ሙሉቀን ፈቃዴ ዘሪሁን (ረዳት ፕሮፌሰር) የሎዛ ኒውትሪሽን ኮንሰልቲንግ ኤንድ ቴራፕ መሥራች ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሜዲካል ባዮኬምስትሪ መምህር ናቸው፡፡ ተወልደው ያደጉትና እስከ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁት በደቡብ ጎንደር ፋርጣ ወረዳ ክምር ድንጋይ በተባለው አካባቢ ሲሆን፣ ከጎንደር መምህራን ኮሌጅ በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በኬምስትሪና በጤና ሳይንስ ሁለት ዲግሪዎቻቸውን ሠርተዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅም በሜዲካል ባዮኬምስትሪ ሁለተኛ (ማስተርስ) ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ ቀደም ሲል ከመምህራን ኮሌጅ እንደተመረቁ አዲስ ዘመን ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ በመምህርነትና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በረዳት ላቦራቶሪ ቴክንሽያንነት አገልግለዋል፡፡ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት የሆኑትን ሙሉቀን (ረዳት ፕሮፌሰር) በሥነ ምግብ፣ ሕክምናና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የሥነ ምግብ ሕክምና ማለት ምን እንደሆነና ከመድኃኒቶች ጋር ያለውን ተያያዥነት ቢገልጹልን?
ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉቀን፡- የሥነ ምግብ ሕክምና (ኒውትሪሽናል ቴራፒ) ማለት ሰዎች ያለባቸውን የጤና ሁኔታ መሠረት በማድረግ ጤናቸውን የሚያባብሱ ምግቦችን መከልከል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ያሉባቸውን የጤና ሁኔታዎች ለማስተካከል የሚችሉ ምግቦችን በዝርዝር በማውጣት እነሱን እንዲመገቡ ማድረግ ነው፡፡ ይህም ማለት መድኃኒት ያልጀመሩ ከሆነ ከመድኃኒት ሕክምና በፊት ጤናቸውን መመለስ ነው፡፡ መድኃኒት የጀመሩና የጤና ሁኔታቸው በመድኃኒት ብቻ መስተካከል የሚችል ከሆነ የመድኃኒት ሕክምናውን ውጤታማነት ማስቻል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ የስኳርና የግፊት መድኃኒት እየወሰዱ አብዛኛዎቹ አይስተካከልላቸውም፡፡ በዚህም የተነሳ ተቸግረው ወደ ሆስፒታሎች ይመለሳሉ፡፡ ምክንያቱም መድኃኒቶቹ ብቻቸውን ውጤታማ አይሆኑም፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት እንደሚያመለክተው ከሆነ፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመድኃኒት ብቻ መቆጣጠር አይቻልም፡፡ ለምሳሌ የስኳር በሽታ የሞት ቁጥር ከወትሮው ዘንድሮ ከፍ ብሎ ወደ 93 በመቶ መድረሱን አጋግጧል፡፡ ይህም ማለት መድኃኒቶቹ ያላቸው ሚና በጣም ትንሽ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ድጋፍ ይፈልጋሉ፡፡ የግለሰቡ የአኗኗር ሁኔታ እና ያለው የአመጋገብ ሁኔታ እስካልተቀየረ ድረስ የስኳርና የግፊት መድኃኒት በመውሰድ ብቻ ዋስትና ሊኖረው አይችልም፡፡ የግፊት ችግር ያለባቸው ሰዎች ሕመም ከግፊት ወደ ስትሮክ ከፍ የሚልባቸው ምክንያት የሚወስዱት መድኃኒት ብቻ ለውጥ ማምጣት ስለማይችል ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ያሉባቸው ወገኖች ከሚወስዱት መድኃኒት ባሻገር ምን ማድረግ አለባቸው?
ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉቀን፡- ጤናማ የሆነ የአኗኗር ዘዴን መከተል፣ በተለይም የምግብ ሥርዓትን ማስተካከል አስፈላጊ ነው፡፡ የእኛ የኢትዮጵያውያን የአመጋገብና የአኗኗር ዘዬ ሳይንሳዊ እንዳልሆነ፣ በዘፈቀደ ብቻ የሚሆን ነገር እንደሆነ ብዙ ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ሰዎች የሚመገቡት ከጤናቸው አንፃር ሳይሆን ሆዳቸው እንዳይጎድል፣ በምግብ የሚያገኙትን እርካታ ታሳቢ አድርገው ነው እንጂ ስትሮክ፣ ግፊትና ስኳር አለብኝ ስለዚህ ከበሽታዬ አንፃር እነዚህ እነዚህ ምግቦች አይመለከቱኝም፣ እነዚህ እነዚህ ምግቦች ደግሞ የግድ መመገብ አለብኝ ብሎ የሚያስብ ታካሚ ብዙም የለም፣ አልተለመደምም፡፡ ከዚህ አንፃር እያንዳንዱ ግለሰብ ስለሚመገባቸው ምግብ ተገቢነት ማረጋገጥ አለበት ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡
ሪፖርተር፡- የስኳር ችግር ያለበት ሰው ከመድኃኒት ሕክምና ባገሻር ምን ዓይነት ምግብ መጠቀም አለበት ይላሉ?
ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉቀን፡- የደም ግፊትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ቅመማ ቅመሞችና የምግብ ዓይነቶች አሉ፡፡ በዚያው ልክም የደም ግፊትን፣ ኮሌስትሮልን፣ ከልብ ጋር የተያያዙ የጤና ችግሮችን የሚያባብሱ የቅባት ዓይነቶች እንዳሉ ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል፡፡ አንደኛው ‹‹ትራንስፋስት›› ይባላል፡፡ ትራንስፋስት (የአማርኛ አቻ ትርጉም ለማግኘት ከባድ ነው) በአትክልት ቅቤ ውስጥ ይገኛል፡፡ በአገራችን በየሱቁና በየምግብ ቤቱ በብዛት የምናገኘው የቅባት ዓይነት ነው፡፡ አብዛኛው ማኅበረሰብ የሚያስበው የአትክልት ቅቤ ጣዕም ያለውና መደበኛውን ቅቤ ተክቶ የሚያስፈልግ ይመስለዋል፡፡ ነገር ግን የአትክልት ቅቤ በከፍተኛ ሙቀትና በከፍተኛ ፕሬዠር የተቀነባበረና ለጤና በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ አምራቾች የአትክልት ቅቤ በተጠቀሰው ሙቀትና ፕሬዠር የሚያመርቱና በብዙ ፕሮሰስ እንዲያልፍ የሚያደርጉ በራሳቸው ምክንያቶች ነው፡፡ ምክንያቶቹም ምርታቸውን ከፍተኛ ለማድረግ፣ የጠረጴዛ ቆይታውን (ሼልፍ ላይፍ) ለመጨመር፣ ሴቶች የሚወዱት ዓይነት ጣዕም ለመፍጠር ሲባል ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ለጤና በጣም አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ይህም በመሆኑ ኩላሊትን የሚጎዳ ኬሚካል አለው፡፡ በውስጡ የሚይዘው ኦሜጋ ሲክስ የሚባል ፋቲ አሲድ አለ፡፡ ስለሆነም የኦሜጋ ሲክስ መጠን ከኦሜጋ ስሪ መጠን ጋር ንፅፅሩ አንድ ለአንድ ነው መሆን ያለበት፡፡ ነገር ግን የአትክልት ቅቤ ውስጥ ኦሜጋ ሲክስ በ40 እጥፍ ኦሜጋ ስሪን ይበልጣል፡፡ ይህ ዓይነቱ ዘይት ወይም ኦሜጋ ሲክስ ከፍ ማለቱ ሰውታችን ውስጥ ቁስል/ብግነት (ኢንፋላሜሽን) የሚባለውን ሒደት እንዲባባስ ያደርገዋል፡፡ ይህ ደግሞ ለብዙ የጤና ችግሮች መነሻ ምክንያት ነው፡፡ ስኳር እንዲመጣ፣ ግፊት እንዲባባስ ያደርጋል፣ የልብ ጤናን ያውካል፡፡ ከካንሰር ጋር ይገናኛል፡፡ እነዚህ ችግሮች ደግሞ በአገራችን በብዛት እየታዩ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ጤናማ ያልሆኑ ዘይቶች የሚያስከትሉትን ችግሮች ቢያብራሩልን?
ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉቀን፡- ጤናማ ያልሆኑ ዘይቶች ማለት ከፍ ብሎ እንደተጠቀሰው ሁሉ፣ የተቀነባበሩ የአትክልት ዘይቶች የሚያልፉበትን ሒደት ተከትለው ስለሚመረቱ ጤናማ አይደሉም፡፡ የአትክልት ቅቤም ሃይድሮጅኔሽን (ሃይድሮጅንን መጨመር) በሚባል ሒደት ነው የሚመረተው፡፡ ከፈሳሽ ወደ ጠጣር የአትክልት ቅቤ መቀየር ወይም ሰው ሠራሽ የአትክልት ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ይህ ዓይነቱ ቅቤ ባለበት ትራንስፋስት ኮሌስትሮልን ያግዛል፡፡ ይህም ማለት በጣም ጠቃሚ የሆነውንና ‹‹ኤችዲኤ›› የተባለውን ኮሌስትሮል ይቀንስና መጥፎውን የኮሌስትሮል መጠን ከፍ እንዲል ያደርጋል፡፡ ከዚህም ሌላ ትራንስፋስት ኢንፍላሜሽን ስለሚያመጣ ከካንሰር እስከ ኮሌስትሮል ድረስ በጣም የጤና ችግር ያስከትላል፡፡ እንደ እነዚህ ዓይነቶች የቅባት ወይም ዘይት ዓይነቶችን ጤና ካልሆኑ የቅባት ምግቦች ውስጥ እናገኛቸዋለን፡፡
ሪፖርተር፡- ለጤና ተስማሚ ነው ያሉት የዘይት ዓይነት ምንኛ ነው? በአገር ውስጥ በብዛት ይገኛል? ከተጠቃሚው የመግዛት አቅም አኳያ እንዴት ያዩታል?
ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉቀን፡- ለጤና ተስማሚዎቹ ምንም ዓይነት ሙቀት፣ ፕሬዠርና ኬሚካል ሳይታከልባቸው የሚመረቱ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል አንደኛው የወይራ ፍሬ ዘይት ነው፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ምንም ዓይነት ሒደት ሳያልፍና ኬሚካል ሳይገባበት ወይራ ፍሬን በመጭመቅ ብቻ የሚመረት ዘይት ነው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ያለው የኦሜጋ ስሪ መጠን ከኦሜጋ ሲክስ ከፍተኛ የሆነ ነው፡፡ ይህም የወይራ ፍሬ ዘይት አንዱ ሊትር እስከ 1,500 ብር ይሸጣል፡፡ በየሱፐር ማርኬት ይገኛል፡፡ ጥቅሙን የሚያውቁና የመግዛት አቅም ያላቸው ሰዎች ይህንን ዘይት ይጠቀማሉ፡፡ ዘይቱ ‹ኤክስትራ ሰርጂክ›› ይባላል፡፡ ይህም ማለት ምንም ዓይነት ኬሚካል ሳይጨመርበት የተመረተ ለመሆኑ የሚያሳይ ምልክት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የወይራ ፍሬ ዘይት ለመሆኑ ማረጋገጫው ወይም ምልክቱ ምንድነው?
ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉቀን፡- ምልክቶቹ በውስጡ ዘይቱን በያዘው ጠርሙስ ላይ ‹‹ኤክስትራ ቨርጅን›› የሚል ጽሑፉ ያለበት ሲሆን፣ እንዳልተቀነባበረና ሙቀትን ተጠቅሞ እንዳልተመረተ ለማሳየት ደግሞ ‹‹ፈርስት ኮልድ ፕሬስድ›› የሚልም ጽሑፍ ታክሎበታል፡፡ ነገር ግን ‹‹ሆት ፕሬስድና ብሌንድድ›› ወይም ደግሞ ‹‹ራፋይንድ›› የሚሉ ጽሑፎች ካለበት ዘይቱ ተቀነባብሯል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሸመታ ላይ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበረሰቡ ከመግዛት አቅሙ ጋር ተመጣጣኝ የሆነና ለጤናው ተስማሚ የሆነ ዘይት እንዴት ሊያገኝ ይችላል?
ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉቀን፡- ከፍ ብሎ የተጠቀሰውን የወይራ ፍሬ ዘይት ለመሸመት ወይም ለመጠቀም ከአቅም አንፃር ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎች ካሉ፣ አንደኛ ዘይትን ጭርሱኑ ባይጠቀሙ ወይም መጠቀምን ቢተዉት፣ ይህ የማይሆንላቸው ከሆነ መጠኑን በጣም ቢቀንሱ ይመከራል፡፡ ከዚህ ውጪ በቤታቸው አቡካዶ፣ ተልባ፣ ሰሊጥ፣ ለውዝ/አቾሎኒ፣ ዓሳ፣ በተለያየ መንገድ እየተዘጋጀ ቢጠቀሙ ጤናማና ተፈጥሯዊ ይዘት ማግኘት ይቻላል፡፡ አጠቃቀማቸው እንደ ባህላቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ዞሮ ዞሮ ተፈጥሯዊነታቸውን እንዳይለቁ ከተፈለገ በወጥ መልክ አለበለዚያም በጁስ መልክ መጠቀም ይቻላል፡፡ የተልባ አጠቃቀም ግን ጥንቃቄን ይፈልጋል፡፡ ተልባን ጨምሮ አንዳንድ የቅባት ዓይነቶች ሙቀት አይፈልጉም፡፡ በተለይ ተልባ ውስጥ የሚገኝ ቅባት ሙቀት አይፈልግም፡፡ ስለዚህ ምግብ ከበሰለ በኋላ ተልባውን እላዩ ላይ መጨመር ያለበለዚያም የተልባ፣ የአቦካዶና የሰሊጥ ጁስ እያዘጋጁ መጠጣት፣ ሾርባ ላይ ተልባን ጣል አድርጎ መጠቀም ሌላው ዘዴ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ታካሚዎቻችሁ የሚያስፈልጋቸውን ምግብ እናንተ ናችሁ የምታዘጋጁላቸው ወይስ እነሱ በየቤታቸው እያዘጋጁ እንዲጠቀሙ ነው የምታደርጉት?
ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉቀን፡- አንድ ታካሚ ከመጣ በኋላ እንዳለበት የጤና ሁኔታ የሚያሻሽልበትን ምግቦች በዝርዝር በወር ውስጥ ቁርስ፣ ምሳና እራት ፆመኛ ከሆነ እንደሚከተለው የሃይማኖት እምነት መሠረት የምናዘጋጅለት ምግቦች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህ የሚዘጋጁት የምግብ ዓይነቶች ግን ከተለመደው ትንሽ ወጣ ይላል፡፡ ለምሳሌ ሽሮ፣ ምስርና እንቁላል እኛ በዘይት ተቁላልቶ እንዲሠራ አንፈቅድም፡፡ ሁሉም ታካሚዎቻችን የላቦራቶሪ ውጤት ያመጣሉ፡፡ ውጤቱንም መሠረት አድርገን የምግብ ዕቅድና ክትትል እናደርግላቸዋለን፡፡
ሪፖርተር፡- ከተዘረዘሩት የምግቦች ዓይነት አንዱን መርጠው እንዴት እንደምትሠሩ ወይም እንደምታበስሏቸው ቢጠቁሙን?
ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉቀን፡- ለምሳሌ ያህል ምስር ጠቃሚ ይዘቶች አሉት፡፡ እነዚህ ጠቃሚ ነገሮች እንዳይታጡ መጀመርያ ማጠብ፣ ከዚያም መቀቀልና ከበሰለ በኋላ ግብዓቶችን ከላይ መጨመር፣ ግብዓቶቹም ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ዘይት፣ ወዘተ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም የተጠቀሱት ግብዓቶች በተለይ ምስሩ ከበሰለ በኋላ የሚጨመሩበት ምክንያት ጠቃሚ ይዘታቸውን እንዳያጡ ይረዳል፡፡ እኛ አገር ሆኖ ነው እንጂ በሌሎች አገሮች ሽንኩርት በጥሬ ነው የሚመገቡት፡፡ ጥቅሙንም ያውቁታል፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያውያን የመኖር ዕድሜ ጣሪያ ከሌሎች አገሮች ሰዎች ዕድሜ ጋር ሲነፃፀር ምን ይመስላል?
ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉቀን፡- ብዙ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ቢኖሩም፣ በእኛ እምነትና ግምት አመጋገባችን ጤናማ ስላልሆነ ከሌሎች በተለይ ከእስያ አገሮች ማኅበረሰባቸው ጋር ሲወዳደር ዝቅተኛ የሆነ የዕድሜ ጣሪያ ነው ያለን፡፡ የኢትዮጵያውያን የመኖር ዕድሜ 70 ሲሆን፣ የጃፓኖች የመኖር ጣሪያ እስከ 130 ዓመት ድረስ መኖር እንደሚችሉ ተረጋግጧል፡፡ ዋናው ልዩነታችን ተብሎ የሚታሰበው የአኗኗር ሁኔታችን ነው፡፡ ጃፓኖች ለምንድነው ረዥም ዕድሜ ያላቸው ከተባለ፣ ምግብ ላይ በጣም ከፍተኛ በሆነ ሁኔታ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመጠቀም ኅብረተሰባቸውን አሠልጠነዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በአብዛኛው በቁጥጥራቸው ሥር አውለዋቸዋል፡፡ ምግብ ዕድሜን ይወስናል፡፡ እኛ ጋ በዘይት የተቀቀለና የተጠባበሰ ምግብ እየበላን ዕድሜያችን እንዲያጥር ወይም የእርጅና ስሜት እንዲፈጠር እያደረግን ነው፡፡ ሰዎች ሥጋ ቤት የሚሄዱት ለጊዜያዊ እርካታ ነው፡፡ ነገር ግን ከተመገቡ በኋላ ሥጋው ልብ ላይ ምንድነው የሚፈጥረው፣ ወዘተ በሚለው ዙሪያ ትኩረት አይደረግበትም፡፡