የተዋናይ መድረክ ዓለም በደፈና፤
ወንዱም ሆነ ሴቱ ተጫዋች በተራ።
መውጫቸው መግቢያቸው የተወሰነ ነው፤
አንድ ሰው በዕድሜው ብዙ ዓይነት ተራ አለው፤
ተራዎቹ ደግሞ ሰባቱ ዕድሜዎች፤ በፊት ሕፃን ሆኖ፤
በሞግዚቱ አንቀልባ የሚያለቅስ አስታውኮ።
ቀጥሎም አልቃሻ ተማሪ የሆነው፤ ኮረጆ ያዘለው
የማለዳ ገጹ እንዲያ የሚያበራው፤ ፍላጎት የሌለው
ልግመኛ ቀንዳውጣ ወደ ትምህርት ቤት የሚንፏቀቀው።
ግሎ እንደምድጃ ፍሞ እያቃሰተ፤ በሚያሳዝን ቅኔ
ለጮኛው ቅንድቦች የተገጠመላት አንድ ግሩም ዝማሬ፤
በውትድርና ዘብራቃ መኃላ ዘፍቆት ጢመ ነብሮ፤
ለክብሩ የሚቀና፤ ችኩል ላምባጓሮ፤
ሁሌም የሚያሳድድ የዝናን አረፋ
የመድፍ አፍም ቢሆን ከቶ የማይፈራ።
ከዚያም ዳኛ ሆኖ፤ ሙክት ዶሮ ሥጋ ቦርጩን የሞላው፤
ኮስተርተር ያሉ ዓይኖች፤ ጢምም እንደዚያው፤
ቋሚ ሕጎች ሆኑ ዘመናይ ደምቦችም ከቶ የማይገደው፡
እንደዚህ ተጫውቶ፤ ወደ ስድስተኛው ዕድሜ የሚያሸጋግረው
ወደ ከሲታና ሞላጫው ቦላሌ የተንቦለቦለ፤
ባፍንጫው መነጥር፤ ከረጢት በጎኑ የተንጠለጠለ፤
የልጅነት ሱሪው ይቅር ይቀመጥ፤ ዓለም ሰፍቶበታል
ዳሌውም ጠውልጓል፤ ደማቁ ልሳኑም ቀጭጯል አብቅቷል፤
የጭቅላ ድምጽ ሆኗል፤ ያናፋል ያፏጫል። በመጨረሻውም፤
እንደ ማሳረጊያ ለዚህ ድንቅ ታሪክም፤
ዳግመኛ ጭቅላነት መናኛ ዝንጋታ፤
ጥርስ አልባ፤ ዓይን አልባ፤ ጣዕም አልባ፤ ሁሉ አልባ።
*****ተፈጸመ*****
- በዊልያም ሼክስፒር፤ ነፃ ትርጉም በዳዊት ዘኪሮስ