Saturday, September 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከ316 ሺሕ በላይ ሰዎች በወባ መጠቃታቸውን የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ

ከ316 ሺሕ በላይ ሰዎች በወባ መጠቃታቸውን የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ

ቀን:

  • በአማራ ክልል የወባ በሽታ ሥርጭት መጨመሩ ተገልጿል

ከ316 ሺሕ በላይ ሰዎች በወባ በሽታ መጠቃታቸውን የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ የወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ፕሮግራም በተለይ በክልሉ ደቡባዊ ክፍል ማለትም በደራሼና ባስኬቶ፣ በኮንሶ ዞን፣ በጋሞ ዞን፣ በወላይታ ዞን፣ እንዲሁም በደቡብ ኦሞ ዞን በዳሰነችና ሰላማጎ ወረዳዎች የበሽታው ሥርጭት ከፍተኛ በመሆኑ ነዋሪዎቹ መጠቃታቸውን ገልጿል፡፡

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር የወባ ማስወገድ ፕሮግራም አማካሪ አቶ ሔኖክ በቀለ፣ ከ316 ሺሕ በላይ ሰዎች በወባ በሽታ መጠቃታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በበሽታው ሳቢያ የሞቱ ሰዎች መኖርና አለመኖራቸውን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነችና ሰላመጎ ወረዳዎች ሁለት ሰዎች መሞታቸውን አቶ ሔኖክ ተናግረዋል፡፡

በሽታው በተለይ በደቡብ ኦሞ ዞን ሊስፋፋና ሞት እስከ ማስከተል ደረጃ የደረሰው ማኅበረሰቡ ለአጎበር አጠቃቀም ያለው አመለካከት ዝቅተኛ ስለሆነ፣ እንዲሁም በአካባቢው ሙቀት የሚበረታበት ወቅት በመሆኑ ነዋሪዎች ከቤት ውጪ ማደርን ስለሚመርጡ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ከ316 ሺሕ በላይ ሰዎች በበሽታው የተጠቁት ከ2014 ሐምሌ ወር ጀምሮ መሆኑን፣ በሽታው እንዳይስፋፋ የወባ ማጥፊያ ኬሚካል እርጭት እየተደረገ እንደሆነ፣ ተጠቅተዋል የተባሉት ሰዎች ሕክምና እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም አቶ ሔኖክ አስረድተዋል፡፡

በተያያዘ ዜና በአማራ ክልል የወባ በሽታ በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ መሆኑንና በ2015 በጀት ዓመት በበሽታው የሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለሪፖርተር አስታውቋል፡፡

በ2015 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ብቻ ከ910 ሺሕ በላይ ሰዎች በወባ በሽታ መጠቃታቸውን፣ የክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወባ በሽታ ማስወገድ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዳምጤ ላንክር ገልጸዋል፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት በበሽታው የተጠቁ ሰዎች ቁጥር በስምንት ቀናት ብቻ 751 ደርሶ እንደነበር የገለጹት አስተባባሪው፣ በአጠቃላይ በ2015 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ብቻ ከ910 ሺሕ በላይ ሰዎች በበሽታው መጠቃታቸውን አስረድተዋል፡፡

በበሽታው የተጠቁ ከፍተኛ የሕሙማን ቁጥር የተመዘገበባቸው ደቡብ ጎንደር ዞን 293 ሺሕ፣ ምዕራብ ጎጃም ዞን 231 ሺሕ፣ ማዕከላዊ ጎንደር ከ257 ሺሕ በላይ፣ ምዕራብ ጎንደር ከ117 ሺሕ በላይ፣ እንዲሁም ደቡብ ጎንደር ከ114 ሺሕ በላይ ሰዎች በበሽታው እንደተጠቁ አቶ ዳምጤ ተናግረዋል፡፡

ከፍተኛ የወባ በሽታ ሥርጭት ያለባቸው አካባቢዎችን ሲዘረዝሩም በምዕራብ ጎንደር (በተለይ መተማ፣ ቋራ፣ አርማጭሆ)፣ በደቡብ ጎንደር፣ በማዕከላዊ ጎንደር፣ በወልቃይት ጠገዴ፣ በአዊ ዞን፣ በባህር ዳርና በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከፍተኛ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በ2015 በጀት ዓመት 24 ሰዎች በወባ በሽታ ምክንያት ሕይወታቸው እንዳለፈም አስተባባሪው አክለው ገልጸዋል፡፡

የወባ በሽታን ለመከላከል የሚያስችለው አጎበር እጥረት እንዳጋጠመ ያስረዱት አቶ ዳምጤ፣ ‹‹በክልሉ ሁለት ሚሊዮን ሰዎች አጎበር አላገኙም፤›› ብለዋል፡፡

በተያዘው ዓመት 3.9 ሚሊዮን አጎበሮችን በ82 ወረዳዎች ማሠራጨት ቢቻልም፣ ለሥርጭት ያስፈልግ የነበረው ከ4.8 ሚሊዮን በላይ አጎበር ስለነበር ለሁሉም አካባቢዎች ማሠራጨት አልተቻለም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በክልሉ ያለው የወባ ሥርጭት በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ክልሎች ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዝ አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡ በአማራ ክልል ሥርጭቱ ከፍተኛ የሆነበት ምክንያት ምን እንደሆነ እንዲያስረዱ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹በክልሉ 82 በመቶ የሚሆኑት ቦታዎች ለወባ መራቢያ ምቹ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

ከሁለቱም ክልሎች የተገኘው ገለጻ የሚያሳው፣ የበሽታው ሥርጭት ከፍተኛ እንደሆነ ነው፡፡ በአጠቃላይ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወባ በሽታ ሲጠቁ፣ የሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...