Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአንባቢ ትውልድ ለማፍራት ያለመው የንባብ ሳምንት

አንባቢ ትውልድ ለማፍራት ያለመው የንባብ ሳምንት

ቀን:

በአበበ ፍቅር

‹‹ማንበብ ትልቅ ሰው ያደርጋል›› የሚለው አባባል ለብዙዎች ምስክር ሲሆን ይታያል፡፡ ከአራተኛ ክፍል ባልዘለቀ የትምህርት ደረጃ በማንበብ ብቻ ዕውቅ ጋዜጠኛና ጸሐፊ መሆን የቻለው አንጋፋው ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞን ማንሳት ይቻላል፡፡ በንባብ ራሳቸውን አንጋፋ ካስባሉ ሰዎች መካከል በብሬል የሚጻፉ ጽሑፎችን ብቻ በማንበብ ራሷን እንደቀየረች የሚነገርላት ሔለን ኬለር ተጠቃሽ ናት፡፡

እናም ሰዎች በንባብ ራሳቸውን ካበለፀጉና ካሳደጉ መድረስ ካለባቸውና የሚፈልጉትን ዓላማ ለማሳካት የሚያግዳቸው እንደሌለ በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ ደራሲዎችና ጸሐፊዎች የተለያዩ መጻሕፍትን በመጻፍና በማሳተም ለአንባብያን ያቀርባሉ፡፡ ይሁን እንጂ የሚጽፉቸው መጻሕፍት ለትውልድ ምን ያህል ጠቃሚ ናቸው? ራሳቸው ጸሐፊዎቹስ በሚጽፉት ዙሪያ ምን ያህል የታሪክ መዛግብት አገላብጠዋል? አንብበውስ ምን ያህል ተረድተው ነው የሚጽፉት? የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳት ተገቢ ነው፡፡

በሌላ በኩል ትውልዱ በቴክኖሎጂ ተፅዕኖ ሥር በመውደቅ፣ የማንበብ ባህሉን በመርሳት ላይ ነው የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ (ባኪቱ) ኃላፊ ሒሩት ካሰው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹አንባቢ ትውልድ የለም ብሎ ለመናገር አያስችልም፤›› ያሉት፣ ለንባብ ምቹ ባልሆነበት ሁኔታ እንኳን ሰዎች ቁጭ ብለው ሲያነቡ መታዘባቸውን በመጥቀስ ነው፡፡  ነገር ግን አንባቢውን የሸፈነው ነገር አለ፡፡ እሱም ቲክቶክ፣ ፌስቡክና የመሳሰሉት ማኅበራዊ ሚዲያዎች ናቸው፡፡ በዚህም ንባብ እንደጠፋ ተደርጎ የሚወሰደው እሳቤ ተገቢ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

‹‹በሚፈለገው ደረጃ ባይሆንም አንባቢ ትውልድ አለ፤›› ያሉት ኃላፊዋ፣ ነገር ግን ትውልዱ ጥልቅ አንባቢ እንዲሆን ምቹ ሁኔታን መፍጠርና የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራን መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

እንደሳቸው አገላለጽ፣ ለንባብ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ማለት የማንበቢያ ቦታን ማዘጋጀትና የተመረጡ መጻሕፍትን ለአንባብያን ማቅረብ ነው፡፡ ለአንባቢያን ተመርጠው መቅረብ ያለባቸው መጻሕፍትም ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ለትውልዱ መርዝ የሚረጩ መጻሕፍት ስላሉ፤ ለአገርም ለትውልድም ጠቃሚና አሻጋሪ የሆኑ መጻሕፍት በተቋም ደረጃ ተጽፈውና ታትመው መቅረብ አለባቸው፡፡

ማንም ሰው መጽሐፍ ሲጽፍ በተቋም ተገምግሞ ለአንባቢያን ቢቀርብ፣ ለአገርም ለትውልድም ጠቃሚ መሆኑንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

በሌላ በኩል ‹‹ኃላፊነት ያለበት ሁሉ ወደ ትውልዱ መሄድና መጠጋት እንዲሁም ከጎኑ በመሆን ድጋፍ መስጠትና ማበረታታት አለበት፡፡ ከዚህ ባለፈ ለአንባቢያን ምቹ ቤተ መጻሕፍት መሥራት ባንችልም፣ በእጅ ስልካቸው እንዲያነቡ መሥራት ይጠበቅብናል፤›› ያሉት ሒሩት (ዶ/ር)፣ ትውልዱ በንባብ የንባብ አድማሱን ያሰፋ ዘንድና ጥልቅ አንባቢና መርማሪ እንዲሆን የሚመለከተው ሁሉ ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡

ኃላፊዋ ይህንን ያስገነዘቡት በባ.ኪ.ቱ. ቢሮ አዘጋጅነት ሰባተኛው ዙር የንባብ ባህል ሳምንት፣ ‹‹ንባብ ለዘለቄታዊ ልማት›› በሚል በተጀመረበት ወቅት ነው፡፡ አንባቢ ትውልድን ለማትጋት ያለመው መርሐ ግብሩ ከሰኔ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት፣ ትግላችን ሐውልት በሚገኝበት የኢትዮ ኩባ ወዳጅነት ፓርክ ተከናውኗል፡፡   

‹‹በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትን ለማምጣት አንባቢ ትውልድን መፍጠር ተገቢ ነው፤›› ያሉት ደግሞ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ደኤታ ወርቅነሽ ብሩ ናቸው፡፡

ላለፉት ሰባት ዓመታት በዓመት አራት ጊዜ እየተካሄደ ያለው ከተማ አቀፍ የንባብ ሳምንት፣ በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል፡፡

የመጻሕፍት መሸጫ ቤት ባለቤቶችንና ደራስያንን ከአንባቢያን ጋር እንዲገናኙ ያግዛል ተብሏል፡፡   

‹‹አንድ ሰው በቀን አምስት ገጽ በማንበብ መጀመር አለበት፤›› ያሉት ሒሩት (ዶ/ር)፣ የንባብ ባህሉንና ዕውቀቱን ከቀን ወደ ቀን እያዳበረ በቀን አንድ መጽሐፍ እስከ መጨረስ መድረስ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

በከተማዋ ያሉት የሕዝብ ቤተመጻሕፍት የት ይገኛሉ? በውስጣቸውስ ምን ምን  ይዘዋል? የሚሉትን ከዓውደ ርዕዩ ማየት እንደሚቻል፣ አንባቢያን በቂ መረጃን ከያዙ በኋላ የሚፈልጉት መጽሐፍ የት እንደሚገኝ አውቀው መሄድ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

የንባብ ባህሉ ይዳብር ዘንድ የንባብ ማዘውተሪያ ቦታዎች ምቹ መሆን እንዳለባቸው ይታወቃል፡፡ ለዚህም የአዲስ አበባ ባህል ቢሮ በጀት መድቦ እየሠራ ነው ያሉት ሒሩት (ዶ/ር)፣ ነባሩን በማደስና በማስፋት እንዲሁም አዳዲስ ንባብ ቤቶችንም በመክፈት እያበረታታ ይገኛል ብለዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር የኅብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎም የማይተካ ሚና አለው ብለዋል፡፡ ቤተ መጻሕፍት የሕዝብ በመሆኑም ኅብረተሰቡ ቤተ መጻሕፍትን በማደስና በመጠገን እንዲሁም በግል ደረጃ በመክፈት የንባብ ባህልን ማሳደግ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡  

ሰው የማያውቃቸው፣ በገንዘብ ሊገዙ የማይችሉ፣ የታሪክ መዛግብትን የያዙ፣ በጣም የድሮ፣ የመካከለኛና የአሁን ዘመን መጻሕፍት በመንግሥት ቤተ መጻሕፍት ይገኛል ያሉት ደግሞ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የቤተ መጻሕፍት አስነባቢዋ ወ/ሮ እህተ ሀብቴ ናቸው፡፡

መጻሕፍቱን ለሕዝብ ለማሳየትና መኖራቸውን ለማሳወቅ መድረኩ ጥሩ አጋጣሚ ነው ብለዋል፡፡ እነዚህን ታሪካዊ የሆኑና ለተማሪዎችም ለትምህርታቸው አጋዥ የሚሆኑ መጻሕፍትን ማንበብ ለሚፈልጉ ሁሉ ሙሉ ቀን በሚባል ደረጃ ለሁሉም ክፍት ነው ብለዋል፡፡

ከሕፃናት እስከ ወጣት ከመካከለኛው እስከ ትልልቅ ሰዎች በቤተ መጻሕፍታቸው እየመጡ እንደሚጠቀሙ የተናገሩት ወ/ሮ እህተ፣ በብዛት ግን የተማሪዎች ፈተና በሚቀርብበት ወቅት ከወትሮው በተለየ ቤተ መጻሕፍቱ እስኪሞላ ተማሪዎች እንደሚጠቀሙ፣ ከዚህ ባለፈ በቀን ከ15 እስከ 30 የሚደርሱ ሰዎች ለማንበብ እንደሚመጡ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...