Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ትርፉ ድካም ብቻ!

ሰላም! ሰላም! የተከበራችሁ ወገኖቼ ሰኔ ተጋምሶ ዝናብ የቀደመው ክረምት ሰተት ብሎ ሲገባ፣ ‹‹እስኪ እንጨዋወት ጨዋታ ምን ከፋ፣ የሆድን በሆድ እያልን ጊዜ ከምንገፋ…›› ያለው ዘፋኝ መቼም አይረሳኝም። ስንትና ስንት ነገሮች በሚረሱበት በዚህ ዘመን ይኼማ አይረሳም አይደል? በእውነቱ እንዲህ ያለ ነገር ሲታወስ ምን እንደሚወሰውሰኝ እርግጠኛ ባልሆንም፣ አንድ ነገር ግን በጭራሽ አይዘነጋኝም። ‹‹ያሳለፍነው ዘመን ደስታን ያየንበት አሁን ተመልሶ ቢገኝ ምናለበት…›› የሚለው የዘመን አይሽሬው ጥላሁን ገሠሠ ዘፈን ነው፡፡ ለመሆኑ በዚህ ጊዜ እርግጠኛ ሆነን እናውቃለን? ብንሆንስ በምን? እንዳትሉኝና የጨዋታው ርዕስ መፍታታት እንዳይጀምር። እንዲያ ነው እንጂ፣ ነገር ካነሳን አይቀር ታዲያ ያለፈን እየቀበርን እንለፍ የሚሉ እየበዙ ስለሆነ ተጠንቀቁ እላለሁ። አይመስላችሁም? የቆመን እንጂ የሞተን መቅበር እርግፍ ያደረገ ዘመን ትውልድ ውስጥ ሆነን፣ ጨዋነታችንና ወጋችን አጥንቱ ሰግጎ በወጣበት በዚህ ዘመን፣ ለወደቀ ሞራል ምስክር ከመሆን ያድነን ነው የሚባለው። ሌላ ምን ይባላል? እናም ወደ ታወሰኝ ነገር ዘግይቼ ስታጠፍ ያለፈውን ከአሁን፣ የአሁኑን ከነገ ጋር እያስተሳሰርን ካልሆነ ዋጋ የለንም። ለማስታወስ ያህል ነው!

በዚህች በውድ አገራችን ሲለን በምናፍርባት ሲለን በምንኮራባት፣ ‹ሁለት ሞት ሙቱ› ሲለን ደግሞ ‹አያሳየን› ብለን በምንርቃት ምስኪኗ አገራችን እርግጠኛ መሆን ብሎ ነገር መዝገበ ቃላታችን እንዳይጓደል ያለ ቃል እንጂ፣ በበኩሌ የሚቀር ምሳሌ ያለው አይመስለኝም። የታየው እንግዲህ ማሳየት ነው። በልዩነት ማመን ከእኔና ከእናንተ ካልጀመረ ከላይ ይመጣል ብሎ መጠበቅ አላዋጣም። ለነገሩ በዚህም እርግጠኛ አይደለንም። አንድ ቀን ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ሳይቀር በነፈሰው ነፍሶ በነደደበት ስለሚያነደን ኑሯችን ስንጫወት፣ ‹‹እኔ አንዳንዴ ሳስበው እንኳን ስለዕርምጃችን፣ በልተን ስለማደራችን፣ ስለኢኮኖሚ ዕድገታችን ቀርቶ ስለድህነታችንም እርግጠኞች ነን ብዬ አላስብም። ዓይናችን ስለማየቱ፣ ጆሯችን ስለመስማቱ፣ በማሰባችን ከእንስሳት የምንለይ የዓላማ ፍጡራን መሆናችንን ማመን ብሎ ነገርማ እርሳው…›› አለኝ። ከሁሉ ደሃ ስለመሆናችንም እርግጠኞች አይደለንም አባባሉ አስደንግጦኝ ትንሽ ቆይቶ (የምሁር ነገር ምን ይታወቃል) ‹ድህነታችን በጥናት ይረጋገጥ› እንዳይለኝ ፈርቼ ዞር አልኩ። ዞር ስል ለስንት አሥርት ዓመታት በኖርኩበት መንደር ውስጥ ተወልዶ፣ አድጎ፣ ተምሮና ተድሮ ለወግ ለማዕረግ የበቃ ጎልማሳ ሁለት ታዳጊ ልጆቹን በፈረንጅ አፍ እያናገረ በኩራት ሲራመድ፣ ‹የባሰ አለና አገርህን አትልቀቅ› የሚለው ዕድሜ ጠገብ ምሳሌ ጭንቅላቴ ውስጥ ስንቅር ብሎ ገባ፡፡ ጉድ እኮ ነው ዘንድሮ!

እንዲህ የኖርኩትን ሁሉ በዜሮ የሚያጣፋ ግራ መጋባት ሲጠናወተኝ ታዲያ መድኃኒቴን አውቀዋለሁ። እሱም በሥራ መወጠር ነው። መድኃኒት በመግዛትና መድኃኒት በማሠራት ያዳከምነው ወኔ ሥራ ላይ ውሎ ቢሆን ኖሮ አቤት ዛሬ እኛን ነበር ማየት። ለነገሩ አድርገነው ቢሆን ዛሬ የያዝነውን ይዘን እንዳለነው፣ ቢሆን የምንለው ዕድሜ ይመርበት ይክፋ እርግጠኛ መሆን አንችልም። ነገርኳችሁ እኮ መራገጥ እንጂ ማረጋገጥ የእኛ አይደለም ስላችሁ? እኔን ካላመናችሁ አዛውንቱ ባሻዬ አንድ የሚሉት አባባል አለ። ‹‹ላለፈው ዕድሜ ከመቆጨት ለሚመጣው አስብ›› ይላሉ። ይህንን የባሻዬ አባባል፣ ‹ከዚህ በፊት የሰማነው ስለመሰለን የራሳቸው ይሁን አይሁን እርግጠኛ መሆን አንችልም› ካላችሁ ደግሞ እንደፈቀዳችሁ። የመጠርጠር መብታችሁ በሕገ መንግሥቱም ሆነ በጎዳናው ያልተጻፈ ሕግ የተፈቀደ ነው። ታዲያ ‹በሕግ ያልተከለከለ እንደተፈቀደ ይቆጠራል› የሚለውን እንዳትዘነጉ፡፡ ግን አደራ ባሻዬን በኩረጃ ስማቸውን ስታጠፉ እንዳልሰማና እንዳንጣላ። የምሬን ነው ፍራሽ ማደስ በእሳቸው አልተጀመረም። ስንቱ ብርሁነቱን ንቆ፣ ትኩስ ኃይሉን በመምሰልና በማስመስል አምክኖ በሰው ወርቅ እየደመቀ እያየን፣ አንድ የአገር አንጡራ ሀብት አረጋዊ ያለችውን ቢያሽሞነሙንና ቢጥፍ ነውር አይመስለኝም። አያችሁ ሰው መጠየቅ ያለበት ባለው አቅም ዕውቀት ልክ መሆን አለበት፣ አልተሳሳትኩም መቼም። ‹‹ጥሬ እፈጭ ብለሽ ዱቄት አታፍሺ›› ሲባል የሰማሁበት ጊዜ ለምን እንደሆነ እንጃ ሩቅ ይመስለኛል። እናንተ ሰዓቱ ነው ትውስታችን ነው እየፈጠነ ያስቸገረን ግን? በ50 ሳንጨማደድ እንደባለ 80 ምርኩዝ ማለት አበዛና!

አዲስ አበባችን ይዝነብ አይዝነብ እርግጠኛ መሆን ባቃታት ሰዓት አንድ ያሻሻጥኩትን ቤት ‹ኮሚሽን› ልቀበል ጉዞ ጀመርኩ። ያሻሸጥኩት ቤት ስደርስ መጠነኛ ስለላ ለማድረግ ዕርምጃዬን ገታሁ። ስለላ የምትለዋ ቃል በአንጎሌ መስቀለኛ መንገድ መብራት ጥሳ ስታቋርጥ ዓይኔን ወደ ሰማይ አቀናሁ። ወተቱን መግምጎ ሲያበቃ ቁንጣን ይዞት እንደሚያጎላጅ ሕፃን የተደበረ ወፍራም ደመና ብቻ ይታየኛል። ግን ተጠራጠርኩ። ይህችን ለዕለት እንጀራ ለቀማ የምትረዳኝን የድለላ አሰሳ ትታችሁ ወጪ ወራጁን ዝንብና ትንኙን በሰው አልባ አውሮፕላኖቻቸው ሲያጠኑ የሚውሉ እንዳሉ ስታስቡ፣ እናንተም እንደ እኔ ማንጋጠጣችሁ አይቀርም። አንዴ ለምሁሩ የባሻዬ ልጅ ስለኃያላኑ ለስለላና ለጥቃት ስለሚጠቀሙባቸው እጅግ ዘመናዊ፣ እንደ ገለባ የቀለሉ ሰው አልባ አውሮፕላኖች አንስቼበት ብዙ ካስረዳኝና ካስተማረኝ በኋላ፣ ‹‹አንበርብር እኛም እኮ እጃችን ካስገባናቸው የቆየን መሰለኝ፡፡ ያኔ የጦርነቱ ጊዜ የታሪክ አቅጣጫ የተለወጠው እኮ በእነዚህ ድሮን በሚባሉ ጉዶች ነው። ማን ያውቃል ወደፊት ከጦርነት ወጥተን ለልማት በእጅጉ እንጠቀምባቸው ይሆናል፡፡ አንተ ጭምር የበረከቱ ተሳታፊ መሆንህ አይቀርም…›› እያለ ሲስቅ ለወትሮው የዕለት እንጀራዬን ወደ የሚሰጠኝ አምላኬ የማንጋጥጥ ሰውዬ፣ ‹ድሮን› ተከትዬ እንጀራዬን ሳበስል በራሴ አዘንኩ። ብለው ብለው በሰማይ መጡብን አትሉም? ‹የምድሩንስ ነገር እኛ ችለነዋል፣ ከፍ በል ጌታዬ ወደ አንተ መጥተዋል› ያለችው ሴት ማን ነበረች? ወይ ነዶ ዘመኑ ራቀ እኮ እናንተ!

ወዲያው በቆምኩበት አንድ ደቂቃ ውስጥ የሊስትሮ ዕቃ የያዘ ልጅ ድንገት ከተፍ ብሎ፣ ‹‹ይጠረግ?›› አለኝ። ‹‹ምኑን?›› አልኩት። ‹‹ጫማውን!›› አለኝ። ‹‹ዛሬ ይለፈው፣ ከጭቃ ውስጥ ወጥቼ ተመልሼ ወደ ጭቃው ስለምገባ ተወው ለዛሬ…›› ከማለቴ፣ ‹‹ገብጋባ!›› ሲለኝ ሰማሁት። ልጅ ሆኜ እንዳላደግኩ ልጅነትን ሊያስረግመኝ እየተፈታተነኝ፣ ‹‹ምን አልክ አንተ?›› ብለው፣ ‹‹ጫማ አላስጠርግም የምትለው የትኛውን የኤሌክትሪክ መኪናህን ተማምነህ ነው?›› ብሎ ቀረቀረልኝ። በምንንቀው ባሰብን እኮ ተግሳፁና ስድቡ። የሊስትሮው ዕቃ ግማሽ አካሉን ከሚያጥፈው ጩጬ ጋር ስሯሯጥ ታይቼ ደግሞ ሌላ ስም ከማወጣ ብዬ፣ ‹‹በል እሺ ጥረግ…›› ብዬ ጫማዬን ማስጠረግ ጀመርኩ፡፡ ‹‹ለመሆኑ አንተ ጩጬ ስለኤሌክትሪክ መኪና ምን አውቀህ ነው የምትፈላሰፈው…›› ከማለቴ ከአፌ ነጥቆ፣ ‹‹ጩጬዎቹ ሴቶች አይደሉ እንዴ አይዲ ፎርና ሲስክ ይዘው አፈር አይንካን ሲሉ፣ መንግሥት ከቻይና ቆራሌው ተገዝተው የገቡ ስለሆነ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ አግጃለሁ ብሎ በድንጋጤ ላብ በላብ ያደረጋቸው…›› ብሎኝ እርፍ፡፡ ‹‹ታዲያ ይህንን ከእኔ ጋር ምን አገናኘው…›› እያልኩ መናገር ስጀምር፣ ‹‹ሰው ሁሉ እነዚህን መኪኖች የሚረከቧቸው ደላሎች ናቸው ብሎ እያወራ መሆኑን አልሰማሁም እንዳትለኝ ብቻ…›› እያለ ሲስቅብኝ ፈዝዤ ነበር ያየሁት፡፡ የባሰ አታምጣ!

ጫማዬን እያስጠረግኩ አንድ ‹አይሱዙ› ከተፍ አለ። ደንበኞቼ ዕቃቸውን ጭነው ቤቱን ሊገቡበት መምጣታቸው ነበር። ከመቅፅበት ሠፈሩ በጠብደል ጎረምሶች ተወረረ። ሌሎች የማላውቃቸው ሰዎችም ካደፈጡበት ብቅ ብቅ አሉ። ደላሎች ኖረዋል። ደንበኛዬ ግራ ተጋብቶ ከአውቶሞቢሉ ወረደ። አንዴ ወደ ጎረምሶቹ አንዴ ወደ ተሰባሰቡት የሠፈሩ ደላሎች እያየ ጤና የማይታይበትን አቀባበል ሲያጠና፣ ‹‹ይኼ ዕቃ የሚወርደው የድለላችን ከተከፈለን በኋላ ነው…›› አለ አንዱ ከደላሎች መሀል። ከጎረምሶች አንዱ ደግሞ፣ ‹‹በቤተሰብ ተደራጅቼ አወርዳለሁ ማለት ሕጋዊ ካለመሆኑም በላይ፣ ማግለልና አድልኦ ያለበት አስተሳሰብ በመሆኑ በቀላሉ አንላቀቅም…›› ብሎ ተገተረ። የጎረምሶቹ አልገረምኝም፣ ምንም እንኳ የልብ ማበጥን ዛሬ ዕድሜ ሳትለይ መገኘት በማይገባት ቦታ እየተገኘች ብታስቸግረንም ያስተንፍስልን ብሎ ማለፍ ነው። ደላሎቹ ግን ቤቱ እንደሚሸጥ ያውቁ ስለነበር ብቻ ‹በሠፈራችን እንዴት የሩቅ  ደላላ ቤት ያሸጣል?› ማለታቸው ክልላዊነት፣ ጠባብነትና ዘረኝነት ምን ያህል ወሰን እየተሻገረ እንደሆነ አስታውሶኝ ከልቤ አዘንኩ። በቃ ሠፈሩ ድብልቅልቁ ወጣ። ኋላ ለውዷ ማንጠግቦሽ ስለውሎዬ በአጭሩ የተጠናቀረ ዘገባ አቅርቤ ይኼን ነግሬያት፣ ‹‹ጉድ እኮ ነው። ውሻ ብቻ ይመስለኝ ነበር በሽንቱ ድንበር የሚከልል። ለካ ሰውም ከሰውነት ተራ ሲወርድና ሲዘቅጥ ነው እንደ ውሻ ጩኸትና ንክሻ የሚጀምረው…›› ብላ ዕንባዬ እስኪረግፍ አሳቀችኝ። እንግዲህ ይኼን ሰምተው ትከሻቸውን እያሳበጡ ‹እንተያያለን› የሚሉ ቢኖሩም፣ ለማንኛውም እውነታው ግን ይህንን የመሰለ መርዝ በውስጡ መደበቁን አለመናገር ጥሩ አይደለም። እናንተ ግን አደራ!

በሉ እንሰነባበት። ከስንት ግብግብ በኋላ ‹ኮሚሽኔን› ተቀብዬ እዚያ ሠፈር እንዳልደርስ ከባድ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶኝ ስመለስ፣ ሆድ ስለባሰኝ ለምሁሩ የባሻዬ ልጅ ደወልኩለት። የተለመደችዋ ግሮሰሪያችን ተገናኝተን አንድ አንድ ስንል አመሸን። የምሽቱ ብርድ አጥንት ድረስ ይዘልቃል። ለነገሩ ከዘንድሮ ቅዝቃዜ የፖለቲካ ሁካታችን ነው የባሰበት፡፡ ‹‹የዘንድሮ ክረምት ደግሞ በንፋስ ሊያጥበን ነው መሰል ፍላጎቱ…›› ይለኛል የባሻዬ ልጅ። ይኼን ሲል አንዱ ከሩቅ ሰምቶት፣ ‹‹ንፋስ ምን አለን? ከሕግ በላይ የሚወበራው፣ አላስቆም አላስቀምጥ ያለን አልጠግብ ባይ ጉቦኛና ዘራፊ አይብስም?›› አለው። ‹‹አየህ ሳትፈልገው ነገር ሰተት ብሎ መጣልህ…›› አልኩና የካፖርቴን ኮሌታ ወደ ላይ ቀስቼ ጠንቀቅ ብዬ ተቀመጥኩ። ተጠንቅቀንም መዳናችንን እርግጠኛ አይደለንም እንዳትሉ ብቻ። ለነገሩ ለጥንቃቄ ሲባል የሚሰጡ ምክረ ሐሳቦች በራሳቸው አደገኛ እንደሚሆኑ ልብ ብላችሁ ታውቃላችሁ ወይ እንዳልል፣ እኔ ራሴ ልብ ማለት አቅቶኝ ሰለባ የሆንኩባቸውን ጊዜያት ግን አልረሳቸውም፡፡ ስለተደጋገመብኝ ነው ይህንን የማስታውሳችሁ፡፡ አደራ አትርሱ!

ወደ ግሮሰሪው ወግ ልመልሳችሁና፣ ‹‹እና ምን ይሻላል?›› አለው አንዱ ተናግሮ አናጋሪ ከማዶ በኩል። ‹‹ማጥራት ነዋ፣ ማፅዳት ነው መፍትሔው። ሳይታክቱ መጥረግ…›› አለው። ‹‹ነገሩ ሁሉ ድብልቅልቅ ብሎ ምኑ ነው የሚጠራው? ቤተ መንግሥት ብትሄድ ለነፍሳቸው ያደሩ ጭምር የፖለቲካ አማካሪ ተብለው ምን ሲሠሩ እንደሚውሉ እንጃ፡፡ ቄሱ፣ ሼኩና ፓስተሩን ማለቴ ነው፡፡ ቤተ እምነቶች ጎራ ብትል ለነፍሳቸው ካደሩት ይልቅ ለሥጋቸው ያደሉት ምዕመኑን ይቀልዱበታል፡፡ ፖለቲከኞቹ ዘንድ ጎራ ስትል ደግሞ ራሱን የቻለ ተውኔት በማን እንደተደረሰ ሳይታወቅ በደመ ነፍስ ይተወናል፡፡ ብልጦቹ ግን ከተውኔቱ በስተጀርባ ያለውን መልዕክት በሚፈልጉት መንገድ እያስተላለፉ ተመልካች መስለው ይታደማሉ፡፡ ይህ ሁሉ ድብልቅልቅ ባለበት ማን ነው ተዋናዩ፣ ማን ነው ታዳሚው፣ ማነው ሴረኛው፣ ማነው ግራ የተጋባው… እያልክ መልስ ፍለጋ ብትባዝን ትርፉ ድካም ነው…›› ብሎ ንግግሩን ሲገታ የግሮሰሪው ታዳሚዎች በሙሉ በሚቻል ሁኔታ ፀጥ እረጭ ብለው ነበር ያዳመጡት፡፡ አዳማጭ አያሳጣ ማለት አሁን ነው አትሉም ታዲያ፡፡ የሆነስ ሆነና ድከሙ ቢለን እንጂ ይህንን ያህል መልፋት ነበረብን ያሰኛል፡፡ መልካም ሰንበት!.

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት