Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናከ2.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ዕዳ የተሸከመው ባቡር ኮርፖሬሽን መፍትሔ እንዲሰጠው ጠየቀ

ከ2.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ዕዳ የተሸከመው ባቡር ኮርፖሬሽን መፍትሔ እንዲሰጠው ጠየቀ

ቀን:

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የተሸከመውን ከ2.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ዕዳ ማቅለል የሚችልባቸው የመፍትሔ አማራጮች በማቅረብ፣ መንግሥት ውሳኔ እንዲሰጠው ጥያቄ አቀረበ፡፡

የኮርፖሬሽኑ አመራሮች እንደሚሉት፣ ኮርፖሬሽን ከፍተኛ የአገር ውስጥና የውጭ ብድር ተሸክሟል። ከአገር ውስጥ ባንኮች ተበድሮ ያልከፈለውን ዕዳ ገሚሱን በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር የተደራጀው የዕዳና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን የወሰደለት ቢሆንም፣ የውጭ ዕዳው ግን ምንም ሳይነካ እንዳለ በኮርፖሬሽኑ ጫንቃ ላይ መውደቁን አመራሮቹ ጠቁመዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ረቂቅ አዋጅ ላይ ከሳምንት በፊት ባካሄደው የባለድርሻ አካላት ውይይት ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ  መኮንን ጌታቸው (ኢንጂነር)፣ የኮርፖሬሽኑን የውጭ ዕዳ ለመክፈል ታሳቢ የተደረገው የገቢ ምንጭ የአዲስ አበባ – ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር ትርፍ መሆኑን አስረድተዋል። ነገር ግን በአደረጃጀት ምክንያት አክሲዮን ማኅበሩ የሚያገኘውን ትርፍ ኮርፖሬሽኑ የመጠቀም መብቱ እንዳልተከበረለት ተናግረዋል።

- Advertisement -

‹‹አክሲዮን ማኅበሩ ከሚሰጠው አገልግሎት ከፍተኛ ትርፍ እያገኘ ከመሆኑ በተጨማሪ ከዕዳ ነፃ ነው፤›› ያሉት መኮንን (ኢንጂነር)፣ ‹‹ነገር ግን አክሲዮን ማኅበሩ ከኮርፖሬሽኑ ጋር ምንም ዓይነት የሥራ ግንኙነት የለውም፡፡ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እንኳን አያቀርብም፤›› ብለዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከአገር ውስጥና ከቻይና ኤግዚም ባንክ ባገኘው ግዙር ብድር ያስገነባው የአዲስ አበባ – ጂቡቲ የባቡር መስመር እስከ ጂቡቲ ድንበር ድረስ 656 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ሲኖረው፣ ከጂቡቲ ድንበር እስከ ነጋድ ወደብ ድረስ ያለውን 100 ኪሎ ሜትር ጨምሮ አጠቃላይ የባቡር መስመሩ 756 ኪሎ ሜትር የሸፈነ ነው፡፡

ሪፖርተር የተመለከታቸው የሰነድ መረጃዎች እንደሚያስገነዝቡት፣ ይህ የባቡር መስመር ዝርጋታ መጠናቀቁን ተከትሎ የኢትዮጵያና የጂቡቲ መንግሥታት የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ለመመሥረት የሁለትዮሽ ስምምነት አድርገው፣ እ.ኤ.አ. በ2017 የኢትዮ ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበርን አቋቁመዋል። ተቋሙ በአክሲዮን መልክ የተደራጀ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት 75 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ ሲይዝ የተቀረው 25 በመቶ ድርሻ ደግሞ የጂቡቲ መንግሥት ነው። 

የኢትዮጵያ መንግሥት ከያዘው ድርሻ ውስጥ ደግሞ 72 በመቶው የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ሲሆን፣ ሌሎች ሦስት የኢትዮጵያ መንግሥት ተቋማት እያንዳንዳቸው አንድ በመቶ ድርሻ ይዘዋል።

በዚሁ መሠረት የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር በ500 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል በሁለቱ መንግሥታት ባለቤትነት የተመሠረተ ሲሆን፣ አክሲዮን ማኅበሩም በታኅሳስ ወር 2010 ዓ.ም. የመንገደኞችና የጭነት የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንደጀመረ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከላይ በተገለጸው የአክሲዮን ድርሻ ድልድል መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮ ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበርን ለማቋቋም በጥሬ ገንዘብና በዓይነት የሚጠበቅበትን 360 ሚሊዮን ዶላር የከፈለ ሲሆን፣ የጂቡቲ መንግሥት ለያዘው 25 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ የሚጠበቅበትን 125 ሚሊዮን ዶላር የካፒታል መዋጮ እስካሁን እንዳልከፈለ ሪፖርተር ከምንጮች ለመረዳት ችሏል።

ይህ ቢሆንም አክሲዮን ማኅበሩ የትራንስፖርት አገልግሎቱን በአሁኑ ወቅት በመስጠት ላይ ይገኛል። ኮርፖሬሽኑም ለአዲስ አበባ – ጂቡቲ ባቡር መስመር ግንባታ ከቻይና ኤግዚም ባንክ የወሰደውን 2.5 ቢሊዮን ዶላር የወለድና የግዴታ ክፍያ ከ2009 ዓ.ም. አንስቶ ለተወሰኑ ዓመታት ሲከፍል እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። በተጨማሪም  ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር መስመር ግንባታ ከወሰደው 439.1 ሚሊዮን ዶላር ብድር ውስጥ እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ 285.4 ሚሊዮን ዶላሩን መክፈሉን፣ ሪፖርተር ከፌዴራል ዋና ኦዲተር የክዋኔ ኦዲት ሰነድ ላይ ለመገንዘብ ችሏል።

መኮንን (ኢንጂነር) ለምክር ቤቱ በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹ኮርፖሬሽኑ በአክሲዮን ማኅበሩ ላይ 71 በመቶ ድርሻ ቢይዝም የመወሰን ኃላፊነቱ አልተከበረለትም። የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎትም ለአዲስ አበባ አስተዳደር ተላልፎ የተሰጠ ቢሆንም ዕዳው ግን ኮርፖሬሽኑ ላይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በመሆኑም የኮርፖሬሽኑ ህልውና እንዲቀጥል የሚፈለግ ከሆነ መንግሥት ኮርፖሬሽኑ ያለበትን የውጭ ዕዳ በተመለከተ፣ ተገቢና ጠቃሚ ይሆናል ያለውን ውሳኔ በፍጥነት ማሳለፍ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በዚህም መሠረት የኢትዮ ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር የኮርፖሬሽኑ ተቀፅላ ድርጅት መሆኑ ታምኖ ግልጽ የሆነ የመወሰን ሥልጣን ለኮርፖሬሽኑ እንዲሰጥ፣ እንዲሁም ኮርፖሬሽኑ ከአክሲዮን ማኅበሩ የሚገኘውን ትርፍ ተጠቅሞ የውጭ ዕዳውን እንዲከፍል እንዲወሰን ጠይቀዋል። ይህ ካልሆነ ደግሞ ኮርፖሬሽኑ ያለበትን የውጭ ዕዳ መንግሥት ወይም አክሲዮን ማኅበሩ ሙሉ በሙሉ እንዲወስዱ ጠይቀዋል፡፡

የቀረበውን ጥያቄ በተመለከተ ምላሽ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስቴር አማካሪ ወ/ሪት ሒንጃት ሻሚል፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ጥያቄ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ከኢትዮጵያ ጅቡቲ የባቡር መሠረተ ልማትና ከባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበሩ ጋር ያለው ግንኙነት ብዥታ ያለበት መሆኑን እንደሚረዱ ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን ችግሩ ከገንዘብ ሚኒስቴር አመራሮች ጋር በመወያየት ሊፈታ እንደሚችል ጠቅሰው፣ የውይይት መድረኩን እንደሚያመቻቹ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ለአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር ፕሮጀክትና የሮሊንግ ስቶክ ግዥ ከቻይና ኤግዚም ባንክ ለወሰደው 2.5 ቢሊዮን ዶላር ብድር ወለድና የግዴታ ክፍያ ከ2009 ዓ.ም. አንስቶ መፈጸም የጀመረ ሲሆን፣ ለአብነትም በሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም. ለነበረበት የግዴታ ክፍያና ወለድ 47 ሚሊዮን ዶላር ወይም በወቅቱ የምንዛሪ ተመን 1.3 ቢሊየን ብር መክፈሉን የፌዴራል ዋና ኦዲተር በ2012 ዓ.ም. በኮርፖሬሽኑ ላይ ካካሄደው የክዋኔ (Performance) ኦዲት ሪፖርት ለማወቅ ተችሏል።

በተጨማሪም በጥር ወር 2011 ዓ.ም. መክፈል ለነበረበት 62 ሚሊዮን ዶላር የክፍያ ግዴታ ኮርፖሬሽኑ 1.8 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ ተበድሮ መፈጸሙን፣ እንዲሁም እስከ 2011 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ የነበረበትን ያልተከፈለ ወለድና የግዴታ ክፍያ አካቶ በ2012 ዓ.ም. 104 ሚሊዮን ዶላር መክፈሉን የክዋኔ ኦዲት ሪፖርቱ ይጠቁማል።

ነገር ግን መንግሥት ከቻይና ጋር ባደረገው ድርድር ለባቡር መሠረተ ልማቱና ለሮሊንግ ስቶክ ግዥ ከቻይና ኤግዚም ባንክ የተወሰደው ብድርና ወለዱን መክፈያ ጊዜ እንዲራዘም በመደረጉ፣ ተጀምሮ የነበረው የወለድና የግዴታ ክፍያ ከ2012 ዓ.ም. በኋላ መቋረጡን ለማወቅ ተችሏል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ላይ አተኩሮ በ2014 ዓ.ም. ያደረገው ሌላ የክዋኔ ኦዲት ደግሞ፣ ኮርፖሬሽኑ ለዚህ ፕሮጀክት ከተበደረው 439.1 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 285.4 ሚሊዮን ዶላሩን ከፍሎ 153.7 ሚሊዮን ዶላር እንደሚቀርበት አረጋግጧል። በአጠቃላይ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የትራንስፖርት አገልግሎት ከጀመረበት 2008 ዓ.ም. አንስቶ እስከ 2013 ዓ.ም. በነበሩት ዓመታት ብቻ፣ 16 ቢሊዮን ብር ኪሳራ እንዳስከተለ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ሰነድ ያመለክታል። 

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በ2000 ዓ.ም. በተፈቀደ ሦስት ቢሊዮን ብር ካፒታል የተመሠረተ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ብር 750 ሚሊዮን በጥሬ ገንዘብና በዓይነት የተከፈለ ነበር። ከጥቂት ዓመታት በኋላም የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኮርፖሬሽኑን ማቋቋሚያ ደንብ በማሻሻል የተፈቀደ ካፒታሉን ወደ 39 ቢሊዮን 780 ሚሊዮን ብር እንዲያድግ የወሰነ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ብር 9 ቢሊዮን 945 ሚሊዮን ብር በገንዘብና በዓይነት ተከፍሏል፡፡

በተጨማሪም በመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም. የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንን ማቋቋሚያ ደንብ እንደገና በማሻሻል፣ የተፈቀደና የተከፈለ ካፒታሉን በከፍተኛ መጠን አሳድጎታል።

ምክር ቤቱ በመጋቢት 2015 ዓ.ም. ባፀደቀው ማሻሻያ ደንብ መሠረትም የኮርፖሬሽኑ የተፈቀደ ካፒታሉ ወደ 221 ቢሊዮን ብር፣ በጥሬ ገንዘብና በዓይነት የተከፈለ ካፒታሉ ደግሞ ወደ 120 ቢሊዮን ብር አድጓል፡፡ ካፒታሉን ማሳደግ ያስፈለገበት ምክንያትም፣ ኮርፖሬሽኑ የተቋቋመበትን ዓላማና ተልዕኮ ለማሳካት እንዲችል በተለይም በግንባታ ላይ ያሉ የባቡር መሠረተ ልማቶች እንዲጠናቀቁ፣ የተጠናቀቁትም ወደ ሥራ እንዲገቡና በቀጣይ ለሚገነቡ የባቡር መሠረተ ልማቶች የተሻለ አቅም እንዲኖረው ለማድረግ መሆኑ በወቅቱ ተገልጿል፡፡

ኮርፖሬሽኑ የተቋቋመበት መሠረታዊ ዓላማዎች መካከል አገር አቀፍ የባቡር መሠረተ ልማት ግንባታ (አገር አቀፍ የባቡር ኔትወርክ) ግንባታ ማካሄድ ሲሆን፣ ይህም የሚያተኩረው የአገሪቱን የጭነት ትራንስፖርት ፍላጎት በማሟላት መንገደኞችን የሚያጓጉዝ፣ የገቢና የወጪ ንግድን የሚያቀላጥፍ፣ ከጎረቤት አገሮች ወደቦች ጋር የሚያገናኝ፣ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩና የሚፈጠሩ አገራዊ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸውን የልማት ማዕከላት፣ የኢንዱስትሪ መንደሮች፣ የማዕድንና የኃይል ማመንጫ መስመሮችን በባቡር መሠረተ ልማት ማስተሳስር ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...