Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በመጪው ዓመት በኦሮሚያ ክልል ብቻ 130 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

እስከ ተያዘው ሰኔ ወር ድረስ 71.9 ቢሊዮን ብር ገቢና ቀረጥ መሰብሰቡን ያስታወቀው የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ቢሮ፣ በ2016 የበጀት ዓመት 130 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱ ተገለጸ፡፡

በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ መስከረም ደበበ እንዳስታወቁት፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የክልሉን ወጪ በክልሉ ገቢ ለመሸፈን ገቢ ሰብሳቢ ተቋሙ በሠለጠነ የሰው ኃይልና ቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ሰፊ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡

ቢሮው በ2010 ዓ.ም. ይሰበሰብ የነበረው 16 ቢሊዮን ብር ገቢ በፍጥነት እያደገ፣ በ2015 ዓ.ም. እስከ ተያዘው ወር ድረስ 71.9 ቢሊዮን ብር መድረሱን የቢሮ ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡

በ2016 የበጀት ዓመት ይሰበሳባል የተባለው 130 ቢሊዮን ብር ገቢ በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ 24 ሺሕ የደረጃ ‹‹ሀ›› ግብር ከፋዮች፣ 18 ሺሕ የደረጃ ‹‹ለ›› ግብር ከፋዮች፣ እንዲሁም 456 ሺሕ ከሚጠጉ የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች ይሆናል ተብሏል፡፡

በክልሉ ከገቢ ግብር በተጨማሪ በኬላዎች የተለያዩ አገልግሎቶችን መሠረት ያደረገ የሚሰበሰብው ቀረጥ መኖሩንና በምዕራብ አርሲ ሻሸመኔ፣ በምዕራብ ሐረርጌ ቦርደዴ፣ በምሥራቅ ሐረርጌ አወዳይ፣ ባቢሌ፣ ደንገጎና ጉርሱም ከተሞች፣ እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ተጂ ከሚገኙ ማዕከላት የሚሰበሰብ ቀረጥ ነው ብለዋል፡፡

በ2016 የበጀት ዓመት 130 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ እንደታቀደ ይፋ ያደረጉት ወ/ሮ መስከረም፣ የኦሮሚያ ክልል እንደ አገራዊው የአሥር ዓመት ዕቅድ ሁሉ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያመነጨውን ገቢ ጋር ሊመጣጠን የሚችል ግብርና ቀረጥ መሰብሰብ አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑን በማቀድ መሆኑን አክለዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የታክስ አሰባሰብ ሥርዓቱ አሁን ካለው አሠራር ይበልጥ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ፣ ተደራሽ፣ ወጪ ቆጣቢና ከብልሹ አሠራር የፀዳ ለማድረግ ቁርጠኛ አቋም ይዟል ሲሉ ያስረዱት ኃላፊዋ፣ ለዚህም አሠራሩን  ከቴሌ ብር የአሠራር ሥርዓት ጋር በማቀናጀት የክልሉን ገቢ አሰባሰብ ወደ ዲጂታል በመቀላቀል ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል ብለዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ከኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ባደረገው ስምምነት መሠረት የኦሮሚያ ክልል የገቢዎች ቢሮ የግብር አሰባሰብ ሥርዓቱን በዲጂታል ሲስተም የተደገፈ በማድረግ የዘመነ የግብርና የቀረጥ አሰባሰብ ሥርዓት ለመዘርጋት፣ ለደንበኞች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት፣ የሥራ ማስኬጃ ወጪንና ጊዜ ለመቆጠብ፣ የክፍያ ደረሰኝ ማጭበርበርን ለማስወገድ፣ ኢንቨስትመንትን ወደ ክልሉ ለመሳብና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚያስችለው እንደሚሆን ሁለቱ ተቋማት በስካላይት ሆቴል ባደረጉት የስምምነት ሥነ ሥርዓት ላይ ተገልጿል፡፡

የቴሌኮም ኩባንያው በቅርቡ ከገቢዎች ሚኒስቴርና ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በፈጸመው ስምምነት የከፍተኛ ግብር ከፋዮችን ግብር በወቅቱ ለመሰብሰብ፣ እንዲሁም ወደ አገር ውስጥ ለሚገቡ ዕቃዎች የጉምሩክ ቀረጥ ክፍያን በቀላሉ መፈጸም የሚያስችል አሠራር ተግባራዊ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ ከሌሎች ክልሎች ጋርም በተመሳሳይ የግብር ክፍያን በቴሌ ብር መፈጸም የሚያስችል አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝ ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች