Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ከሁለት ሺሕ በላይ አመራሮቼና ደጋፊዎቼ ታስረዋል አለ

የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ከሁለት ሺሕ በላይ አመራሮቼና ደጋፊዎቼ ታስረዋል አለ

ቀን:

‹‹ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በነበረው ግጭት ከ1,500 በላይ የሰው ሕይወት ጠፍቷል›› ብሏል

የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቅዴፓ) ከሁለት ሺሕ በላይ ከፍተኛ አመራሮቹ፣ አባላቱና ደጋፊዎቹ ከአምስት ዓመት በላይ ያለ ክስና ፍርድ እንደታሰሩበት አስታወቀ፡፡

የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎችና የሕዝብ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ያለ ምንም ክስና የፍርድ ቤት ውሳኔ ከአምስት ዓመት በላይ በእስር ላይ እንደሚገኙ፣ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ አውግቸው ማለደ ተናግረዋል፡፡

ምክትል ሊቀመንበሩ ይህን ያሉት ፓርቲው ‹‹በቅማንት ሕዝብ ላይ እየደረሰ ነው›› ያለውን በደል አስመልክቶ ያጠናቀረውን መረጃ፣ ሰኔ 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ ሲያስታውቅ ነው፡፡

‹‹በተለይ በአማራ ክልል የቅማንት ሕዝብ ሰፍሮ በሚገኝባቸው ማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በነበረው ግጭት ከ1,500 በላይ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤›› ያለው ፓርቲው፣ ‹‹ግምቱ ከ334 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን ሀብትና ንብረት እንዲዘረፍ፣ እንዲቃጠልና ከጥቅም ውጭ እንዲሆን ተደርጓል፤›› ሲል በመግለጫው አስታውቋል፡፡

ከመንግሥት ሥራቸው የተፈናቀሉ ከ443 በላይ ሠራተኞች መሆናቸውን፣ ከ80 ሺሕ በላይ የሚሆኑ የብሔረሰቡ ተወላጆች በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ተፈናቅለው እስካሁን (ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ) ወደ መኖሪያ ቤታቸው መመለስ እንዳልቻሉ የገለጸው ቅዴፓ፣ ‹‹በተለይም ከአገር ውጭ በሱዳን መጠለያ ካምፕ ከ12 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ንፁኃን ዜጎች ከሁለት ዓመት በላይ በረሃብ እየተሰቃዩ ይገኛሉ፤›› ብሏል፡፡

ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ የብሔረሰቡ ተወላጆች ባልተጣራና በሐሰት ውንጀላ ተከሰው በፍርድ ቤት ተወስኖባቸው እንደነበር ገልጾ፣ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ያለ ምንም ክስና የፍርድ ቤት ውሳኔ ጎንደር ማረሚያ ቤት በእስር እየተሰቃዩ ይገኛሉ፤›› ሲል በመግለጫው ጠቅሷል፡፡

በአካባቢው ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ምክንያት በማድረግ በተለያዩ ማረሚያ ቤቶችና ፖሊስ ጣቢያዎች ከሁለት ሺሕ በላይ የሚሆኑ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች፣ እንዲሁም የሕዝቡ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ያለ ምንም ክስና የፍርድ ቤት ውሳኔ ከአምስት ዓመት በላይ እየተሰቃዩ እንደሚገኙ ፓርቲው አስታውቋል፡፡ በተለይ ታኅሳስ 7 ቀን 2015 ዓ.ም. በክልሉ መንግሥት፣ በመከላከያ፣ በሃይማኖት አባቶችና በአገር ሽማግሌዎች አማካይነት ሸሽተው ጫካ የነበሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች በምኅረት እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ 134 ያህል የፓርቲው አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎችና የኮሚቴ አስተባባሪዎች እንደታሰሩበት ገልጾ አፋጣኝ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡

ችግሩ የተፈጠረበትን ምክንያት በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት የፓርቲው ምክንትል ሊቀመንበር አቶ አውግቸው፣ የቅማንት ብሔረሰብን እንደ ኢትዮጵያዊ የማይቆጥሩ፣ ማንነቱንና ባህሉን እንዲያሳድግ የማይፈልጉ ምክንያት መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የቅማንት ብሔረሰብ የጠየቀውን ትክክለኛ ሕገ መንግሥታዊ የሆነ የማንነነትና የራስ አገዛዝ ጥያቄ በሕዝቡ ፍላጎት መሠረት አወያይቶ ዘላቂ መፍትሔ በአግባቡ እንዲያገኝ፣ በጎንደር ከተማ ‹‹ተዘግተውብኛል›› ያላቸው የፓርቲው የማስተባባሪያ ቢሮዎች እንዲከፈቱ፤ በአካባቢው በ2013 ዓ.ም. ያልተካሄደው ምርጫ በ2016 ዓ.ም.  ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ያለ ምንም የፀጥታ ችግር እንዲከናወን  መንግሥት ኃላፊነት እንዲወስድ ሲል ፓርቲው አሳስቧል፡፡

አሁንም ሰላሙ ባልተረጋገጠበት መተማ ወረዳ የንፁኃን ዜጎች ዕገታና የአርሶ አደሮች ሀብት ዘረፋ፣ ማፈናቀልና ወካባ ተጠናክሮ እንደቀጠለና አፋጣኝ ዕርምጃ ተወስዶ ሰላም እንዲረጋገጥ፣ የሚመለከተው አካል የተፈናቀሉ ባለሀብቶችና አርሶ አደሮች ወደ ቤታቸውና ሥራቸው እንዲመለሱ እንደያደርግም ፓርቲው ጠይቋል፡፡

ፓርቲው ‹‹ኢመደበኛ አደረጃጀቶች›› ሲል በጠራቸው ‹‹የፋኖ ታጣቂዎች›› ወደ አጎራባች ወረዳዎችና ወደ ሱዳን የተሰደዱ የብሔረሰቡ ተወላጆች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ፣ ከመንግሥት ሥራ የተፈናቀሉ ሠራተኞች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ፣ ኪሳራ በደረሰባቸው ዜጎችን መልሶ ማቋቋሚያና የካሳ ክፍያ እንዲፈጸም ፓርቲው ጥያቄ አቅርቧል፡፡

ፓርቲው አክሎም፣ ‹‹በተለይ የአማራ ክልል አርሶ አደሮች በአፈር ማዳበሪያና  በምርጥ ዘር እጥረት ችግር ውስጥ የገቡ ስለሆኑ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥ የመንግሥትን ትኩረት እንጠይቃለን፤›› ሲል አሳስቧል፡፡

ቅዴፓ ደርሶብኛል ያለውን በደል በተመለከተ ምን ምላሽ እንዳላቸው ሪፖርተር በስልክ ያነጋገራቸው የአማራ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ፣ ‹‹ቅማንት የሚባል ፓርቲ አናውቅም፣ ካለ አጣርቼ እናገራለሁ፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...