በባዮሎጂ ትምህርት ክፍል ስሠራ የተከሰቱ ሌሎች ዓይነቶች ትዝታዎች ፦ ሥራ እንደ ጀመርን፤ በ1960ዎች መጀመሪያ አካባቢ ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር እና እኔ፣ የአንድ ቢሮ ደባሎች ነበርን፡፡ አንድ ቀን አንድ ትንሽ አስቂኝ ችግር ተከሰተ፡፡ በሰላሌ አውራጃ ውስጥ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት የነበረ አስተማሪ፣ የእሳት ራት የእፀዋት ዘር ነች የሚል ማስረጃ ይዞልን መጣ፤ ይህም ድምዳሜ የተደረሰበት በሳይንስ «ኤክስፐሪሜንት» ላይ ተመስርቶ ነው ብሎ አስረዳን፡፡ ኤክስፕሬሜንቱም እነሆ፤ መምህሩ ማታ ሻማ አብርቶ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ሳለ፣ ሻማው የቆመ አንድ አፉ ክፍት ከሆነ ጠርሙስ አፍ ላይ ሲሆን፣ አንድ የእሳት እራት አዚህ ሻማ ከተቀመጠበት ጠርሙስ ውስጥ ገባች፡፡ የእሳት እራቷ ጠርሙስ ውስጥ እንደገባች ሲረዳ፣ መምህሩ ጠርሙሱን በሻማ ጢስ እንዲሞላ፣ በወረቀት ከደነው᎓᎓ መምህሩ የገመተ የእሳት እራቷ ጢስ ስለሚያፍናት፣ ወዲያውኑ ትሞታለች ብሎ ነበር፤ ሆኖም መምህሩ በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ያች የእሳት ራት በሕይወት እንዳለች ተረዳ፡፡
እንግዲህ ሌሊቱን በሙሉ በጢስ (በካርቦን ዳይኦክሳይድ) በተሞላ ጠርሙስ ውስጥ የእሳት እራቷ መቆየት ከቻለች የእፀዋት ዘር መሆን አለባት ብሎ ደመደመ፡፡ የእንስሳት ዘርማ ብትሆን በኦክስጅን እጥረት ሕይወቷ ያልፍ ነበር፣ ስለሆነም፣ የእፀዋት ዘር መሆን አለባት ብሎ ሊያስረዳን ሞከረ፡፡ ተወልደም እኔም ለዚህ ክስተት ብዙ ምክንያቶች አቀረብን፤ ምንም ጠርሙሱ በወረቀት ቢሸፈን፣ ለእሷ ሕይወት ማቆያ ብቁ የሆነ ኦክስጂን ወደ ጠርሙስ ሊገባ፣ ወይም በመጀመሪያ እዚያ ሊገኝ እንደሚችል አስረዳን፡፡ በተጨማሪ የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠቀም አለመጠቀም የሁለቱን አንጋፋ ባለሕይወት ቅርንጫፎች፣ ስፍነ-እንስሳትን እና ስፍነ-እፀዋትን (እፀዋትና እንስሳት) መለያ፣ መከፋፈያ ያ ብቻ እንዳልሆነ ለማስረዳት ሞከርን፤ ደግመን ደጋግመን አዲስ ግኝቱን እንደማንቀበለው ገለጥንለት፡፡
እርሱም በዚህ በጣም ተበሳጨ፣ ወትሮም ምሁራን ከእናንተ በዕውቀት የሚልቅ ሰው አትቀበሉም፤ ቅናት አለባችሁ ብሎ በኩርፊያ መልክ የበራችንን በር ደርግሞት ሄደ። ከጥቂት ቀናት በኋላ በአንድ ጽሑፍ ላይ (ጋዜጣ ወይም መጽሔት) የእሳት እራት የእፀዋት ዘር መሆኗ ተረጋገጠ የሚል ርዕስ ይመስለኛል ታትሞ ወጣ፡፡ ይህን ጽሑፍ በወቅቱ ባነብም ቅሉ፣ ቅጂ ስለ አላስቀመጥኩ፣ የዚያን ጽሑፍ ቅጂ አሁንም በማፈላለግ ላይ እገኛለሁ፡፡
- ሽብሩ ተድላ “ከጉሬዛም ማርያም እስከ አዲስ አበባ”