Tuesday, October 3, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዋጭ ላልሆኑ አካባቢዎች የቴሌኮም አገልግሎት ለማዳረስ በጀት መመደብ ኃላፊነቱ እንዳልሆነ ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የቴሌኮም ዘርፉ ለውድድር ገበያ በመከፈቱ የቴሌኮም አገልግሎት ላልተዳረሰባቸውና አዋጭ ላልሆኑ የገጠር አካባቢዎች በጀት መመደብ ኃላፊነቱ እንዳልሆነ፣ ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ይህንን ያስታወቀው የሁሉን አቀፍ ተደራሽነት ኃላፊነትን ለመወጣት በጀት መበጀቱን አስመልክቶ፣ የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ላነሱት ጥያቄ ነው፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ የተቋማቸው የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም በፓርላማው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዓርብ ሰኔ 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ሲገመገም ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል፣ የቴሌኮም አገልግሎት ያልተዳረሰባቸው አካባቢዎችን ለማዳረስ ተፈላጊው በጀት ተበጅቷል ወይ? ካልተበጀተ ምን ታስቧል? የሚሉ ይገኙበታል፡፡

በኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያ ለውድድር ክፍት በመሆኑ ሁሉን አቀፍ ተደራሽነት ለማረጋገጥ በገጠር አካባቢዎችና አዋጭ ባልሆኑ አካባቢዎች በጀት መበጀት የኢትዮ ቴሌኮም የሥራ ድርሻ ብቻ ተደርጎ ሊወሰድ እንደማይገባ፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ለቀረቡት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ አስረድተዋል፡፡

ዘርፉን የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን በመሆኑ፣ ባለሥልጣኑ ከመንግሥትም ሆነ ከሌሎች አካላት በጀት አፈላልጎ በኢንዱስትሪው አሠራር መሠረት ለቴሌኮም ኦፕሬተሮች እንደሚያቀርብ፣ እስካሁን ውይይቶች ከመደረጋቸው ውጪ የቀረበ ነገር አለመኖሩን ወ/ሪት ፍሬሕይወት ለቋሚ ኮሚቴው አባላት አብራርተዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ቢዝነሱን ብቻ ሳይሆን ከማኅበራዊ ኃላፊነቱ ጋር በተገናኘ ለገጠር አካባቢዎች ተደራሽነት ምላሽ ለመስጠትና ለማረጋገጥ እየተጋ መሆኑን ያስታወሱት ወ/ሪት ፍሬሕይወት 121 የሥራ ትዕዛዝ የወጣላቸው፣ ጥናት የተከናወነላቸውና የቦታ አቅርቦት የተመቻቸላቸው ማስፋፊያዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

‹‹በ2016 የበጀት ዓመት ደግሞ ተጨማሪ 161 ይኖረናል፤›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ ሥራው ሙሉ ኃላፊነቱ የኢትዮ ቴሌኮም ስለሆነ ሳይሆን አገልግሎት እንዳይቋረጥ የሚወሰድ ዕርምጃ መሆኑንና ተጨማሪ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ ቢሆንም፣ ከሚመለከተው አካል ለዚህ ተብሎ የተመደበ ምንም ዓይነት በጀት የለም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹ጥገና ላደረግንላቸው፣ በጦርነትና በፀጥታ ምክንያት ወድመው መልሰን ለገነባናቸው መሠረተ ልማቶች ምንም ዓይነት ተጨማሪ በጀት ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ አካል አግኝተን እንዳልሆነ ከግንዛቤ ይያዝ፤›› ሲሉ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ለቋሚ ኮሚቴው ገልጸዋል፡፡

አዋጭ ባልሆኑ አካባቢዎች 52 በመቶ ኢንቨስትመንት ለሚሆኑ ማስፋፊያዎች መደረጉን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ ‹‹የሚነሱት ጥያቄዎች ምንም እንዳልተሠራ ነው፣ ይኼ በጣም አደገኛ ነው፡፡ ማስፋፊያዎቹ የሚደረጉት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ መሆናቸውን ታሳቢ ያላደረገ ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት አጠቃላይ የደንበኞቹን ቁጥር 71.5 ሚሊዮን ሲያደርስ፣ ከዚህ ውስጥ 69.1 ሚሊዮኑ የሞባይል ድምፅ፣ 34.1 ሚሊዮን የሞባይል ዳታና ኢንተርኔት ደንበኞች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ 52.7 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱን ያስታወቀው ኢትዮ ቴሌኮም፣ የውጭ ምንዛሪ ከሚያገኝባቸው አገልግሎቶች ደግሞ 103.1 ሚሊዮን ዶላር አግኝቻለሁ ብሏል፡፡

በፀጥታና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የሚደርሱ ጉዳቶች በበጀት ዓመቱ እንደፈተኑት በሪፖርቱ የገለጸው ኢትዮ ቴሌኮም፣ በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት በሰባት ክልሎች አገልግሎት ላቋረጡ 853 የሞባይል ጣቢያዎችና ለ1,886 ኪሎ ሜትር ፋይበር ጥገና ማድረጉን አስታውቋል፡፡

በተደረገው አፋጣኝ ጥገና 172 አገልግሎት ተቋርጦባቸው የነበሩ ወረዳዎች እንደገና አገልግሎት እንዳገኙ፣ በዚህም 29 የፋይናንስ ተቋማት ተመልሰው አገልግሎት መስጠት ቢጀምሩም ቀሪ ያልተጠገኑ 352 የሞባይል ጣቢያዎች አሁንም መኖራቸውን ኢትዮ ቴሌኮም ገልጿል፡፡

ከኢትዮ ቴሌኮም ትርፋማት ጋር በተያያዘ ለመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጻ ያደረጉት የኩባንያው ቺፍ ፋይናንስ ኦፊሰር አቶ አሰግድ አየለ፣ ኢትዮ ቴሌኮም እ.ኤ.አ. ከ2016 በፊት ትርፍ ለማግኘትና ኢንቨስት ለማድረግ የተቸገረበት ሁኔታ እንደነበር አስታውቀው፣ ከሪፎርሙ በኋላ ግን ደረጃ በደረጃ ከ12 በመቶ ተነስቶ አሁን 22 በመቶ አትራፊ የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል፡፡ በአኃዝ ግን አልገለጹም፡፡

ኃላፊው በርካታ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ያለፈው ኢትዮ ቴሌኮም ከተፈተነባቸው ጉዳዮች ውስጥ፣ በግብዓት ዋጋ ላይ የተፈጠረው ንረትና የውጭ ምንዛሪ ኪሳራ ዋነኞቹ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት አምስት ዓመታት ከ31 ቢሊዮን ብር በላይ የውጭ ምንዛሪ ኪሳራ እንደገጠመው አቶ አሰግድ አክለዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ኢትዮ ቴሌኮም ጥሩ እንቅስቃሴ ያለው ተቋም መሆኑን ተናግረው፣ የተቋሙ እንቅስቃሴ ስኬት የበለጠ እንዲያድግ ያሉ ውስንነቶች ቢስተካከሉ ደግሞ የተሻለ ይሆናል ብለዋል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ሥራቸው የሚሆነው ትርፋማነትና የሕዝብ ተጠቃሚነት ነው ያሉት ምክትል ሰብሳቢው፣ ይህንን ማመጣጠን የሚለውን በደንብ ማየት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

ኔትወርክን በተመለከተ የሚከናወኑ ሥራዎች እንዳሉ ሆነው ከተደራሽነት ጋር በተገናኙ ያሉ ውስንነቶች በቶሎ ሊታረሙ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች