- መንግሥት ስለሰላም አብዝቶ የሚናገረው ለምን እንደሆነ ታውቂያለሽ?
- ኧረ ጨርሶ ሲናገር ሰምቼ አላውቅምኧ ይናገራል እንዴ?
- እንዴታ፡፡
- ስለሰላም ይናገራል?
- አዎ፣ የመንግሥትም ሆነ የፓርቲያችን የሙሉ ጊዜ ሥራ በሰላም ላይ ነው።
- ይህንን አላውቅም ነበር።
- ለምን ይመስልሻል በዚህ ልክ ስለሰላም ከፍተኛ ትኩረት የሰጠነው?
- እንኳን ምክንያቱን ትኩረት መስጠታችሁንም አላውቅም እያልኩህ?
- የሰላም ጉዳይ ዋናው ትኩረታችን ነው ስልሽ፣ ቆይ ለምን እንደሆነ ላስረዳሽ።
- እህ…
- ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት በመሆኑ ነው።
- እህ… ለዚያ ነው?
- አዎ፣ ምክንያቱም ሰላም ከሌለ ተቃራኒው ነው የሚኖረው።
- ተቃራኒው ምንድነው?
- ግጭትና ጦርነት ነዋ።
- አዎ፣ ልክ ብለሃል።
- ግጭትና ጦርነት ደግሞ የዜጎችን ደኅንትና ነፃነት አደጋ ላይ ይጥላሉ።
- እህ… ለሰላም ትኩረት የሰጣችሁት በዚህ ምክንያት ነው?
- በዚህ ብቻ አይደለም፣ ሌሎችም ምክንያቶች አሉ።
- ምንድናቸው?
- ቅድም ግጭትና ጦርነት የዜጎችን ደኅንነትና ነፃነት አደጋ ላይ ይጥላሉ ነበር ያልኩሽ አይደል?
- አዎ።
- ሌላው ደግሞ ግጭትና ጦርነት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ያውካሉ።
- አሃ… በዚህ መልኩ አልተረዳሁትም ነበር።
- ይኼ ብቻ መስሎሽ ነው?
- እ…?
- ግጭትና ጦርነት ካለ የሰው ልጆች ሕይወት ይቀጥፋል፣ ሀብትና ንብረትም ይወድማል።
- እህ… ለዚህ ነዋ መንግሥት ለሰላም ትኩረት የሰጠው?
- በሚገባ፣ አለበለዚያማ ይቻልም።
- ምንድነው የማይቻለው?
- ብልፅግናን ማረጋገጥ።
- አሃ… እንደዚያ ነው?
- አዎ፣ አዲሱ የፓርቲያችን ፍልስፍናም በዚህ ላይ ተመሥርቶ የተቀረፀ ነው።
- አዲሱ ፍልስፍና ምንድነው የሚለው?
- ግጭትና ጦርነት የብልፅግና ፀር ናቸው የሚል ነው።
- እጅግ ጥሩ የአስተሳሰብ ለውጥ ነው ያደረጋችሁት።
- የአስተሳሰብ ለውጥ አድርገን አይደለም።
- እህ…?
- የፓርቲያችን ተፈጥሯዊ ባህሪይ ነው።
- እንደዚያ ነው?
- እየነገርኩሽ፣ ትጠራጠሪያለሽ እንዴ?
- መጠራጠሬ ሳይሆን ትዝ ብሎኝ ነው።
- ምኑ?
- ያሳለፍናቸው ሦስት ዓመታትና…
- እና ምን?… ቀጥይ
- አሁን ያለንበት ሁኔታ አንተ ከምትለው ጋር አልታረቅ ብሎኝ ነው።
- ለምን አልታረቅ ይልሻል? ምን ለማለት ፈልገሽ ነው?
- ሰላም የሙሉ ጊዜ ሥራችን ነው ብትሉም፣ አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች አሉ ብዬ ነው።
- ግጭቶች ቢኖሩስ?
- ግጭትና ጦርነት የብልፅግና ፀር ነው ብለኸኝ አልነበርም እንዴ ቅድም?
- አዎ።
- ጠመንጃ ይዘው በየአካባቢው የሚታገሉ ባሉቡት ሁኔታ የምትሉት ሰላም እንዴት ሊመጣ እንደሚችል እያሰብኩ ነው።
- ይመጣል፣ ቀላል ነው።
- ቀላል ነው?
- አዎ፣ በጣም ቀላል ነው።
- እንዴት?
- የአገር ሽማግሌዎችንና የሃይማኖት አባቶችን በመጠቀም ወደ ሰላም እንዲመጡ ጥሪ እናቀርባለን።
- ጥሪውን ካልተቀበሉስ?
- እንደመስሳቸዋለን!
- Advertisment -
- Advertisment -