Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከ27 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው የደብረ ብርሃን መጠለያ ካምፖች ኩፍኝ መከሰቱ ተገለጸ

ከ27 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው የደብረ ብርሃን መጠለያ ካምፖች ኩፍኝ መከሰቱ ተገለጸ

ቀን:

  • የተፈናቃዮች ቁጥር በመጨመሩ ተጨማሪ የመጠለያ ካምፕ ሊዘጋጅ ነው ተብሏል

ከ27 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው የደብረ ብርሃን ከተማ የመጠለያ ካምፖች የኩፍኝ በሽታ መከሰቱን፣ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሰሜን ሸዋ ዞን አስታወቀ፡፡

የዞኑ አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ በደብረ ብርሃን ከተማ በሚገኙ የመጠለያ ካምፖች የኩፍኝ በሽታ መከሰቱን፣ በፀጥታ ሥጋት ምክንያት ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎቹ የተጠለሉ ሰዎች በበሽታው እየተጠቁ ነው፡፡

የኩፍኝ በሽታው ተከሰተ የተባለው ከ27 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች በተጠለሉባቸው ወይንሸትና ቻይና መጠለያ ካምፖች ነው፡፡

በመጠለያ ጣቢያዎቹ የኩፍኝ በሽታ በመከሰቱ ተፈናቃዮች እየተጠቁ መሆናቸውን፣ የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት መምርያ ኃላፊ አቶ አበባው መለሰ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

በተፈናቃዮች ላይ የተከሰተውን የኩፍኝ በሽታ ለመከላከል የጤና አገልግሎት ሠራተኞች ርብርብ እያደረጉ እንደሆነ ኃላፊው አክለው አስረድተዋል፡፡

ሪፖርተር በስልክ ያነጋገራቸው የደብረ ብርሃን ከተማ ጤና መምርያ ኃላፊና የተፈናቃዮች አስተባባሪ አቶ በየነ ሳህሉ በበኩላቸው፣ በሁለቱም ካምፖች የኩፍኝ በሽታ መከሰቱን አረጋግጠው፣ እስካሁን (ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ) ከ116 በላይ ተፈናቃዮች መጠቃታቸውን ተናግረዋል፡፡

ኩፍኝ የተከሰተው ከመቼ ጀምሮ እንደሆነና ችግሩን ለመከላከል እየተወሰደ ያለው  መፍትሔ ምን እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ የተከሰተው ከሁለት ሳምንት ወዲህ መሆኑንና በሽታው ወደ ማኅበረሰቡ እንዳይስፋፋ ከሚመለከታቸው የጤና ተቋማት ጋር በመተባበር የክትባት አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሽታው በመጠለያ ጣቢያው ሊከሰት የቻለበትን መነሻ ምክንያት ሲስረዱም፣ በመጠለያ ጣቢያዎቹ ከፍተኛ የምግብ እጥረት በማጋጠሙና ተፈናቃዮች በሽታውን ለመቋቋም አቅም ስላነሳቸው ነው ሲሉ አክለዋል፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪ አቶ ደረጀ ይነሱ በበኩላቸው፣ መንግሥት በየወሩ ድጋፍ ማድረግ ቢኖርበትም ዕርዳታው በየወሩ እየደረሰ እንዳልሆነ፣ ለአብነትም ተፈናቃዮቹ በዓመት ውስጥ ያገኙት የሦስት ወራት ድጋፍ ብቻ መሆኑንና ከፍተኛ የምግብ እጥረት መከሰቱን አስረድተዋል፡፡

‹‹አብዛኞቹ ተፈናቃዮች በማኅበረሰቡ ውስጥ ነው ተጠልለው የሚገኙት፤›› ያሉት አቶ ደረጀ፣ በዞኑ በሚገኙ 17 የመጠለያ ካምፖች ብቻ ከ90 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች እንዳሉና ሁሉም ተፈናቃዮች የምግብ እጥረት እንዳጋጠማቸው አክለው ገልጸዋል፡፡

ከ146 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች ከመጠለያ ውጪ ማኅበረሰቡ ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከሸገር ከተማ ቤት ፈርሶባቸው ወደ ዞኑ በመሄድ ወደ መጠለያ ካምፕ ለመጠጋት የጠየቁ በርካታ ተፈናቃዮችን ካምፖቹ ጠባብ በመሆናቸው መጨመር እንዳልተቻለ፣ ተጨማሪ ካምፕ ለመሥራት መታቀዱም ተመላክቷል፡፡

በምግብ እጥረት ምክንያት ዕቃቸውን እየሸጡ እየተሰደዱ መሆናቸውንና በምግብ እጥረት ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች እንዳሉ ተፈናቃዮች ለሪፖርተር ቢናገሩም፣ አቶ ደረጀ ጉዳዩን በተመለከተ ምላሽ ሲሰጡ፣ ‹‹የምግብ እጥረት ቢከሰትም የተሰደደ ተፈናቃይ የለም፣ የሞተ ሰውም የለም፤›› ብለዋል፡፡

አጋጥሟል የተባለውን የምግብ እጥረት በተመለከተ ምን ምላሽ እንዳላቸው ሪፖርተር የጠየቃቸው የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበባው፣ ‹‹የምግብ እጥረት የለም፤›› ሲሉ አስተባብለዋል፡፡

ከብሔራዊ አደጋ መከላከልና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመተባበር ድጋፍ እየሰጠን ነው ያሉት ኃላፊው፣ በወር የሚደረገውን ድጋፍ እያከፋፈሉ መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡

በዞኑ የመጠለያ ካምፖች የሚገኙ ተፈናቃዮች ከፍተኛ የምግብ እጥረት እንደገጠማቸው በመረጃ መረጋገጡን ለአቶ አበባው ጥያቄ ቢቀርብላቸውም፣ ‹‹እጥረት የለም፤›› ከማለት ውጪ የሰጡት የተለየ ምላሽ የለም፡፡

የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ በቅርቡ ከ12 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለከፍተኛ የምግብ እጥረት መጋለጣቸውን ለሪፖርተር ማረጋገጡ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...