Tuesday, March 25, 2025
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበትግራይ ክልል ጦርነቱ በተማሪዎች ላይ ከፍተኛ የመማር አቅም መቀነስና የሥነ ልቦና ጉዳት...

በትግራይ ክልል ጦርነቱ በተማሪዎች ላይ ከፍተኛ የመማር አቅም መቀነስና የሥነ ልቦና ጉዳት ማስከተሉ ተገለጸ

ቀን:

spot_img

በትግራይ ክልል በጦርነቱ ሳቢያ ተማሪዎች ለበርካታ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት መዳረጋቸውን የሚያረጋግጥ ጥናት ይፋ ተደረገ፡፡ የሁለተኛ፣ የሦስተኛና የአራተኛ ክፍል ታዳጊዎችን ትምህርት አቀባበል አቅም የፈተሸው ጥናቱ፣ ጦርነቱ የተማሪዎቹን የመማር አቅም በከፍተኛ ሁኔታ እንደጎዳው የሚያረጋግጥ ግኝት ይፋ አድርጓል፡፡

ሐሙስ ሰኔ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. በመቀሌ ከተማ ጥናቱ ይፋ ሲደረግ 2.4 ሚሊዮን የትግራይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን ጨምሮ፣ ጦርነቱ በዘርፉ ያስከተላቸው ጉዳቶችን አመላካች የሆኑ አኃዞች ቀርበዋል፡፡  

መሠረታዊ የሒሳብ፣ የእንግሊዝኛና የትግርኛ ቋንቋ ትምህርቶች ፈተና ከተሰጣቸው 600 ታዳጊ ተማሪዎች ውስጥ አምስት በመቶ የሚሆኑት ብቻ አጥጋቢ ውጤት ማምጣታቸውን በጥናቱ ተመላክቷል፡፡ ወደ 35 በመቶዎቹ ዝቅተኛ የሚባለውን የማሟያ ውጤት እንዳመጡ የተነገረ ሲሆን፣ ከ50 በመቶ በላይ የሆኑት መሠረታዊ ከሚባለው የትምህርት አቀባበል ወለል በታች የሆነ እጅግ ዝቅተኛ ውጤት አምጥተዋል ተብሏል፡፡

በመቀሌ ከተማና ዙሪያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ የሚኖሩ 600 ታዳጊ ተማሪዎችን ጨምሮ ወደ 450 ወላጆችን፣ እንዲሁም 400 መምህራንን ጥናቱ ማካተቱ ተነግሯል። በ20 መረጃ አሰባሳቢዎች የተመራው ጥናቱ በትግራይ ጦርነት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ለመሆን ከመገደዳቸው በተጨማሪ፣ ለሥነ ልቦናና የአካል ጉዳት ተዳርገዋል ይላል። በጦርነቱ ከ77 እስከ 93 በመቶ የትግራይ ክልል ትምህርት ቤቶች ለጉዳት መዳረጋቸውም ተነግሯል። ተማሪዎች፣ መምህራንና ወላጆች የመማር ማስተማሩ ሥርዓት በመቆሙ በቀጥታ ተጎጂ ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ በጦርነቱ ሳቢያ ለአካልና ለሥነ ልቦና ጉዳት መጋለጣቸው ተረጋግጧል ተብሏል።

ወደ ሰባት በመቶ ተማሪዎች በጥይት የመመታት አደጋ እንደገጠማቸው፣ 40 በመቶ ታዳጊዎች የሞተ ሰው አስከሬን ማየታቸው፣ እንዲሁም 29 በመቶ ሰዎች ሲገደሉ መመልከታቸውን አረጋግጠዋል ተብሏል፡፡ በተጨማሪም 72 በመቶዎቹ በቅርበት ተኩስ ሲካሄድ መመልከታቸውን፣ 62 በመቶዎቹ በጦርነት እሞታለሁ ብለው ይሠጉ እንደነበርና 70 በመቶዎቹ ደግሞ በረሃብ እንዳይሞቱ መፍራታቸውን እንደተናገሩ በጥናቱ ተገልጿል፡፡

የቤተሰባቸው አካል በግጭት ሲሞት ማየት፣ የጥይት ድምፅ በቅርበት መስማት ብቻ ሳይሆን ማስፈራራት፣ እስራት፣ አስገድዶ መድፈርና ሌሎች አሰቃቂ ክስተቶች ሲፈጠሩ በቅርበት ተማሪዎች፣ ወላጆችና መምህራን ለመመልከት ተገደዋል ይላል ጥናቱ። ይህ ደግሞ ብዙዎቹን ለሥነ ልቦና ጉዳት ዳርጓቸዋል ተብሏል።

እስከ አራተኛ ክፍል ባለው የትምህርት እርከን ታዳጊዎች መሠረታዊ የትምህርት ዕውቀት የሚጨብጡበት መሆኑን የጠቀሱት የጥናቱ መሪ በላይ ሐጎስ (ዶ/ር)፣ ጦርነቱ በትግራይ ክልል ተማሪዎች ላይ የመማር አቅም መቀነስን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ጉዳት ማድረሱ በጥናቱ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡  

በትምህርት ዘርፍ የሚሠራው ዓለም አቀፉ የሉሚነስ ፈንድ ድርጅት ከትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር ድጋፍ የተደረገለት ጥናቱ ገለልተኛ በሆነው የትምህርት፣ የጤናና የልማት ጥናት ተቋም ከአዲስ አበባና ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በተውጣጡ ምሁራን ተጠንቶ መቅረቡ ተነግሯል፡፡

በጥናቱ የተገኘው ውጤት ጦርነቱ በትግራይ ክልል ትምህርት ዘርፍ ላይ እጅግ ከባድ ተፅዕኖ ማሳደሩን እንደሚያረጋግጥ የጠቀሱት የሉሚነስ ፈንድ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዓለማየሁ ኃይሉ (ዶ/ር)፣ ጦርነቱ በሌሎች ክልሎች ያስከተለው የትምህርት ጉዳትም ሊጠና እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

‹‹አንዳንዶች የችግሩን ግዝፈት አሳነሳችሁት ይላሉ፡፡ ነገር ግን እኛ አንድ ድርጅት እንደ መሆናችን ሰፊ የሆነውን የትግራይ ክልል ለማዳረስ ከባድ ነው የሚሆነው፡፡ በአማራና በአፋር ክልሎች በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማትና ተራድኦ ድርጅት (USAID) በኩል የጦርነቱ የትምህርት ዘርፍ ጉዳት እየተጠና መሆኑን አውቃለሁ፡፡ እኛ የሠራነውም ሆነ እነሱ የሚሠሩት ጥናት ተመጋጋቢና አጠቃላይ የጦርነቱን ጉዳት ስፋት የሚያሳይ ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤›› ሲሉ የተናገሩት ዓለማየሁ (ዶ/ር)፣ የአሁኑ መነሻ እንጂ መጨረሻ እንደማይሆን ገልጸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም ኢኮኖሚ ከቀውስ ሥጋት የሚወጣው መቼ ነው? የኢትዮጵያስ እንዴት?

በጌታነህ አማረ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ኢትዮጵያ ለምታበስረውና ለምትከውነው ትንሳዔ ይረዳ...

የንብረቶች ዋጋ ማሽቆልቆልና የምግብ ነክ ሸቀጦች ዋጋ ንረት ተቃርኖ የነገሰበት የአገራችን ገበያ

በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ያልተቋረጠ የዋጋ ዕድገት እያሳዩ ሲጓዙ ከነበሩ...

ቀጣናዊ ቀውስ ሊፈጥር የሚችለው ውጥረት ይርገብ!

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በትግራይ ክልል ውስጥ በስፋት እየተስተዋለ ያለው...
error: