Saturday, September 23, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ የተኪ ምርት ስትራቴጂ ለመጀመሪያ ጊዜ ተዘጋጀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተኪ ምርት (Import Substitute) ስትራቴጂ ለመጀመርያ ጊዜ አዘጋጅቶ፣ ከመጪው የበጀት ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑ ታወቀ፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ ራሱን ችሎ ለመጀመርያ ጊዜ የተዘጋጀው ስትራቴጂ በየዓመት እየተከፋፈለ እስከ አሥር ዓመት የሚዘልቅ ዕቅድ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም አገሪቱ የተኪ ምርት ስትራቴጂ እንዳልነበራት የተናገሩት ሚኒስትር ደኤታው፣ ለተኪ ምርት ትኩረት ሳይሰጥ እንደቆየና ከዚያ ይልቅ ትኩረት ሲደረግ የነበረው የወጪ ምርት ላይ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ከተኪ ምርት አኳያ በዕቅዱ የተቀመጠው ምርትን መሠረት ያደረገ እንደሚሆንና ሁሉንም ምርቶች ይተካሉ ተብሎ የተነደፈ ሳይሆን፣ ምን ይተካሉ በሚል የተለዩ ምርቶችን ያስቀመጠ መሆኑን ሚኒስትር ደኤታው ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የአገር ውስጥ ተኪ ምርት ድርሻ ትልቅ ትኩረት እንዳገኘ፣ ከስትራቴጂ ዝግጅት ጀምሮ የፖሊሲና የዕቅድ ትኩረት እንዳለው፣ አነስተኛ የሆነውን የአገር ውስጥ ድርሻ በሒደት ማደግ እንዳለበትና ፖሊሲውም የአገር ውስጥ ምርትን ማበረታታት፣ አቅም እያለ ከውጭ የሚገቡትን ማስቀረት አቅጣጫው በመሆኑ ስትራቴጂው በልዩ ትኩረት ይኼንን እንደሚመራ ማድረጉ የተለየ እንደሚያደርገው አቶ ታረቀኝ ገልጸዋል፡፡

የተኪ ምርት ስትራቴጂ ከ2016 ዓ.ም. ጀምሮ ኢትዮጵያ ታምርት ውስጥ ትልቁ ኢንሼቲቭ ሆኖ እንደሚቀጥልና በስትራቴጂው ላይ ውይይት እንደተደረገበት ተጠቅሷል፡፡

በኢትዮጵያ ታምርት የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ውስጥ የቅንጅት ሴክተሮችና ክላስተሮች ሥራ በመጀመራቸውና ከሰሞኑም በተከታታይ የፋይናንስና ሲስተም ክላስተር፣ የመሠረተ ልማትና የግብዓት ክላስተር፣ የአቅም ግንባታና የምርምር ክላስተር፣ እንዲሁም የኢንቨስትመንትና የግሉ ዘርፍ በተመሳሳይ ውይይት አድርገው ዕቅዱን እንዳፀደቁት ተብራርቷል፡፡

እስከ ሰኔ ወር ድረስ ሁለት ቢሊዮን ብር የሚደርስ ምርት የተተካ መሆኑን ያስረዱት አቶ ታረቀኝ፣ ጥሩ የሚባል ሒደት ቢሆንም ነገር ግን በአጠቃላይ በሸቀጥ ድርሻ ሲታይ 37.5 በመቶ እንደሆነና አነስተኛ የሚባል ስለሆነ በሒደት ይህንን ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡

በስትራቴጂው የሦስት ዓመት ዕቅድ የተኪ ምርት ድርሻ ወደ 60 በመቶ ለማድረስ የታቀደ ሲሆን፣ ኢንዱስትሪ በየትም አገር ድርሻው መቶ በመቶ ስለማይሆን  ነገር ግን መሠረታዊ የሚባሉትን፣ ለማምረት ቀላል የሆኑትን፣ ለፋይናንስም ሆነ ቀላል ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙትን በአገር ውስጥ በማምረት እንደሚቀጥል ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ከተተኩ ምርቶች በዋናነት የምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ውጤቶች ከፍተኛውን ድርሻ (80 በመቶ) የሚይዙ ሲሆን በዋናነት የምግብ ዘይት፣ ፓስታና አልሚ ምግቦች፣ እንዲሁም የቢራ ብቅል እንደሚገኙበት ከዚህ ቀደም መገለጹ ይታወሳል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ባለፈው ወር ሲገመገም እንደተገለጸው፣ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካት ከ1.9 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማዳን የተቻለው የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂና ኢንጂነሪንግ፣ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ፣ የምግብና መጠጥ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት በመቻሉ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በዘጠኝ ወራት የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፉ መቶ በመቶ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች 77.6 በመቶ፣ የማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂና ኢንጂነሪንግ መቶ በመቶ፣ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ መቶ በመቶ፣ የምግብና መጠጥ ዘርፍ 84.3 በመቶ ዕቅዳቸውን ማሳካታቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች