Saturday, September 23, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ ኢንዱስትሪዎች በተጣለባቸው የንብረት ግብር ላይ ተቃውሟቸውን አሰሙ

ተዛማጅ ፅሁፎች

አዲሱን የንብረት ታክስ መሬት ላይ ለማውረድ እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች ብዥታ እየፈጠሩ ነው፡፡ በተለይ ሰሞኑን ‹‹የንብረት ታክስ›› አዋጁን ለመተግበር የንብረት ባለቤቶች መክፈል ይጠበቅባቸዋል ተብሎ እየደረሳቸው ያለው የንብረት ታክስ ዋጋና የስሌት ሒደቱ ብዥታ ፈጥሮብናል እያሉ ነው፡፡

ለንብረት ታክሱ እየተጠየቀ ያለው ዋጋ ግነት ብቻ ሳይሆን፣ ሕጋዊነቱ ላይም ጥያቄ እየተነሳ ነው፡፡ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ወገኖች ዘንድ አነጋጋሪነቱ እየጨመረ የመጣው የንብረት ታክስ በተለይ በአምራች የኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ አካላትን አስደንግጧል፡፡ በአዲስ አበባ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች አሁን መንግሥት ባወጣው ሥሌት መሠረት ግብሩን ለመክፈል አዳጋች እንደሚሆንባቸው እየገለጹ ነው፡፡

የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ይወክላሉ ተብለው ከሚጠቀሱ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው አገር አቀፍ የዘርፍ ምክር ቤትና በተለያዩ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ውስጥ ያሉ የንግዱ ኅብረተሰብ አባላትም የጉዳዩን አሳሳቢነት እያመለከቱ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ኢንዱስትሪዎች በርከት ብለው በሚገኙበት አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የአነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንትና የአገር አቀፉ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አበባየሁ ግርማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ማኅበራቸው ከአባላቱ በሰባሰበው መረጃ በኢንዱስትሪዎቹ ላይ የተጣለው የንብረት ግብር ኢንዱስትሪዎቹን እንደሚያዳክም መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡

የማኅበሩ አባላት እያደረሳቸው ካሉ የንብረት መረጃዎች መረዳት እንደቻሉትም፣ አብዛኛዎቹ ባለኢንዱስትሪዎች የተጠየቁትን ያህል የንብረት ግብር ተመን ለመክፈል የማይችሉ መሆኑን ነው፡፡

አባላቱ ባደረጉት ስብሰባም አዲሱ የግብር ዓይነት በዚህ መጠን በኢንዱስትሪዎች ላይ የተጣለበት ምክንያትና የግብር ስሌቱ ግራ ያጋባቸው ከመሆኑ ባሻገር የተጠየቁትን ያህል ግብር ለመክፈል የማይችሉ ከሆነ ዕጣ ፈንታቸው እንደሚያሳስባቸ አቶ አበባየሁ ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ አበባየሁ ገለጻ፣ የንብረት ግብር ከዚህ ቀደም በተለያየ መጠን ሲከፈል እንደነበር አስታውሰው፣ በዓለም ላይም የተለመደ የግብር ዓይነት ቢሆንም አሁን በኢትዮጵያ እንዲተገበር የተፈለገበት መንገድ፣ በተለይም በካሬ ሜትር እንዲከፈል የተቀመጠው ዋጋ ፍፅሞ የባለኢንዱስትሪውን አቅም ያላገናዘበ፣ ወጪና ገቢያቸውን ግምት ውስጥ ያላስገባ ነው ብለው ያምናሉ፡፡

በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስ ቢሮ የንብረት ግብርን በተመለከተ ካስተላለፈው ሰርኩላር መረዳት እንደሚቻለው፣ የንብረት ግብር የሚመለከተው የመኖሪያና የንግድ ተቋማትን ብቻ ሆኖ ሳለ ኢንዱስትሪዎች የተካተቱበት ምክንያት ግልጽ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ሰርኩላር ላይ ኢንዱስትሪዎች በሚል የተጠቀሰ ነገር ባለመኖሩ፣ የንግድ በሚለው ታሪፍ መሠረት ግብሩን እንዲከፍሉ መጠየቃቸው አግባብ እንዳልሆነም ጠቅሰዋል፡፡  

ከሁኔታው አሳሳቢነት አንፃር ማኅበራቸው ኢንዱስትሪዎች በርከት ብለው በሚገኙበት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት፣ ሰባትና 14 ያሉ ኢንዱስትሪዎችን አነጋገሮ አብዛኛዎቹ የተጣለባቸው የንብረት ግብር መክፈል እንደማይችሉ አረጋግጧል፡፡

ኢንዱስትሪዎቹ ላይ በተጣለው የንብረት ግብር ተመን ከፋይናንስ ቢሮዎች ያገኟቸው መረጃዎች በአማካይ 700 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፉ የአዲስ አበባ ኢንዱስትሪዎች በዓመት፣ በዓመት ከ118 ሺሕ ብር በላይ መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢንዱስትሪዎች በአብዛኛው ከአንድ ሺሕ ካሬ ሜትር በላይ ይዞታ ላይ ያረፉ በመሆናቸው፣ በግብር ስሌቱ መሠረት ኢንዱስትሪ በዓመት በርካታ መቶ ሺሕ ብሮችን መክፈል ይጠበቅበታል፡፡ ችግሩ የዋጋ ተመኑ ብቻ አለመሆኑን የሚገልጹት አቶ አበባየሁ፣ ኢንዱስትሪዎች በብሎኬት ከገነቡት ሕንፃዎችና መጋዘኖቻቸው ሌላ ለተለያዩ አገልግሎቶች በቆርቆሮ የተሠሩ ሼዶች ሳይቀሩ በካሬ ሜትር 417 ብር ትከፍላላችሁ መባሉ የግብሩን መጠን ከፍ እንዳደረገባቸው ገልጸዋል፡፡

ቋሚ ያልሆነንና በቆርቆሮ የተሠራን ሼድ ሳይቀር በመለካት ግብሩን ክፈሉ መባሉ አግባብ እንዳልሆነም አመልክተዋል፡፡ ብዙዎቹ ኢንዱስትሪዎች ከዋናው የፋብሪካና የቢሮ ሕንፃዎቻቸው ሌላ በጊዜያዊነት የሚጠቀሙባቸው የቆርቆሮ ሼዶች ያሉባቸው በመሆኑ እነዚህን ከቋሚ ግንባታዎች ጋር በመደመር ግብሩ እንዲሰላ መደረጉ ትክክል እንዳልሆነ ጠቅሰዋል፡፡

‹‹የኢንዱስትሪ ዘርፍ በዚህ ታክስ ላይ መሠረታዊ የሚባል ችግር የለውም፤›› የሚሉት አቶ አበባየሁ፣ መንግሥት ይዞት የቀረበው የታክስ ምጣኔ ግን ተጋንኖ መቅረቡ ተገቢ ነው ብለው አያምኑም፡፡ በተለይ የዋጋ ተመኑ ኢንዱስትሪውን ብቻ የለየ መሆን ሲገባው ያለመለየቱም አግባብ አይደለም፡፡

በማኅበራቸው የመስክ ቅኝት በሦስቱ ወረዳዎች ባሰባሰቡት መረጃ በአካባቢው ያሉ ኢንዱስትሪዎች በአማካይ 700 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ግንባታ ያላቸው ናቸው፡፡ ይህም በዚህ አካባቢ ብቻ አንድ ኢንዱስትሪ በዓመት በመቶ ሺሕ ብር የሚገመት ግብር ይከፍላል፡፡ የቆርቆሮ ቤቶቹ ሲጨመሩ ደግሞ ዋጋውን በዕጥፍ እንዲጨምር የሚያደርግ በመሆኑ ጉዳዩ ሊታይልን ይገባል ብለዋል፡፡  

‹‹ከዚህ ጎን ለጎን ይህ ዘርፍ ላለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ለመከላከያ፣ ለኮቪድና ለተለያዩ መዋጮዎች ሲጠየቅ ሲያወጣ ነበር፡፡ ይህንን አልፈው ኢንዱስትሪዎች አሁን መነቃቃት በጀመሩበት በዚህ ጊዜ፣ የከተማ አስተዳደሩ ይህንን ታክስ ይዞ መምጣቱ ስለእውነት ያስደነግጣል፤›› ያሉት አቶ አበባየሁ፣ አሁን ባለው ሥሌት የንብረት ግብር ይተግበር ከተባለ ችግሩ ኢንዱስትሪዎችን ከመጉዳት ባሻገር፣ በርካታ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሶችን ሊያስከትል እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ኢንዱስትሪዎች የግድ ግብሩን እንዲከፍሉ የሚደረግ ከሆነ የመጣባቸው ይህንን ያልታሰበ ወጪ በሚያመርቱ ምርት ዋጋ ላይ በመጨመር ኪሳራቸውን ሊያጣጡት ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ አሁንም ተባብሶ ያለውን የዋጋ ንረት የበለጠ የሚያባብሰው መሆኑን አቶ አበባየሁ ገልጸዋል፡፡

በኤክስፖርት ላይ የተሰማሩም ኩባንያዎች በተመሳሳይ ችግር የሚገጥማቸው በመሆኑ የንብረት ግብር ግድ ከሆነ የኢንዱስትሪውን አቅም ያገናዘበ መሆን እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡ የዚህ የግብር ዓይነት ሊያስከትል ከሚችለው ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ባሻገር፣ የዜጎች የንብረት መብት ላይም ጥያቄ የሚያስነሳ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡ ግብሩ የሚከፈለው ከትርፍ ላይ በመሆኑም ከአሠራር አንፃር አፈጻጸም ላይ ችግር ሊፈጥር የሚችል ስለመሆኑ የጠቀሱት አቶ አበባየሁ፣ ይህንን ግብር ያለመክፈል ደግሞ በኢንዱስትሪው የሥራ እንቅስቃሴዎችን ሊያስተጓጉል ይችላል፡፡

ምክንያቱም ይህንን የንብረት ግብር ሳትከፍል አገልግሎት የምትከለከል ከሆነ ሥራ ቆመ፣ ፋብሪካው ተዘጋ ማለት ነው፡፡ ኢንዱስትሪዎች በአብዛኛው ሥራቸውን የሚሠሩት በባንክ ብድር በመሆኑ፣ ብድር ለማግኘት የግድ የግብር ክሊራንስ ማቅረብ የሚጠይቅ በመሆኑ ለሥራ ማስኬጃ የሚሆን ብድር እንኳን ላያገኙ የሚችሉበት ዕድል እንደማይኖር ገልጸዋል፡፡  

ስለዚህ እንደ ዘርፍ ምክር ቤትም፣ እንደ ማኅበርም መንግሥት ኢንዱስትዎቹ ያሉበትን ተጨባጭ እውነታ ቀርቦ እንዲመለከት አቶ አበባየሁ ጠይቀዋል፡፡

ለሠራተኞቹ መመገቢያ፣ ልብስ መቀየሪያና ለጥበቃ ቤት ተብለው በቆርቆሮ የተሠሩ ሼዶችን ከቋሚ ንብረት እኩል ታክስ እንዲከፍሉባቸው መጠየቁ ፈጽሞ ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከወረዳ አስፈጻሚዎቹ ያገኙት መልስ ከላይ የመጣ መመርያ በመሆኑ በብሎኬት የተሠራውም ሆነ በቆርቆሮ የተሠራው ለብሎኬት ግንባታ በተተመነው 417 ብር በካሬ ታክስ መክፈል እንደሚጠበቅባቸው ነው፡፡  

ኢንዱስትሪዎቹ ይህንን ክፍያ እንዲከፍሉ የሚገደዱ ከሆነ ሠራተኛ በመቀነስ ወጪ የማጣጣት አማራጭ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ የሚል ሥጋታቸውንም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም፣ የንብረት ግብሩን ክፈሉ የተባሉበት ወቅት ዋናው ዓመታዊ ግብር የሚከፈልበት ወቅት ጋር የተገናኘ በመሆኑ ጫናው ከባድ እንደሚሆን አቶ አበባየሁ አብራርተዋል፡፡

እንደ እሳቸው እምነት የፌዴራል መንግሥትም ጣልቃ ገብቶ ይህንን ነገር ማስተካከል መቻል አለበት፡፡ ‹‹በጥቅል ሲታይ እንደ ዜጋ ማድረግ የሚገባን ነገር እንዳለብን እናምናለን፤›› ያሉት አቶ አበባየሁ፣ ጥያቄያቸው እንዲህ ያለ የታክስ ዓይነት መጣል የለበትም ሳይሆን ተጋንኖ መቅረቡና የኢንዱስትሪውን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ በመሆኑ ታሪፍ እንዲስተካከል ጋር መነጋገር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ኢንዱስትሪው መደገፍ አለበት እየተባለ የበለጠ የሚያቀጭጨውን ተግባር መፈጸም ተገቢ እንዳልሆነም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ኢንዱስትሪው ከባህሪው አንፃር መመዘን እንደሚኖርበትና ዘርፉ እንደ ሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ መታየት እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ወደ መስመር ለማስገባት ጊዜ የሚጠይቅ ከመሆኑ አንፃር፣ እንዲህ ያሉ ጫና ሊያሳድሩ የሚችሉ የተጋነኑ ክፍያዎች ሊጤኑ እንደሚገባ አቶ አበባየሁ ተናግረዋል፡፡  

‹‹ኢንዱስትሪ ሒደት በመሆኑ የግንባታ ፈቃድ ከተገኘ በኋላ የሦስትና አራት ዓመታት ሊወስድ ይችላል፡፡ ግንባታው ካለቀ በኋላ የውጭ ምንዛሪ አግኝቶ ማሽኑን ለመግዛትና ሥራ ሳይጀምር የሚወስደው ጊዜም ስላለ በዚህ ውጣ ውረድ ብዙ ነገር ይታጣል›› ያሉት አቶ አበባየሁ፣ ‹‹እንዲህ ያሉ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ ውስጥ የንብረት ታክስ ክፈሉ መባላቸው ምን ያህል ትክክል ነው?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

መንግሥት ሆነ የከተማ አስተዳደሩ ኢንዱስትሪዎች በመክሰራቸው የሚያተርፉት ነገር ስለሌለ ጉዳዩን ሊፈተሹ ይገባልም ብለዋል፡፡ ይህ የንብረት ታክስ ጉዳይ የንግዱ ኅብረተሰብ ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተፅዕኖ በተመለከተ፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በነገው ዕለት የውይይት መድረክ ያዘጋጀ መሆኑም ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች