡ ወሬና ቧልት፣ ጠቃሚ መረጃና የጥፋት ሐሳብ ሁሉ አየር መሙላት ችለዋል፡፡ ሌላም ምክንያት ቢደማመርባቸውም በአንፃራዊነት የተሻሉ የመረጃ አመንጪ የኅትመት ውጤቶች ተዳክመዋል፡፡ ይህን መሟሟት ማንም የሚያስቆም አካል ያለም አይመስልም፡፡

     ወደ ነጥባችን ስንመለስ ግን በፕሬስና በሐሳብ ነፃነት ረገድ ወደ ኋላ የመመለስና የከፋ ገጽታ የመላበስ ተግዳሮት ነው እንደ አገር እየገጠመን ያለው ማለት ይቻላል፡፡ በተለይ ተካሮ በቀጠለው የብሔር ፖለቲካ ማኅበራዊ አንቂዎች የሚባሉትና ጋዜጠኞች ብቻ ሳይሆኑ፣ ፖለቲከኞችና ዩቲዮበሮችም ተደበላልቀው በመገኘታቸው በሕግና በሥነ ምግባር መመራት ቀርቶ መወነጃጀል፣ መካሰስና እስር ተበራክቷል፡፡ መንግሥትም ለጀመረው የለውጥ መንገድ ሐሳብን ያለ ገደብ ማስተናገድ ይበጃል ብሎ የተመለከተው አይመስልም፡፡ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ፍርኃት ዳሱን ጥሏል፡፡

     ለአባባሉ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከሕግ አግባብ ውጪ 63 ጋዜጠኞች እንደታሰሩ (ያውም በቅርብ የሉትን 12 ገደማ ሳያካትት) የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል በጥናት ያረጋጋጠው መረጃ ከወር በፊት መውጣቱ ነው፡፡ እነዚህ ጋዜጠኞች ከሕግና ከሥርዓት ውጪ ታፍነው ከመታሰራቸው ባሻገር፣ ሁለት ጋዜጠኞች መገደላቸውንም ነው  በጥናቱ የተመላከተው፡፡

     ጋዜጠኞች ከሕግ አግባብ ውጪ ታፍነው መታሰራቸው፣ ከታሰሩ በኋላም ያሉበት ሳይታወቅ ቆይተው መለቀቃቸው አሳሳቢ ጉዳይ በመሆኑ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ፣ ችግር ሲደርስባቸው ለመሟገት ያመች ዘንድ ጋዜጠኞች ማኅበራትን እንዲቀላቀሉ ተጠይቋል (በነገራችን ላይ ሁሉም ታሳሪዎች ጥፋት የለባቸውም ባይባልም፣ ሕግና ሥርዓት ተከትሎ እንደ ፕሬስ ካውንስል ያሉ ተቋማትን በመጠቀም መፍትሔ አለመፈለጉ የዴሞክራሲ ውድቀትን እንደሚያመላክት ነው ሲነገር የከረመው)፡፡

        ከዚህም ባሻገር በኦሮሚያ ክልል በተለይም በወለጋ ዞኖች ካለፉት አራት ዓመታት ጀምሮ የሚፈጸመውን የንፁኃን ዜጎች ሞት ጋዜጠኞች በአካል ተገኝተው አለመዘገባቸው በጋዜጠኞች ማኅበር ቅሬታ አስነስቶ ነበር፡፡ የትግራዩም እንዲሁ ነበር፡፡  በወለጋ በንፁኃን ዜጎች ላይ የሚፈጸመውን ሞት ለመዘገብ ጋዜጠኞች ግፊት አለማድረጋቸው ከተጠያቂነትና ወቀሳ የማያድን መሆኑን፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ማኅበር ፕሬዚዳንት ሲናገርም ዴሞክራሲው የገጠመውን ፈተና በማመስጠር ነበር፡፡ ለነገሩ አሁን የት የደረሰን ጉዳት ማን ሊናገረው ይችላል? 

       በተመሳሳይ በፕሬስ ቀን ላይ የተገኙ የየማኅበራቱ መሪዎች በአገሪቱ አስተማማኝ መረጋጋትና የፖለቲካ ስክነት ባለመረጋገጡ፣ ግጭት አገናዛቢ ዘገባን ግምት ውስጥ በማስገባት ግጭት እንዳይባባስ ከማድረግ አኳያ የሚዲያ ተቋማት ከእውነታው እየሸሹ መሆናቸውን ነበር ያነሱት፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ ተቋማቱ ሳይዘግቡ ከመቅረት ይልቅ ሁሉንም ወገን በማካተት እውነታውን በመዘገብ ለውጥ ለማምጣት ባለመቁረጣቸው ነው፡፡ ምቹ ምኅዳርም በመጥፋቱ ነው፡፡ ይህም ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚበጅ መንገድ እንዳልሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

      እውነት ለመናገር በአገራችን ከ22 በላይ የጋዜጠኝነት ማኅበራት ቢኖሩም፣ 65 በመቶ የሚሆኑት ጋዜጠኞች የተለያዩ የጋዜጠኝነት ማኅበርን እንዳልተቀላቀሉ ነው የሚታወቀው፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን በብዙዎቹ የመንግሥት ሚዲያዎች ውስጥ የሚገኙ ሙያተኞች በነፃነት ተደራጅተው መሥራት አለመቻላቸው ብቻ ሳይሆን፣ የሙያ ነፃነትና በራስ የመተማመን መብት ያላቸው አይመስሉም፡፡ የሚዲያ አመራሩ ገለልተኛ ባለመሆንና በመሪው ፓርቲ ፖለቲካ በመጠለፍም ነፃነት መፈተኑ አይቀርም፡፡ ከዚህ ውስጥ መውጣት ደግሞ ቁልፍ የሚባለውን  የዘርፉን ችግር እንደ መቅረፍ ይቆጠራል፡፡

የኢሰመጉ ምክሮችና ጩኸቶች

     በአገራችን ለውጥ ከጀመረ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ (ኢሰመጉ) የመሰለ በሕግና በሥርዓት ወይም ለሕዝብ በወገነ መንገድ የታገለ ተቋም ስለመኖሩ እርግጥኛ አይደለሁም፡፡ ይህ ገለልተኛና ለሰብዓዊም ሆነ ለዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ከፍተኛ ሚና ያለው አካል፣ ሠራተኞቹ እየታሰሩና እየተንገላቱ ጭምር በርካታ ሁነቶችን በተጨባጭ በመመርመር መግለጫዎችና እርምት የሚሹ ክስተቶችን ለመንግሥትና ለሕዝብ እያሳወቀ ነው፡፡

    እንዳለመታደል ሆኖ በፖለቲካ ብልሽት በተነሳው የእርስ በርስ ጦርነት፣ ፅንፈኛ ኃይሎችና በመንጋ ፍርድ ላይ ያተኮሩ ግለሰቦች ባደረሱት ጉዳት፣ በመንግሥት የመልካም አስተዳዳር ማስፈን አለመቻልና ግብታዊ ዕርምጃዎች (ለምሳሌ የዜጎችን ቤቶች ማፍረስ)፣ ያላግባብ በሚታሰሩ ሰዎች (በተለይ የሚዲያና የፖለቲካ ሰዎች)፣ በየአካባቢው በሚወሰዱ ሰላም የማስከበር ዕርምጃዎች በሚደርሱ ጉዳቶች፣ በሰላማዊ ሠልፈኞች ላይ በሚወሰዱ ዕርምጃዎች፣ ወዘተ በአንድም ይሁን በሌላ የዜጎች መብቶች እንዳይጣሱና የተጣሱትም እንዲታረሙ፣ ጥፋተኞችም ተጠያቂ እንዲደረጉ ሲጎተጎት ከርሟል፡፡

     ይህ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ጩኸትና ሙግት ግን በመንግሥት በኩል ሰሚ አግኝቶ እርማት ሲከተለው አይታይም፡፡ እንዲያውም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ችግሮች ሲደራረቡ፣ የዜጎች መከራና ሥቃዮችም ሲደጋገሙ ነው የሚታዩት፡፡ ይህ ደግሞ ተስፋ አስቆራጭ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ወደ ከፋ ቀውስ ነው የሚወስደን፡፡ እናም በአፋጣኝ መታረም ይኖርበታል፡፡

    በአጠቃላይ የዴሞክራሲ ግንባታ ሒደቱን፣ የግልጽነትና የተጠያቂነት ባህል ግንባታ ትልቁን ሥራ ቸል ብሎ የትኛውም ዓይነት የአገር ግንባታ ሙከራ ከዳር ሊደርስ እንደማይችል መታወቅ አለበት፡፡ ውጤት ታየ ቢባልም ዘለቄታ ስለማይኖረው መፍረሱ አይቀርም፡፡ እናም መታረሙ ይበጃል እላለሁ፡፡

     ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...