Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምሩሲያውያንን ለሰዓታት የፈተነው የዋግነር ቡድን አመፅ

ሩሲያውያንን ለሰዓታት የፈተነው የዋግነር ቡድን አመፅ

ቀን:

በሩሲያ የመደበኛ ጦር አባል ያልሆነው ዋግነር ቡድን፣ ከሩሲያ ጋር ያለውን ስምምነት በመጣስ በሩሲያ መከላከያ ላይ ያመጸው ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ነበር፡፡

የቡድኑ መሪ ይቪግኒ ፕሪጎዢን፣ በዩክሬን የሚገኘው የቡድናቸው ጦር ላይ የሩሲያ መከላከያ የቦንብ ድብደባ አድርጓል፣ በርካታ የቡድኑን አባላት ገድሏል በሚል ባቀረቡት ጥሪ ለሳቸው ታማኝ የሆኑ የቡድኑ አባላት ሮስቶቭ ኦንዶን የሚገኘውን የሩሲያ መከላከያ ጽሕፈት ቤት ተቆጣጥረው ነበር፡፡

በሞስኮ የሚገኘውን ወታደራዊ አመራር ከሥልጣን ለማስወገድ ጉዞ የጀመረው ቡድኑ፣ ከሞስኮ ሳይደርስ በመሪው ፕሪጎዢን ትዕዛዝ ከጉዞው ታቅቧል፡፡

ሩሲያውያንን ለሰዓታት የፈተነው የዋግነር ቡድን አመፅ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የዋግነር ቡድን አባላትን እንደማይቀጡ አስታውቀዋል

በሩሲያና አብሮ በሚሠራው የሩሲያ መደበኛ ባልሆነው የዋግነር ቡድን መካከል ለተፈጠረው ግጭት መነሻ፣ ቡድኑ ከሩሲያ መከላከያ ጥቃት ተቃጥቶብኛል ማለቱ ቢሆንም፣ የሩሲያ መከላከያ በዋግነር ቡድን ላይ ድብደባ አለማድረጉን የሩሲያ መንግሥት ገልጿል፡፡ የዋግነርን እንቅስቃሴም በሩሲያ ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣ አመፅ ሲሉ ፕሬዚዳንት ቭላድሚ ፑቲን ኮንነዋል፡፡

በምዕራባውያኑ መገናኛ ብዙኃን ወደ ሞስኮ እያቀና እንደሆነ የተነገረለት የዋግነር ቡድን፣ በቤላሩስ ፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ አማካይነት በተደረገ ውይይት አመፁ ቆሟል፡፡

በተለይ ቅዳሜ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን አጀንዳ ሆኖ የዋለው የዋግነሩ ቡድንና የሩሲያ አጀንዳ፣ በሰላማዊ መንገድ መቋጨቱን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ፑቲን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የሩሲያው አርቲ ኒውስ ፕሬዚዳንቱን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ አብዛኞቹ የቡድኑ አባላት በተሳሳተ መረጃ የተመሩ ቢሆንም፣ የዋግነር ቡድን ወታደሮች የሩሲያ አርበኞች ናቸው፡፡

ሩሲያውያን ለአገራቸው አንድነትና ላሳዩት ድጋፍ ምሥጋና የቸሩት ፑቲን፣ የዋግነር ቡድን ወታደሮች ከሩሲያ መከላከያ ጋር ውል ገብተው አገልግሎታቸውን አንዲቀጥሉ አሊያም ወደ ቤላሩስ እንዲሄዱ አማራጭ አቅርበዋል፡፡

አብዛኞቹ የዋግነር ተዋጊዎችና ኮማንደሮች የሩሲያ አርበኞች፣ ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ዘብ የቆሙ ናቸው ሲሉም አክለዋል፡፡

እንደ ፑቲን፣ የዋግነር መሪዎች ወታደሮቻቸውን በጨለማ ውስጥ ከተው ትከሻ ለትከሻ ሆነው ሲዋጉ በነበሩ ወንድሞቻቸው ላይ እንዲነሱ ተጠቅመውባቸዋል፡፡ ሆኖም የዋግነር ወታደሮችና ኮማንደሮች የደም መፋሰሱን አስቁመዋል፡፡

የዋግነር ወታደራዊ ቡድን አባላት በትጥቅ የታገዘ አመፅ ለማድረግ መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ የሩሲያ ሕግ አስፈጻሚ አካላት፣ ልዩ አገልግሎት ሰጪዎችና የሩሲያ ብሔራዊ ፀረ ሽብር ኮሚቴ ሊከሰት የሚችል የሽብር ጥቃትን ለመመከት በአንድ ላይ የቆሙበትም ነበር፡፡

በሩሲያ ደም አፋሳሽ ጦርነት ሊያስከትል ይችላል ተብሎ የተሠጋው የዋግነርና የሩሲያ ፍጥጫ በሰላም ውይይት የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ሩሲያ በቡድኑ ላይ ልትወስድ የነበረውን ሕጋዊ ዕርምጃም ሰርዛለች፡፡

የዋግነርን አመፅ ተከትሎ ፕሬዚዳንት ፑቲን ‹‹ሩሲያን የካዷትን እንቀጣለን›› ብለው የነበረ ቢሆንም፣ ፕሪጎዢን ወደ ቤላሩስ ለማቅናት ከተስማሙ በኋላ ውጥረቶች ረግበዋል፡፡  ሮይተርስ ትናንት ሰኔ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. እንደዘገበው ደግሞ ፕሬጎዢን ወደ ቤላሩስ አቅንተዋል፡፡

የዋግነር ቡድን የሩሲያን መከላከያ ለምን መፈንቀል ፈለገ?

የዋግነር ቡድን መሪ ፕሪጎዢን፣ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾጉን እና በዩክሬን የሩሲያ ጦር መሪ ቫልሪ ግራሲሞቭ ብቃት የላቸውም ሲሉ ሲኮንኑ ከርመዋል፡፡

በሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር የቀረበውን የዋግነርን ቡድን በሚኒስቴሩ ቁጥጥር ሥር የማድረግ ሐሳብም ከዚህ ቀደም ተቃውመዋል፡፡

ባለፈው ዓርብ፣ ደግሞ የሩሲያ ጦር በዩክሬን ያለውን የዋግነር ወታደሮች ማረፊያ በቦንብ መትቷል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡ የሩሲያ መከላከያ ይህን ቢያስተባብልም፣ የዋግነር ቡድን አባላት ከአዛዣቸው በደረሳቸው ትዕዛዝ መሠረት፣ በደቡብ ሩሲያ የሚገኘውን ሮስቶቭ ኦንዶን የሚገኘውን የሩሲያ መከላከያ ተቆጣጥረው ሞስኮ የሚገኘውን መከላከያ ለመፈንቀል አልመው ጉዞ ጀምረው ነበር፡፡

ሆኖም ከክርምሊን ጋር በተደረገ ስምምነት የዋግነር መሪ ፕሪጎዢንና ለእሳቸው የታመኑ ወታደሮች ወደ ቤላሩስ ለማቅናት ሲስማሙ፣ ቀሪዎቹ በሩሲያ መከላከያ የሚቀላቀሉበት ካልሆነም ወደ አገራቸው የሚገቡበት ዕድል ተመቻችቷል፡፡ በቡድኑ አባላት ላይ ሊወሰድ የታሰበው ቅጣትም ተሽሯል፡፡

የዋግነር  ታጣቂ ቡድኖች በምዕራባውያኑ እንዴት ይታያሉ?

እ.ኤ.አ. በ2014 እንደተመሠረተ የሚታመነው የዋግነር ቡድን፣ በምዕራባውያኑ ዘንድ ሩሲያ የቀጠረችው የግል የውትድርና አገልግሎት ሰጪ ተቋም ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

ሰሞኑን ቡድኑ የፑቲንን መከላከያ ተቃውሞ ወደ ሞስኮ ሲያመራ፣ እንግሊዝና አሜሪካ ጉዳዩን በንቃት እንደሚከታተሉ አስታውቀዋል፡፡ ቡድኑ ከ2015 ጀምሮ ከሶሪያ መንግሥት ጎን ተሠልፎ እንደሚዋጋና የነዳጅ ማውጫ አካባቢዎችን እንደሚጠብቅ ይናገሩም ነበር፡፡

በሊቢያ ወታደሮች እንዳሉት የሚታመነው ዋግነር፣ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የዳይመንድ በሱዳን ደግሞ የወርቅ ማዕድናት የሚገኙባቸውን ሥፍራዎች እንደሚጠብቅም ይታመናል፡፡

በምዕራብ አፍሪካ የማሊ መንግሥት አይኤስን ለመዋጋት ቡድኑን የሚጠቅም ሲሆን፣ የቡድኑ የገንዘብ ምንጭም በውጭ አገሮች የሚሰጠው የውትድርና አገልግሎት ነው፡፡

ጀርመን በ2022 በቡቻ ለተፈጸመ ጭፍጨፋ የዋግነር ቡድንን ትኮንናለች፡፡ ዩክሬንም የዋግነር ቅጥረኞች ከሩሲያ መከላከያ ጋር በመሆን በኪየቭ ንፁኃንን ማሰቃየታቸውንና መግደላቸውን አሳውቃ ነበር፡፡

ፈረንሣይ ቡድኑ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ የዘረፋና የመድፈር ወንጀል መፈጸሙን ዓምና አሳውቃ ነበር፡፡ አሜሪካ በቡድኑ ላይ ማዕቀብ የጣለችው የሩሲያና የዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...